ከቻይና የሚመጡ መንገደኞች በማቆያ ክፍል እንዲቆዩ ሊደረግ ነው

0
802

ከቻይና የሚመጡ መንገደኞችን በመለየት በማቆያ ክፍል እንዲቆዩ ለማድርግ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለፀ። የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እና ክትትል ለማድረግ የሚያስችል ማእከልም በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ተቋቁሟል።

በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከቻይና የሚመጡ መንገደኞች ከሌላው መንገደኛ ጋር ሳይቀላቀሉ የሙቀት ምርመራ የሚደረግላቸው ሲሆን፣ ከቻይና ለሚመጡ መንገደኞች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ የኢሚግሬሽን ልዩ መስኮት ተዘጋጅቶላቸዋል። ከቻይና የሚመጡ መንገደኞችን የጤና ሁኔታ መከታተል እንዲቻል ለባለሙያዎች ሥልጠና ተሰጥቶ አገልግሎት መጀመሩም ተገልጿል።
ቫይረሱ ከተቀሰቀሰባት ከቻይናዋ ዉሃን ከተማ የሚመጡ ማናቸውም መንገደኞች ወደ ለይቶ ማቆያ ማእከል እንዲገቡ ተወስኗል። በመሆኑም ወደ አገር እንደገቡ በተዘጋጀው ለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆነው አስፈላጊው የሕክምና ክትትል በመደረግ ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

እስከ አሁን በኢትዮጵያ ከኮሮና ቫይረስ ሳይያዙ እንዳልቀሩ ተጠርጥረዋል የተባሉ 29 ሰዎች ጥቆማ ቀርቦ እንደነበር የገለፀው ኢንስቲትዩቱ፣ ጥቆማዎቹ ኢንስቲትዩቱ ውስጥ ለሚገኘው የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማእከል እንደቀረቡ ታውቋል።

በተደረገው ማጣራት 14ቱ በቫይረሱ የመያዝ ምልክት በማሳየታቸው ተለይተው ወደ መቆያ ስፍራ እንዲገቡ ተደርገዋል። ወደ ደቡብ አፍሪካ 11 ናሙናዎች ተልከው ስምንቱ (8) ከቫይረሱ ነፃ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን ሌሎች ሦስት ናሙናዎች ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልከው የምርምራው ውጤት በቀጣዮቹ ሦስት ቀናት ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በቻይና እስከ አሁን ከ31 ሺሕ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁ ሲሆን፣ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ምሽት 635 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል። በቫይረሱ የተጠቁ እና ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር በቀጣይ ቀናት ከዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችል ይገመታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 30 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here