‹‹የክልል መንግሥታት የሚፈጽሙት የመብት ጥሰት መንግሥት እንደፈጸመው ነው የሚቆጠረው››

0
915

ከ2010 አጋማሽ ጀምሮ በኢትዮጵያ የነፈሰው የለውጥ አየር በአገር ውስጥ ብዙዎችን በደስታ ሲያስተነፍስ፣ በውጪ ያሉ የተለያዩ ተቋማት ደግሞ ዐይናቸውን ጥለው የሆነውንና የሚሆነውን እንዲከታተሉ ጋብዟል። ያለ ፍትህ ታስረው የነበሩ መፈታታቸው፣ በብዙ የመብት ጥሰት ውስጥ የነበሩም መብታቸው እንዲከበርላቸው መደረጉንም መስክረዋል። ኢትዮጵያም በሰብአዊ መብት አጠባበቅ ትልቅ መሻሻል የታየባት፣ ከፖለቲካ ጋር የተገናኘም ሆነ የጋዜጠኛ እስረኛ የሌለባት ተብላ ተወድሳለች።

ይህ ሙቀት ዓመትም በቅጡ የዘለቀ አይመስልም። በአንድም በሌላም መልኩ አሁን ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በየቦታው እየተሰሙ ይገኛሉ። በደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበሩ ሴቶች ታግተዋል የሚለው ክስተትም ትኩሳቱን አብሶታል። በቅርቡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰት የደረሰበትን ደረጃ በሚመለከት ከቅኝቱ የተቀነጨበ ሪፖርት/ዘገባ አቅርቧል። በዚህ ዘገባ፣ በታገቱት ተማሪዎች ዙሪያና አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት የሰብአዊ መብት አጠባበቅ ዙሪያ አዲስ ማለዳ ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ቀንድ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች አጥኚ ፍስኃ ተክሌ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።

ታግተው ስላሉት ሴት ተማሪዎች ያለውንና የደረሰበትን ሁኔታ እየተከታተላችሁ ነው?
ከመጀመሪያ ጀምሮ እየተከታተልን ነበር። መጀመሪያ ሪፖርት ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ። ነገር ግን እንደሚታወቀው የመረጃ እጥረት አለ። ግልጽ የሆነ ነገር የለውም። ምን ያህል ናቸው፣ ማን ነው አጋቹ፣ መንግሥት ምን እያደረገ ነው የሚሉ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ። ምንአልባት የትላንትናው (ሐሙስ ጥር 20/2012) የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት መግለጫ የተወሰኑ ነገሮችን ያብራራ ይመስለኛል። ግን እሱም ቢሆን መጣራት አለበት።

ስለዚህ በዛ ምክንያት በይፋ ወጥተን ለመናገር የተወሳሰበ ሁኔታ ነው ያለው። ያልተረጋገጠ መረጃን ይዞ መውጣትን ስላልፈለግን ነው።

ግን እናንተ ጋር የደረሰ መረጃና በእናንተ በኩል የተደረገ ማጣራት አለ?
አዎን! በእኛ በኩል በራሳችን ያጣራናቸው ነገሮች የተወሰኑ ናቸው። ሁሉም የሚያውቀውን ነገር ነው ያጣራነው። የተወሰኑትን ሰዎች አግኝተን አናግረናል። ግን እነርሱም የሚሰጡን መረጃ ብዙ የተሟላ አይደለም። ብዙ ሰውም የተሟላ መረጃ የለውም። ታፍና የነበረችውና ያመለጠችው ልጅም ብትሆን፣ በጥቅሉ ብዙ መረጃ የላቸውም። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን በራሳችን በኩል ለማጣራት ያደረግነው ጥረት አለ።

ብሔር ተኮር ውጥረት ባለበት ሰብአዊ መብት ላይ ምን ዓይነት ተጽእኖ ይደርሳል?
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ረጅም ጊዜ ፈጅቷል፤ በተለይ ከ2017 ጀምሮ የታየ ነገር ነው። ብዙ የኦሮሞ ተወላጆች ተፋናቀሉ፣ ሕጻናትን ጨምሮ። ከዛ ጊዜ ጀምሮ ነው እየባሰ የመጣው። ከዛም ቤኒሻንጉል ላይ የነበረው፣ በጉሙዝና በአማራ ተወላጆች መካከል የነበረው ሁኔታ አለ። በደቡብ ክልልም በጉራጌ ዞን ጨምሮ ሸካ እና አማሮ ላይ ብዙ ቦታዎች እንዲህ ያሉ ነገሮች ተከስተዋል።
በዚህ ላይ ብቻ አተኩረው የሚሠሩ ድርጅቶች ባወጡት ዘገባ እንደውም በ2019 ብቻ ኢትዮጵያ ውስጥ 100 የሚደርሱ ብሔር ተኮር ጥቃቶች ነበሩ። ከነዛ ውስጥ ብዙዎቹን ማለት ባይቻልም፤ ያው በአቅም ውስንነት፤ የተወሰነውን እየተከታተልን ነበር።

አማራ ክልል ውስጥ ቅማንት፣ በትግራይ ክልል ውስጥ የአማራ ተወላጆች በወልቃይት አካባቢ የሚደርስባቸው ተጽእኖዎች በሙሉ፣ ሰዎች ላይ የሚደርሰው የእለት እለት የአካልና የሕይወት ጉዳት ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ እና ሌሎች እንደ ኢኮኖሚ ያሉ መብቶች ችግር ውስጥ ይገባሉ። የተፈናቀሉ ሰዎች በቂ እርዳታ ያገኛሉ ወይ? የሚለው ጥያቄ ነው። የትምህርት መብታቸው ይስተጓጎላል፣ ለጤና ያላቸው ተደራሽነት የቀነሰ ነው። እና እነዚህ ብሔር ተኮር የሆኑ ግጭቶች ብዙ ገጽታ ያላቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ይፈጥራሉ።

እና አሁን ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ነው። በዚህ ሁኔታ ደግሞ አገሪቷ ወደ ምርጫ እየገባች ነው። የበለጠ ምርጫ ሲመጣ ደግሞ እነዚህ ነገሮች እየተካረሩ እንደሚሄዱ ነው የሚያሳዩት። ስለዚህ አሳሳቢ ነው።

በዚሁ ከምርጫው ጋር በተገናኘ በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት በምዕራብ ኦሮሚያ ክፍሎች ተቋርጧል። የቴሌኮም አገልግሎት ሰብአዊ መብት ነው?
የቴሌኮም አገልግሎት የስልክ፣ ቴክስት፣ ኢንተርኔትና ኢንተርኔትን መሠረት ያደረጉ አገልግሎቶች በሙሉ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ናቸው። አንደኛ እነዛን ተጠቅመው ሰዎች ሐሳባቸውን መግለጽ ይችላሉ፤ በማኅበራዊ ሚድያ እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች። ኹለተኛው መረጃ የማግኘት መብት በራሱ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም በዓለም አቀፍ ሕጎችም የተረጋገጠ ነው።
ኢንተርኔት ደግሞ ይህን በማመቻቸት የታወቀ ትልቅ መድረክ (Platform) ነው። ፍጹም የሆነ መብት አይደለም። ሐሳብን የመግለጽ ወይም መረጃ የማግኘት መብትም ፍጹም መብቶች አይደሉም። ግን በሚገደቡበት ጊዜም መሟላት ያለባቸው መስፈርቶች አሉ። ሲገደቡም በታወቀና ግልጽ በሆነ በሕግ መሠረት መሆን አለበት። በተቻለ መጠንም በፍርድ ቤት መሆን አለባቸው።

የሚገደብበት ምክንያትም ለአገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም፣ መረጋጋት፣ ለሕዝብ ጤንነት እና ደኅንነት እንዲህ እንዲህ ለሚሉ ነገሮች ብቻ መሆን አለበት። ከዛ ውጪ ደግሞ አስፈላጊ ናቸው ወይ የሚለው መታየት አለበት። ምን ያህል ተመጣጣኝ ናቸው የሚለውም እንደዛው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ሁኔታ ያው ምክንያቱ ይነገረናል ግን በየትኛው ሕግ መሠረት ነው? እነዚህ የኢንተርኔት አገልግሎቶች ሲቋረጡ ምን ያህል ተመጣጣኝ ናቸው? የሚለውን የሚመዝን ነጻ የሆነ አካል የለም። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች የሚያሳስቡን ናቸው።

አዎን መብቶች ናቸው! መብቶችም በማመቻቸት ይታወቃሉ። እንደ መብትነታቸው ግን ብዙ ክብር ሲሰጣቸው አላየንም።

ከምርጫው ጋር በተያያዘስ ይህ ሊቀጥል ይችላል የሚል ግምት አለ?
ከምርጫ ጋር በተያያዘ እንግዲህ ሁሌም የምንለው ሰብአዊ መብቶች የበለጠ መከበር አለባቸው። እንጂ ምርጫ በመምጣቱ በመብቶች አለመከበር ምክንያት መሆን አይችልም። ያውም ምርጫ በሚኖርበት ጊዜ ሰዎች የመንቀሳቀስ መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል፣ ሐሳባቸውን የመግለጽ መብታቸውም ሊከበርላቸው ይገባል፣ የመሰብሰብ እና የመደራጀት መብታቸውም እንደዛው። ማኅበራዊ ሚድያ መድረኮችን መጠቀም መቻል አለባቸው። ለምርጫውም ግብዓት ናቸው።

እናም የበለጠ መከበር ነው እንጂ ያለባቸው ምርጫ መኖሩ እነዚህን መብቶች ለመገደብ ምክንያት እንዲሆን አንፈልግም። እንደዛም መሆን የለበትም። አሁን ያሉት አካሄዶች ግን እንደዛ ናቸው። ያ አሠራር ይቀጥላል አይቀጥልም የሚለውን ወደፊት የሚሆነውን መተንበይ አይቻልም። ግን መብቶች ይከበራሉ፣ ለመብቶች ትኩረት እንዲሰጥ ነው የምናሳስበው።

ቅድመ ግምት ሰጥታችሁ ይሆን፣ የምርጫው ሰሞን ከመብቶች ጋር በተያያዘ ሊኖረው በሚችለው ድባብ ዙሪያ?
መገመት ከባድ ነው። ግን አሁን ያሉ ነገሮች መስተካከል አለባቸው ብለን ነው የምናስበው። ወደፊት ችግር እንዳይኖር አሁን ያሉ አካሄዶች በዚህ መልክ መቀጠል የለባቸውም። ሰዎችን የመሰብሰብ መብት መከልከል የለብንም፣ ሐሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ መብታቸው በየትኛውም መልኩ ቢሆን ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ ሊገደብ አይገባም። መረጃ የማግኘት መብት እንደዚሁ ተገቢ ያልሆነ ክልከላ መቀጠል የለበትም። እነዚህ ነገሮች ሁሉ መከበር አለባቸው።

ይሄ ለምርጫው አስፈላጊ ከመሆኑ በላይ አገሪቱ ውስጥ ላለው ሰላምም አስፈላጊ ነው። መገመት ከባድ ነው ጥሩም ላይሆን ይችላል። ግን እነዚህ አሁን የታዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መቆም አለባቸው። ይህን የፈጸሙ ወገኖችም ላይ አስፈላጊውን ምርመራ አድርጎ ተገቢ በሆነ ሁኔታ በፍርድ ሂደት መዳኘት አለባቸው። የመንግሥት አካላት የሆኑ ይሁኑ ያልሆኑትም ቢሆኑ።

በመከላከያ እና በታጣቂዎች መካከል ጦርነት እንዳለ ነው አሁን ባለው ሁኔታ መረዳት የተቻለው። የጦርነት ሕግ ደግሞ አለ። እና ከመከላከያ ሠራዊት ምን ይጠበቃል?
ዓለማአቀፍ ግጭቶችና ዓለም አቀፍ ያልሆኑ ግጭቶች የሚተዳደሩባቸው የየራሳቸው ሕጎች አሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ እዛ ውስጥ ድርሷል ወይ ለሚለው ራሱ ትሬሽ ሆልድ አለው። እዛ ውስጥ ደርሷል ወይ ለሚለው አስተያየት መስጠት አልፈልግም። በዚህ ላይ የሚሠሩ አካላት አሉ፤ እንደ ዓለም ዐቀፍ የቀይ መስቀል ማኅበር ያሉ። እና እነርሱ ናቸው በዚህ ላይ ምላሽ የሚሰጡት።
አሁን ባለው ሁኔታ እነዛ ሕጎች ይተገበራሉ ወይ ብሎ ለማለትም መረጃ የለኝም። ግን አሁን እየተፈጸመ ያለው ነገር ጦርነትም ይሁን ሕግ የማስከበር ሂደት፣ ሁሉም አካሄዳቸው ግልጽ ነው። አንደኛ በሚደረጉ ግጭቶች ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል። ሕግ የማስከበርም ይሁን ጦርነት፤ እዛ ውስጥ የሌሉበትን ሰዎች ሰለባ ማድረግ የለበትም።

ከድርጊቱ ጋር ያልተያያዙ ሰላማዊ ሰዎች ተገቢ ያልሆነ እስር ሊደረግባቸው አይገባም። የማዋከብ ድርጊቶች መቀነስ አለባቸው። እነዚህ ነገሮች አሉ ማለት የሰብአዊ መብት ግዴታዎች ይጠፋሉ ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል። ግን ሁኔታው በሚመጥነው መልኩ ነው ሊገደብ የሚገባው።

ለምሳሌ ወለጋ ላይ ወደ 4 ሳምንት የኢንተርኔት አገልግሎትና የስልክ ግንኙነት የለም። ወደ ደቡብ ጉጂ ለረጅም ጊዜ አንድ ዓመት ለሚሞላው ጊዜ ገጠር አካባቢ ያሉትን ሰዎች ሞባይል ይቀማሉ። የአካባቢው ሚሊሻዎች ነዋሪዎች ስልክ ሲያወሩ ሲያዩ እንዲሁም ስብሰባ እየጠሩ ይወስዱባቸዋል።

ይህ ራሱ ትክክል አይደለም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ በሌሎች ሰዎች ላይ ጭምር ጅምላ የሆነ የመብት ጥሰት ማካሄድ ተገቢ አይደለም፤ መስተካከል አለበት።

ከዚህ ጋር በተያያዘ እናንተ ጋር የደረሰ ተጨባጭ ማስረጃ ይኖር ይሆን?
አዎን! ሰሞኑን ያወጣነውን መረጃ ተከታትላችሁ ከሆነ፣ በዚህ በወለጋ አካባቢ የጅምላ እስሮች አሉ። ጉጂም ላይ እንደዚሁ ብዙ ሰዎች ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሲታሰሩ ነበር። ፍርድ ቤት አይቀርቡም፤ ክስም አይመሰረትባቸውም። በኢትዮጵያ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ሕግ አንድ ሰው በተያዘ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ አለበት፤ ያ ግን አይፈጸምም። የተከሰሱበት ወንጀል አይታወቅም። አንዳንዱቹ በዋስ አንዳንዶቹ ያለ ዋስ ይለቀቃሉ። በተደጋጋሚ የታሰሩ ሰዎችም አሉ።

በቅርብ የታሰሩ ሰዎች ባለፈው ዓመት ሰንቂሌ እና ጦላይ ማሠልጠኛ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ታስረው የቆዩ ናቸው። እና በምን እንደተከሰሱ እንኳ አይታወቅም።
ብዙ ዓይነት የመብት ጥሰቶች አሉ። ጉጂ አካባቢ ላይ ከገጠር ተፈናቅለው ወደ ከተማ እንዲሰባሰቡ የተደረጉ ሰዎች አሉ። የሸኔ ደጋፊ ናችሁ ተብለው ቤታቸው የተቃጠለ፣ ከብቶቻቸው የታረዱ ብዙ ሰዎች አሉ። እንዲህ ያሉ መረጃዎች አሉን።

የሕግና የፖለቲካ አካሄድ ተቀላቅሎ እየታየ ነው። ይህን እንዴት ታዘቡት?
ሰብአዊ መብቶች በሕገ መንግሥትም ሆነ ዓለም አቀፍ ሕጎች ላይ በተቀመጡበት መልኩ፣ የመንግሥትን ባህርያት የሚገዙ መሆን አለባቸው። የፖለቲካም ይሁን ኢኮኖሚያዊ ወይም ማንኛውንም ድርጊት የሚገዙ መሆን አለባቸው። ‹ይህ ነገር የፖለቲካ ነው፤ ስለዚህ ያለ ሕግ ትታሰራለህ፤ ወይም ደግሞ ታስረህ ያለ ፍርድና ክስ ቤተሰብህን ሳታገኝ ትቆያለህ› የሚል ነገር የለም።
አንድ ሰው ሊታሰር ይችላል፤ በወንጀል ከተጠረጠረ። ፖለቲካ የሚለው ነገር ለዚህ ማስተማመኛ አይሆንም። አንድ ሰው መታሰር ያለበት በወንጀል ከተጠረጠረ ብቻ ነው። እና ደግሞ በፍርድ ሂደት ማለፍ አለበት። ስለዚህ ይህ መቀላቀል የለበትም።

ቀለል አድርገን ስናየው፤ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ላይ የተቀመጡ መብቶች ናቸው፤ ሌሎቹ የምንተዋቸው የዓለም አቀፍ ሕጎች። እዛ ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የሁሉም የበላይ ነው ይላል፤ ለኢትዮጵያ ፖለቲካም፣ ማኅበራዊውም ወዘተ፤ ያንን የሚጥስ የለም። ስለዚህ ሕገ መንግሥት ላይ የተቀመጡ መብቶች በሙሉ በማንኛውም ምክንያት ሊጨፈለቁ አይገባም።

አሁን የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳለ ይታያል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በሰብአዊ መብት አያያዝ ኢትዮጵያ ደኅና ሁኔታ ላይ ነች ተብሎ ነበር። አሁን ወደኋላ እየተመለሰች ይሆን?
አዎን! አቅጣጫውን ስናይ የተገኙ ድሎች ወይም የሰብአዊ መብት እርምጃዎች ወደኋላ እየሄዱ ይመስላል። ወይም ደግሞ እየተሸረሸሩ ይመስላል። ያ ደግሞ የሚያሳስብ ጉዳይ ነው። ለውጡ በተካነወነበትና ብዙዎች ያለአግባብ ከሆነ እስር በተለቀቁ ጊዜ፣ ሕዝቡ በጣም ተደንቆ ነበር። እኛ ብቻ ሳይሆን ዓለም ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብም ደስ ብሎታል።

አሁን ደግሞ እንደገና ወደ ጅምላ እስር፣ ማፈናቀል የሚሄደው ነገር ወደ ኋላ እንዳይመለስ የሚያሰጋ ነው። ይህ ነገር መቆም አለበት፣ ጅምላ ፍርድ ይሁን ግድያና ያለ ፍርድ ማሰር መቆም አለባቸው ነው የምንለው።

በፊት ጨቋኝና ተጨቋኝ ይታወቃል፤ መንግሥትና ሕዝብ ነው። አሁን ግን በመሃል ‹የማይታወቁ አካላት› አሉ። በዚህ ላይ የሕግ ስርዓቱ በምን መንገድ ነው የሚሄደው?
የሕግ ስርዓቱ በዚህ ላይ ግልጽ ነው። ሰብአዊ መብት ስንል አንደኛ መንግሥት የማክበር ግዴታ አለበት፤ ራሱ። ሌላው ደግሞ የማስከበር ግዴታ አለበት። ይህ ማለት ከመንግሥት ውጪ ያሉ አካላት ይህንን የመብት ጥሰት ሲፈጽሙ መከላከል አለበት ማለት ነው።

የተደራጁ አካላት፣ ወንጀለኞች ወይም ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይሁኑ፣ መንግሥት እነዚህ አካላት ወንጀል እንዳይፈጽሙ የመከላከል ግዴታ አለበት። ሕግ የማክበር ሥራ ማለት ነው።
በፊት ላይ ምንአልባት ግልጽ ነበር፤ ከ2018 በፊት የነበረው ሁኔታ። ብዙዎቹን የመብት ጥሰቶች የሚፈጽሙት የመንግሥት አካላት ነበሩ። ስለዚህ መንግሥት ያንን የማክበር ግዴታውን አልተወጣም ነበር። አሁን ደግሞ የማስከበር ግዴታውን አለመወጣት ነው የምናየው። የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ያልሆኑ፣ ኅቡዕ ሊሆኑ ይችላሉ ወይም በራሳቸው የተደራጁ መደበኛ ያልሆኑ አደረጃጀቶች ሊሆኑ ይችላሉ፤ አንዳንድ ቦታዎች ላይም የክልል መንግሥታት አካላት ሊሆኑ ይችላሉ።

እነዚህ አካላት የመብት ጥሰት በሚያደርጉበት ጊዜ መንግሥት የመከላከል ግዴታ አለበት። በነገራችን ላይ የክልል መንግሥታት የሚፈጽሙት የመብት ጥሰት መንግሥት እንደፈጸመው ነው የሚቆጠረው። ዓለም አቀፍ ሕጉ ሆነ ሕገ መንግሥቱ እንደ መንግሥት አካል ነው የሚያያቸው።

‹‹አይ የእንትን ክልል ፖሊስ ነው የፈጸመውና የኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊነት አይደለም›› ማለት አይቻልም። አጠቃላይ እንደ አገር ነው የሚታየው። አገሪቷ ሰብአዊ መብትን ማክበር አልቻለችም ነው የሚባለውም።

ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አዲስ ኮሚሽነር ተሾሞለታል። ያንን ተከትሎ ብዙ ለውጥ ተጠብቆ ነበር። ግን ሪፖርቶች ሲወጡ አናይም። በቦታ ላይ ያሉ ባለሥልጣናትና የሚመለከታቸው ጉዳዩን ምን ያህል ትኩረት ሰጥተዋል?
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ራሱን የቻለ ድርጅት ነው። ምንአልባት እንደሚታወቀው አዲስ ኮሚሽነር ከተሾሙ ዓመትም አልሞላውም። ባለፈው ሰኔ ላይ ስለ ኮሚሽኑ ሥራ አፈጻጸም አንዳንድ ጥያቄዎችን አንስተን ነበር። በመደበኛ ሁኔታ በኮሚሽኖችና ሰብአዊ መብት ተቋማት አፈጻጸም ላይ አስተያየት አንሰጥም።

ግን ባየነውና በምናውቀው ኮሚሽኑ አዲስ ኮሚሽነር ቢሾምለትም ብዙ ተግዳሮቶች እንዳሉበት ነው። ኮሚሽነሩን ማድነቅ አለብን፤ በጣም ብዙ ነገር መጠበቅ እንዳለብን አይሰማኝም። ምክንያቱም ኮሚሽኑ ለረጅም ጊዜ ገለልተኛ ሳይሆን የቆየ፣ አቅሙን ያላጎለበተ ድርጅት ነው።

እናም በእኔ ግምት ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የውስጥ ማሻሻያዎችን ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነ አውቃለሁ። እና በዛ ምክንያት ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ። ግን በዚህ ጉዳይ ላይ በተለይም ኮሚሽኑ ሪፖርት አላቀረበም በሚለው ዙሪያ ራሳቸውን ኮሚሽነሩን ማናገር የተሻለ ይሆናል።

ተጽእኖ ፈጣሪ የምንላቸው ሰዎች ብዙ ትኩረታቸው ፖለቲካዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ ነው፤ ሰብአዊ መብቶች ላይ ምን ያህል ትኩረት ተሰጥቷል ይላሉ?
እኔ ዴሞክራሲያዊ የሚባል መብት አላውቅም፤ ዓለም አቀፍ ሕግም አያውቀውም። መብቶች በሙሉ ሰብአዊ መብቶች ናቸው ነው የምንለው። እና የኢትዮጵያ መንግሥት ሕገ መንግሥትን ተከትሎ የመጣ መረዳት እንደሆነ አውቃለሁ። ግን በአጠቃላይ ሰብአዊ መብቶች በሙሉ የማይከፋፈሉ፣ የማይነጣጠሉ እና ለሁሉም የተሰጡ መብቶች እንደሆኑ ነው የምናውቀው፤ ዓለም አቀፍ ሕጉም የሚለው ያንን ነው።

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ላይ ሰብአዊ መብት እና ዴሞክራሲያዊ መብት ብሎ ያስቀመጠው ክፍፍል ትክክለኛ አይደለም። እሱ መስተካከል ያለበት ነው። ይህን መረዳት ብዙ ቦታዎች ላይ ስለምመለከት በዚህ ላይ አስተያየት መስጠት እፈልጋለሁ።

ከዛ ውጪ ተጽእኖ ፈጣሪ የተባሉ ሰዎች ትኩረታቸውን በሰብአዊ መብቶች ላይ አላደረጉም፤ ለምን ሰብአዊ መብት ላይ አልሠራችሁም ልንል አንችልም። የምርጫ ጉዳይ ነው። ሰዎቹም በራሳቸው ትኩረት የሚሰጡት ነገር ይኖራል።

ግን አንደኛው መታየት ያለበት ነገር ማንኛውም በዚህ ጉዳይ ላይ አክቲቪስት ነኝ፣ ተጽእኖ ፈጣሪ ነኝ የሚል ሰው ለሰብአዊ መብቶች በሙሉ መቆም አለበት። ኹለተኛ ለዚህኛው ወገኔ ለዚያኛው ወገኔ ማለት የለበትም። ሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ለአንዱ ሃይማኖት ወይም ለአንዱ ብሔር ብቻ የተሰጡ አይደሉም፤ ለሁሉም የተሰጡ ናቸው።

ሌላው ደግሞ የአንደኛው ወገን መብት ካልተከበረ የሌላኛው መብት አይከበርም። ዛሬ የመብት ጥሰት የተፈጸመበት ነገ ደግሞ እንደ ‹ደም መላሽ› ወይም ተበቃይ እንቅስቃሴ ውስጥ ይገባል። ስለዚህ ለእኔ ወገን ሰብአዊ መብቱ እንዲከበርለት ለሌላውም ወገን እንደዚሁ መከበር አለበት። እና ሁሉን አቀፍ የሆነ አተያይ ቢኖራቸው የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ።

በየጊዜው አዳዲስ የሚወጡ እንዲሁም የሚሻሻሉ ሕጎች አሉ። እነዚህ ሕጎች ሰብአዊ መብትን ያከበሩ መሆናቸውን ትከታተላላችሁ?
አዎን! በተወሰኑት ላይ እንደውም ተሳትፈናል። ያው የኮሚቴ አባል ባንሆንም ሐሳብና አስተያየት በመስጠት ተከታትለናል። ከእነዚህ ውስጥ በጣም ጥሩ የሚባለው የሲቪል ማኅበራት ሕግ ነው። አንድ ዓመት አካባቢ ሆኖታል። እሱ በጣም ጥሩ ነበር፤ እኛም ጥሩ ተሳትፈናል።

በቅርቡም የጸደቀው የፀረ ሽብር አዋጅ አለ። እሱም ቢሆን በፊት ከነበረው አንጻር ብዙ እመርታ ያሳየ፣ የተሻለ ሕግ ነው። አሁንም ግን የተወሰኑ የሚነሱ ጉዳዮች ይኖራሉ። ለምሳሌ የሞት ቅጣት አለበት። ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ የሞት ቅጣት ሊያስቀጣ የሚችል ጥፋት አድርጎ ያስቀምጠዋል። ማስፈራራት የሚልም አለ። እንዲሁም የውሸት የሽብር ጥቃት ያለ አስመስሎ ማቅረብ ብሎም የሚቀጣው ነገር አለ።

እነሱ ገደብ ሊኖራቸው ይገባል። አለበለዚያ የሰዎችን ሐሳብ የመግለጽ መብት ሊገድብ ይችላል። ትንሽ አሻሚና ግራ የሚያጋቡ ነገሮች አላቸው።

ከዛ ውጪ ግን በተለይ ከበፊት አንጻር ስናየው ብዙ እመርታዎች አሉት። በፊት የነበረው ሕግ ለምሳሌ ከፍርድ በፊት ሰው ለአራት ወር እንዲታሰር ይፈቅድ ነበር። ዋስትና የማግኘት መብትንም ይከለክል ነበር። እነዛ ነገሮች አሁን ተነስተዋል።

ሰሞኑን የኦነግ 75 አባላት በፖሊስ መያዛቸውን አስመልክቶ የአምነስቲ ኢንተርነሽናል ባልደረባ ያወጡት አጭር መልዕክት ነበር። ከግንባሩ ጋር ይሁን ከታጣቂው ጋር ግን በግልጽ አልተጠቀሰም።

ጫልቱንም ጠቅሶ ነው የሰፈረው። እና ሪፖርቱ ትክክል ነው ወይ በሚለው ላይ ጥያቄ እየተነሳ ነው፤ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
እኛ እስከምናውቀው የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር የሚባለው አካል በሰላማዊ መንገድ ለመታገል አገር ውስጥ ገብቷል። በይፋ የሚታወቅ ድርጅት እሱ ነው። ጫካ ውስጥ የሚታገሉት ሥማቸው አይታወቅም፤ ኦነግም በተለያየ ጊዜ ‹የሚታገል አካል የለኝም፣ የእኛም አይደሉም› ብለው በይፋ ገልጸዋል። ስለዚህ ኦነግ የሚለው ቃል ከዛ ጋር በተገናኘ ነው።

ስለዚህ ጫልቱም እንደ ግንባሩ አባል እንጂ እንደ ታጣቂው ቡድን አባል አይደለም የተጠቀሱት ማለት ነው?
ወይዘሮ ጫልቱ የታጣቂው ቡድን አባል ብትሆን ኖሮ፣ ከተማ ውስጥ ከቤተሰቦቿ እየኖረች አናገኛትም ነበር። ወይም ደግሞ ከመሪው (ጃልመሮ) ጋር ያላት ግንኙነት ደግሞ በቂ ምክንያት አይደለም። አንድን ሰው ለማሰር ‹ባለቤትሽ ጫካ ነውና በዛ ምክንያት ትታሰሪያለሽ› የሚል ነገር የለም።

ከዚህ ጋር ሌላው ማብራራት የምፈልገው ነገር፣ ምንአልባት ጫልቱ በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲህ ብላለች የሚል ነገር ካለ፤ እስከ ትላንት ስንከታተል ነበር፤ አንደኛ ፍርድ ቤት አልቀረበችም። በምን እንደተጠረጠረች እንኳ አታውቀውም። የተያዘችበት መንገድም ትክክል አይደል። መግለጫው ላይ ስላላሰፈርነው እንጂ ንጋት 11 ሰዓት ላይ የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ አጥር ዘልሎ በመግባትና ቤት በመስበር ነው የተያዘችው።

መያዟ አስፈላጊ ነው ቢባል እንኳ፣ ከዛ በኋላ የነበሩት የሰብአዊ መብት አጠባበቆች ትክክል አልነበሩም። ስለዚህ ይህ አንዱ ነው።

ኹለተኛ መግለጫውን በደንብ ካያችሁት፤ አባላት አይልም። የሚለው ደጋፊ ተብለው የሚገመቱ ወይም መንግሥት ደጋፊ ናቸው ብሎ ያሰባቸውን ሰዎች ተያዙ ነው። እንጂ አባላት ታሰሩ የሚል አይደል። አባል ለመሆናቸውም እኛ መረጃ የለንም።

ግን በተለያየ ጊዜ እነዚህ ሰዎች ሲታሰሩ የሚነገራቸው ነገርና አሁንም ሲታሠሩ የሚነገራቸው፤ የኦነግ ደጋፊ ናችሁ ተብለው ነው የሚታሰሩት። ሌላው ጫካ በሚታገለውና በግንባሩ መካከል በመንግሥት በኩልም ግልጽ ልዩነት ያለመፍጠር ነገር አለ። ምንአልባት ከተማ ላይ ይሆናል እንጂ፣ ብዙ ሰዎች ሲታሰሩ የኦነግ ሸኔ ደጋፊዎች ናችሁ ተብለው ነው።

እናም ያ ግራ መጋባት በመንግሥት አካላት በኩል አለ። እኛ በምናውቀው በይፋ ኦነግም እንደገለጸው፤ በጫካ የሚታል ሠራዊት የለኝም ብሏል። ስለዚህ ራሱን አለያይቷል።

የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መብቶቸ ላይ ቢያተኩሩም ሪፖርቶቻችሁ ግን ፖለቲካ ላይ ብቻ ያተኮሩ ይመስላሉ። ለምንድን ነው እዚህ ላይ ብቻ ለማተኮር የተፈለገው?
ቀደም ብዬ እንዳልኩት፣ ሰብአዊ መብቶች አንደኛው ከአንደኛው የማይነጣጠል እርስ በእርሳቸውም የሚገናኙና አንደኛው አንደኛው ላይ ተጽእኖ የሚፈጥሩ ናቸው። ምንአልባት በቅርቡ ባወጣናቸው ዘገባና መግለጫ ላይ አጫጭር ስለሆኑ፣ ያንን ሁሉ ነገር ለመዘርዘር ጊዜና ቦታ ላይኖር ይችላል።

ግን በቅርብ የምናወጣቸው ረዘም ያሉ ሪፖርቶች ይኖራሉ። በእነዚህ መግለጫዎች ላይ በዜጋና ፖለቲካዊ መብቶች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ኢኮኖሚ፣ የባህልና ማኅበራዊ መብቶች ላይም ያተኮሩ፣ ሴቶች፣ ወጣት ሴቶችና ሕጻናት ላይ የተፈጠሩ ተጽእኖዎችን ያካተተ ይሆናል። ግን ባለን ቦታ ያችን ብቻ ማካተት ስለቻልን ነው።

ኹለተኛ መሠረታዊ ምክንያት የሚባል ነገር አለ። አንድ አካባቢ ላይ መንግሥት በሚወስደው ወይም ሌላ አካል በሚወስደው እርምጃ ሰዎች ሲታሰሩ እና ቤተሰብ ሲፈናቀል፤ በዛ ምክንያት የመማርና ጤና የማግኘት መብት ችግር ላይ ይወድቃል። እና ዋናው መሠረታዊ ሰበብ ላይ የማተኮር ጉዳይ ሊኖር ይችላል።

እና አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ሁኔታ በዜጋና ፖለቲካዊ መብቶች ላይ ያተኮሩ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ውጤቶች ናቸው። ከዛም አንጻር ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 65 ጥር 23 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here