ዳሰሳ ዘ ማለዳ (ጥር 27/2012)

0
1005

የውሃ መሰረተ ልማት ላይ ባእድ ነገር የጨመሩ ተጠርጣሪዎች እጅ ከፍንች ተያዙ

………

ባለቤትነቱ  የአዲስ አበባ ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን የሆነ የፍሳሽ መሰረተ ልማት ላይ ባእድ ነገር ሲጨምሩ የተገኙ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ባለስልጣኑ አስታወቀ፡፡ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት የፋብሪካ ተረፈ ምርት በቦቴ ተሸከርካሪ በማጓጓዝ በባለስልጣኑ የፍሳሽ መስመር ውስጥ ሲደፉ በመገኘታቸው ነው፡፡ጥር 24 ቀን 2012 ዓ.ም ከምሽቱ 5 ሰዓት ላይ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት በተለምዶ ጠማማው ፎቅ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ባእድ ፍሳሹን ወደ መስመር ሲጨምሩ የተገኙ ሁለት ግለሰቦች ከነተሸከርካሪው በጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑን የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ ወ/ሮ ሰርካለም ጌታቸው ተናግረዋል(ኢቢሲ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ 22 መዞሪያ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ትላንት ከእኩለ ለሊት በኋላ በተፈጠረው ችግር ለወጣቶች ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑ አካላት ተጠያቂ እንደሚሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ተናገሩ።“እነዚህን ወጣቶች ለማጣት ያበቁንን በየትኛውም ወገን ያሉ የጥፋቱ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ እናደርጋለን” ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ገልጸዋል፡፡ በድርጊቱ ማዘናቸውን በመግለጽም ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል። (ፋና ቲቪ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተገናኘ ወደ ቻይና በረራ ማቆሙ ዋስትና እንደማይሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ተናገሩ።አየር መንገዱ ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተገናኘ ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ እንደማያቋርጥም ዋና ስራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል፡፡አየር መንገዱ በትራንዚት ከሌሎች መዳረሻዎቹ በርካታ ቻይናውያንን እንደሚያጓጉዝም ጠቅሰዋል።መፍትሄው ለደንበኞች እና ሰራተኞች ጤንነት ጥንቃቄ ማድረግ ብቻ ነው ሲሉም አስረድተዋል።(ፋና ቲቪ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በቡኖ በደሌ ዞን ዴዴሳ ወረዳ ትናንት ምሽት በደረሰ የትራፊክ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት ማለፉን የዞኑ ፖሊስ  አስታወቀ። የዞኑ  የትራፊክ ደህንነት ዲቪዥን አስተባባሪ ኢንስፔክተር በኃይሉ ገዛኸኝ እንደገለፁት አደጋው የደረሰው የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-80032-ኢት የሆነ የጭነት ተሽከርካሪ በመገልበጡ ነው ብለዋል ።ተሽከርካሪው ሰዎችና እህል ጭኖ ከበደሌ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ እንዳለ በወረዳው መዲና ደምቢ ሲደርስ መገልበጡንም ተናግረዋል።(ኤዜአ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በማእከላዊ ጎንደር የኪንፋዝ በገላ ወረዳ እናቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሃኒት ለማግኘትም ሆነ የነፍሰጡር ምርመራ ለማድረግ የሶስት ሰአት የእግር ጉዞ ለማድረግ እየተገደዱ መሆናቸውን ተናገሩ። ችግሩ የተከሰተው በወረዳው በሚመደቡ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ፍልሰት እንደሆነ ተነግሯል።በወረዳው የወርቄ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ጎዳዳ የሻንበል እንደተናገሩት በቀበሌው ተመድበው የነበሩ የጤና ባለሙያዎች በመልቀቃቸው ምክንያት የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሃኒት አቅርቦት ከተቋረጠ ሁለት አመት አልፎታል ብለዋል፡፡በዚህ ሳቢያም በመውለድ የእድሜ ክልል የሚገኙ ሴቶች አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ወረዳው ዋና ከተማ ስላሬ የሶስት ሰዓት የእግር ጉዞ ለማድረግ እንደተገደዱ አስታውቀዋል ፡፡(ኢዜአ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በአደራ እንዲጠብቅ የተሰጡትን ንብረቶች የሰረቀው ግለሰብ በ8 ዓመት ተኩል   እስራት ተቀጣ፡፡ ተከሳሽ ግዛቸው ገነነ የማይገባውን ብልፅግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ፤ የሰው ንብረት እንዲጠብቅ አደራ ተቀብሎ እያለ ከሌሎች ግብረአበሮቹ ጋር በመሆን ከባድ የስርቆት ወንጀል በመፈፀም ተፈርዶበታል፡፡ ነሀሴ 16/2011 በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋአካና ባርና ሬስቶራንት ግቢ ውስጥ የጥበቃ ሰራተኛ ሆኖ በመስራት ላይ እያለ የዚሁ ባርና ሬስቶራንት ንብረቶችን ካልተያዙ ግብረ አበሮቹ ጋር በመኪና ጭነው የወሰዱ በመሆኑ በስርቆት ወንጀል ተከሶ ነበር፡፡ በአጠቃላይ 194 ሺህ ብር የሚገመቱት ንብረት ዘርፈዋል ሲል አቃቤ ህግ ክስ መስርቷል፡፡ ክሱን የተመለከተው የፌዴራልሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በተከሳሽ ግዛቸው ገነነ ላይ 8 አመት ከ6 ወር የእስራት ቅጣት ወስኖበታል፡፡(የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በደቡብ ክልል ቴፒ ከተማ በተነሳ ግጭት የ ስምንት ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን ከ20 በላይ ደግሞ የተለያየ ጉዳት ደረሰባቸው፡፡ ግጭቱ ትናንት አመሻሽ አካባቢ የደቡብ ክልል ልዩ ፖለስ አባላት በአንድ ግሮሰሪ ውስጥ በመዝናናት ላይ የነበሩና በህግ ይፈለጋሉ ያሏችውን ግለሰቦች ለመያዝ መሞከራቸውን ተከትሎ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ በከተማው ከርጫ በር በተባለው ሰፈር በጸጥታ አባላቱና ተጠርጣሪ በተባሉ ግለሰቦች መካከል የተከሰተው አለመግባባት ወደ ሁከት በማምራት ወደ ሌሎች የከተማዋ ክፍሎች መዛመቱን ነዋሪዎች ተናግረዋል። ለሰዓታት የዘለቀ የተኩስ ልውውጥ መካሄዱንና አስከአሁንም ስምንት ሰዎች በጥይት ሲሞቱ ከሃያ በላይ የሚሆኑ መቁሰላቸውን በአካባቢው ነበርን ያሉ የአይን አማኞች ገልጸዋል። ከሟቾቹ መካከል አንዱ የክልሉ ልዩ ሀይል የጸጥታ አባል ሲሆን የተቀሩት ሰባቱ የከተማው ሲቪል ነዋሪዎች ናቸውም ተብሏል፡፡(ዶቼ ቨለ)

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here