የትግራይ ንግድ ምክር ቤት የወልቃይት የስኳር ፋብሪካን ለመግዛት ሀብት ማሰባሰብ ጀመረ

0
625

ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች መካከል የሆነውን የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ወደ ግል ይዘዋወራሉ ተብለው ከሚጠበቁ ፋብሪካዎች መካከል መሆኑን ተከትሎ፣ የትግራይ ንግድ እና ዘርፉ ማኅበራት ምክር ቤት ሀብት በማሰባሰብ ለመግዛት ፍላጎት እንዳለው ገለፀ።

የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት አሰፋ ኃይለ ሥላሴ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ የአዋጪነት ጥናት በምክር ቤቱ ተጠንቶ በመጠናቀቁ የክልሉን ምሁራን፣ ባለሀብቶች እና በውጪ የሚኖሩ ዳያስፖራዎችን በማሳተፍ እና ሀብት በማሰባሰብ ጨረታውን ለማሸነፍ እንደሚሠሩ ተናግረዋል። ይህንን እቅድ ምክር ቤቱ ይፋ ካደረገ ገና አንድ ሳምንቱ መሆኑን የገለፁት አሰፋ፣ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ግን ከፍተኛ ፍላጎቶች መምጣታቸውን ገልፀዋል።

በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን ወልቃይት ወረዳ የሚገኘው ይህ ፋብሪካ እስከ አሁን 12 ቢሊዮን ብር በላይ የጠየቀውን የዛሬማ ሜይዴይ ግድብን ተመሥርቶ የተቋቋመ ነው። ምንም እንኳን ግድቡ ባጋጠመው የግንባታ መጓተት ምክንያት ወደ ሥራ ባይገባም፣ ይህንን እንቅስቃሴ የሚመራው የክልሉ የንግድ ምክር ቤት ፋብሪካውን በመጫረት ሂደት ውስጥ የገንዘብ እጥረት እንዳያጋጥም በሚል ቀድሞ ገንዘቡን ለማሰባሰብ መወሰኑን ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል። የሀብት ማሰባሰቡንም ከተለያዩ የውጪ አገር የኢምፖርት እና ኤክስፖረት ባንኮች (ኤግዚም ባንኮች) ገንዘብ እናፈላልጋለን ሲሉም ተናግረዋል።

‹‹የተለያዩ የአገር ውስጥ ባንኮችም ብድር እናቅርብ ብለው እየጠየቁ ነው›› ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል። ‹‹በአካባቢው ምንም አይነት የፖለቲካ ያለመረጋጋት የለም። ቢኖርም በሕጉ መሰረት ይፈታል ብለን ስለምናምን በአካባቢው ሀብት ለማፍሰስ አንፈራም።›› ሲሉም ተናግረዋል። ‹‹በትግራይ ክልል ፋብሪካ የሚያቃጥልም ሆነ ድንጋይ የሚወረውር አካል የለም›› በማለትም አክለዋል።

ምክር ቤቱ ይህንን ኃላፊነት ወስዶ ለመሥራት ከተቀበለ በኋላ የካቲት 17/2012 የሰጠውን መግለጫ ተከትሎ ከታቀደው በላይ ፍላጎቶች ከአገር ውስጥ እና ከውጪ መምጣታቸውን ግልጸዋል። ‹‹እኔ ኢትዮ ስኳር ውስጥም አለሁኝ፤ የዚህኛው ፍላጎት ግን ከፍተኛ ነው›› ሲሉም በማነፃፀር ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከትግራይ የንግድ ምክር ቤት በሻገር ኢትዮ ስኳር የተባለ ድርጅትም ወንጂ ስኳርን ለመግዛት በሚሊዮን ብሮች የሚቆጠር አክሲዮን እየሸጠ ይገኛል። እንዲህ አይነት ቀድሞ ሀብት የማሰባሰብ ተግባራት ፋብሪካዎቹን ወደ ግል የማዞር ሂደቱ ላይ የተለየ ጫና አያመጡም። እንደውም የአገር ውስጥ ባለሀብት በገበያው ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው እንዲመጡ ያግዛል ሲሉ የገንዘብ ሚኒስቴር አማካሪ ብሩክ ታዬ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

መንግሥት በአጠቃላይ 13 የስኳር ፋብሪካዎች ያሉት ሲሆን፣ እነዚህን ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ቢይዟቸው ለአገርም እድገት ጠቃሚ ይሆናል ብለው ያምናሉ። መንግሥትም ይደግፋቸዋል፤ እንደ ብሩክ ገለፃ።

እያንዳንዱ የስኳር ፋብሪካ ያለውን ንብረት እና እውነታ የማጥናት ስ,ሥራ እንደተሠራ እና ከንብረት ባሻገር ውጤታም መሆን እንዳይችሉ አድርጎ የያዛቸውን ችግሮች መንግሥት እንዳጠናም ይናገራሉ። ፋብሪካዎቹ የወጣባቸው ወጪ እና ገበያ ላይ ሲቀርቡ ምን ያህል ያወጣሉ የሚለው ጥናት ተጠንቶ ተገባዷል።

ወደ ግል የማዘዋወሩ ስትራቴጂ መጠናቀቁን የተናገሩት ብሩክ፣ እነዚህን ፋብሪካዎች በአንዴ እናዘዋውር ወይስ በየተራ የሚለው ተጠናቆ ስድስቱ እንዲዘዋወሩ መወሰኑን ብሩክ ተናግረዋል። ‹‹ነገር ግን እንደዚህ ሀብት የሚያሰባስቡ ሰዎች ስለ ስትራቴጂው መረጃ የሌላቸው ናቸው ብዬ አስባለሁ፤ ምክንያቱም ገና ብዙ ያላለቁ ሥራዎች አሉ።›› ሲሉ አውስተዋል።

‹‹ሪፖርቶቹን ለማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴው አቅርበናል፣ ግን የተኞቹ ለገበያ ይቅረቡ ዋጋቸውስ የሚለውን ኮሚቴው ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር ተነጋግሮ የሚወስነው ሲሆን፣ ይህም ገና ብዙ የሚቀረው ነው›› ብሩክ እንዳሉት።

‹‹በዙሪያችን ከኻያ በላይ ባንኮች አሉ። እና ኢትዮጵያውያን እነዚህ የአገር ውስጥ ሀብት አሰባስበው መምጣት ይችላሉ፣ ልምድ ያለው የውጪ ባለሀብት ቢመጣ እንኳን አብሮ ለመሥራት የድርድር አቅም ይሰጣቸዋል›› የሚሉት ብሩክ ‹‹ይህ ፋብሪካ የሕዝብ ስለሆነ የአካባቢው ሰዎች በጋራ ሆነው ጨረታው ሲወጣ ቢሳተፉ በመርህ ደረጃ ችግር የለውም።››

እነዚህ ድርቶች በጨረታ ተወዳድረው ቢሸነፉ ደግሞ የግል ድርጅት እንደመሆናቸው ሙሉ ኃላፊነቱን ይወስዳሉ ሲሉ ብሩክ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here