በቀጣዩ ሳምንት በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የመጨረሻው ስምምነት ሊደረስ እንደሚችል ተገለፀ

0
1028

ኢትዮጵያ፣ግብፅ እና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በቀጣዩ ሳምንት ከስምምነት ሊደርሱ ይችላሉ ሲል የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

ከዓለም ባንክ እና ከአሜሪካ መንግስት ጫናዎች ካሉ እንዲገልፁ የተጠየቁት ኢኒጅነር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር ) ሁልጊዜም ጫና ይኖራል ነገር ግን ኢትዮጵያ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ ከባድ ጉዳት ሳታደርስ ውሃውን መጠቀም ነው የምትፈልገው ብለዋል።

‹‹እንደዚህ ዓይነት ትልቅ ድርድር ይቅርና ማኛውም የተለያየ ፍላጎት ያለበት ውይይት ሲኖር ጫና የማሳደር ነገር አይቀርም›› ሲሉ ኢንጂነሩ ትላንት ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልፀዋል።

ከአንድ ሳምንት በፊት በአሜሪካ ዋሽንግተን በተደረገው የሦስቱ አገራት ስብሰባ ላይ በውይይቱ 11ኛ ሰዓት ላይ ሰፊ የሚባሉ ልዩነቶች ጠበዋል ያሉት ኢንጂነሩ በስምምነቱ የመጨረሻ ረቂቅ ላይም በቀጣይ ሳምንት በዋሽንግተን ሚኒስተሮች ውይይት እንደሚደረግ እና ስምምነት ላይ ይደረሳል ተብሎ እንደሚገመትም ተናግረዋል።

የሦስቱም አገራት የሕግ ቡድን አባላት ወደ አገራቸው ሳይመለሱ እዛው አሜሬካ በመሆን የመጨረሻውን ስምምነት እያረቀቁ ሲሆን ብቃት ያላቸው አምስት የኢህግ በለሞያዎች ከቴክኒክ ቡድን አባላት ጋር በመሆን በአራት ነጥቦች ላይ ያተኮረ ውይይት እያደረጉ ነው።

‹‹ይህ ስምምነት በጣም የምንቸኩልበት ወይም በጣም ወደ ኋላ የምንቀርበት ጉዳይ አይደለም ተጠንቅቀን በቻልነው ፍጥነት ግድቡን ለማጠናቀቅ እና በየአመቱ የምናጣውን አንድ ቢሊዮን ዶላር ወደ ስራ ለማስገባት እንሰራለን›› ሲሉም ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ በተለይ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት የድርቅ ትርጉም ላይ ግብጽ ያቀረበችው የአባይ ወንዝ በአመት ከ 40 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በታች የሚለው ላይ በተደረገ ድርድር ከ 37 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በታች ከሆነ ድርቅ እንዲባል ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here