የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ለአምስት ፕሮጀክቶች የመጀመሪያውን ድጋፍ አደረገ

0
455

ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድ በቀን አንድ ዶላር ከዲያስፖራው ህብረተሰብ በጠየቁት መሰት የተሰበሰበ ገንዘብን የልማት ስራዎች ለማዋል በቀረበ ጥሪ መሰረት ተወዳድረው ላሸነፉ አምስት ፕሮጀክቶች የመጀመሪያውን ገንዘብ ለቀቀ።

ከዚህ ቀደም ትረስት ፈንዱን ከሚስተዳድረው ቦርድ በወጣ ማስታወቂያ መሠረት 466 ፕሮጀክቶች ንደፈ ሀሳብ ያቀረቡ ሲሆን ሌሎች ቀሪ ፕሮጀክቶችም ወደፊት በሚደረግ ማጣራት ወደ ስራ እንደሚባቡ ገልጿል።

የገንዘብ ድጋፉን ካሸነፉ ተቋማት መሃልም “ሕይወት ኢነተግሬትድ ደቨሎፐመንተ” የተባለ ድርጅት በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራኒዎ ክፍለ ከተማ በ10 ሚሊዮን 491 ሺሕ 724 ብር ለሚያሰራው ለወላጅ አልባ እንዲሁም ህፃናት የትምህርት አገልግሎት የሚሰጥ ፕሮጀክት ነው ተብሏል። ፕሮጀክቱ እድሜያቸዉ ከሶስት እስከ ስድስት ዓመት ለሚሆኑ 400 ህፃናት ፣ ወላጅ አልባዎች እና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ህፃናት እንክብካቤ እንደሚያደርግም ድጋፉ በይፋ በተሰጠበት ወቅት ተገልጿል።

በአዲስ አበባ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢም የዉሃ አቅርቦትን ለመጨመር፣ የጤና አጠባበቅና የአካባቢ ፅዳትን ለማሻሻል ደግሞ “ግሬት ቻርቲ ሆፕ” ለተባለ ግብረ ሠናይ ድርጅት ‹‹የጤና አጠባበቅና የአካባቢ ፅዳትን ማሳደግ›› በሚል ፕሮጅክት በ10 ሚሊዮን 314 ሺሕ 255 ብር ለመተግበር ማሰቡም ተጠቁሟል። ይህ ፕሮጀክት በአካባቢዉ ላይ ያለውን የጤና አጠባበቅና የአካባቢ ፅዳት በተመለከተ የአመለካከት ለዉጥ ያመጣል ተብሎም ይጠበቃል።

ከአዲሰ አበባ በተጨማሪ ትረስት ፈንዱ ድጋፍ ካደረገላቸው መካከል የአፋርና ትግራይ ክልል የሚገኙ ተቋማት ናቸው። በእነዚህ አካባቢዎች በገጠራማ አካባቢ ለሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የንፁህ መጠጥ ዉሃ ተደራሽነትን ለማሳደግ ለሚሰራው ፕሮጀክት ‹‹ፕሮ ደቨሎፕመንት ኔትዎርክ ›› ለተባለ ድርጅት በስምንት ሚሊዮን 924 ሺሕ 780 ብር ድጋፍ አድርጓል። ሌሎች ተጨማሪ አጋር አካላት ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ የሚሆን አንድ ሚሊዮን 359 ሺሕ 200 ብር ገቢ የሚደረግ ድጋፍ እንዳለም ትረስት ፈንዱ አስታውቋል ። በዚህ መሰረትም አካካቢዎቹ የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻል፣ የቤተሰብ ጤና አጠባበቅ ለማዳበር፣ በዉሃ አማካኝነት የሚመጡ በሽታዎችን ለመቀነስና ለጤና ጥበቃ የሚወጣውን አላስፈላጊ ወጭ ያቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተመላክቷል።

አራተኛዉ ፕሮጀክት የህፃናት መማሪያ አካባቢን ለማሻሻል በኦሮሚያ ክልል በሶስት ዞኖች በ10 ሚሊዮን 628 ሺሕ 855 ብር የሚተገበር ፕሮጀክት ሲሆን ይህንን ለመፈፀምም እቅድ ያቀረበው ‹‹ ጉርሙ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን›› የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው። ፕሮጀክቱም በአራት የመጀመሪያ ደረጃ ትምርት ቤቶች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን ይህም የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል፣ የመማሪያ አካባቢዎችንና የትምህርት ተግበራውን ወይም የመማር ማስተማር ሂደትን ለማሻሻል ያስችላል ነው የተባለው።

አምስተኛዉ ፕሮጀክት ልዩ ፍላጎት ለሚያስፈልጋቸው አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የትምህርት ስርዓቱን ለማሻሻል እንዲሁም አቅም ለመገንባት የሚስችል ሲሆን ድጋፉም ‹‹ሀልፐ ፎር ፐርሰን ዊዝ ዲስኤብሊቲ›› ለተባለ ድርጅት ተሰጥቷል። በዚህ መሠረት በአማራ ክልል በሰሜን ሽዋ ዞን ለሚገኙ ሶስት ወረዳዎች በ15 ሚሊዮን 651 ሺሕ 374 ብር የሚከናወን እንደሆን ተነግሯል።

የተባበሩት መንግስታት የእድገት ፕሮግራም አዲስ አበባ ለሚገኘው ለኢትዮጽያ ዲያሰፖራ ትረስት ፈንድ ጽህፈት ቤት ሙሉ የሁለት አመት ወጪ እንደሚሸፍን ማረጋገጫ መስጠቱንም የትረስት ፈንዱ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ ሃና አጥናፉ የገለጹ ሲሆን ጽህፈት ቤቱም ለስራ ማሰፈፀሚያ የሚዉል ምንም አይነት ገንዘብ ከዲያሰፖራዉ እንደማይጠቀምም የቦርዱ የህዝብ ግንኙነት ሃና አጥናፉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የኢትዮጽያ ትረስት ፈንድ ከተመሰረተበት ግንቦት 2011 ጀምሮ በ93 አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጽያዉያን ወደ ስድስት ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉን ለአዲስ ማለዳ ጠቅሷል። ገንዘቡም የተሰበሰበዉ ከ25 ሺሕ 735 ኢትዮጽያዉያን ነዉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 30 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here