የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ግልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዓሊ (ዶ/ር)

0
1099

መድፉመሸሻ ንጉሴ

 

1.     ሪክ እንደ መንደርደሪያ የአባይ ጉዳይ እና የቀደሙ መሪዎቻችን

አባይን በጦርነት የማስገበር ሙከራዎች

የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዝም ብሎ ግድብ አይደለም። ዝም ብሎ የውሃ ማቆሪያ ኮንክሪት እና ኃይል ማመንጫ ብቻ አይደለም። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግድብ ብሎ ዝም ነው!!! ታሪኩ እና መሰረቱ፣ መልዕክቱ እና አንድምታው፣ ትናንቱ እና ነገው፣ ታሪኩ እና የወደፊት ኣሻራው ይለያል። ዛሬን እና ነገን የሚሻገር፣ ትናንትናን እና ከትናንት ወዲያን እንደ መስታወት የሚያሳይ፣ የሀገራችንን ውጣ ውረድ እና ትንሳዔ የሚያመለክት የትውልዶች ቅብብሎሽ ውጤት ነው። ለምን ቢሉ የሚገነባው በአባይ ላይ ነውና ነው! አባይስ ምን ሆነ እና ቢሉ ደግሞ የውድ ሀገራችን ኢትዮጵያ ፈተና እና ተስፋ ማሰሪያ ገመድ መሆኑ ነው።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በ19ኛው እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን የገባችባቸው ሁሉም ጦርነቶች የዓድዋ ጦርነትን ጨምሮ ከጀርባቸው ውሃ አለ። ያ ውሃም አባይ ነው። ከግብጽ ጋር ብቻ በ19ኛው ክፍለ ዘመን እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ1832-1876 ብቻ፣ ከገዳሪፍ እስከ ጉንደት ድረስ አስራ ስድስት ጦርነቶች ተደርገው በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት ተጠናቀዋል። የጦርነቱ መንሰዔ ደግሞ ዐረባዊቷ ግብጽ “የአባይን/ናይልን ሸለቆ በአረንጓዴው የግብጽ ባንዴራ ስር ማድረግ” በሚል ቅዠት የተጸነሰሰ መሆኑ ነበር።

በአፋር እነ ሞሐመድ ሐንፍሬ፣ በጉራዕ እና በጉንደት እነ ራስ አሉላ አባ ነጋ ወዲ ቁቢ ወራሪውን የግብጽ ሰራዊት አንደ አሻሮ ቆልተው፣ ለወሬ ነጋሪም ሳያስተርፉ ጠላትን ረፍርፈው የሀገር ሉዓላዊነትን፣ ክብርን እና ብሔራዊ ጥቅምን አስጠብቀዋል። አባይም ተከበረ! ኢትዮጵያም ተከበረች! ዓድዋም የአባይ ጦርነት ነው የሚያስብለው በግብጽ ቅኝ ገዥ የሆነው የእንግሊዝ መንግስት ከጠንካራዋ ፈረንሳይ ይልቅ ደካማዋ ጣሊያን የአባይን ምንጭ እንድትቆጣጠር ለማድረግ በ1884 (እ.ኤ.አ.) “የሒወት/Hewett ወይም ዓድዋ ውል” ቃሉን ሽሮ ኢትዮጵያን ለጅብ አሳልፎ የሰጠበት ሲሆን ዋና ምክንያቱም በግብጽ ላለው የጥጥ ማሳው ውሃ እንዲቀርብ ለማረጋገጥ ነበር። የእንግሊዝ የትሮይ ፈረስ የነበረው ጣሊያንም ክብርና ሞገስ በእምዬ ምኒልክ እና እተጌ ጣይቱ መሪነት ለዘመቱት ቀደምት እናቶቻችን እና አባቶቻችን ሀገራችን ተከበረች። ቅኝ ግዛትም አፈረ! አባይም ተከበረ።

ከዚህ ቀጥሎ የመጣው የውክልና ጦርነቱ ነበር። በተለይ በ1952 (እ.ኤ.አ.) የግብጽ ወታደሮች በመፈንቅለ መንግስት ወደ ስልጣን ሲመጡ የመጀመሪያ ስራቸው የነበረው ኢትዮጵያን ለማተራመስ መንቀሳቀስ ነበር። የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል። ሌላው ቢቀር እነ መንገስቱ ነዋይ እና ግርማሜ ነዋይ ባቀነባበሩት መፈንቅለ መንግስት ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ተረባርበዋል። ከሶማሊያ ጋር ባደረግናቸው ተከታታይ ጦርነቶች ግብጽ ከጀርባ በሶማሊያ በኩል ትጥቅ እና ስንቅ አቅራቢ ነበረች። ከሶማሊያ እየተነሳ ኢትዮጵያን ለመውጋት ለተነሳ ማናቸውም ዓይነት አሸባሪ ከአል ኢትሃድ አል ሲስላሚያ እስከ ኢስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት ግብጽ እጇ ረጅም ነው።

ኤርትራን ማዕከል ባደረገው በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ሀገር አፍራሾቹ እነ ወልደአብ ወልደማርያም ስንቃቸውም ትጥቃቸውም ከግብጽ ነበር። ሻዕቢያን ተንከባክቦ አስመራም አዲስ አበባም ያስገባው የግብጽ ድጋፍ ነበር። እነዚህ የውክልና ጦርነቶች ሌላኛው አንድምታቸውም ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር መንቀል ነበር። ይህም በተሳካ ሁኔታ ተፈጽሞላቸዋል-ዕድሜ ለእኛው ድንቁርና!

ታዲያ በዚህ ሁሉ ሂደት፣ ይህ ሁሉ ዱላ እና ጦርነት እየወረደባት ኢትዮጵያ ሳትሸነፍ እና ረሷን አስከብራ ቆይታለች። ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ከፍተኛ መሰዕትነት ከፍላለች። በተከፈለው የህይወት ዋጋም የሀገር ክብርና ቅርስ፣ ሉዓላዊነት እና ነጻነት ተከብሯል። በዚህ አጭር ጽሁፍ ስለ ሁሉም ጦርነቶች ላውራ ብል አይቻልም። እንዲያው ለማስታወስ ያክል ጫፉን ነካሁት እንጂ። ታሪካችን በደንብ ሲጻፍ በደንብ ይህ ሐቅ እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስ በሀገራችን የሚሸረበውን ሴራ፣ የሚሰራውን ተንኮል ለታሪክ መዝግበን እናስቀምጣለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በዚህች አጭር ጽሁፍ ለመዳሰስ የምሞክረው ከአባይ ውሃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ መሪዎቻችን ሁሉም “አንድ ዓይነት አቋም ነበራቸው። አላቸው” እየተባለ በተደጋጋሚ ይነገራል።

እና ይህ ማለት ምንድን ነው? መገለጫዎቹስ ምንምን ናቸው? መሪዎቻችን በአባይ ላይ ምን አለሙ? ምንስ አጠፉ? የሚሉትን ጥያቄዎች በመዳሰስ በዚህ ባለንበት ወቅት አሁን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ያላቸው ተግዳሮት እና ተስፋ ምንድን ነው? ከፊታቸው ያለው የአባይ ጉዳይስ እሳቸውን እና ዘመነ-መንግስታቸውን በአባይ ወንዝ አሻራ በየትኛው መዝገብ ያስቀምጣቸው ይሆን? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ለመሻት እንሞክራለን። ስለሆነም፣ ከአጼ ምኒልክ እስከ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ድረስ ያሉ የኢትዮጵያ መሪዎች እና የአባይ ጉዳይ አቋም እና እንቅስቃሴ አበየት ማሳያዎችን እንጠቁማለን።

ግርማዊ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ

          ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የአባይን ጉዳይ ለእንግሊዝ በእጅ አዙር ለግብጽ አሳልፈው እንዲሰጡ ለማድረግ ብዙ ተሸርቦባቸው ነበር። ዋናው ግን የ1902 የሱዳንን ወሰን/ድንበር ለመወሰን ከእንግሊዝ ጋር የተደረገው “ስምምነት” ነበር። በዚህ ስምምነት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ “የአባይን ውሃ ተዳር እዳር የሚደፍን ስራ ላይሰሩ ወይም እንዲሰራ ላይፈቅዱ ውል አድርገዋል” የሚል ድንጋጌ በሶስተኛው የስምምነቱ አንቀጽ ተካቷል። እንገሊዞቹ አጼ ምኒልክን “ሸወድናቸው። አባይን ተቆጣጠርነው” ብለው ሲፎክሩ ንጉሱ መልሰው ልእንግሊዝ መንግስት “እግዚአብሔር የሰጠንን ውሃማ ከመጠቀም የሚከለክለን የለም። ወንዙን ተዳር እዳር አንደፍንም አልን እንጂ” የሚል መልዕክት ላኩ። በኋላም አልጋ ላይ በነበሩበት ጊዜ እንግሊዝ፣ ጣሊያን እና ፈረንሳይ የሶስትዮሽ ውል በ1906 (እ.ኤ.አ.) በማድረግ ኢትዮጵያን እንደ ቅርጫ ሊቀራመቱ ሲያስቡ “የእናንተ ድጋፍ አያሻንም” ብለው ሶስቱንም አስጠነቀቁ።

ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ

          ከአባይ አንጻር መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ የነበረው በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት ነበር። እንግሊዝ እና ጣሊያን ከፍ ያለ ወከባ በኢትዮጵያ ላይ ለማሳደር ደፋ ቀና ሲሉ በ1920ዎቹ (እ.ኤ.አ.) መጨረሻ አጼ ኃይለሥላሴ በእንግሊዝ አምባሳደራቸውን ሐኪም ወርቅነህን ወደ አሜሪካ ልከው በጣና ሐይቅ ላይ ግድብ እንዲሰራ ኩባንያ እንዲፈለግ በማድረግ ፈር ቀዳጅ ስራ ሰርተዋል። ይህን ያደረጉበት ዐቢይ ምክንያት ለእንግሊዝ እና ለጣሊያን መልዕክት ለመላክ የኢትዮጵያን የመጠቀም መብትም ለማረጋገጥ ነበር። ከዚያ በማስቀጠል ጣሊያን ኢትዮጵያን በመውረሩ፣ እንግሊዝም በአሜሪካ ላይ ጫና በማድረሷ ንጉሱ እንዳሰቡት የጣና ሐይቅ ግድብ ግንባታ አልተከናወነም።

          ነገር ግን ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ በአባይ ተፋሰስ መጠነ ሰፊ የአቋም እና የጥናት እንዲሁም ተግባራዊ የውሃ መጠቀም እንቅስቃሴ አድርገዋል። ለዚህም ታሪክ ሲዘክራቸው ይኖራል። በርሳቸው ዘመን የጢስ እሳት ኃይል ማመንጫ፣ የፊንጯኣ ባለ ፈርጀ ብዙ ግድብ ተገንብተዋል። ከ1956-1964 (እ.ኤ.አ.)አሜሪካኖቹን በመጋበዝ የአሜሪካ ጠፍ መሬት መልሶ ልማት (United States Bureau of Reclamation-USBR) በአባይ ሸለቆ ላይ ሰፊ ጥናት እንዲያደርግ አስደርገዋል። የዚህ ጥናት ውጤቶችም ለአሁን የልማት ስራዎቻችን መሰረቶች ሆነው በርካታ ውጤት እየተመዘገበ ነው-ይህ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ይጨምራል።

          ሌላኛው ከፍ ያለ የአጼ ኃይለሥላሴ ስራ በዲፕሎማሲው መልክ የነበረው ነው። ግብጽ እና ሱዳን ከጀርባ ሆነው ኢትዮጵያን እና ሌሎቹ የአባይ ምንጭ ሀገራትን አግልለው የ1959 “ስምምነትን” መደራደር ሲጀምሩ ለዓለም ማህበረሰብ ይህን ጉዳይ ይፋ በማድረግ የኢትዮጵያን አቋም በግልጽ አሳወቁ። “ኢትዮጵያ የአሁን እና የወደፊት ትውልዶችን ፍላጎት ለማሟላት እግዚአብሔር የሰጣትን ውሃ ትጠቀማለች።

የንጉሰ-ነገስት መንግስቱም ይህን የማድረግ መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታም አለበት” ሲሉ አወጁ። እ.ኤ.አ. በ1956 ኮሚኒይኬ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለዓለም ተሰራጨ። በ1957ም የዲፕሎማቲክ ማስታወሻ/Aide-memoire ለመላው ዓለም ተሰራጨ። የኢትዮጵያን አቋም ማሳወቅ ተቻለ። “ግብጽ እና ሱዳን በድብቅ የአባይን ውሃ ለመከፋፈል የሚያደርጉትን ድርድር ኢትዮጵያ እንደማትቀበል” እና “ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ ለህዝቧ ጥቅም እንደምታውል” አቋሟን በማያሻማ መልኩ ለዓለም አሳወቀች።  በ1960 እ.ኤ. በታኅሳሱ ግርግር ወቅት እነ መንግስቱ ነዋይ እና ገርማሜ ነዋይ በአጼ ኃይለሥላሴ ላይ መፈንቅለ-መንግስት ሲሞክሩ ግብጽ ማገዟ እና ኮማንዶዎች በአውሮፕላንስ መላኳ ምክንያቱ ምን ይሆን? አባይ አይደለምን?

ዘመነ ደርግ-ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም

          ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር በሚል ፈሊጡ ሀገራችንን የጦርነት አውድማ ማድረጉ እና ሰው በላነቱ ሐቅ ቢሆንም የመንግስቱ ኃይለማርያም አስተዳደር በሀገር ፍቅር እና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ የሚታማ አልነበረም። በአባይም ዙሪያ የሆነው ይሄው ነው። እንደ ደርግ የግብጽ ሴረኝነት እና ተንኮል፣ ለኢትዮጵያ ቋሚ ታሪካዊ ጠላት መሆኑን የተገነዘበ መንግስት አልነበረም ብሎ በድፍርት መናገር ይቻላል።

እውቀት ላይ የተመሰረተ የውሃ ሀብት አጠቃቀም እንዲኖር የአርባ ምንጭ የውሃ ኢኒስቲቲዩት የተቋቋመው ይህን ታሳቢ በማድረግ ነበር። በተግባርም በርካታ የመስኖ ስራዎች እና የውሃ ልማት ስራዎች ታስበው የነበረ ቢሆንም በርስበርስ ጦርነቱ ምክንያት ብዙ ነገር ሳይሳካ ቀርቷል። አንዱ የዚህ ማሳያ የጣና-በለስ ፕሮጄክት ነበር። ፕሮጄክቱ በሙሉ አቅም ከተጀመረ በኋላ በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል የነበረው ጦርነት በመባባሱ የፕሮጄክቱ ገንዘብ ወደ ጦርነት ማስፈጸሚያ እንዲዞር መሆኑ እጅግ የሚያስቆጭ ነው።

          በኣለምአቀፍ መድረክ የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም መንግስት ከቀደመው የአጼ ኃይለሥላሴ መንግስት የተለየ አልነበረም። ኢትዮጵያ በ1977 (እ.ኤ.አ.) በማር ዴል ፕላታ-አርጄንቲና በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት የውሃ ጉባዔ ወቅት “ምንም ዓይነት የውሃ ስምምነት በሌለበት ሁኔታ ሀገራት በተናጠል የውሃ ሀብታቸውን ለማልማት እንደሚገደዱ” እና ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያም ውሃ ሀብቶቿን እንደምታለማ በግልጽ ለዓለም ማህብረሰብ አቋሟን ገልጻለች።

የወቅቱ ሶሻሊስት ኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እ.ኤ.አ.በሜይ 7 ቀን 1980 የኢትዮጵያን አቋም የሚያሳይ ሜሞራንደም ለኣለም አሰራጭቷል። በዚህ ሰነድም ግብጽ የአባይን ውሃ ከተፈጥሮ ፍሰቱ በማውጣት ወደ ሳይናይ በረሐ ለመጥለፍ ማቀዷን በጽኑ አውግዟል። ይህ የግብጽ ድርጊትም በማናቸውም መልኩ የኢትዮጵያን ፍትሐዊ በአባይ የመጠቀም መብት በፍጹም የሚያቅብ እንዳልሆነ አሳውቋል። እ.ኤ.አ. በኤፕሪል 29 ቀን 1980ም በሌጎስ-ናይጄሪያ በተካሄደው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ልዩ ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ በአባይ ውሃ የመጠቀም መብቷን በግልጽ በማስረዳት የግብጽ ወገን የአባይን ውሃ ወደ ሳይናይ ለመጥለፍ መወሰኑን አውግዛለች።

 

ዘመነ ኢህአዴግ-አቶ መለስ ዜናዊ

          የኢህአዴግ ዘመን ወደ ስልጣን ሲመጣ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲው የተንሸረረ ነበር ማለት ይቻላል። ከጎረቤቶቻችን ጋር “የኢትዮጵያ የቀደሙ መንግስታት ክፉ ሆነው እንጂ ግብጽን ጨምሮ በሠላም እና በፍቅር እንኖራለን” በሚል ስሁት አነሳስ ተነስቶ በአባይ ውሃ አጠቃቀም ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተትን ፈጥሮ ነበር። እ.ኤ.አ. በ1993 የወቅቱ የሽግግር መንግስቱ ፕሬዝዳንት መለስ ዜናዊ ከሆስኒ ሙባረክ ጋር የተፈራረሙት ሰነድ እንዲያው የትብብር ማዕቀፍ መሆኑ በጀ እንጂ ኢትዮጵያን የግብጽ ቀንበር ስር የሚጥል ነበር። ይህ የገባቸው መለስ ዜናዊም በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ዘመናቸው የቀደመ ስህተታቸውን የሚያሰተሰርይ ስራ በአባይ ላይ ሰርተዋል።

          አንደኛው በዲፕሎማሲ መስክ የተገኘው ድል ነው። በዚህ ረገድ ሁሉም የአባይ ተፋሰስ ሀገራት በጋራ ጥቅም ለጋራ እንዲቆሙ ለማድረግ ብዙ ተጥሯል። ይሁን እንጂ ግብጽ አሻፈረኝ ብላ ወደ ኋላ ወደ ኋላ ስትል እና የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት/Cooperative Framework Agreement-CFA ድርድር ሲካሄድ የላይኛወን ተፋሰስ ሀገራት በከፋፍለህ ግዛ ልትበትን ስትራወጥ የመለስ ዜናዊ አመራር ሁሉንም የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት በጋራ እንዲቆሙ እና የቅኝ ግዛትን ጠባሳ እንዲሽሩ አድርገዋል።

በመሆኑም፣ CFA በእርሳቸው ዘመን ለ13 ዓመታት ድርድር ተደርጎ እ.ኤ.አ. በሜይ 14 ቀን 2010 ተፈርሟል። የመለስ ዜናዊ ትልቁ መልዕክት በዚህ ቀን ያደረጉት ሌላ አስገራሚ ስራ ነበር። በተመሳሳይ ቀን እሳቸው የጣና-በለስን ባለብዙ ጥቅም ግድብ መርቀው እየከፈቱ፣ ውሃ ሚኒስትራቸው አስፋው ዲንጋሞ ደግሞ ኢንቴቤ ላይ ስምምነቱን እየተፈራረሙ ነበር። ስርየት ማለት ይህ ነው። ከዚሁ ባሻገር በ1997 እ.ኤ.አ. ኢትዮጵዯ በአባይ ውሃ አጠቃቀም ላይ ያላትን አቋም በተመለከተ ለዓለም ማህብረሰብ በተለይ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲሁም ለዓለም ባንክ የኢትዮጵያን አቋም የሚገልጽ ደብዳቤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው በኩል እንዲደርስ ተደርጓል።

          ተግባር ላይ ከተሰሩ ስራዎች ዋናዋናዎቹ እ.ኤ.አ. በ1990ዎቹ የአባይ መሪ ዕቅድ/master plan በሙሉ እንዲከለስ መማድረጋቸው ለቀጣይ ስራዎች መሰረት የጣለ ነው። ከዚሁ ባሻገር በርካታ የግድብ ግንባታዎች በአባይ ላይ ከተናውነዋል። የጨረጨራ ግድብ በጣና ሐይቅ ላይ እና የጢስ አባይ ኃይል ማመንጫ ቁጥር ሁለት፣ የተከሴ ኃይል ማመንጫ ግድብ፣ ጣና-በለስ፣ ቆጋ መስኖ ልማት፣ ዛሪማ፣ የአንገር መስኖ ልማት፣ ከምንም በላይ ደግሞ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋናዋናዎቹ ናቸው።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንዲገነባ ግልጽ እና የማያሻማ አቋም በመውሰድ ማስጀመራቸው የአባይን ተፋሰስ የውሃ ፖለቲካ ሙሉ በሙሉ የሚቀይር ነው። በዚህ ጊዜ ምንም እንኳን በጎ ምክንያት ቢኖራቸውም የሰሩት ትልቅ ስህተት ግን ለብሔራዊ ብረታ ብረት ኮርፖሬሽን/ሜቴክ የግድቡን የሃይድሮ እና ኤሌከትሮ መካኒካል ስራ አሳልፈው መስጠታቸው ነው። ይህ ስህተት አሁን ሀገሪቱን ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል።

ዘመነ-ኢህአዴግ- አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ

          የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በውጣ ውረድ የተሞላ ነው ማለት ይቻላል። ከአባይ ጋር በተያያዘ ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች እጇቸው ላይ ነበሩ። አንደኛው የCFA ጉዳይ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ነው። ከCFA ጋር በተገናኘ አመርቂ ስራ ሰርተዋል ብሎ መናገር ይቻላል። CFAን ኢትዮጵያ አጽድቀላች ሩዋንዳ እና ታንዛኒያም እንዲያጸድቁ የማግባባት ስራ ሰርታለች። በኢንቴቤ እ.ኤ.አ. ጁን 2017 በተካሄደው የናይል ተፋሰስ መሪዎች የመጀመሪያ ጉባዔም በመገኘት ከፕሬዝዳንት ሲሲ ጋር ፊት ለፊት ተፋጠው የግብጽን ሴራ አክሽፈዋል።

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አንጻር የራሱ የሆኑ ክፍተቶችም ስኬቶችም አሉት። የሙዚቃ ተንታኙ ሰርጸ ፍሬስብሐት “የሙሴ በትር ሲሰጥህ፣ የአሮን በትር አድርገው” ብሎ አንዴ ያጫወተኝን አልረሳውም። አቶ ኃይለማርያም የሙሴ በትር ተሰጥቷቸው የአርንም አላደረጉትም የሙሴንም አንዳለ ማስተላለፍ አልቻሉም። ለዚህ ዋናው ምክንያት ሜቴክ የግድቡን ኤሌክትሮ ሜካኒካል እና ኃይድሮ ሜካኒካል ስራ እንዳይሆን እንዳይሆን አድርጎ ሲጫወትበት፣ ግድቡ እየዘገየ እንደሆነ እየታወቀ እና አቶ ጌታቸው ረዳ በቴሌቪዥን እንደነገረን “እየተነገራቸው” እና እያወቁት ምንም ማድረግ አለመቻላቸው ነበር።

ከዚሁ ባሻገር ፕሬዝዳንት መለስ ዜናዊ በ1993 የተሳሳቱትን ስህተት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝም በ2014 እ.ኤ.አ. በማላቦ ኢኳቶሪያል ጊኒ ላይ ደግመውታል። ስርየቱ በኋላ የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት/Agreement on the Declaration of Principles-DoP መፈረሙ እና ግብጾቹ ደጋግመው ሲጠቅሱት “ስብሰባውንም ቢሆን ትታችሁ ነው” ብለው ቀጭን ትዕዛዝ መስጠታቸው ነበር። ይህ ግድብ ማለቅ የነበረበት በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጊዜ ነበር። ግን አልሆነም። እዚህ የደረስነውም በዚያ ምክንያት ነው።

2.    የአደራ ቃል ልከቡር ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ዓሊ

          የዶ/ር ዐቢይ አህመድ ዓሊ ወደ ስልጣን መምጣት ወይም ይህ “ለውጥ” መከሰት አንዳንድ ግድቡን በንቃት ለሚከታተሉ ሰዎች “ይህ ለውጥ የመጣው ለግድቡ ነው” አስብሏቸዋል። የዶ/ር ዐቢይ አህመድ ቁርጥ ያለ እና ታሪክም ለወደፊት በበጎ የሚያነሳው እርምጃ እና ቁርጠኝነት ባይኖር ኖሮ ግድቡን ከውድቀት እና ከብሔራዊ ውረድትነት ማዳን አይቻልም ነበር።

ኢትዮጵያ ይህን ግድብ ለብሔራዊ ክብሯ እና ጥቅሟ የጀመረችው እና ለህዝቡ ከምንም በላይ የምዕራባውያን ሴራ፣ የግብጽ ተንኮል፣ ድህነታችን ሳይበግረን “በይቻላል” መንፈስ “እኛው መሐንዲስ፣ እኛው የገንዘብ ምንጭ” ሆነን የምንሰራው “የህዳሴያችን ማማ” ብለን የጀመርነው ግድብ ቢሆንም፣ ሜቴክ ግን የህጻን አሻንጉሊት አድርጎት ነበር። ዝርዝሩ ብዙ ነው። ነገ ከነገ ወዲያ ታሪክ የሚያወጣው ይሆናል። ከዚህ አንጻር ዞሮ ዞሮ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ይህን ግድብ ታድገውታል ማለት ይቻላል። ይህ ሐቅ ነው።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ ገና ወደ ሁለት ዓመት እየተንደረደሩ ሲሆን በግድቡ ዙሪያ የነበረው ፈተና በዋናነት የውስጥ የፕሮጄክት አስተዳደሩን ማስተካከል ነበር። አሁን ግን የውጭ ፈተናው እና ግፊቱ ከፍ ያለ እና እያየለ መጥቷል። ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ይህን መስቀለኛ መንገድ ይሻገሩት ይሆን?

ታላቁ ጥያቄ

          ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከግብጽም ከሱዳንም መሪዎች ጋር በተደጋጋሚ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ መክረዋል። ያላቸውንም አቋም ተረድተዋል። የሀገራችንን አቋም በተመለከተም ግልጽ ያለ አረዳድ እንዳላቸው በቴሌቪዥን መስኮት ለፓርላማ አባላት ለጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ አስተውለናል። አሁን ሀገራችን ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አንጸር ሀገራችን ወደ ቄራ እየተጎተተ እንደገባ በሬ ሆናለች። እ.ኤ.አ. ከኖቬምበር 6 ቀን 2019 ወዲህ በአሜሪካ “ታዛቢነት” ይሁን “ሸምጋነት” ወይም “አደራዳሪነት” እየተካሄደ ያለው ድርድር እጅግ አደገኛ እና ሀገሪቱን ወደማያስፈልግ የግብጽ ቀንበር እየከተተ እንደሆነ ምልክቶች ታይተዋል።

          በተለያየ የሚዲያ አውታሮች የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ በአሜሪካ እና በዓለም ባንክ ከፍተኛ ጫና እና ዛቻ እየደረሰባት ነው። ኢትዮጵያ እንደትናንቱ ሁሉ በኣለም ሸንጎ “ዐልቦ ዘመድ” ወይም “ብቻዋን የቆመች” ሆናለች። ይህ ሁኔታ ሀገረቱን ወደማትወጣበት አዘቅት እና ቁልቁለት እየከተታት እንደሆነ የውሃ ሚኒስትሩ የሰጣቸውን ግራ የተጋቡ መግለጫዎች እንዲሁም በ Institute for Strategic Affairs ባቀረቡት ገለጻ መረዳት ይቻላል።

ለምሳሌ የግድቡን የውሃ አሞላል ሁኔታ ስንመለከት የድርቅ መለኪያ ሆኖ የወጣው ቁጥር አሁን 37 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነው። ይህ ቁጥር ከኢትዮጵያ የቀደመ አቋም 31 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ሲንሸራተት ግብጽ እየጠየቀች ወዳለው 40 እየተጠጋ መሆኑ እጅግ አስደንጋጭ ነው። ይህ የግድቡን የሙሌት ጊዜ እንደሚያራዝመው ለማወቅ የሮኬት ሳይንቲስት መሆን አይጠይቅም። በአንዳንድ የስምምነት ሰነዱን አገኘን ባሉ ሚዲያዎች እንደተዘገበው በረጅም ጊዜ ድርቅ በተለይ በግድቡ የረጅም ጊዜ ኦፕሬሽን የድርቅ መነሻ 39 ቢሊዮን  ሆኗል።

ዋዜማ ሬዲዮ እንደዘገበው “ከህዳሴው ግድብ የሚለቀቀው ውሀ ከ39 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ በታች ከሆነ ኢትዮጵያ ከህዳሴው ግድብ ከባህር ጠለል 603 ሜትር በላይ ያለውን ውሀ ሙሉ ለሙሉ ለአራት አመታት ከፋፍላ እንድትለቅ ይጠበቃል።” ይህ ኢትዮጵያ ላይ ቀንበር የሚጥል እና ትውልድ ላይ የሚጫን ዕዳ የውሃ ክፍፍልም ይዘት ያለው ነው። ይሁን እንጂ የውሃ ሚኒስትሩ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት “የሚደረሰው ስምምነት የውሃ ክፍፍል አይደለም” ሲሉ ተደምጠዋል። ይህ ፈጽሞ ከዝርዝሩ ጋር የማይገናኝ እና ህዝቡን የሚያሳስት ንግግር ነው።

አሽራቅ  አል አውሳት የተባለ ሚዲያ “ኢትዮጵያ የአሜሪካን ጫና መቋቋም ስለማትችል ስምምነት ላይ እንደሚደረስ ግብጽ” እርግጠኛ መሆኗን ዘግቧል። በሌላ አነጋገር ኢትዮጵያ በጫና እና በዛቻ በእነ ትራምፕ ማስፈራሪያ ለግብጽ የሚጠቅም፣ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ ስምምነት በግዳጅ እንድትፈርም ጫና እየደረሰባት ነው ማለት ነው። በዚህ አኳኋን ግብጽ ቀደም ብላ ጠይቃ እንደነበር የተጠቀሰው “እዚያው ጉባ ገብቼ ከኢትዮጵያ መሐንዲሶች ጋር ግድቡን ኦፕሬት ላድርገው፤ ላስተዳድረው” ብላ የጠየቀችውስ ላለመፈቀዱ ምን ዋስትና አለ? ምንም!  ይህ መቼም እጅግ ቅስም ሰባሪ ነው።

ከዚህ ሲያልፍ እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የውሃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ስለሽ በቀለ ይህን ስምምነት በሚቀጥለው ሳምንት ለመፈራረም ወደ ዋሽንግተን ዲሲ እንደሚያመሩ ነው። ታዲያ አሁን ጥያቄውጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ይህን ነገር ያስቆማሉ ወይ የሚለው ነው።

          ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በፓርላማ ተገኝተው ከህዝብ እንደራሴዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ ስለ ታላቁ የኢትዮጵያህዳሴ ግድብም ተጠይቀው ነበር። በመልሳቸውም “በዚህ  ጉዳይ ላይ ሁሉም የቀደሙ መሪዎች እሳቸውን ጨምሮ አንድ ዓይነት አቋም እንዳላቸው እና ከእሳቸው በኋላ የሚመጣውም እንዲሁ እንደሚቀጥል ተስፋቸው እንደሆነ” ገልጸዋል። ይህ ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው። እንግዲህ “የኢትዮጵያ መሪዎች አንድ ዓይነት አቋም ነው ያላቸው” ማለት የኢትዮጵያን በአባይ ውሃ ላይ የመጠቀም መብት፣ ሉዓላዊነት፣ የአሁን እና የወደፊት ትውልዶች ፍላጎት እና ሀገራዊ ክብር መሰረት በማድረግ ማስጠበቅ ማለት ነው። የታላቁ የኢትዮጵዯ ህዳሴ ግድብም በመግቢያዬ ላይ እንዳልሁት ዝም ብሎ ግድብ አይደለም። የዚህ ጥቅም ማሳረጊያ፣ ማረጋገጫ፣ ማስታወቂያ፣ ማጽኛ ማኅተም ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ የአደራ ቃል ኪዳን ነው! ይህን ቃል ኪዳን የመጠበቅ ግዴታ እና ኃላፊነት ደግሞ በዚህ ዘመን አራት ኪሎ በተገኙት በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ትክሻ ላይ ወድቋል ማለት ነው።

          የግብጽ ፍላጎት ግልጽ ነው። በዚህ ግድብ አስታኮ በጦርነት እና በውክልና ጦርነት፣ በሴራ እና በተንኮል ማሳካት ያልቻሉትን ኢትዮጵያን በግብጽ ቀንበር ስር የማድረግ እና የናይልን ወንዝ መቆጣጠር ቅዣት ወይም ህልም በስምምነት ማድረግ ነው። ይህ አሁን በአሜሪካ ሸምጋይነት እና አደራዳሪነት ወይም ታዛቢነት እየተከናወነ ያለ ነገር ይህን ማሳካት ነው። ከዚህ የተለዬ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም።

ለዚህ ማረጋገጫው በተለያየ መንገድ የወጡትን መግለጫዎች እና የብዙኃን መገናኛ ያፈተለኩ መረጃዎች መመልከት ነው። በጦርነት እና በውክልና ጦርነት ያልሰጠነውን እና ያልተንበረከክንበትን ጉዳይ እና ጥቅማችንን በወዶገብነት “በስምምነት” አሳልፈን ልንሰጠው አይገባም። እጃችንን “የስምምነት” ካቴና የከተትን እንደሆነ ትናንት ከሀገራቸው ክብር እና ነጻነት የወደቁ ኢትዮጵያውያን አጥንት እንደሚወጋን አንጣራጠር። ትናንት አባቶቻችን በተጋድሎ ያጸኑልንን እና ለእኛ ያስረከቡትን ክብርና ነጻነት ሳንጠብቅ፣ ለመጪው ትውልድ ወይም ትውልዶች ሀፍረት እና አንገት መድፋት እንደምናስተላለፍ እና ታሪክም እንደሚፋረደን አንጠራጠር።

          ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አሁን ትልቅ ጥያቄ ከፊትዎ ተደቅኗል። ይህም ወይ ከቀደሙት መሪዎች ጎራ መሰለፍ ነው። ካልሆነ ደግሞ አዲስ “አሻራ” ማኖር ነው። ኳሱ ሙሉ በሙሉ በእሳቸው እጅ እንዳለ መገንዘብ ይቻላል። የውሃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ስለሽ በቀለ አካሄድ እና ገለጻዎች ጉዳዩን ከማለባበስ የዘለለ ትርጉም እንደሌለው እያስተዋልን ነው።

በመሆኑም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከውርደት እና ውድቀት ምንጭ መሆን ያዳኑትን ይህን ግድብ የኢትዮጵያ ኣለምአቀፍ ግንኙነት እና የድርድር ክሽፈት እንዳይሆን ቢታደጉት እንደ ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ግዴታ፣ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ምንም እንኳን ከፍ ያለ ጫና በሀገራችን ላይ እየደረሰ ቢሆንም ያን ተቋቁመው ለሀገራቸው ውለታ እንደዋሉ፣ ለልጆቻቸውም አኩሪ እና ደማቅ ታሪክ እንደሚጽፉ፣ ከመቃብር በላይ የሚኖረው ስም ነውና ስማቸውም ከፍ ከፍ እንደሚል አልጠራጠርም።

ይህን ለማድረግ ግን ጠንካራ ትክሻ እና ለህዝቡ እውነታውን ማሳወቅን ይጠይቃል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በዚህ ዙሪያ ታሪክ እንደሚሰሩ እተማመንብዎታለሁ። ይክ ከፍ ከፍ ያደረጋት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ትቅም ነውና! ይህንም ለማድረግ ጊዜ ወሳኝ ነው። ውሳኔም ቁርጠኛ መሆንን ይጠይቃል።

ይህ ካልሆነ ግን ታሪክ ልክ እንደ ሱዳኑ ጄኔራል ኢብራሂም አቦድ እርስዎንም በአባይ/ናይል ወንዝ ታሪክ በጥቁር መዝገቡ ከማስፈር ወደ ኋላ አይልም።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here