የጥጥ ዋጋ ባለፉት ሳምንታት ከኹለት እጥፍ በላይ ጨመረ

0
1552

የጥጥ ዋጋ በ20 ቀናት ውስጥ ከ150 ብር በላይ ጭማሪ ማሳየቱን ባህላዊ ልብሶችን የሚያመርቱ ማኅበራት ገለፁ።
አንድ ኪሎ ጥጥ ከ20 ቀናት በፊት ከ50 እስከ 70 ብር በሆነ ዋጋ ሲገዙ እንደቆዩ የገለጹት ማኅበራቱ፣ አሁን ግን ይኼው መጠን ጥጥ እስከ 230 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ላለፉት 20 ዓመታት የሸማ እና ባህላዊ አልባሳት ሥራ ላይ ተሰማርተው የቆዩት ጥሩወርቅ፣ ላለፉት ኹለት ዓመታት የራሳቸውን ማኅበር በመመስረት በመሥራት ላይ ይገኛሉ። ጥሩወርቅ ግዛው አይተውት በማያውቁት ሁኔታ ባለፉታ ኹለት ሳምንታት በጥጥ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ መኖሩን በማንሳት፣ በሥራቸው ላይ ችግር እንደፈጠረ ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ መርካቶ ድር ተራ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ተዘዋውራ ባደረገችው ቅኝት፣ ለባህላዊ ልብሶች ማምረቻ የሚሆን የተዳመጠ ጥጥ በኪሎ ከ250 እስከ 280 ብር በመሸጥ ላይ እንደሆነ ታዝባለች።

አማኑኤል እና ለማ የተሰኘ የጥጥ እና የክር ውጤቶች መሸጫ ሱቅ ባለቤቶች እንደገለፁት፣ ካለፈው ወር ጀምሮ ጥጥ የሚያቀርቡ ፋብሪካዎች በዋጋው ላይ ጭማሪ አድርገዋል። ያንንም ተከትሎ የዋጋ ጭማሪውን ለማድረግ መገደዳቸውን የተናገሩ ሲሆን፣ አንድ ኪሎ ጥጥ 260 ብር በመሸጥ ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

ፋብሪካዎቹ ጭማሪውን ለምን እንዳደረጉ አናውቅም የሚሉት አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ነጋዴዎች፣ ከኤክሳይስ ታክሱ ጋር በተያያዘ በሌሎች ምርቶች ላይ የተስተዋለውን ጭማሪ ምክንያት በማድረግ ሊሆን እንደሚችል ገልፀዋል። የጥጥ ገበያ ከጥምቀት በዓል በኋላ መቀዛቀዙንም አያይዘው አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዮት በበኩሉ፣ የዋጋ ጭማሪው በደላሎች እና በነጋዴዎች ምክንያት የተከሰተ እንደሆነ ገልጿል። ነጋዴዎች ከጥጥ አቅራቢ ፋብሪካዎች እና ባለሀብቶች በመግዛት በመጋዘን በማከማቸት በጥጥ ላይ የዋጋ ንረት እንዲኖር እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

ጥጥን ማቅረብ የሚፈቀድላቸው ለጥጥ እና ክር ፋብሪካዎች እንዲሁም ጥጥን ከእርሻ ላይ ለሚገዙ ባለሃብቶች ነው የሚሉት የጨርቃ ጨርቅ ልማት ኢንስቲትዩት የጥጥ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ መሰለ መኩሪያ ናቸው። አክለውም ግለሰቦች እና ደላሎች ጥጥን በሕገወጥ መንገድ በመግዛት መርካቶ ለሚገኙ ነጋዴዎች እንደሚያቀረቡ ተናግረዋል፡፡ ይህም ጥጥ ፈላጊዎች ምርቱን ከሦስተኛ እና አራተኛ አትራፊ በመግዛታቸው ጭማሪ እንዲያስተናግዱ እንደሚያደረጋቸው ገልፀዋል።

ጥጥን በመሰብሰብ እና በመዳመጥ ለአገር ውስጥ እና ለውጪ ገበያ የሚያቀርቡ 21 ፋብሪካዎች አሉ የተባለ ሲሆን፣ ተጠቃሚዎች በቀጥታ ከእነዚህ ፋብሪካዎች ማግኘት እንደሚችሉ ተገልጿል።
የዋጋ ጭማሪው መሰረት የሌለው ነው ያሉት ምክትል ኃላፊው፣ ጥጥ በአነስተኛ ዋጋ መግዛት የሚፈልጉ በልብስ ሥራ ላይ የተሰማሩ ፈላጊዎች በቡድን በመሆን ጥጥን በቅናሽ ዋጋ በኢንስቲትዩቱ በኩል ማግኘት ይችላሉ ብለዋል።

ጥጥ በትግራይ፣ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል፣ በደቡብ፣ በአፋር እና በጋምቤላ ክልሎች በመመረት ላይ ይገኛል። በዓመት ከ60 እስከ 70 ሺሕ ቶን ጥጥ የሚመረት ቢሆንም፣ ባለፈው የምርት ዓመት ከ40 ሺሕ ቶን ሊዘል አልቻለም።

ጭማሪው ከምርት መቀነሱ ጋር የተያያዘ አይደለም የሚለው ኢንስቲትዩቱ፣ ጥጥ መዳመጫ ፋብሪካዎች የተለየ ጭማሪ እንዳላደረጉ ገልጿል። የጥጥ ዋጋ በባህሪው ወጥ ሆኖ የሚቆይ ነው የሚሉት መሰለም፣ እስከ 90 ሺሕ ቶን በዓመት በሚመረትበት ወቅትም ቢሆን የዋጋ ቅናሽ አያሳይም ነበር ብለዋል።

ለጥጥ ምርቱ መቀነስ ምክንያት የሆነው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰሊጥ ዋጋ መጨመሩ ነው የተባለ ሲሆን፣ አምራቾች ጥጥን በመተው ወደ ሰሊጥ ምርት በመሰማራታቸው መሆኑን መሰለ ገልፀዋል። በተጨማሪም ጥጥ በባህሪው በተባይ የመጠቃት ዕድሉ ከፍ ያለ ነው ያሉት መሰለ፣ ባሳለፍነው የምርት ዓመት የፀረ-ተባይ ኬሚካሎች እጥረት ስለነበር ገበሬዎች ጥጥ አላመረቱም ነበር ሲሉ አስታውሰዋል።

በ2012 ስድስት ወራት በጨርቃ ጨርቅ ልማት ዘርፍ የተሰማሩ የውጪ እና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በአጠቃላይ 99.86 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝተዋል። ከገቢው ውስጥ 93 በመቶው በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ባሉ አምራቾች የተገኘ ሲሆን፣ ቀሪው ሰባት በመቶ ደግሞ በአገር ውስጥ ባለሀብቶች የተገኘ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 68 የካቲት 14 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here