በዋግ ኽምራ ዞን 108 ሺሕ ሰዎች ለምግብ እጥረት ተጋለጡ

0
597

በአማራ ክልል በዋግ ኽምራ ዞን በ2010 የክረምት ወቅት የዝናብ እጥረት በማጋጠሙ በተለይም በዝቋላ፣ በሳሃላ እና በሰቆጣ ወረዳዎች ባጋጠመው ድርቅ ለቀጣይ አምስት ወራት 108 ሺሕ ዜጎች አስቸኳይ የእለት የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተባለ።

ችግሩ በከፋባቸው ቀበሌዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ቤታቸውን ጥለው ውሃ ወዳለባቸው ቀበሌዎች በመሄድ ላይ መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። በዞኑ የሚገኙ ከአንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ እንስሳትም የመኖ እጥረት እንዳጋጠማቸው ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ የሆኑት መንግሥቱ ደሳለኝ፣ ከገጠር አካባቢ ወደ ከተማ ገብተዉ የሚማሩ ተማሪዎች ትምህርታቸዉን አቋርጠዉ ወደ ቤተሰቦቻቸዉ እየተመለሱ እንደሆነ መመልከታቸዉን ጠቅሰዋል። አክለውም በአካባቢው ያሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የእለት ምግብ ቢሰጡም፣ በቂ ባለመሆኑ ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ምክንያት መሆኑን አክለው ገልጸዋል።

የዞኑ የአደጋና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መልካሙ ደስታ፣ የችግሮቹን መኖር አረጋግጠው ከየካቲት እስከ ሰኔ 30 ድረስ የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው ነዋሪዎች አስቸኳይ የምግብ አቅርቦት ከክልሉ መጠየቃቸውን ተናግረዋል።

“ዞኑ በተደጋጋሚ የዝናብ እጥረት የሚከሰትበት መሆኑ፣ አካባቢዉ በጦርነት የተጎዳ በመሆኑ እና የሥራ እድል ፈጠራና የመሠረተ ልማት ሥራዎች ባለመሠራታቸው በተደጋጋሚ ለድርቅ እንዲጋለጥ አድርጎታል›› ሲሉ መልካሙ አስታውሰዋል።

በዞኑ ለሚከሰተዉ ተደጋጋሚ ድርቅ ዘላቂ መፍትሄ ለማስቀመጥ በትኩረት አልተሠራም ያሉት ኃላፊው፣ ወጣቱ በአካባቢዉ በሚገኙ የተፈጥሮ ጸጋዎችን መጠቀም አልቻለም ብለዋል። በማዕድን ማውጣት እና በእንስሳት እርባታ በአካባቢዉ በስፋት መሰማራት የሚቻልባቸዉ እድሎች ቢኖሩም፣ ኅብረተሰቡን የማስተማር እና እድሉን የሚጠቀምበት ሁኔታ ባለመመቻቸቱ ችግሩ ተከስቷል። ሆኖም በዞኑ ከፍተኛ የብረት ማእድን መኖሩን የማእድን አጥኚዎች ማረጋጋጣቸውን አክለው ገልፀዋል።

አደጋውን ለመቀነስ የእንስሳት ቅነሳ ለማድረግ ታቅዶ ከገጠር ወደ ከተሞች ለማጓጓዝ አንዳንድ ቦታዎች ከሦስት እስከ አራት ቀን የእግር ጉዞ የሚፈልጉ መሆኑ እንስሳቶቹን ወደ ገበያ ማቅረብ እንዳልተቻለም ነው ያነሱት።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር ጀንበሩ ደሴ፣ ከ189 ሺሕ በላይ የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ዜጎች በፌዴራል መንግሥት አስቸኳይ ድጋፍ እያገኙ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ነገር ግን ለእንስሳቶች እስከ አሁን መኖ እና ውሃ ለማቅረብ ያልተቻለው በዞኑ ያሉ የገጠር ቦታዎችን የሚያገናኝ መንገድ ባለመኖሩ ምክንያት ነው ብለዋል። ዳይሬክተሩ የተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ ተጀምሯል ቢሉም፣ ነዋሪዎች ግን መንግሥት ምንም ዓይነት ምገባ አልጀመረም ይላሉ።

የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ እንደሚሉት፣ ችግሩ በጥናት ተለይቶ እንደ ማንኛውም አካባቢ ድጋፍ እየተደረገ እንደሆነና የሚደረገውም ድጋፍ በአገሪቱ በጥናት ከተለዩ ተረጂዎች የተለየ ነገር እንደሌለዉ ነው።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ስድስት ሚሊዮን የእለት ተረጂዎች ተለይተዉ በየወሩ 15 ኪሎ ስንዴ፣ ግማሽ ሊትር ዘይት፣ አንድ ኪሎ ተኩል ጥራጥሬ እና 35 በመቶ አልሚ ምግብ እየደረሰ መሆኑን ደበበ ተናግረዋል። የዋግ ኸምህራ ዞንም በጥናት ተለይቶ በእርዳታው ውስጥ መካተቱን ጠቅሰዋል።
‹‹የበልግ ዝናብ የማይጥል ከሆነ አንደ አገር አደጋ ሊያጋጥም ይችላል›› ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጽያ በ2012/13 ለሰባት ሚሊዮን ሰዎች መሠረታዊ የምግብ አቅርቦት ድጋፍ እንደሚደረግላቸዉ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ኮሚሽን የተረጂዎች የድጋፍ እቅድ ያመላክታል። ከእነዚህም ውስጥ 75 በመቶው አስቸኳይ እርዳታ የሚደረግላቸዉ እንደሆኑ ሪፖርቱ ያሳያል። እንዲሁም 70 በመቶ ያህሉ በግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ ሲሆን ቀሪዎቹ 30 በመቶ ተረጂዎች በአየር ንብረት ምክንያት የተጎዱ እንደሆኑ ተጠቅሷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 30 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here