ዳሰሳ ዘ ማለዳ (የካቲት 09/2012)

0
712

ዳሰሳ ዘ ማለዳ (የካቲት 09/2012)

የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሚያቀርባቸው እርምጃዎች እየተተገበሩ አለመሆኑ ተገለጸ

 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሚያቀርባቸው የእርምት ርምጃዎች በታችኛውና መካከለኛው የመንግስት አስተዳደር እርከን ተገቢውን ምላሽ እንደማያገኙ ተገለጸ።ተባባሪ የማይሆኑ የመንግስት ባለስልጣናት ተጠያቂነት እንዳለባቸውና ማንኛውም ሰው ያለበቂ ምክንያት በተቋሙ በቀረበ የምርምራ ውጤትና መፍትሄ ወይም ቁጥጥር ውጤት መሰረት በ 30 ቀናት ውሰጥ የእርምት እርምጃ መውሰድ ይገባል ተብሏል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ እንዳለ ሀይሌ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ በተቋሙ የተሰጡ የመፍትሄ ሃሳቦችን ተግባራዊ ያላደረጉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። (ኢዜአ)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

 

የጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል በገጠመው የውሃ እጥረት ምክንያት ወላዶች መቸገራቸው ተነገረ፡፡ በሆስፒታሉ  አዳዲስ ማዋለጃ ክፍሎች ተዘጋጅተው አገልግሎት እየተሰጠ ቢሆንም በውሃ እጥረት ምክንያት ወላዶች ታጥበው ለመውጣት መቸገራው ሆስፒታሉ ገልጿል ።( ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………

ኢትዮጵያ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች ዝውውር በሰፊው ከሚሰራጭባቸው ሃገሮች ተርታ መሰለፏ ተገለጸ፡፡ በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የሕግ ጥናቶች፤ማርቀቅና ማከፋፈል ዳይሬክተር የሆኑት  በላይሁን ይርጋ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት ባለፉት ጥቂት አመታት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በኢትዮጲያ ውስጥ እየጨመረ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡(ኢትዮ ኤፍ ኤም)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ተሰርቆ ኔዘርላንድ የተወሰደውን ዘውድ የቅርስ እና ጥበቃ ባለስልጣን በነገው ዕለት ሊረከብ እንደሆነ አስታወቀ፡፡ ቅርሱ በኔዘርላንድ ለ21 ዓመታት ተደብቆ እንደቆየም ታውቋል፡፡ከዚህ ቀደም በኔዘርላንድ የሚኖሩት ትውልደ ኢትዮጵያዊ  ሲራክ አስፋው የተባሉት ግለሰብ ይህንኑ ቅርስ ለ21 ዓመታት በመኖሪያ ቤታቸው ማቆየታቸውን ስካይ ኒውስ፤ ቢቢሲና ለሌሎችም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን መዘገባቸው ይታወሳል፡፡ (ሸገር ኤፍ ኤም )

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለመራጮች ምዝገባ የሚያገለግሉ የህትመት እና የቁሳቁሶች ግዥ ማጠናቀቁን አስታወቀ።

ቦርዱ ቁሳቁሶቹን ከፍተኛ ጥበቃ ባለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ መጋዘን አስገብቶ ማጠናቀቁን በመግለፅ የቁሳቁስ ድልድል ስራ በቅርቡ እንደሚጀምር ይፋ አድርጓል። (ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በኮሮኖ ቫይረስ ከተጠቁ አገራት የመጡ 465 ሰዎች ክትትል እየተደረገላቸው ነው ሲል የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ 125 ሺህ 850 የሚሆኑ መንገደኞች በሙቀት ልየታ ማለፋቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል። አሁን ላይም 465 የሚሆኑት ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው የጤና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን በመግለጽ እስካሁን ባለው መረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ አልተከሰተም ብሏል። (ጤና ሚኒስቴር)
…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በኢትዮጵያ ባለፉት 6 ወራት ብቻ 583 የሕገ ወጥ መሣሪያ ዝውውር ወንጀሎች መፈጸማቸውን የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።

በወንጀሉ የተጠረጠሩ 98 ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፣ 17 ሰዎች ደግሞ እስካሁን አለመያዛቸው ተገልጿል።

ከተጠርጣሪዎቹ በተጨማሪ 218 ክላሽ፣ 6 ሺህ 823 ሽጉጥ እና ከ168 ሺህ 700 በላይ ጥይት መያዙ ተነግሯል። (ኢቢሲ)
………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

 

የክልል ልዩ ሃይል ፈርሶ በሃገር መከላከያ ሰራዊት እንዲጠቃለል ጽናት ለኢትዮጵያ፣የኢትዮጲያ አሜሪካዊያን ዜጎች ምክክር፣የዘር ፖለቲካ በህግ ይታገድ ዘንድ ግፊት የማድረግ ንቅናቄ እና የኢትዮጵያ አድቮኬሲ ኔትወርክ የተሰኙ የሰብዓዊ ድርጅቶች በጋራ ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ ተገለጸ፡፡በምክክር መድረኩ ላይ ትንታኔ የሰጡት የዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህርት  መስከረም አበራ በአገራችን እየተካረረ የመጣው አክራሪ ብሄርተኝነት በመገናኛ ብዙኀንና በክልል ልዩ ሃይሎች እየተደገፈ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ መንግስት ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ልዩ ሃይሎችን አፍርሶ በሃገር መከላከያ ሰራዊት ውስጥ እንዲያጠቃልል በምክክር መድረኩ ላይ ጥያቄ ቀርቧል፡፡(ኢትዮ ኤፍ ኤም)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here