ኢትዮጵያ፡ ከድሃም ደሃ

0
1401

ኻያ ብር ብቻ በአሁኑ የኢትዮጵያ ሁኔታ ለአንድ ኢትዮጵያዊ ምን ምን ሊያደርግለት ይችላል? የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ ምክንያቶች ይህ ብር ለአንድ ሰው የእለት ወጪ ሊሸፍን እንደሚችል አድርጎ የተናገረበት አንድ ወቅት ነበር። በዚህም ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ዜጎች ብዛት ከ23 በመቶ እንደማይዘል ተደርጎ ተቀምጧል። በኹለት አሃዝ እያደጉ ነው የተባሉ የኢትዮጵያ ውጤቶችም ብዙ ናቸው። የኢኮኖሚ ባለሞያዎች ግን ይህን ሐሳብ አይወዱትም። መንግሥት ሆነ ብሎ ቁጥሮችን እንደሚነካካም የሚናገሩ አልታጡም።

በተጓዳኝ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዛኛው በግል ደረጃ የኑሮ ጫናው ቢሰማውና ድህነት ቢደቁሰውም፣ አገሩ ሀብታም እንደሆነች እንደሚያስብ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚሰጡ የሰዎች አስተያየቶች ይናገራሉ። እውነታው ግን ከዚህ የዜጎች ስሜትም ሆነ መንግሥት በተለያየ ዓላማ ከሚያስቀምጠው አሃዝ የራቀ ነው። ኢትዮጵያ ድሃ ብቻ ሳትሆን ከድህነት ወለል በታች በሚባል ድህነት ውስጥ ትገኛለች።

ብዙ ኢትዮጵያውያን በገጠር እንዲሁም በከተማ ከፍተኛ ድህነት ውስጥ ናቸው። አምራች ዜጎች በብዛት ባሉባት አገር የሥራ እድል አነስተኛ ከመሆን ጀምሮ የተለያዩ ነጥቦች ለዚህ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። እነዚህን ምክንያቶች ጨምሮ የኢትዮጵያን ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ በጉልህ የሚያሳዩ መረጃዎችና ዘገባዎቸን በማገላበጥ እንዲሁም የሚመለከታቸውን ባለሞያዎች በማነጋገር የአዲስ ማለዳው በለጠ ሙሉጌታ፣ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

መንደርደሪያ
ፈጠነች እንግዳው ይባላሉ። በ 80ዎቹ መጀመሪያ የዕድሜ ክልል ውስጥ ይገኛሉ። የተወለዱት በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ ከአርሶ አደር ወላጆቻቸው ሲሆን በቀዳማይ ኃይለሥላሴ መንግሥት የክቡር ዘበኛ ጦር አባል ከነበሩት የትዳር አጋራቸው ጋር በአብዛኛው የአገራችን ክፍል ተንቀሳቀስው የመኖር እድል ገጥሟቸዋል። ኦጋዴን፣ ባህር ዳር፣ አሁን ኑራቸውን ያደረጉባት አዲስ አበባ ተጠቃሾች ናቸው።

በአዲስ አበባም ኑራቸውን መሰረት ካደረጉ ከ 40 ዓመታት በላይ አስቆጥረዋል። በትዳር ስምንት ልጆችን ማፍራት ቢችሉም በኹለት ልጆቻቸው የጀመረው ሞት የትዳር አጋራቸውን ጨምሮ ሰባት ልጆቻቸውን በየተራ ነጥቋቸው አንድ ልጅ ብቻ አስቀርቶላቸዋል።

የትዳር አጋራቸው ጥለውላቸው ባለፉት ብቸኛ ቅርስ የጡረታ አበል እንዲሁም ብቸኛዋ ልጃቸው በምታደርግላቸው መጠነኛ ድጋፍ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት ይውተረተራሉ።
መንግሥት በሰጣቸው ባለ ኹለት ክፍል የቀበሌ ቤት ውስጥ ኑሯቸውን በመግፋት ላይ የሚገኙት ፈጠነች፣ ከድህነት ጋር ግብግብ ውስጥ ስለመሆናቸው የሚኖሩበት ቤት ኮርኒስ እና በእድሜ ብዛት ቀለሙን እንኳን ለመለየት አስቸጋሪ እስኪሆን የተዥጎረጎረው ግርግዳቸው ምስክሮች ናቸው።

ሆኖም በሚያገኙት መጠነኛ የጡረታ አበል መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት ይውተረተራሉ።
በአሁን ሰዓት የሚቀበሉት ጡረታ 600 ብር የደረሰ ቢሆንም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ ከመጣው የሸቀጦች ዋጋ ጋር ተዳምሮ ኑሮዋቸውን አስቸጋሪ አድርጎታል።
አዲስ ማለዳም በቀን 20 ብር (በወር 600 ብር) መሰረታዊ ፍለጎቶትትን ለማሟላት ሁሉንም ወጪ ይሸፍናል ወይ? ብላ ጥያቄ አነሳች።
ፈገግ አሉና አሁን ለዕለት ተዕለት የሚገለገሉባቸውን ሸቀጦች ዋጋ መዘርዘር ጀመሩ፣ ዝርዝሩ ከኹለት ዓይነት ዕቃዎች ሳይዘል ዋጋው ከ 20 ብር ተሻግሯል።
ከመንግሥት በኩል የሚደረግ ድጋፍ ስለመኖሩ ላነሳንላቸው ጥያቄም፣ አረጋውያንን ለመደገፍ በሚል በተደረገ የቤት ለቤት ምዝገባ አባል መሆን ችለው እንደነበር እና በተቆራረጠ መልኩ በወር ከ 200 ብር የማይዘል መጠነኛ የገንዘብ ድጋፍ በመንግሥት በኩል እየተደረገላቸው መሆኑን አስረድተውናል።
ሌላኛው ኑሮን ለማሸነፍ የሚወተረተር በ20ዎቹ መጨረሻ የሚገኘው ወጣት አብነት ኡርኬሳ ይባላል። ከሚኖርበት ሆሳዕና ከተማ ወደ አዲስ አባባ ከመጣ ሦስት ዓመታትን አስቆጥሯል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ከሊስትሮነት አንስቶ እስከ ጉልበት ሥራ ሠርቷል።
አሁን በአነስተኛ የላስቲክ ሱቅ ውስጥ ሊስትሮነትን ጨምሮ ሶፍት፣ ማስቲካ እንዲሁም ካርድ እና መሰል እቃዎችን በመቸርቸር ይተዳደራል። በዚህ ሥራው በቀን እስከ 200 ብር የሚደርስ ገቢ ማግኘት ቢችልም፣ የቤት ኪራይን ከፍሎ የምግብ እና መሰል ወጪዎቸን ለመሸፈን አዳጋች እንደሚሆንበት ይናገራል።

የሚያገኘውንም ገንዘብ ለማብቃቃት የምግብ ወጪን በመቀነስ እንዲሁም ከሦስት ጓደኞቹ ጋር በጋራ አንድ ቤት በመከራየት ኑሮን ለማሸነፍ እንደሚጥር አውግቶናል።
ለአብነት ያህል እነዚህን ታሪኮች አነሳን እንጂ የተሻለ ኖሮ ፍለጋ ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተሰደው ወደ ከተማ የመጡ ሴቶች ሕፃናት እና ወጣቶች፣ አጋዥ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው በጉብዝናቸው ወራት አገራቸውን ያገለገሉ እርጅና ሲጫጫናቸው ጎዳና ላይ ወጥተው የሰው እጅ የሚመለከቱ አዛውንቶች ማግኘት የተለመደ እየሆነ መጥቷል።

በሌላ በኩል መንግሥት በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን እና ለመጨረሻ ጊዜ ባወጣው የድህነት ሪፖርት ላይ፣ አንድ ኢትዮጵያዊ በወር ከ600 ብር በላይ ገቢ ካለው/ካላት ድሃ እንደማይባል ገልጿል። በዚህ ድምዳሜ መሰረት ከ77 በመቶ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ከድህነት አረንቋ ወጥተዋል ቢባልም መሬት ላይ የሚታየው እውነታ ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው።
እንኳንስ 600 ብር ለአንድ ወር የምግብ እና የኪራይ ወጪን ሊሸፍን ቀርቶ አሁን ባለው የኑሮ ውድነት፣ ከሳምንትም ሊያልፍ እንደማይችል የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ።
ቁጥሩን በማሻሻል አንድ ዜጋ በወር 1000 ብር በማግኘት ኑሮውን መግፋት ይችላል ተብሎ ቢታሰብ እንኳን፣ ከድህነት ወለል በታች ያሉ አገራትን ቁጥር ወደ 73 በመቶ ከፍ እንዲል እንደሚያደርገው መረጃዎች ያሳያሉ።

እውነት ኢትዮጵያ ድህነትን መቀነስ ችላለች?
ከዓለማችን አጠቃላይ ሕዝብ ውስጥ 736 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በከፋ ድህነት ውስጥ ይኖራሉ። ከአጠቃላይ የዓለማችን ሕዝብ ብዛት ውስጥም ዐስር በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናሉ። እነዚህ ዜጎች በቀን ከኹለት ዶላር ያነሰ ገቢ የሚያገኙ ናቸው። ከሰሃራ በርሃ በታች የሚገኙ አገራትም ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ በርካታ ዜጎችን መያዛቸውን የዓለም ባንክ ከዓመታት በፊት ይፋ ያደረገው መረጃ ያመላክታል።

አገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበት ከሰሃራ በርሃ በታች ክልል ውስጥም፣ ከ1 ነጥብ 9 ዶላር በታች የቀን ገቢ ያላቸው ከ413 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሚኖሩ ይኖራሉ። ይህ ቁጥር በዓመቱ በ9 ሚሊዮን እየጨመረ እንደሚሄድ ይገመታል። ይህ ሁኔታም በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ፣ በፈረንጆቹ 2030 በዓለማችን በከፋ ድህነት ውስጥ ከሚኖሩ ዐስር ሰዎች መካከል ዘጠኙ በዚሁ ክልል ውስጥ የሚኖሩ እንደሚሆኑ የዓለም ባንክ መረጃ ያትታል። ችግሩም በስፋት ኢትዮጵያ ላይ ሊታይ እንደሚችል የዚሁ ተቋም መረጃ ያመለክታል።

ከ112 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በመያዝ ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ በመቀጠል ኹለተኛዋ የብዙ ሕዝብ ባለቤት አገር ስትሆን፣ ምጣኔ ሀብቷም ባለፉት ዐስር ዓመታት በአማካይ 9.9 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። ነገር ግን ይህ ለዓመታት በተለያዩ ተቋማት የተደነቀው የምጣኔ ሃብት ዕድገት መሬት ላይ ወርዷል ወይ? ድህነትንስ በመቀነስ አኳያ ምን ሚና ተጫውቷል? የሚለው ለብዙዎች ያልተመለሰ ጥያቄ ነው።

ምንም እንኳን የአገሪቷ ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ባለፉት ዐስርት ዓመታት ውስጥ ከሦስት እጥፍ በላይ ዕድገት በማሳየት ወደ 800 ዶላር (በወር 2000 ብር) አካባቢ ደርሷል ቢባልም፣ ይህ ግን እውነታውን እንደማያሳይ በተደጋጋሚ ሲነሳ ይታያል። በተለይም በቀን 1 ነጥብ 25 ዶላር የሚያገኙ ዜጎች ከ80 ሚሊዮን በላይ መሆናቸውን ለተረዳ ሰው፣ እውነትም ድህነት ኢትዮጵያ ውስጥ ቀንሷል ተብሎ የሚነገረው የቀን ቅዠት ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ማጋነን ላይሆን ይችላል።

ድህነት ቀንሷል ወይስ አልቀነሰም የሚለው ጥያቄ ሲነሳም፣ በአገራት ያለው በምግብ ራስን የመቻል ምጣኔ፣ የትምህርት እና የጤና አቅርቦት፣ የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎቶች እና ንፅህና አጠባበቅ በዋነኛነት የሚነሱ ቀዳሚ ጉዳዮች ናቸው።

መንግሥት በበኩሉ ለትምህርት ተደራሽ ያልነበሩ ዜጎችን ቁጥርን ከ70 በመቶ ወደ 50 በመቶ፣ የውሃ አቅርቦትን ደግሞ ከ 17 በመቶ ወደ 34 በመቶ ማሳደጉን እንዲሁም በቀን ከ ከ600 ብር በታች ያገኙ የነበሩ ዜጎች ቁጥር ከ 56 በመቶ ወደ 23 በመቶ መቀነስ መቻሉን እና የእድሜ ጣሪያን ከነበረበት44 ወደ 63 ዓመት ማደጉን በማንሳት በኢትዮጵያ ድህነትን ስለመቀነሱ በተደጋጋሚ ይገልጻል።
ዓለም አቀፉ የውሃ ድርጅት ባለፈው ፈረንጆች ዓመት መጨረሻ ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሰረት ከ60 በመቶ በላይ ኢትዮጵያውያን ንፁህ መጠጥ ውሃ አያገኙም። በርካታ ዜጎችም የትምህርት የጤና አገልግሎቶችን በሚገባ እንደማያገኙ ይገልጻል።

ከ31 በመቶ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ደኅንነቱ ያልተጠበቀ ውሃን ለዕለት ተዕለት አገልግሎት ይጠቀማሉ ፣ ከዚህ ውስጥም ከስምንት በመቶ በላይ የሚሆነውን ድርሻ የያዙት ውሃን ከወንዞች፣ ኩሬዎች እና ሀይቆች የሚያገኙ ናቸው። የተቀሩት 23 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ውሃን በእጅ ከተቆፈሩ ጉድጓዶች እና ከተፈጥሮ ምንጮች እንደሚያገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥትም በበኩሉ የልማት ፖሊሲዎቹ የአገሪቱን አጠቃላይ ተጨባጭ ሁኔታዎች እና የሕዝቦችን የልማት ፍላጎቶች መሠረት በማድረግ የተዘጋጁ እና ሕዝቦችን በየደረጃው ተጠቃሚ የማድረግ ዓላማ ያላቸው መሆናቸውን በተደጋጋሚ ያነሳል።

በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ ያሏትን መሬት እና ሰፊ የሰው ኃይል በመጠቀም ዜጎችን ከድህነት ለማውጣት በርካታ ፖሊሲዎች እና መረሃ ግብሮች ሲዘጋጁ ቆይተዋል። የመሬትና የብዝሀ ሕይወት ደኅንነትን በመጠበቅ፣ ፈጣንና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት በማረጋገጥ፣ የኢኮኖሚ መሠረተ ልማት፣ እንዲሁም ግብርናውን ማዘመን ባለፉት ዓመታት በትኩረት ሲሠራባቸው የቆዩ ጉዳዮች እንደነበሩ ይገለፃል።

ከነዚህም ውስጥ የዘላቂ የልማት ግቦች ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የዘላቂ ልማት ግቦችን ተፈፃሚ ከማድረግ አኳያ የረጅም ዘመን አገራዊ የልማት ዕቅድ (2008-2022) ተቀርጿል። የመጀመሪያ ምዕራፍ በሆነው በኹለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (2008-2012) ቅድሚያ ትኩረት የተሰጣቸው የልማት መስኮች (Development Priorities) ተለይተው ተቀምጠዋል።

እነዚህም የግብርና ዘርፉ የአገሪቱ ፈጣን ኢኮኖሚ ዕድገት ምንጭ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ፣ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እምርታ ማምጣትና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ማፋጠን፣ የኢኮኖሚው የማምረት አቅም ላይ ለመድረስ ቅልጥፍናን በመጨመር ለምርታማነት፣ ጥራትና ተወዳዳሪነት ልዩ ትኩረት መስጠት፣ በጠቅላላ ፍላጎትና በጠቅላላ አቅርቦት መካከል የሚታየውን የተዛባ ክፍተት ማስተካከል የሚሉት ይጠቀሳሉ። ይሁን እንጂ እነዚህን ግቦች ከማሳካት አኳያ የነበሩ ለውጦች ቢኖሩም፣ አጥጋቢ እንዳልነበር እና የዜጎች ሕይወት ላይ ለውጥ እንዳላመጣ ማወቅ ተችሏል።

በተጨማሪም የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማትና የፕሮጀክቶች ማኔጅመንት አቅምን በማጎልበት የሥራ ዕድሎች ለመፍጠር ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ትላልቅ የመንግሥት ግንባታዎች በአግባቡ ባለመከናወናቸው መንግሥት ላይ ከ44 ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ከማምጣታቸው በተጨማሪ ብዙዎቹም ተጠናቀው የታሰበውን ያህል የሥራ ዕድል ሊፈጥሩ አልቻሉም።

መንግሥት ባለፉት ዐስር ዓመታት ሲከተለው የነበረ የ70 : 30 ፖሊሲ (70 በመቶ ተማሪዎች ሳይንስ እንዲሁም 30 በመቶ የሚሆኑት ወደ ማኅበራዊ ሳይንስ ምደባ) ግቡን መምታት ባለመቻሉ፣ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ተመራቂዎች ሥራ እጥ ሊሆኑ ችለዋል። ከከተማ ባሻገር፤ የአንድ ገበሬ ይዞታ በ1960ዎቹ ከነበረበት 1 ነጥብ 2 ሄክታር ወደ 0 ነጥብ 3 ሄክታር መውረዱ በገጠር ያለው መሬት አልባነት እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል። በተለይም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር መጨመሩ መሬት አልባ የሆኑ ወጣቶች ወደ ከተማ እንዲሰደዱ መንስኤ መሆኑን ቀጥሏል።

በሌላ በኩል፤ የአየር ንብረት መለዋወጥን ተከትሎ ድርቅ መስፋፋቱ በኢትዮጵያ ያሉት ተረጂዎች ቁጥር እንዲያሻቅብ ምክንያት የሆነ ሲሆን፣ ይህንን ዓይነት ችግሮችን ለመፍታት እንዲሁም የዜጎችን ምርታማነት ለመጨመር የሴፍቲኔት ፕሮግራም ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት ቢጀመረም ያመጣው ውጤት እምብዛም ነበር። በግብርና ሚኒስቴር ሲመራ የነበረው ፕሮግራሙ ከተጀመረ አንስቶ፣ ከ8 ሚሊዮን በላይ ተረጂዎች ነበሩት። ሆኖም ግን መንግሥት ይህንን ለፖለቲካዊ አጀንዳዎች ያውለው ነበር ተብሎ ወቀሳ የተሰነዘረበት ሲሆን፣ ፕሮግራሙን ከሚመሩት መሥሪያ ቤቶች ጀምሮ ከማኅበረሰቡ ጋር እስከሚገናኙ አካላት ድረስ ለግል ጥቅማቸው አውለውታል የሚሉ ወቀሳዎች በጉዳዩ ላይ ጥናት ባደረጉ ባለሙያዎች በስፋት ተነስተዋል። ፕሮግራሙ ይዟቸው የተነሳቸውን ምርታማትን እና ዕሴት መጨመር የሚሉ ዓላማዎች አንዳቸውንም አልተሳኩም የሚሉም አልጠፉም።

ባለሙያዎቹ ምን ይላሉ?
መንግሥት የድህነት ምጣኔውን ጥናት ባደረገበት ወቅት 20 ብር አንድ ሰው በቀን ለሚያስፈልጉት ወጪዎች በቂ እንደሚሆን በማሰብ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ዜጎችን ከ23 በመቶ እንደማይዘል አድርጎ ማቅረቡ በብዙ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሚወደድ ሐሳብ አይደለም።

አንድ ሥማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ በተባበሩት መንግሥታት በአማካሪነት የሚሠሩ የምጣኔ ሃብት ባለሙያእና የፖሊሲ ተንታኝ፣ መንግሥት ሆነ ብሎ በቁጥሮች ላይ ጭማሪ እንደሚያደርግም ይገልፃሉ። እርሳቸው እንደሚሉትም፣ መንግሥት ሆነ ብሎ በቁጥሮች ላይ ማጭበርበርን የሚፈፅመው ሕዝቡን ከማታለል በተጨማሪ ከዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች የሚገኝ ድጋፍ እንዳይቋረጥ ማድረግን መሰረት በማድረግ ነው ይላሉ።

በማሳያነትም ከ 10 እና 15 ዓመታት በፊት በተዘጋጀ መረጃ ሰዎች በቀን ኻያ ብር (በወር ስድስት መቶ ብር ገቢ) ሙሉ ወጪያቸውን ችለው መኖር እንደሚችሉ በመግለፅ፣ በኢትዮጵያ ካለው አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር ውስጥ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኘው ከ23 በመቶ አይዘልም የሚለው የመንግሥት ሙግት ሐሰት እንደሆነ እና ፖለቲካዊ ትርፍን መሰረት ያደረገ መሆኑን ያነሳሉ።
ይህ ቀመር የኑሮ ውድነትን መሰረት ያላደረገ እንደሆነ የሚገልፁት የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ እና በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በርካታ ጥናቶችን ያደረጉት ዓለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ መንግሥት የሚያቀርበው ይህ የድህነት ወለል መለኪያ ስህተት ነው። በምክንያትነት የጠቀሱትም አሁን ባለው የኑሮ ሁኔታ አንድ ሰው በቀን 20 ብር መኖር የሚያስችለው አለመሆኑን ነው።

የዓለም ባንክ በሚያስቀምጠው መስፈርት መሰረትም፣ አንድ ሰው ከድህነት በታች የሚባለው በቀን ከ1.25 ዶላር ገቢ ካለው ሲሆን ይህም በወር ወደ 1 ሺሕ 120 ብር ገደማ ነው ይላሉ። በወር ከዚህ በታች የሚያገኙ ሰዎች ቢቆጠሩ፣ ከ70 በመቶ በላይ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደቻሉ ጥናታቸውን በመጥቀስ ዓለማየሁ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ፤ መንግሥትም የኑሮ ዋጋውን ባላገናዘበ መልኩ ወደ 20 ብር ዝቅ በማድረግ እና በ 30 በማባዛት፣ የዜጎችን የዕለት ወጪ የገንዘብ መጠን በማሳነስ የድህነት ወለሉን ለማስተካከል ይጥራል ሲሉ ትችታቸውን ሰንዝረዋል።

ድህነቱ ከከተማ ይልቅ በገጠር ጎልቶ እንደሚታይ የሚገልፁት ባለሙያው፣ በገጠር ባለፉት 20 ዓመታት የተከሰተው ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር መጨመር የእርሻ መሬቶች እንዲቆራረጡ ምክንያት ሆኗል። በደርግ ዘመነ መንግሥት ለአንድ ቤተሰብ እስከ 10 ሄክታር መሬት ይደርስ ነበር ሲሉ የተናገሩት ዓለማየሁ፣ አሁን ግን ለቤተሰብ እየተከፋፈለ በመሄዱ ለአንድ ቤተሰብ ከአንድ ሄክታር ያነሰ መሬት እንደሚደረሰው ገልጸዋል።

ግብርናው በቁራሽ መሬት የሚያመርት መሆኑ ዝናብን የሚጠብቅ በቴክኖሎጂ ያልተደገፈ ነው። የተጨመረለት አዲስ ነገር የለም። ይህም ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተዳምሮ ድህነት በገጠር አስከፊ እንዲሆን አድርጎታል ሲሉ ተናግረዋል። በከተማ ያለው ነዋሪም ቢሆን፣ ከዚህ አስከፊ ድህነት የተላቀቀ አይደለም የሚሉት ዓለማየሁ፣ በከተማ ያለው ነዋሪ በኹለት የሚከፈል መሆኑን ይገልጻሉ። እነዚህም በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልሆኑ መሥሪያ ቤቶች ተቀጥረው የሚሠሩ እንዲሁም መደበኛ ባለሆኑ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ናቸው፤ እንደ ባለሙያው ገለፃ።

በእርሳቸው ጥናት መሰረት በመንግሥት እና በሌሎች መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሰዎች አማካኝ የደሞዝ ጣሪያ 2 ሺሕ 500 ብር በታች ሲሆን፣ ይህም በከተማ ካለው የኑሮ ውድነት አኳያ በጣም ያነሰ መሆኑን ባለሙያው አውስተዋል። በተጨማሪ 40 በመቶ የሚሆነው ዜጋ መደበኛ ባልሆነ ሥራ የሚተዳደር በመሆኑ፣ ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ መሆኑ በከተማም ይሁን በገጠር ድህነት መስፋፋቱን የሚያመላክት እንደሆነ አብራርተዋል።

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል የድኀረ ምረቃ መረሃ ግብር አስተባባሪ ምዑዝ ሀዲሽ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ኢሕአዲግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ በርካታ ለውጦች መጥተዋል ብለዋል። ለዚህም እንደማሳያ የሥራ አጥነትን ቁጥር ከ 48 በመቶ ወደ 16 በመቶ መቀነስ መቻሉ፣ ከ44 ዓመት የማይዘል የነበረው የአንድ ሰው የዕድሜ ጣሪያ ወደ 64 ማሳደጉ ነው ሲሉ አውስተዋል። ይሁን እንጂ ባለፉት ዐስርት ዓመታት ውስጥ የአገሪቷ ምጣኔ ሃብት ከ10 በመቶ በላይ ዓመታዊ ዕድገት ቢያሳይም፣ በዜጎች ሕይወት ላይ እና ድህነትን ከመቀነስ አኳያ ብዙ መሠራት እንዳለበት ያሳያል ሲሉ ተናግረዋል።

ለዚህም እንደ ምክንያት ያነሱት የተመዘገበው የምጣኔ ሃብት ዕድገት፣ በመንግሥት የሚመሩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች መስፋፋታቸውን ሲሆን፣ አነስተኛ ገቢ ያለው ኅብረተሰብ የተሰጠው ትኩረት ማነሱንም ነው። ነገር ግን፤ የገቢ አለመመጣጠን መለኪያ የሆነው ‹ጊኒ ኮፊሸንት› በኢትዮጵያ 0 ነጥብ 33 መሆኑ፣ በሃብታም እና ድሃ መካከል ያለው ልዩነት ብዙም ሰፊ አለመሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል። ይህም ሊደነቅ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል፤ በፕላን እና ልማት ኮሚሽን የኮሚሽነሯ ቴክኒክ አማካሪ አባስ መሐመድ፣ ድህነትን ለመለካት ኹለት ዓይነት መንገዶች እንዳሉ ያወሳሉ። እነርሱም የዜጎችን ገቢ መጨመር ተከትለው የሚመጡ ፍጆታዎችን መሰረት የሚያደርጉ መለኪያዎች ሲሆኑ፣ ሌሎቹ ደግሞ እንደ ትምህርት፣ ጤና እና ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮችን የሚያካትቱ ዘርፈ ብዙ መለኪያዎች ናቸው።

በእነዚህ መለኪያዎች መሰረት በኢትዮጵያ በቀን 20 ብር በላይ የሚያገኙ ሰዎች ከጠቅላላው ሕዝብ 77 በመቶ የሚሆነውን ቁጥር ይይዛሉ። ይህም ከድህነት አረንቋ መውጣታቸውን ማሳያ ነው ይላሉ። ሆኖም የድህነት ቅነሳው የድሃ ድሃ የሚባሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያገናዘበ እና ተጠቃሚ ማድረግ የቻለ እንዳልነበር አልሸሸጉም። እርሳቸው ይህንን ቢሉም አሁን ቀርቶ የዛሬ ሦስት ወይም አራት ዓመታት በፊት፣ በኢትዮጵያ ካለው የኑሮ ወድነት አንፃር አንድ ሰው በወር 600 ብር በማግኘት ሕይወቱን መግፋት እንደማይችል የአደባባይ ሃቅ መሆኑን ባለሙያዎች ያወሳሉ።

ለድህነት አለመቀነስ ዐበይት ምክንያቶች
ድህነትን ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ላይ የዜጎችን የማምረት አቅም እንዲሁም የኑሮ ሁኔታ አስቸጋሪ የሚያደርጉ በርካታ ችግሮች አሉ። ከነዚህም ውስጥ፣ የዋጋ ግሽበት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ሥራ አጥነት እና የሰላም እጦት ተጠቃሽ ናቸው። ለምሳሌ፤ በኹለተኛው የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረት አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ከስምንት በመቶ እንዳያልፍ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ ከነሐሴ 2009 ጀምሮ እስከ አሁን ባለኹለት አሃዝ እድገት እያሳየ ይገኛል።

ይህም የአገሪቷ ማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋት ላይ ችግር ከመፍጠሩ ባሻገር፣ በድህነት አረንቋ ውስጥ ያሉ ዜጎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው። በተለይም በከተሞች ውስጥ የሚኖሩ አንድ ሦስተኛ ዜጎች በድህነት ውስጥ መገኘታቸው ከፍተኛ የሚባል የኑሮ ቀውስ እያሳደረ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ በየወሩ የሚያወጣው የዋጋ ግሽበት ሁኔታ መረጃ መሠረት፣ በታኅሳስ ወር 2012 የተመዘገበውን አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት እንኳን ብንመለከት፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር በ19.5 ከመቶ ከፍ ብሎ ታይቷል።

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የዋጋ ግሽበቱ ሁኔታ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር በማነፃፀር የሚገኘው ውጤት ወቅታዊ የዋጋ ግሽበት ሁኔታን የሚያሳይ ነው ይበል እንጂ፣ የምግብ ዋጋ ግሽበት የታኅሳስ ወር 2ዐ12 ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር በ22.7 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ይህም ባለፉት ሰባት ዓመታት ተኩል ውስጥ ከተከሰተው ጋር ሲነፃፀር ትልቁ ነው። በዚህ ደረጃ ላይ የሚገኝ የዋጋ ግሽበት ዜጎችን ወደ ድህነት አረንቋ ከመክትቱም በላይ የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዳይኖር እና የፖለቲካዊ አለመረጋጋቱ እንዲቀጥል ምክንያት እንደሆነ ባለሙያዎች ያነሳሉ።

የድህነት ወለል ሲሠራ የዋጋ ግሽበት ሁኔታን ያካተተ መሆን ይገባዋል የሚሉት ዓለማየሁ፣ ከ 10 ዓመታት በፊት በነበረ የሸቀጦች ዋጋ የዜጎች የድህነት ወለል መለኪያ ሊሠራ እንደማይገባውም ያክላሉ። መንግሥት ሆነ ብሎ ቁጥሮችን ያጭበረብራል የሚሉት ዓለማየሁ፣ የድህነት ወለል መለኪያዎቹ ጥቅል አገራዊ ምርትን ከዜጎች ወቅታዊ ገቢ ጋር ያዋሃዱ አለመሆናቸውንም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል፤ ድህነት ሲነሳ ተያይዞ የሚነሳው የአየር ንብረት ለውጥ ነው:: በኢትዮጵያ በየዓመቱ 92 ሺሕ ሄክታር መሬት የሚሸፍን ደን ይጨፈጨፋል። በአንፃሩ 20 ሺሕ ሄክታር መሬት ብቻ በደን የሚለማ ሲሆን፣ ከአጠቃላይ የሕዝብ ብዛት 80 በመቶ የሚሆነው የሚሸፍኑት እና በገጠራማ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚኖሩት ዜጎች ለኃይል ፍጆታ እንጨትን መጠቀማቸው ከፍተኛ የደን መጨፍጨፍ እንዲኖር አድርጓል።

አጠቃላይ የደን ሽፋኑም አሁን 15 በመቶ ላይ የሚገኝ ሲሆን የደን መጨፍጨፍ ከ40 እስከ 60 በመቶ ለአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሲሆን ይስተዋላል። ይህም ለሙቀት መጨመር እና ለዝናብ እጥረት ምክንያት በመሆን ላይ እንደሚገኝ ይገለፃል። ለዚህም የውሃ አካላት መቀነስ እንዲሁም እንደ ሀሮማያ ያሉ ሀይቆች መድረቅ ማሳያዎቹ ተደርገው ይወሰዳሉ። ይህም ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑ ዜጎችን አቅፎ የያዘውን እና ለጥቅል አገራዊ ምርቱ ከ 40 በመቶ በላይ የሚያዋጣውን ግብርና በመጉዳት ላይ ይገኛል።

በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ 1983 እስከ 2015 ድርቅ ክፍኛ ጎድቷታል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥም ከ20 ያላነሱ ድርቆች ተፈራርቀዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ በየዐስር ዓመቱ ሲከሰት የነበረው ድረቅም አሁን ቢያንስ በየሦሰት ዓመቱ መከሰቱ አይቀሬ እየሆነ መምጣቱን የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ያወሳል። ከዚህ በፊት ድርቅ በየ10 ዓመቱ ይከሰት የነበረ ሲሆን፣ ወደ ሦስት ዓመት ዝቅ ማለቱ ችግሩ እየሰፋ መምጣቱ ማሳያ እንደሆነ ይወሳል።

የአየር ንብረት ለውጡ በርካታ አካባቢዎችን በድርቅ በመጉዳት እና የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ በማዳከም አርሶ አደሮችን ለተረጂነት እንዲዳረጉ ማድረጉ ድህነትን ለመቀነስ አስቸጋሪ ሁኔታን ፈጥሯል። ይህ የአየር ንብረት ለውጥ ከሚያመጣቸው ብዙ ቀውሶች መካከል የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ቁጥር ከፍ ማድረጉ ይገኝበታል። ከፈረንጆቹ 1990 እስከ 2005 ባሉት ዓመታት በአማካኝ 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች ድጋፍ ጠባቂ እንዲሆኑ አድርጓል። ለነዚህ ዜጎችም በየዓመቱ 654 ሺሕ ቶን ምግብ ድጋፍ ይደረጋል።

በሌላ በኩል፤ የፀጥታ ችግሮች ለድህነት መስፋፋት ቀላል የማይባል ሚና እንዳላቸው የሚገልፁት ደግሞ ከ1987 እስከ 1993 የኢትዮጵያ አየር ኃይል በመሆን ያገለገሉት እና በሰላም እና ደኅንነት እጩ ዶክተር የሆኑት ጄነራል አበበ ተክለ ሀይማኖት ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ በድህነት እንድትታወቅ ያደረጋት አብዛኛው ታሪኳ ከጦርነት ጋር የተያያዘ መሆኑ ነው። ከመሳፍንቶች ዘመን ጀምሮ የውጪ ወራሪዎችን ለመከላከልም ይሁን እርስ በእርስ የተደረጉ ጦርነቶች ለድህነት መንስኤ ስለመሆናቸው ገልጸዋል።

በአገር ውስጥም የሰላም እጦት ችግሮች በሚከሰቱበት ጊዜ ከትራንስፖርት ጀምሮ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን እንሚያዛባ የገለፁ ሲሆን፣ በኢንቨስትመንት ላይም መሰል ተፅዕኖ እንዳለው አውስተዋል። በየቦታው መታገት እና ነውጥ የሚኖር ከሆነ ኢንቨስትመንቱን በመጉዳት የሥራ እድል እንዳይፈጠር ያደርጋል ሲሉም የሰላም እጦት ከድህነት ጋር ያለውን ግንኙነት ጠቅሰዋል። በእርግጥ፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት የነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከ1 ነጥብ ቢሊየን ዶላር በላይ ቅናሽ እንዲያሳይ ምክንያት እንደሆነ በቅርቡ ይፋ የሆነው የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።

በተጨማሪ፤ የሰላም እጦት በሚኖርበት ወቅት ኅብረተሰቡ ተስፋ እንዲቆርጥ እና ለነገ ብሎ የሚያስቀምጠው ነገር እንዳይኖር ያደርጋል የሚሉት አበበ፣ ያለውንም ገንዘብ ባልሆነ ነገር እንዲያጠፋ ያደርገዋል ብለዋል። አክለውም አሁን አሁን ለሚከሰቱ የሰላም እጦት ችግሮች መንስኤ ሕገ መንግሥቱ በሚገባ አለመከበሩ መሆኑን ይጠቁማሉ። ሕጉ ላይ የተቀመጠው እና መሬት ላይ የሚተገበረው መለያየቱንም አንስተዋል።

ሰላም እና ልማት ከፍተኛ ቁርኝት እንዳላቸው የሚገልፁት ምዑዝ፣ በዘመናዊ ኢኮኖሚ ውስጥ አገልግሎቶች እና ሸቀጦች 24 ሰዓት በሚፈለገው መጠን መንቀሳቀስ ይገባቸዋል ይላሉ። ኢንቨስትመንት ሲስተጓጎል ድርጅቶች ሠራተኞችን ለመቀነስ ይገደዳሉ የሚሉት የምጣኔ ሀብት ምሁሩ፣ ሕዝቡ ሥራ ከሌለው አቅራቢዎች እና አምራቾች ምርቶቻቸው ባለመሸጣቸው መጎዳታቸው አይቀርም። ይህም መልሶ ኢንቨስትመንትን የሚጎዳ ነው በማለት አብራርተዋል።

የድህነት ጉዳይ በርካታ ፖለቲካዊ አጀንዳዎችን የያዘ ጥያቄ ይነሳበታል። በኢትዮጵያም ለበርካታ ጊዜያት የድህነት ቅነሳ ፕሮግራሞች በፍትሃዊነት ያልተከፋፈሉ ናቸው የሚሉ ውዝግቦችን ሲያስነሳ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ሊቀ መንበር መረራ ጉዲና (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ድህነት ቅነሳን እና የሥራ ዕድል ፈጠራን የሚመለከቱ ጉዳዮች ከፖለቲካዊ አጀንዳዎች ጋር የተያያዙ ናቸው። የድህነት ቅነሳ ፕሮግራሞችም መንግሥት ሹመኞች (ካድሬዎች) ፖለቲካዊ ጥቅምን ለማግኘት የሚያደርጉት እንጂ፣ የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና ለውጥ ለማምጣት ያለመ አይደለም፤ እንደ መረራ ገለፃ።

ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት የተለየ ጥቅም ያገኙ አካባቢዎች አሉ የሚለውን ለማረጋገጥ ጥናት ይፈልጋል የሚሉት መረራ፣ በአጠቃላይ መንግሥት ቃል የገባውን ምጣኔ ሀብታዊ ለውጥ እያመጣ አይደለም ብለዋል። ባለፉት ዐስር ዓመታት የታየው የምጣኔ ሃብት ለውጥም በወረቀት ላይ ያለ እንጂ በሰዎች ኪስ ውስጥ ያልደረሰ ነው። ዜጎች በኑሮ ውድነት፣ በሥራ አጥነት እና በድህነት እንዲማረሩ ሆኗል ሲሉ ሐሳባቸውን አጋርተዋል።

ባለፉት ዐስርት ዓመታት ኢኮኖሚው ስለማደጉ ጥያቄ የሚያስናሳ አይደለም የሚሉት የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ወብን) ሊቀመንበር ኃይለሚካኤል ግዛው፣ ነገር ግን ዕድገቱ ሀብት ማፍራት ሲጀምር የተከፋፈለበት መንገድ ጥያቄ ያስነሳል ይላሉ። ለአብነትም በወላይታ ዞን ምንም አይነት የመንግሥት ኢንቨስትመንት አለመኖሩን የጠቀሱ ሲሆን፣ ይህም የሥራ አጥነት እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።
በኢትዮጵያ ማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ መሠረት፤ በኢትዮጵያ እድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆኑ ዜጎች ቁጥር 71 ከመቶ ይደርሳል። ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 34 ዕድሜ ያሉ ወጣቶች ቁጥር ደግሞ 25 ሚሊዮን የሚጠጋ ነው። እስከ 16 ነጥብ 5 በመቶ የሚያድግ የሥራ አጥነት እንዳለም ይነገራል። ምንም እንኳን ኢኮኖሚው በዕድገት ላይ ነው ቢባልም፣ በየዓመቱ በእጅጉ እየጨመረ ለሚመጣው ለዚህ አምራች ኃይል አቻ የሚሆን በቂ የሥራ ዕድል መፍጠር ግን አልቻለም።

በ2011 የወጣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ 77.8 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ወጣት ኑሮውን የሚገፋው በቀን ከኹለት ዶላር ባነሰ የገንዘብ መጠን ነው። በየዓመቱም ከኹለት ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በየዓመቱ ወደ ሥራ ፈላጊው የእድሜ ክልል ይቀላቀላሉ። በቀጣዮቹ ዐስር ዓመታትም አጠቃላይ የሥራ ፈላጊዎች ቁጥር ከ 90 ሚሊዮን በላይ እንደሚደርስ ይገመታል።

ከአርባ በላይ ከሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎችም በየአመቱ ከ150 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ይመረቃሉ። እነዚህ ሁሉ አገሪቷ ተጨማሪ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር እንዳለባት የሚያሳዩ ናቸው። ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ግን ድህነት ሊባባስ እንደሚችል ባለሙያዎች ያነሳሉ።

ድህነትን ለመቅረፍ ዘላቂ መፍተሄ
መንግሥት መዋሸት አይገባውም የሚሉት ዓለማየሁ ገዳ፣ እውነተኛው እና ትክክለኛው መረጃ ለዜጎች መቅረብ እንዳለበት በአፅንኦት ይናገራሉ። ይህ መሆኑም ዜጎችም ሆኑ ኢኮኖሚው ያለበትን ደረጃ በመገንዘብ፣ ተገቢውን ሥራ እና ጥንቃቄ ለማድረግ ያግዛል የሚሉት ባለሙያው፣ ዘርፉ በባለሙያዎች ሊመራ እንደሚገባው ሳያሳስቡ አላለፉም። ድህነቱንም ለመቀነስ በአነስተኛ መሬት ላይ የሚያመርቱ ገበሬዎችን መሰረት ያደረገ እንዲሁም ድህነት ተኮር መንገድ ሊኖር ይገባል፤ እንደ ዓለማየሁ ገለጻ። እነዚህ ገበሬዎች በአነስተኛ መሬት ላይም ቢሆን የተሻለ ምርት እንዲያመርቱ የሚያስችል የቴክኖሎጂ ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባም አያይዘው ገልጸዋል። በከተማ ለሚኖሩ ዜጎችም ተቋማት ወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታን ያገናዘበ እና ተቀጥሮ የሚሠራውን ዜጋ ያገናዘበ እና የተሻለ ገቢ እንዲያገኝ የሚያስችል መንገድ ሊፈለግ ይገባል ብለዋል።

አበበ መፍትሔ ብለው የሚያስቀምጡት መንግሥት ሕገ መንግሥቱን መሰረት አድርጎ መሥራት እንደሚገባው ነው። መብቶቹ የተከበሩለት ዜጋ ሰላሙን በራሱ መጠበቅ ይችላል ሲሉ የመፍትሔ ሐሳባቸውን ያቀርቡት አበበ፣ የሕዝቡን ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ሊመልስ የሚችል ፖሊሲ ሊቀርፅ እንደሚገባውም አብራርተዋል። ሌላው መፍትሔ ደግሞ ከውጪ አገራት የሚመጡ የግጭት አፈታት ዘዴች ላይ ብቻ ከመመርኮዝ ይልቅ፣ መንግሥት በአገሪቱ ያሉ አቅሞችን እና የግጭት አፈታት መንገዶችን ተግባራዊ ቢያደርግ የሚሉ ምክረ ሐሳቦችን አቅርበዋል።

የመቀሌ ዩኒቨርስቲው ምዑዝ ሀዲሽ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ መንግሥት የሚከተላቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ግልፅ ሊሆኑ ይገባቸዋል ይላሉ። አዲሱ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን የመመልከት እድል ገጥሞኝ ነበር የሚሉት ምዑዝ፣ ሐሳቡ ቁንፅል አጀንዳዎችን የያዘ ነው እንጂ እንዴት አድርጎ ለውጥ እንደሚያመጣ የሚዘረዝር አይደለም ሲሉ ሐሳባቸውን አጋርተዋል። አክለውም ኢትዮጵያ የምትከተለው ኢኮኖሚያዊ መንገድ ተገማች አይደለም ያሉ ሲሆን፣ መንግሥት ሰላሙን፣ ኢኮኖሚውን ተገማች እና የውጪ አልሚዎችንም ሊስብ የሚችል ማድረግ ይገባዋል ሲሉ ሐሳባቸውን ደምድመዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 65 ጥር 23 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here