መቼም ቢሆን በጫና አንንበረከክም!

0
722

በሐምሌ 2007 የያኔው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት አዲስ አበባ ሲደርሱ፣ የወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንታዊ አውሮፕላን ኤርፎርስ ዋን ተቀብለው ከጀርባቸው የቆመው ዘ ቢስት እየተባለ ወደሚጠራው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት መኪና አስገብተዋቸው ነበር። ከዚያ ግን ኦባማ እና ቡድናቸው በተመሳሳይ መኪኖች ገብቶ ጉዞ ሲጀምር፣ ኃይለማርያም በዝናብ በእግራቸው ረጅም መንገድ ከተጓዙ በኋላ ነበር መኪናቸው ጋር የደረሱት። ይህም የሆነው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የደኅንነት ቡድን የጠቅላይ ሚኒስትሩ መኪና በአቅራቢያው ዝር እንዳይል በመከልከላቸው ነበር። የሚገርመው ነገር ግን በኢትዮጵያ በኩል ያሉት ሰዎች ይህንን መቀበላቸው ነው።

ኦባማ ታዲያ ኢትዮጵያን ከመጎብኘታቸው በፊት ኬንያ ከርመው ነበር። በእኛ አገር ከተገረምን የኬንያው ደግሞ አስደንጋጭ ነበር። የኦባማ አባት ቤተሰቦች አገር የሆነችው ጎረቤታችን፣ ፕሬዝዳንቱ ወደ አገር ሊገቡ ሲቃረቡ ለአንድ ሰዓት ግድም የአየር ክልሏን ዘግታ የቆየች ሲሆን፣ በቆዩባቸውም ቀናት ከ20 ሺሕ ጫማ በታች መብረር ተከልክሎ ነበር። ፕሬዝዳንቱ ከአገሪቱ ሲወጡ ደግሞ ለ40 ደቂቃ ያህል የአየር ክልሏን ዘግታ ነበር።

ባራክ ኦባማ ሲመጡ የተደረገው የደኅንነት ዝግጅት በኬንያ ታሪክ ትልቁ ነው። የአሜሪካ ባህር ኃይል፣ ሲአይኤ እና የአሜሪካ የምስጢር አገልግሎት ድርጅት ሰዎች አውሮፕላን ማረፊያዎችን ብቻ ሳይሆን ከተማውንም ሲቆጣጠሩ ነበር። ናይሮቢ በአሜሪካ የውትድርና ሔሊኮፕተሮችም ስትቃኝ ከርማለች።

እንግዲህ ከኹለቱ አጋጣሚዎች መረዳት የሚቻለው አሜሪካኖቹ እድሉ ከተሰጣቸው ራሳቸውን ወደ ሰማይ ሌላውን ጫማቸው ስር የሚያደርግ የፕሮቶኮል አጠባበቅ ለማድረግ ወደ ኋላ እንደማይሉ ነው። ምንም እንኳን ኃይለማርያም ደሳለኝ በእግራቸው ብዙ ርቀት ቢሔዱም፣ ሌሎች የአሜሪካኖቹ የደኅንነት ሰዎች የጠየቋቸውን ጥያቄዎች ኢትዮጵያ ውድቅ አድርጋ በራሷ መንቀሳቀሷ የሚታወስ ነው። ይህም ለራሳችን ያለንን ክብር በብቃት ልንደግፍ መቻላችንን የሚያሳይ ነው።

ወቅታዊ ወደ ሆነው ጉዳይ ስንሔድ ደግሞ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በአሜሪካ እና የዓለም ባንክ አደራዳሪነት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አሞላልና ውሀ አለቃቀቅ ላይ ሲወያዩ ከርመዋል። ይህ ድርድር በተደራዳሪዎች መካከል ስምምነት ላይ መድረስ ከባድ ሆኖ ስለተገኘ የተቋረጠ ሲሆን፣ የተለያዩ ምንጮች አሜሪካኖቹ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ላይ ጫና ሲያሳድሩ እንደነበር ሲገልጹ ከርመዋል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ በዚህ ሳምንት ኢትዮጵያን በጎበኙበት ጊዜ፣ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ከተወያዩባቸው ጉዳዮች አንዱ፣ ይህን ስምምነት ዳር ስለማድረስ እንደሆነ ምንጮች ጠቁመዋል።

ሪፖርተር ጋዜጣ በዚህ ሳምንት እንዳሳወቀው፣ ሰኞ የካቲት 9 ቀን 2012 በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተደራዳሪዎቹ፣ ባለሥልጣናት እና የሚመለከታቸው ባለሙያዎች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የሚደራደሩት የሕግ እና የቴክኒክ ባለሙያዎች ጫና እንደደረሰባቸው በግልጽ ተናግረዋል። ከዚህ በዘለለ የተደራዳሪ ቡድኑ አባላት ድርድሩ ኢትዮጵያን የሚጠቅም ሂደት ነው ብለው እንደማያምኑ መናገራቸው ተዘግቧል።

ጋዜጣው እንደ ዘገበው ‹‹የአሜሪካ መንግሥትን ወክለው ድርድሩን የሚታዘቡ ኃላፊዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች፣ ‹“ኮንሲኩዌንስ” (ችግር) ያመጣባችኋል› በማለት በኢትዮጵያ ቡድን አባላት ላይ ጫና ያደርጉ ነበር።” ሪፓርቱ እንደሚያሳየው የግብጽ ተደራዳሪዎች ይህንን አዝማሚያ ተረድተው ግብጽ በዓባይ ውሀ ላይ የበላይነቷን መልሳ ልትይዝ እንደሚገባ የሚጠቁሙ አቋሞችን ወደማራመድ አዘንብለው ነበር።

እንደሚታወቀው ግብጽ በአሜሪካ ከፍተኛ የጦር መሣሪያ እና ሌሎችም ዓይነት እርዳታ ከሚቀበሉ አገሮች መካከል የምትጠቀስ ናት። በመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ ውስጥ እስራኤልን በመወገን የምትንቀሳቀሰው አሜሪካ፣ የሕዳሴውን ግድብ ድርድር ግብጽን በሌሎች የፖለቲካ ጉዳዮች ከጎኗ ለማሰለፍ ልትጠቀምበት እንደምትችል መገመት ይቻላል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ላይ ጫና ማሳደሯ የማይጠበቅ ጉዳይ አይደለም። እንደውም ለረጅም ዘመን በወንዙ ላይ አገሮቹን ለማደራደር ስትጥር ብትቆይም፣ እድሉ ተነፍጓት መቆየቷ ግምት ውስጥ ሲገባ ዋነኛው ችግር እንድታደራድር እድሉ መሰጠቱ ላይ ነው።

በቅርቡ ድርድሩን አስመልክቶ ግብጻዊ ፀሐፊ የከተበው አንድ ጽሑፍ ኢትዮጵያ ግብጽ ያቀረበችውን የሕዳሴውን ግድብ የውሀ የመያዝ አቅም ከአስዋን ግድብ ጋር የማመጣጠን ሐሳብ እንዳልተቀበለች ይገልጻል። በዚህ የግብጾች ሐሳብ መሠረት የአስዋን ግድብ 70 በመቶ የሚሆን ውሀ ሲኖረው ሕዳሴውም ወደ 70 በመቶ እንዲስተካከል የሚጠይቅ ነው። ሌላው ጽሑፉ የሚጠቁመው የግብጽ ጥያቄ ደግሞ ኢትዮጵያ የሕዳሴው ግድብ ተሠርቶ ካለቀ በኋላ ሥራ ሲጀምር እንቅስቃሴውን አስመልክቶ ያለውን መረጃ ለግብጽ እንድትሰጥ የሚል ነው። ይህንንም የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች የአገር ሉዓላዊነትን የሚነካ መሆኑን በመግለጽ ውድቅ እንዳደረጉት ጽሑፉ ያትታል።

ከላይ የተጠቀሰው ጽሑፍ እንደሚያሳየው፣ ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች በአሜሪካ እና ዓለም ባንክ አደራዳሪዎች ጫና ቢደረግባቸውም፣ የአገራቸውን ጥቅም አሳልፈው የሚሰጡ ዓይነት ሆነው ያለመገኘታቸውን ነው። እንዲህ ማድረጋችሁ ችግር ይፈጥርባችኋል ወይም ይዞት የሚመጣው መዘዝ አለ የሚሉ ማስፈራሪያዎች በኃያሏ አገር ሰዎች ቢደቀንባቸውም፣ አገር የጣለባቸውን ኃላፊነት በቁርጠኝነት እየተወጡ እንደነበር የግብጻዊው ጽሑፍ ያሳያል።

ከዚያም በተጨማሪ በዚህ ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት በተደረገው ውይይት ላይ በግልጽ ጫና ሲደረግባቸው እንደነበር እና ድርድሩ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብር እንዳልሆነ አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸው፣ ለሕሊናቸውም ሆነ ለአገር ታማኝ ሆነው ለመንቀሳቀሳቸው እማኝ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ማይክ ፖምፔዮ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ለመገናኘት በዚህ ሳምንት አጋማሽ ጽሕፈት ቤታቸው በተገኙበት ጊዜ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቆመው እየጠበቋቸው የመኪናቸው በር ከተከፈተ በኋላ ይወርዳሉ ብለው ሲጠበቁ ‹የምጠብቀው ሰው አለ› ማለታቸው እና ይህም ሰው ፎቶ አንሺያቸው መሆኑ ዐቢይን አስቀይሟቸው እንደነበርም ተዘግቧል። ይህም አሜሪካኖቹ በአጠቃላይ ትራምፕ “የቆሻሻ ትቦ” ብለው የገለጿቸውን የአፍሪካ አገሮች ከልባቸው እንደሚንቁ የሚያሳይ ገጠመኝ ነው።

በሕዳሴው ግድብ አሞላል እና ውሀ አለቃቀቅ ላይ ኢትዮጵያን ለመጫን የሚሞክሩትም በዚሁ ሌሎችን አኮስሶ የማየት አመላቸው ነው። የእነሱን ስሜት ለመቀየር ምንም ማድረግ ባይቻልም፣ እኛ ለእንደዚህ ዓይነት ፀያፍ ተግባራት የምናሳየው ምላሽ ግን የወደፊቱን የእነሱን ባሕሪይ የሚወስን ነው። በዚህም ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፊታቸውን አዙረው ፖምፒዮን ጥለዋቸው ወደ ቢሯቸው መመለሳቸው፣ ብልግናን የምንታገስበት ጫንቃ እንደሌለን ማሳያ ነው።

ይህንንም ተከትሎ አሜሪካዊው ባለሥልጣን ተደናግጠው ተከትለዋቸው ገብተው ሰላምታ መስጠታቸው ደግሞ በሚገባቸው ቋንቋ መልዕክቱን እንዳደረሷቸው ማረጋገጫ ነው። ምንጮች እንደሚሉት ዐቢይ ስምምነቱን እንዲስማሙ ጫና ይፈጥራሉ የተባሉት ፖምፔዮም፣ ሳይሳካላቸው ቀርቆ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስምምነቱን እንደማይፈርሙ ነግረዋቸዋል።

በዚህ ገንዘብ እና ሥልጣንን በፈለገው መንገድ ማግኘትን እንደ አሸናፊነት፣ ለአእምሮ ታማኝ ሆኖ ለፍቶ ጥሮ ግሮ መኖር ደግሞ እንደ ተሸናፊነት በሚወሰድበት ዓለም፣ ሕዝብን ወይም ሙሉ አኅጉርን በንቀት ለሚመለከቱ እና በዚህም መንገድ ተግባራቸውን ለሚገልጹ ደፋሮች ከሚመጥናቸው መልስ በቀር መስጠት እንደማበረታታት ይቆጠራል። በቅኝ ግዛትነት የበታችነት እንዲሰማን ማድረግ ያቃታቸው ሁሉኅ በኢኮኖሚ የበላይነት እድላቸውን ሲሞክሩ ዝም ብለን ልናያቸው አይገባም። በመሆኑም የኢትዮጵያ የሕዳሴው ግድብ አሞላልና ውሀ አለቃቀቅ ተደራዳሪዎች የደረሰባቸውን ጫና ተቋቁመው፣ ኃላፊነታቸው የሆነው የአገር ጥቅም እንዳይነካ ማድረጋቸው እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሜሪካም ብትሆን ለአገር ጥቅም ማስጠበቅ የማይረዳ ነገር ያለመቀበላቸው ሊበረታታ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 68 የካቲት 14 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here