ንግድ እና ኢንዱስተሪ ሚኒስቴር ለ 20 ዓመታት የተገለገለበትን ሕንፃ ሊለቅ ነው

0
1129

ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከልማት ባንክ በመከራየት ከ20 ዓመታት በላይ ሲገለገልበት ከነበረው እና በባንኩ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከሚገኘው ባለ ስምንት ወለል ሕንጻ ሊለቅ እንደሆነ አስታወቀ።
ባንኩ አገልግሎቶችን ለደንበኞች አመቺ በሆነ መልኩ ለመስጠት የቦታ ጥበት እንደገጠመው የገለጸ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የባንኩን የሥራ ክፍሎች ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት በመሰብሰብ ላይ በመሆኑ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሕንጻውን እንዲለቅ መደረጉ ተገልጿል።

ልማት ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ ከዋናው መሥሪያ ቤት ውጪ አምስት የሥራ ክፍሎች እና 12 ዲስትሪክቶች እንዲሁም ከ 88 በላይ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች ደግሞ በመላው አገሪቱ ያሉት ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከ 2 ሺሕ 500 በላይ ሠራተኞችን በማስተዳደር ላይ ይገኛል።

በዋናው መሥሪያ ቤት የሠራተኞች ቁጥር በመጨመሩ፣ የቢሮ ጥበት በመኖሩ እና ተበታትነው የሚገኙ የሥራ ክፍሎችን ለማሰባሰብ ባለው እቅድ መሰረት የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሕንጻውን እንዲለቅ መደረጉን የባንኩ አገልግሎት ክፍል ኃላፊ ሰሎሞን መገርሳ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

‹‹አሁን የልማት ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ያለበት ሕንጻ አምስት ወለሎችን ያያዘ ነው። ነገር ግን ባንኩ ከሚሰጠው አገልግሎት እና ካለው የሠራተኛ ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ አይደለም›› ያሉት ኃላፊው፣ አክለውም ‹‹ከንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር ሕንጻውን እንዲለቁ ወስነናል›› ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከ20 ዓመታት በላይ ሕንጻውን በካሬ ሜትር 200 ብር እየከፈለ ሲገለገልበት ቆይቷል። ሚኒስቴሩ በአጠቃላይ 6 ሺሕ 300 ካሬ ሜትር የሚሸፍን ስፍራ ተከራይቶ በወር 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ለባንኩ ሲከፍል መቆየቱም ታውቋል።

ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ ልማት ባንክ ሕንጻውን እንዲለቁ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት አዲስ የሥራ ቦታ ለማግኘት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል።
የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዴኤታ እሸቴ አሰፋ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ የንግድ እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ተዋህደው በጋራ እንዲሠሩ ከተደረገ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል። መሥሪያ ቤቶቹ በተራራቀ ቦታ ላይ መሆናቸው ለሥራ አስቸጋሪ ሆኖ ነበር ብለዋል።

ኹለቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች መቀላቀላቸውን ተከትሎ፣ ሠራተኞችን ሊይዝ የሚችል እና ለአገልግሎት ምቹ የሆነ ቢሮ በማስፈለጉ፣ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ወደ ሌላ ቦታ በመሸጋገር ላይ እንደሆነ ገልጸዋል። ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በስሩ ከአንድ ሺሕ በላይ ሠራተኞችን በማስተዳደር ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

‹‹በቀጣይ ኹለት ዓመታት አራት ኪሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ለፊት እያስገነባን ያለነውን የራሳችን የሆነውን ሕንጻ እናጠናቅቃለን። ሕንጻው ለመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዩች ሚኒስቴር ሊገነባ ተጀምሮ የነበረ ነው። አሁን ለእኛ ተሰጥቶን ግንባታውን በማከናወን ላይ እንገኛለን›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሕንጻውን ለመከራየት ግልፅ ጨረታ ወጥቶ የተሻለ ዋጋ እና የቦታው ምቹነት ታሳቢ በማድረግ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አዲስ ቢሮ በጊዜያዊነት አራት ኪሎ አካባቢ በተከራየው ሕንጻ ላይ እንዲሆን መደረጉንም ጠቅሰው፣ የኪራዩን ዋጋ ከመግለፅ ግን ተቆጥበዋል።

ልማት ባንክ በ 2010 እና 2011 የሰጣቸው የተበላሹ ብድሮች መጠን ይህንንም ተከትሎ በተደረገ የአመራር ለውጥ እንዲሁም በብድር አሰጣጥ እና አመላለስ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራቱ የተገለፀ ሲሆን፣ ብድራቸውን መክፈል ያልቻሉ ድርጅቶችን ንብረት እስከመውረስ የሚደርስ እርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 30 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here