የውጪ ጉዲፈቻ የተከለከለበት ምክንያትና አስከልካዮቹ!

0
1529

ጥር 20/2012 ለህትመት የበቃችውን አዲስ ማለዳ ጋዜጣ በመጥቀስና በእለቱ የሐተታ ዘ ማለዳ ጉዳይ የሕጻትን ጉዳይ በጉዲፈቻ መነጽር ቃኝታለች። ይልቁንም የውጪ ጉዲፈቻ በመከልከሉ ሊድን የሚችል በሽታ የሚሰቃዩና እድሉን ማግኘት ሲችሉ ግን ስለተከለከሉ ሕጻናትም አስነብባለች። ሙሉጌታ በቀለ ከዚህ ዘገባ በመነሳት ‹ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮኻል› እንዲሉ፣ መንግሥት በጉዲፈቻ ላይ አስቀድሞም ከፍተኛ ድርሻ ያለው ሆኖ ሳለ፣ በብልሹ አሠራር ሰበብ የውጪ ጉዲፈቻ እንዲቀር ማድረጉነ ይጠቅሳሉ። ሕጉ እንዲሰረዝ የተሄደበት መንገድም ሆነ የቀረበው ምክንያት ውሃ የሚያነሳ አልነበረም የሚሉት ሙሉጌታ፣ ሕጉ በተሰረዘ ጊዜ በተወካዮች ምክር ቤት የነበረውን ሁኔታ በምልሰት በማስታወስ የሕጻናት ማሳደጊያዎች ያደረጉትን ሙግት አቅርበዋል።

በአዲስ ማለዳ ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 20/2012 ለህትመት የበቃችው ጋዜጣ ላይ በሐተታ ዘ ማለዳ የጋዜጣዋ ክፍል ላይ ‹‹የሕጻናት ዓለም-በጉዲፈቻ መነጽር›› በሚለው ዘገባ ላይ ሐሳብ ከተጠየቁ ሰዎች መካከል አንዱ ነበርኩ። በጋዜጣዋ ላይ የወጣውን ጽሑፍ ካነበበኩት በኋላ፣ በሴቶችና ሕጻናት ዙሪያ የሚሠሩ ሥራዎችን በተለይ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሕጻናትን ጉዳይ አስመልክቶ በለጠ ባዬ (በሴቶችና፤ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የሕጻናት ድጋፍና የአገልግሎት ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር ተወካይ) እንዲሁም አናንያ ያዕቆብ (በአዲስ አበባ ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ቢሮ ሠራተኛ) የሰጡት አስተያየትና የሕጻናትን ጉዳይ በተመለከተ አገራዊ እይታ ላይ ያላቸው መረጃ አነስተኛ እንደሆነ አስተውያለሁ።

ወይም የሕጻናትን ጉዳይ የሚሠሩበት የኃላፊነት መጠሪያቸው ስለሆነ ብቻ እየሠሩና ያሉና የሕጻናቱን ጉዳይ ከቁብ እንደማይቆጥሩት፣ ይህ ደግሞ በሕጻናት ላይ የሚደርሰውን ችግርና ጉዳት በዚህ ግንዛቤ ደረጃ አቅጣጫ መስጠትና ማስተባበር የማይቻል በመሆኑ፤ የሰጧቸው መረጃዎችም እጅግ የተሳሳቱና የሚያሳስቱ በመሆናቸው በተጨማሪም የሕጻናቱን ችግርና የመብት ጥሰት በተለይ በመንግሥት ደረጃ የሚከናወነውን ከመፍታት ይልቅ አድበስብሶ የሚያልፍ መስሎ ስለተሰማኝ ነው። ብሎም የአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ተከታታዮች እውነታውን እንዲያውቁት በማሰብ ይህችን ጽሑፍ አዘጋጅቻለሁ።

የሕጻናት ዓለም ኢትዮጵያ ውስጥ የተዘጋና በጭለማ የተዋጠ ነው። በአገራችን መንግሥት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ሲነደፉም ሆነ ለሕዝብ ይፋ ሲደረጉ፣ ቀድሞ የሚታየው ጉዳይ ፖሊሲው የሚመለከታቸው አካላት/ ተጠቃሚዎቹ የምርጫ ካርድ ማውጣት ይችላሉ ወይስ አይችሉም? በዚህ ብጠቅማቸው ይመርጡኛል አይመርጡኝም? የምትል የአምስት ዓመት ሥልጣን ጥማት ማርኪያ ስልት አልያም የዓለም አቀፍ ተቋማት በፖሊሲው መውጣት ምክንያት ፈንድና ድጋፍ አገኛለሁ አላገኝም ከሚል የስግብግበነትና የሙስና መጠቀሚያ ስሌት ነው።

እንጂ በተጨባጭ የዜጎችን ችግር ይቀርፋል ወደ ብልጽግናና ስኬት ይወስደናል የሚል አይደለም። የወጣቶች ፖሊሲ፤ የሴቶች ፖሊሲ፤ የመሳሰሉትን ማየት ይቻላል። እነዚህ የአገሪቷ ሕዝብ ብዛት ከ75 በመቶ በላይ የሚሸፍኑ ሲሆኑ፣ ከፍተኛ የሆነ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉ በመሆናቸው መንግሥት በሥልጣን የማቆየት ሆነ ያለማቆየት አቅም አላቸው። መንግሥት መረዳት ያለበት ወጣቶችም ሆኑ ሴቶች ማንኛውም ዜጋ የሕጻንነት ጊዜ የሚያልፍ መሆኑን ነው። በሕጻንነቱ መልካም ዕድገቱና መብቶቹ በአግባቡ ሳይተገበሩና ሳይከበሩ ያደገ ህጻን፣ አገር ማፍረስ እንጂ መገንባት አይሆንለትም።

የተቃማዊ ፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፤ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ከመንግሥት በባሰ የሕጻናትን ጉዳይ ትተውት በጨለማ ውስጥ ጥለውት ያለ ጉዳይ ነው። ዓላማቸውን በሕጻናት ጉዳይ ያደረጉም ቢሆኑ ለሕጻናት መብት የሚታገሉት እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ነው። ሕጻናት የአባልነት መዋጮ አይከፍሉም፤ መንገድ መዝጋትና ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ አይችሉም። ስለሆነም ለህጻናት መሥራት አዋጭ አይደለም ብለው ያስባሉ። እነዚህ ተቋማትም ቢሆኑ የሕጻናትን ጉዳይ በፖሊሲያቸውና በፕሮግራማቸው ውስጥ ሊያካትቱና ሊተገብሩ ይገባል። አገር የምትቀጥለው ተተኪ ሲኖራት እንጂ እነሱ ስላሉ አለመሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል ባይ ነኝ።

አሁን አገራችን በለውጥ ላይ ነች። ለሕጻናት መብትና ደኅንነት መከበር እኛ ብቻ ነው የምናውቀው የሚለው የመንግሥት አስተሳሰብ ተመትቷል። አሁን በለውጡ ሁሉም በጋራ ስለ አገሩ ያገባዋል። የሕጻናት ጉዳይም ከመቼውም በላይ ሁሉንም ይመለከታል። በተለይ በለውጡ ምክንያት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን አስሮ የሕጻናት መብት እንዳይከበርና ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዳይኖረው በሕግ ተደርጎ የነበረው ገደብ ተነስቷል። የመንግሥት ሹመኛ ነኝ የሚል ማንም ብድግ ብሎ የሕጻናትን መብትና ደኅንነት ሊያፍን፤ ሊሸረሽር፤ ሊሰርዝና ሊደልዝ አይችልም፤ መብቱም የለውም።

ይህን ያላወቁና ያልተገነዘቡ አሁንም በቁጥጥርና በክልከላ መንፈስ፤ በፈላጭ ቆራጭ ሥነ ልቦና ላይ ያሉ ምንም የማያውቁ ግን እናውቃለን የሚሉ የመንግሥት ሠራተኞችም ሆኑ ማንኛውም የሕጻናትን መብት ሊደፈጥጥ የሚሞክር አሠራር ላይ ያሉ አካላት፣ አሁን ቦታ እንደሌላቸው መገንዘብ ይኖርባቸውል። በመሰለኝና በደሳለኝ በሕዝብ እየተከፈለው እየቀለደና ትውልድ እየገደለ የሚኖር ሹመኛም ሆነ ሠራተኛ አይኖርም። ጊዜው የለውጥ፣ የዴሞክራሲ፣ የብልጽግናና የእኩልነት ነው። ሁሉም ዜጋ ሕጻናትን የመንከባከብ መብትም ግዴታም አለበት፤ ሕጻናት በአገር ውስጥና ከአገር ውጭም በቤተሰብ ውስጥ የማደግ መብታቸው ሊከበር ይገባል።

አገራችን እንደሌሎቹ የአፍሪካና ታዳጊ የእስያ አገራት ከሕዝቧ ግማሽ በላይ የሚሆነው ሕጻናት ናቸው። በማእከላዊ ሰታስቲክስ ኤጀንሲ የሕዝብ ትንበያ መሰረት በ2010 የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ግምት 96 ሚሊዮን በላይ ሲሆን፣ ከጠቅላላው የሕዝብ ብዛት ግምት ውስጥ 47 ሚሊዮን በላይ ወይም 52 በመቶ ሕጻናት ናቸው። መንግሥት የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ስርዓት ግንባታ እንዲፈጠር ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርጉና ፈጣን ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ችግር ፈቺ ሕጎችና ፖሊሲዎች ለመንደፍና አፋኝና የመብት ገዳቢ ሕጎችን በማሻሻል ላይ ነው። የነገ አገር ተረካቢ ጤናማና ስብዕናው የተሟላ ዜጋ በመፍጠር ረገድም፣ የሕፃናት መብቶች በአገሪቱ የሕጎች ሁሉ የበላይ በሆነው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 36 ራሱን ችሎ የተካተተውን እንዲሁም አገራችን የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ተግባራዊ ማድረግ፣ የለውጡ አንድ አካል በማድረግ መሥሥ አለበት የሚል እምነት አለኝ።

የሕፃናትን መብትና ደኅንነት በማክበር፣ በማስከበርና ፍላጎታቸውን በማሟላት በኩል፣ ይበልጥ ቀጣይነት እንዲኖረው ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶች፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ሕፃናትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በተቀናጀ አግባብ ትኩረት ሰጥተው በአገሪቱ እና በዓለማቀፍ ሕጎች መሰረት ሊንቀሳቀሱ ይገባል።

ወደ ቀደመው ፍሬ ነገር ልመለስ፤ ሕጻናት በተለይ ወላጅ የሞተባቸውና ተጥለው የሚገኙ በጉዲፈቻ ቤተሰብ የማደግ መብታቸው መከበር ይኖርበታል። ነገር ግን እነዚህ ሕጻናት ከዚህ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ መንግሥት የውጭ ጉዲፈቻን የዘጋበት መንገድ አግባብነት የሌለው መሆኑን በተለያዩ መድረኮች ተገልጽዋል። የኢሕአዴግ መንግሥት እጅግ በጣም በግለሰቦች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ አሰራር እንደነበረው አንዱ ማሳያ የውጭ ጉዲፈቻ የቀረበት መንገድ ነው።

በወቅቱ የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ግለሰብ፣ የውጭ ጉዲፈቻ መቅረት አለበት የሚል አቋም አላቸው። ስለሆነም እንዲዘጋ አሳብ አቀረቡ። እንቶ ፈንቶ ምክንያቶችን ዘረዘሩ። ‹‹የውጭ ጉዲፈቻ እንዲቀር ያቀረብነውን ሐሳብ ምክር በቤቱ ካልወሰነ፣ ፖለቲካዊ ኪሳራ ነው።›› አሉ፤ ሕጉ ተሻረ። ነገር ግን በሕገመንግሥቱም ሆነ በዓለማቀፉ የሕጻናት መብቶች ስምምነት ሰነድ፣ ሕጻናትን የሚመለከት ጉዳይ ላይ ውሳኔ በሚሰጥበት ወቅት ቅድሚያ መሰጠት ያለበት የሕጻኑ ጥቅምና ደኅንነት መሆን እንዳለበት በግልጽ ተቀምጧል። ያንን ችላ በማለት የአዋቂዎችን ፍላጎትና ትምክህት ላይ በመመርኮዝ እንዲሻር ተደርጓል።

የነበረው አካሄድም እጅግ ትክክል ያልሆነና የቀረበው ምክንያትም ሚዛን የሚደፉ ያለመሆናቸውን በርካታ አካላት ተቃውመውታል፤ ሆኖም ሰሚ አልነበረም። እነዚያው ሰዎች አሁንም በሌላኛው ገጽታ ለውጡ ውስጥም ሊያደናቅፉ ይሁን የኢትዮጵያ ሕዝብን ለመካስ በመጸጸት ባይታወቅም፣ ተነክረው ይታያሉ።
አንባቢዎች ግልጽ እንዲሆንላቸው ከውጭ ጉዲፈቻ ጋር ተያይዞ የሚሳተፉ አካላት እነማን ነበሩ የሚለውን እንመልከት። የሕጻናት ማሳደጊያዎች፤ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች፤ የጉዲፈቻ አስፈጻሚ ድርጅቶች፤ የሴቶችና ሕጻናት ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ አደረጃጀቶች ናቸው። 98 ከመቶ የሚሆነውን ጉዳይ የሚያስፈጽመውም መንግሥት ነው። መንግሥት ሕጻናትን ወደ ማሳደጊያ እንዲገቡ ያደርጋል፤ ማሳደጊያ ድርጅቶችንና የጉዲፈቻ አስፈጻሚ የውጭ ድርጅቶችን ፕሮጀክት ገምግሞ ፈቃድ ይሰጣል፤ ሕጻናቱ ለጉዲፈቻ ብቁ መሆናቸውን ለፍርድ ቤት ያረጋግጣል፤ ጉዲፈቻ አድራጊ ቤተሰቦች ሕጻናቱን የማሳደግ ብቃት ይገመግማል፤ ለፍርድ ቤት አስተያየት ይሰጣል።

ፍርድ ቤት ደግሞ ጉዲፈቻው መጽደቁን ሲወስን፣ ፓስፖርት እና የልደት ሰርተፊኬት የሚሰጠው መንግሥት ነው። በተመሳሳይ የሕጻናቱን ሁኔታ ከሄዱ በኋላ የሚከታተለው መንግስት ነው። ይህ የሚያሳየው የውጭ ጉዲፈቻ ላይ 98 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የያዘው መንግሥት እንደነበር ነው። የሕጻናት ማሳደጊያ ድርሻ የውጭ ጉዲፈቻ ላይ የጉዲፈቻ ውል ላይ መፈረምና ፋይል መክፈት ነው። የጉዲፈቻ አስፈጻሚ ድርጅቶች ደግሞ የጉዲፈቻ አድራጊ ቤተሰቦችን የሕግ ሂደቶች በውክልና መከታተል።

ታዲያ መንግሥት የውጭ ጉዲፈቻ የዘጋበት አንድ ምክንያት እነዚህ አካላት ያለ አግባብ በሙስና ውስጥ ተዘፍቀዋል እና ያለ አግባብ ይጠቀማሉ በሚል ነው። ይታያችሁ! በፍትህ ስርዓቱና በመንግሥት ግዢ የሚፈጸሙ ሙስናዎች ስላሉ እነዚህ ተቋማት አልተዘጉም።

የውጭ ጉዲፈቻ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉት ሕጻናት ናቸው፤ ያውም ተጥለው የሚገኙ የአዕምሮና የአካል ጉዳት ያለባቸው፤ የኤች.አይቪ/ኤድስ ተጠቂ በመሆናቸው ወላጆቻቸው የጣሏቸው፤ ወላጆቻችው ስለሞቱ የሚደግፋቸው ያጡ ሕጻናት። እነዚህን ሕጻናት የሚጠቅም አማራጭ አገልግሎት መቅረቱ የሚጎዳው ሕጻናቱን ቢሆንም የሚጠቅመው ግን በወቅቱ የነበሩ የመንግሥት ኃላፊዎችንና ሠራተኞችን ነው። ምክንያቱም ከላይ እንደገለጽኩት 98 በመቶ ተሳታፊው መንግሥት ነው። በዚህ ደረጃ በሙስና የተዘፈቁት የመንግሥት አካላት ጉዳዩ ይድበሰበስላቸዋል፤ በውጭ ጉዲፈቻ ስበብ የላኳቸውን የራሳቸውን ሆነ የዘመዶቻቸውን ልጆች ጉዳይ ይታለፋል፤ የድኅረ ጉደፈቻ ሪፖርቶችን የህጻናቱን መረጃዎች በቸልተኝነት ያጠፉት ከተጠያቂነት የሚያስመልጣቸው ሲዘጋ ብቻ እንደሆነ ስለሚያውቁት ነው የውጭ ጉዲፈቻ እንዲቀር ያደረጉት። እንጂ ለሕጻናቱማ ጥቅም ነበረው!

በዚህ አማራጭ መጠቀም እየቻሉ ያልተጠቀሙ ሕጻናት በሕይወት ከመከራዎቻቸው ጋርና ከሕመማቸው ጋር እንዲኖሩ ፈርደውባቸዋልና፣ የውጭ ጉዲፈቻ እንዲቀር የሠሩና የተሳካላቸው ተጠያቂ መሆናቸው አይቀርም። የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ መዋቅር የውጭ ጉዲፈቻ ለመቅረቱ ምክንያት ያደረጋቸው ማሳደጊያ ድርጅቶች ልጆችን ለውጭ ጉዲፈቻ በመስጠት የገቢ ምንጭ ያገኛሉ፣ በሙስና ተዘፍቀዋል የሚል ምክንያት ነው። ይሄም ቢሆን አግባብነት የለውም። በዚህ ምክንያት አገልግሎት የሚዘጋ ከሆነ እራሱ የሴቶችና የሕጻናት ጉዳይ መዋቅር ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጀምሮ እስከ ታችኛው እርከን ምን ያደርጉልናል? ግብር ከፍለን ደሞዝ ሰጥተናቸው፣ የልጆቻችንን ሕይወት የሚያጨልሙ ከሆነና በሙስና ደረጃቸው 98 በመቶውን የሚይዙት እነርሱ ስለሆኑ መዘጋት ነበረባቸው።

ነገሩ ግልጽ እንዲሆን ስለ ማሳደጊያ ድርጅቶች ትንሽ ልበላችሁ። ማሳደጊያዎች ተጥለው የሚነሱ፣ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውና ተንከባካቢ የሌላቸውን፣ የጎዳና ተዳዳሪ የሆኑ፤ የአእምሮና የአካል ጉዳት ያለባቸው፤ ወሲባዊና አካላዊ ጥቃት የደረሰባቸው፤ የቤተሰብ ኃላፊ በመሆን በችግር ውስጥ ያሉ እንዲሁም በከፍተኛ ድህነት ውስጥ ከወላጆቻቸው ጋር የሚኖሩና ትምህርት መማር ያልቻሉ ሕጻናትን፤ ሥራ አጥ ሴቶችንና ወጣቶችን፤ በአካባቢና በሥነ ተዋልዶ፤ ሌሎች በርካቶችን በመደገፍ የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸውና ራሳቸውን እንዲችሉ እያደረጉ ያሉ ተቋማት ናቸው። እነዚህ ማሳደጊያዎች በቀጥታ ተጠቃሚ ከሚያደርጓቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች በተጨማሪ ለበርካታ ሺዎች የሥራ ዕድልን በመፍጠር የአገራችንን ሥራ አጥ በመቀነስ ጉልህ ድርሻ አላቸው። እነዚህ ማሳደጊያዎች ይህንን ያከናውኑ እንጂ፣ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሆነ ከማንም የመንግሥት አካል ድጋፍና እርዳታን አያገኙምሕጻ

በሕጻናት ማሳደጊያ ውስጥ የሚገኙ ሕጻናት በተመለከተ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት፣ የኢኮኖሚ አቅም በፈቀደ መጠን ወላጅ ለሌላቸው ሕጻናት መንግሥት ድጋፍ ያደርጋል እንዲሁም መንግሥት ለሕጻናት ማሳደጊያዎች ልዩ ጥበቃ ያደርጋል ተብሎ ቢደነገግም፣ ተግበራዊ አልተደረገም። የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ አረጋውያንንም ይጨምራል። ተመልከቱ! መንግሥት ለአረጋውያን አቅሙ በፈቀደው ድጋፍ ያደርጋል፤ ለህፃናቱ ግን አያደርግም። ለምን ለሚለው ሕጻናት አይመርጡም። መንግሥትን ባገኙት አጋጣሚ አይወቅሱም። እነ አቶ በለጠ ደግሞ ምን ያህል ሕጻናት ችግር ውስጥ እንደሚገኙና በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ምን ያህል ፍላጎት እንደተፈጠረ የከተማ አስተዳደሩን ቢሮ ጠይቁት የሚል መልስ ይሰጣሉ።

ይህ የሚያሳየው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ሊያስተባብርና ሕጻናቱን ከችግር እንዲወጡ መሥራት ሲገባው፣ የአንድ ከተማ አስተዳደር መረጃ በመውሰድ አገራዊ ለማስመሰል ይጥራልሕጻ ይህ አግባብ የሌለው መረጃ ነው። እንዴት የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው ለማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መረጃ ይጠቀሳል። ያውም በእጃቸው የሌለውን። ለዚህ ነው የሕጻናትን ችግር ለመፍታት ቁርጠኝነት የላቸውም የምለው። የሚሰጡትም መረጃ አገራዊ አይደለም። ከሁሉ በላይ ከእርሳቸው የማይጠበቅ ሐሳብ መስሎ የታየኝ ልጆች የሚጣሉበት ምክንያት ግልጽ ነው። ስለሆነም ጥናት ማጥናት አያስፈልግም ያሉት ነው።

ይህ አባባላቸው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አቅጣጫ እንደሆነም ነው የሚሰማኝ። እሳቸው እንዳሉት ልጆች የሚጣሉበት መንገድ ግልጽ ነው ይጣላሉ፤ ይነሳሉ፤ ማሳደጊያ ይገባሉ። በቃ! ለእርሳቸው የሕጻናት ችግር የሚፈታው በዚህ ደረጃ ነው የሚል አቅጣጫ ያላቸው ይመስላል። በእኔ እምነት ሕጻናት የሚጣሉበት ምክንያት ግልጽ አይደለም፤ በጣም ውስብስብና ጥናት የሚያስፈልገው ነው። አንዲት እናት በምን ምክንያት ነው ልጇን የምትጥለው፤ የሞራል ጉዳይ ነው? የድህነት ጉዳይ ነው? የቤተሰብ ግፊት ነው? ምክንያቱ ምንድነው መጠናት አለበት።

ከጥናቱ በሚገኝ ምክንያት ነው ስልት የሚነደፈውና የሕጻናት የመጣል ችግር ከስሩ እንዲቀረፍ የሚሠራው። የሚጣሉበት ምክንያት ግልጽ ከሆነ፣ እንዳይጣሉ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ምን ሠራ? እነዚህንና ሌሎች ጉዳዮችን ሳያስተውሉ በዘፈቀደ መረጃ መስጠት ዋጋ የሚያስከፍለው የአንድ ንጹህ ሕጻን ሕይወት ነው። ስለሆነም አቶ በለጠም ሆኑ ኃላፊዎች ሕጻናት እየተጠቀሙ እንዳሉ ለማስመሰል የሚሰጡት መረጃ ላይ ጥንቃቄ ቢያደርጉ መልካም ነው። የሕጻናቱንም ችግር ጥናት ላይ በተመሰረተ እንጂ ግምታዊ በሆነ አሰራር መሥራት አግባብ ባለመሆኑ፣ ትኩረት ሰጥተው በጥናትና በፕሮግራም ቢሠሩ ጥሩ ነው እላለሁ።

የሕጻናት አማራጭ የእንክብካቤ መመሪያዎች በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ላይ እንዳለ እናውቃለን። ነገር ግን አቶ በለጠም ሆነ ማንም የሚኒስቴሩ መሥሪያ ቤቱ ኃላፊ፣ በማሕበረሰብ አቀፍ ምን ያህል ሕጻን በአገር አቀፍ ደረጃ ተጠቃሚ ነው? ምን ያህል ሕጻን አካል ጉዳተኞች በአገር ደረጃ ተጠቃሚ ናቸው? የአካል ጉዳተኛ ሕጻናት ቁጥርስ ምን ያህል ነው? በጎዳና ላይ የሚገኙ ሕጻናት ስንት ናቸው? ወደ ጎዳና እንዲወጡ የሚያደርጉ ገፊ ምክንያቶችስ ምንድን ናቸው? እነሱንስ ለመፍታት ምን እየሠራችሁ ነው? በአደራ ቤተሰብ ምን ያህል ሕጻናት ተጠቃሚ ናቸው? በመልሶ ማቀላቀልና ማዋሃድ ምን ያህል ሕጻናት ተጠቃሚ ሆኑ? በማሳደጊያዎች ውስጥ ያሉ ሕጻናት በአገር አቀፍ ደረጃ ስንት ናቸው? በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ተጠቃሚ የሆኑ ሕጻናት ስንት ናቸው? ህጻናቱን በጉዲፈቻ እየወሰዱ ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች የኢኮኖሚ፤ ማኅበራዊ ሁኔታ ምን አይነት ነው?

በሁሉም አማራጮች ሕጻናቱ የሚያገኟቸው አገልግሎቶች ምንድናቸው? በየተቋም ውስጥ የሚገኙ ሕጻናት የሚያገኙትን አገልግሎት ክትትል የሚያደርጉት እንዴት ነው? በሕጻናትና በሴቶች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች በአገር አቀፍ ደረጃ ምን ያህል ናቸው? በሕጻናት ዙሪያ የተቀረጹትን ፖሊሲዎች፤ ፕሮግራሞች፤ መመሪያዎች እና ጥናቶች ላይ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ምን ያህል ተሠርተዋል? ምን ያህል ቁጥር ያለው ዜጋ ያውቃቸዋል? የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በበቂ ሁኔታ መመለስ አይችሉም። ስለሆነም የተሳሳቱ መረጃዎችን ለመስጠት ከመድፈር፤ የሕጻናትን ችግር ለመፍታት በእነዚህ ላይ መሥራት ይቀድማል ባይ ነኝ።

አቶ አናንያም በንግግራቸው ለግል ሕጻናት ማሳደጊያ የምንመድባቸው ሕጻናት አሉ ሲሉ ያነሱበት መንገድ አግባብነት የለውም። በኢትዮጵያ ሕግ የግል የሚባል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት የለም። የግል ማሳደጊያ ነው የሚለው አመለካከት ነው ለግል ጥቅማቸው ነው የሚል የተንሻፈፈ አመለካከትን የወለደው። እና በማሳደጊያ ውስጥ የሚገኙ ሕጻናትን እንደ ግለሰቦቹ ንብረት የማየትና ያለመደገፍ ችግሮቻቸውን ያለመፍታት ተነሳሽነት የሚያጡት በዚህ እና ለሕጻናቱ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በምናደርገው ጥረት ላይ እጅግ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮት የሚያጋጥመን።

ኹለቱም ግለሰቦች አስተያየታቸው የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳለን የሚያስገነዝብ መልዕክት ለማስተላለፍ መሞከራቸው፣ አሁንም ማኅበረሰባችንን የሚያሳስት መረጃ ነው። በተጨባጭ የሚታየው ጥቂት ጉዲፈቻ ለማድረግ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች ማመልከቻ ቢያስገቡ፣ በሕጻናት ምርጫ ላይ ሴቶችን ብቻ የመፈለግ አዝማሚያ ይታያል። ይህ በራሱ ጥናት የሚያስፈልገውና ብዙ መሠራት እንዳለበት ነው የሚያሳየው። እንጂ እንዳሉት ብዙ ጉዲፈቻ አድራጊ የለም። የውጭ ጉዲፈቻ መቅረቱ አሁንም አግባብነት የሌለውና መንግሥት ማየት አለበት። በዚህ በለውጡ መስተካከል ካለባቸው ነገሮች አንዱ የሕጻናት አማራጮችን መገደብ አላስፈላጊ መሆኑን ነው።

እኛ ግንዛቤ ስላልፈጠርን እንጂ ሕጻናትን በጉዲፈቻ ወስዶ የማሳደግ ፍላጎት ከፍተኛ ነው ያሉት ከምን መነሻነት እንደሆነም ግልጽ አይደለም። እንደዛ ለማለት ማኅበረሰቡ በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ያለው ግንዛቤ ምንድን ነው? ፍላጎቱ ምን ያህል ነው? የሚለው በግምት ሳይሆን በጥናት መረጋገጥ አለበት። ከእሳቸው ንግግር የተረዳሁት፣ ከፍተኛ ግንዛቤ የተፈጠረበትንና ዓለማቀፍ አሰራር ያለውን የውጭ ጉዲፈቻ ከመዝጋት በፊት መሠራት ከነበረባቸው ሥራዎች አንዱ የአገር ውስጥ ፍላጎትን መለካትና ከፍ እንዲል መሥራት ነበር። እንደዚያ ባለመደረጉና አሁን ለመሥራት እንደታሰበ መግለጻቸው፣ ምን ያህል በሕጻናት ሕይወት ላይ እየተቀለደ መሆኑን ማሳያ አድርጌ እወስደዋለሁ።

የውጭ ጉዲፈቻ ከመቅረቱ በፊት የሕግ ማሻሻያው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበበትና የሕዝብ ድምጽ በሚሰማበት ወቅት በዚያ ነበርኩ። ለምክር ቤቱ ቀርበው የነበሩ የተቃውሞ ሐሳቦችን ቀጥሎ አካፍላችኋለሁ። ይህን ጽሑፍ የምታነቡ የሕግ ባለሞያዎች፤ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፤ ዳኞች፤ የሴቶችና የወጣቶች ማኅበራት የሕጻናት መብትና ደኅንነት እንዲጠበቅ በተለይ የአዕምሮና የአካል ጉዳት ያለባቸው፤ የኤች አይቪ/ኤድስ ተጠቂዎች፤ በቅርብ ዘመዶች የሚወለዱ ሕጻናት የውጭ ጉዲፈቻ መብታቸውና ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅላቸው በመሆኑ፣ መመለስ ይኖርበታልና አብረን እንድንታገል በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

በአገሪቱ የሚገኙ ማሳደጊያ ድርጅቶች ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች በርካታ ተግባራትን በማከናወን በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሕጻናትንና እናቶችን ታድገዋል። ለበርካታዎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። ነገር ግን በሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር ይሁን በሌሎችን አካላቶች ይህ ሥራቸው ዕውቅና ሲሰጠው አይታይም። ነገር ግን ማሳደጊያዎች እነዚህን ተግባራት ሲያከናውኑ በአገሪቷ በሥራ ላይ ያሉ ሕጎችን መሰረት በማድረግ የሕጻናቱን ጥቅምና ደኅንነት በማስቀደም ነው። የሕጻናትን ጥቅምና ደኅንነት ለማስጠበቅ በሕግ ላይ የሰፈሩት የሕጻናት መብቶችና ደኅንነቶች፤ ጥበቃዎችና አገልግሎቶች ያለምንም መሸራረፍ መተግበር እንዳለባቸው ሁሉም ማሳደጊያ ድርጅቶች ግንዛቤው አላቸው።

የሕጻናቱን ጥቅምና ደኅንነት የሚጎዳ ማንኛውንም ተግባር በሕግ አግባብ ይቃወማሉ። በመሆኑም በወቅቱ በሕጻናት ዙሪያ እየሠሩ የነበሩ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት፣ በጽሑፍ ቅሬታቸውን ለተከበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል።

የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ ጉዲፈቻን አስመልክቶ በቤተሰብ ሕጉ ላይ የተቀመጡት ድንጋጌዎች እንዲሻሩ ያቀረበውን ሐሳብ፣ የሕጻናቱን መብትና ደኅንነት እንዲሁም ጥቅማቸውንና ከመንግሥትም ሆነ ከማኅበረሰቡ እንዲሁም ከዓለማቀፍ ማኅበረሰብ የሚያገኙትን አገልግሎት የሚጎዳ በመሆኑ፣ ሕጉ መሻር የለበትም በማለት ለተከበረው ቋሚ ኮሚቴ የሚከተለውን ሐሳባችንን እናቀርባለን።

1. ሕጉ የሚሻርበት ምክንያት ተብለው በሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ የቀረቡት ሐሳቦች ሕጉን የሚያሽሩ አለመሆናቸውን፡-
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሕጉ መሻር አለበት በማለት ያቀረባቸው ምክንያቶች የውጭ ጉዲፈቻን አስመልክቶ ያሉ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግር፤ ሕጻናት በጉዲፈቻ ከሄዱ በኋላ አድራሻቸውንም ሆነ ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ አለመቻሉን፤ የሕጻናቱ ወላጆች የልጆቻቸውን ጉዳይ በተመለከተ ጥያቄዎች እያነሱ በመሆኑ፤ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲወዳደር ከፍተኛ በመሆኑ፤ የአገር መልካም ሥም ላይ ጥላሸት እየቀባ በመሆኑ ምክንያት ሕጉ መሻር አለበት የሚል ሐሳብ በመያዝ ለተከበረው ምክር ቤት አቅርቧል። እነዚህ ምክንያቶች መነሻ አድርጎ ሕጉን መሻር አግባብ አይደለም እንላለን። ምክንያቱም፡-

ሀ) አንድ ሕግ ሊሻር ወይም ሊሰረዝ የሚችለው ሕጉ በራሱ የማያሠራ ሆኖ ሲገኝ፤ አልያም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በቂ ሥልጣን አልሰጠኝም የሚል ከሆነ፤ ሕጉ ምንም ጥቅም የሌለው ከሆነ ነው። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶችን በመዘርዘር፣ ሕጉ እንዲሻርና የውጭ ጉዲፈቻ እንዲቆም ያቀረበው ሐሳብ የሕጉ ችግር ሳይሆን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የአሰራር ችግር፤ የአቅም ችግር ነው። እንጂ ሕጉ የፈጠራቸው ችግሮች አይደሉም። ስለሆነም በአካሄድ ደረጃ ራሱ ሕጉን የሚያሽር አይደለም። ስለሆነም ሚኒስቴሩ ከጉዲፈቻ ጋር ተያይዘው ተከስተዋል ያላቸው ችግሮች በጠቅላላ ሕጉ ሳይሻር ሊያስተካክላቸውና የተሻለ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ሊያርማቸው የሚችሉ ናቸው። ስለሆነም የተከበረው ቋሚ ኮሚቴው ይህን ሐሳብ በማየት ሕጉ ከመሻር ይልቅ አሰራሩን እንዲያስተካክል ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መመሪያ በመስጠት ሕጉ እንዳይሻር ቢያደርግ።

ለ) በውጭ ጉዲፈቻ ላይ ተሳታፊ ከሆኑ ከሌሎች አገሮች ጋር የአሰራር ስምምነት በመፈራረም የድኅረ ምደባ በኋላ ያሉ የጉዲፈቻ ሪፖርቶችን መመካከር እየተቻለና ግንኙነታችንን ወደተሻለ ደረጃ ማሸጋገር ሲገባ፣ ሕጻናቱ በሄዱበት አገር የማንነት ጥያቄዎች እያነሱና የማንነት ችግር ውስጥ ገብተዋል በሚል ምክንያት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሕጻናትን ከዚህ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ፣ ከእነዚህ አገራት ጋር በማኅበራዊ ጉዳዮች የሚኖረን ግንኙነትና ትብብር ላይ ጥላ የሚያጥል ነው። በመሆኑም አሰራሩን ማሻሻል እንጂ ሕግ መሻር መፍትሄ ሊሆን አይችልምና የተከበረው ቋሚ ኮሚቴ ከዚህ አንፃር በመመልከት ይህን የሚያጠናክሩ ሕጎች እንዲወጡ እንጂ የቤተሰብ ሕጉ እንዲሻሻል አስፈላጊ አለመሆኑን ከግንዛቤ እንዲያረግልን እንፈልጋለን።

ሐ) በዲያስፖራ ፖሊሲ ላይ ማንኛውም ትውልደ ኢትዮጵያዊ በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ወደትውልድ አገራቸው በመምጣትም ሆነ ባሉበት ሆነው ለአገራቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ መንግሥት በመጋበዝና በከፍተኛ ትጋት በመቀስቀስ ላይ መሆኑን እናውቃለን። ጉዲፈቻው አንዱ የማኅበራዊ ጉዳይ በመሆኑ፣ ሙሉ በሙሉ የሚቀር ከሆነ በአንድ ራስ ኹለት ምላስ የሆነ ፖሊሲ ያለን የሚያስመስል ይሆንብናልና፣ ከስሜታዊነት ነፃ በመሆን ለአገር የሚበጅ ውሳኔ እንዲወሰን ሐሳባችንን እናቀርባለን።

በሌላ በኩል በአገራችን ኢትዮጵያ በስደት ላይ የሚገኙ የተለያዩ አገራት ስደተኛ ሕጻናት፣ በስደተኛ ጣቢያዎች እንዳያድጉ፣ መንግሥት በአገሮች መካከል በሚፈጸም ጉዲፈቻ ድረስ፣ በቤተሰብ ውስጥ የሚያድጉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እየሠራ ባለበት በአሁን ወቅት፣ የአገራችን ሕጻናት በተለይ የአእምሮና የአካል ጉዳትና ሌሎች ውስብስብ የጤና ችግር ያለባቸው ሕጻናት፣ በውጭ ጉዲፈቻ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ሕጉ መሻሩ ፖለቲካዊ ጉዳት ያለው ይመስለናልና በዚህ አቅጣጫ እንዲታይ እንፈልጋለን።

2. የሕጉ መሻር የሕጻናትን ጥቅምና ደኅንነት የማያስጠብቅ በመሆኑ ሕጉ መሻር የለበትም፤
ሀ) የሕጻናት ጥቅምና ደኅንነት፤
የሕጻናት ጥቅምና ደኅንነት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት፤ ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው በዓለማቀፍ ሕጎች፤ በቤተሰብ ሕጉ እና በሌሎች ሕጎች ውስጥ የተደነገጉ ድንጋጌዎች በአግባቡና በተገቢው መንገድ ሲፈጸሙ ነው የሚረጋገጠው። እነዚህ ድንጋጌዎች ደግሞ ሕጻናትን ከአካላዊና ስነ ልቦናዊ ጥቃቶች፤ ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፤ ከአድሎና ከማንኛውም ጉዳቶች የሚጠብቁና የሚከላከሉ ናቸው። ሌሎች ደግሞ ለመልካም እድገታቸው የሚያስፈልጉ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ የሚያስገድዱ ናቸው። እነዚህ ሲከበሩ ነው የሕጻናት ጥቅምና ደኅንነት ተከበረ የምንለው። ምክንያቱም ድንጋጌዎቹ ጥቅምና ደኅንነታቸውን ያስጠብቃሉ ተብለው በባለሙያዎች የተጠኑ ስለሆኑ። በመሆኑም የውጭ ጉዲፈቻ አማራጭ የአገራችን ሕጻናት እንዳያገኙ የተቀመጠውን ሕግ መሻር ጥቅምና ደኅንነታቸውን አለማክበር ነው።

ለ) ቤተሰብ፡-
ሕጻናት በቤተሰብ ውስጥ የማደግና የእነሱን እንክብካቤ የማግኘት መብት አላቸው። በአገር ውስጥ የቤተሰብ አማራጭ የሚገኝላቸው ሕጻናት ያሉ ቢሆንም፣ በአገር ውስጥ ምንም አይነት ቤተሰብ የማግኘት ዕድል የሌላቸው ሕጻናትም አሉ። የውጭ ጉዲፈቻ መቅረቱ የእነዚህን ሕጻናት መብት የሚጋፍ በመሆኑ፣ ሕጉ መሻር የለበትም እንላለን።

ሐ) በሕይወት የመኖር መብት፡-
ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት አለው። ይህ መብት በተለይ ለሕጻናት ሲሆን የተለየ ትኩረት ይሰጠዋል። ለዚህም ነው በሁሉም ዓለማቀፍ ድንጋጌዎች ላይም ሆነ በሕገ መንግሥታችን ላይ በግልጽ ሰፍሮ የሚገኘው። አንድም ሕጻን መሞት የለበትም የሚል አቅጣጫ የያዘው መንግሥት፣ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል፣ እየሠራም ነው። በኤች አይቪ ኤድስ የተያዙ፤ የአእምሮና የአካል ጉዳት ያለባቸው ሕጻናት፤ በከፍተኛ ደረጃ ውስብስብ የጤና ችግር ያለባቸውና በአገር ውስጥ በየትኛውም ደረጃ እና አሁን ባለን የጤና አገልግሎት ሊያገኙ የማይችሉ በውጭ ጉዲፈቻ አማካይነት የተሻለ ሕክምና አግኝተው በሕይወት መኖር የሚችሉበት ዕድል እያላቸው፣ ይህን ሕግ በመሻር ይህን ዕድል ማሳጠት አግባብነትም ተቀባይነትም የሌለው ነው እንላለን።

3. ከፍተኛ የሆነ የበጀት እጥረት
አገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ በዕድገት ጎዳና ላይ መሆኗንና በከፍተኛ ቁጥር ድህነትን እየቀነሰች እንደሆነ እንደ ዜጋም እንደ ዘርፍም እናውቃለን። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች የሚኖርባት አገር ነች። ስለሆነም ይህን አማራጭ የመዝጊያው ጊዜ አሁን አይደለም እንላለን። ይህ የውጭ ጉዲፈቻ ይቀራል የሚባለው በሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር የሚናፈስ ወሬ፣ ማሳደጊያዎችን እና በእነርሱ ውስጥ ያሉ ሕጻናትን እየጎዳ ይገኛል። ለማሳያም፡-
ማሳደጊያዎች በሚሰጡት የተሟላ አገልግሎት የተነሳ ወጪያቸው ከፍተኛ ነው። እንዲሁም በዚሁ ላይ የተለያዩ የሕጻናት ማሳደጊያዎችን ሲረዱ የነበሩ የውጪ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ቢሮአቸውን በመዝጋታቸው የተነሳ ለከፍተኛ በጀት እጥረት ተዳርገዋል።

በዚህም የተነሳ የተለያዩ ለአንድ ሕጻናት ማሳደጊያ ተቋም አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶችን ለማቅረብ አስቸጋሪ ሁኔታ እየገጠማቸው ነው። ለምሳሌ የቤት ኪራይ ወጪ ከምንም በላይ ከኢኮኖሚው እድገት ጋር በተያያዘ እየጨመረ በመምጣቱ የቤት ኪራይ ለመክፈል ከባድ ሆኗል። እንዲሁም የሸራተኛ ደመወዝ እና ታክስ ለመክፈል ከባድ ሆኗል።

በተለይም ልዩ ፍላጎት እና አካል ጉዳት ያለባቸውን ሕጻናት ይዘው የሚሸሩ ማሳደጊያዎች፣ ከጤና አገልግሎት እና ከሚያስፈልገው የሸራተኛ ብዛት የተነሳ ሽራቸውን ለመቀጠል አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል።

4. በመንግሥት በኩል ድጋፍ አለማግኘት፤-
ሀ) የገንዘብ ድጋፍ፡- በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 41 ንዑስ አንቀጽ 5 ላይ መንግሥት የአካል እና የአዕምሮ ጉዳተኞችን፤ አረጋውያንንና ያለወላጅ ወይም ያለአሳዳጊ የቀሩ ሕጻናትን ለማቋቋምና ለመርዳት የቸገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም በፈቀደው ደረጃ እንክብካቤ ያደርጋል በማለት በግልጽ የተቀመጠ ድንጋጌ ቢኖርም፣ እስከ ዛሬ ድረስ የሕጻናትን ጉዳይ ለመከታተል ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት ይህን አልተገበሩም። በዚህም ሳቢያ ማሳደጊያ ድርጅቶች በጉዲፈቻ አስፈጻሚ ድርጅቶች ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

ለ) የመሬትና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ፡- መንግሥት ለሥራ አጥ ወጣቶችና የሥራ ዕድል ለሚፈጠርላቸው ሴቶች የመሥሪያ ቦታ በመስጠትና በሌሎች የኢኮኖሚ ጉዳዮች ድጋፍ ይደረግላቸዋል። በተጨማሪም የመሥሪያ ቁሳቁሶችና የሥልጠና ድጋፎች ይመቻችላቸዋል። ለሕጻናቱ መኖሪያነት የሚያገለግሉ ቤት መሥሪያ ሆነ ለሕጻናቱ ጥቅምና ደኅንነት ቅድሚያ በመስጠት ማሳደጊያ ድርጅቶች ቦታ የሚያገኙበት ሁኔታ አልተመቻቸም። በዚህም ምክንያት የግለሰቦችን ቤት በመከራየት እነዚህን ሕጻናት ድጋፍ እንዲያደርጉ ተገድደዋል።

ግለሰቦችም በየግዜውና በትናንሽ ምክንያቶች በየጊዜው ዋጋ በመጨመር ለሕጻናቱ ጥቅም መዋል የሚገባው ገንዘብ በቤት ኪራይ እንዲወሰድ አድርጓል። በዚህ ሁሉ ውስጥ መንግሥት እየሄደበት ባለው እና በሚያስቀምጣቸው የፎስተር እና የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ አማራጮች፣ የሕጻናት ማሳደጊያ ተቋማት ምንም አይነት ተቃውሞ እንደሌላቸው እና ጥናት አዘል በሆነና የሕጻናትን ጥቅም ባስቀደሙ ውሳኔዎች ላይ፣ ከመንግሥት ጋር ተባብረው ለመሥራት ሙሉ ፈቃደኛ እንደሆኑ ለመግለፅ እንወዳለን።

በመሆኑም የተከበረው ምክር ቤት የሴቶችና ሕጻናት ቋሚ ኮሚቴ፣ የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳትና ችግሩን እንዲፈታልን እየጠየቅን ማንኛውም ውሳኔ በስሜታዊነትና በግላዊ ጥቅም ላይ ሳይሆን በጥናትና ምርምር እንዲሁም በሕግ አግባብ እንዲከናወን የሚመለከታቸው አካላት መሥራት እንዲችሉ ክትትል እና ድጋፍ እንዲደረግ እንጠይቃለን።

በአጠቃላይ ከላይ በጠቀስናቸውና ሌሎች ምክንያቶች የቤተሰብ ግጉ የሚሻሻልበትና የውጭ ጉዲፈቻ የሚቀርበት ወይም ድንጋጌዎቹ የሚሻሩበት ምንም ምክንያት አለመኖሩን እንገልጻለን።

በዚያን ወቅት በዚህ ደረጃ ብንቃወመውም፣ ሰሚ አጥተናል። አሁን ግን ይህ የአምባገነንነት አካሄድ የሚቀጥል አይደለም።
እንደማጠቃለያ

የውጭ ጉዲፈቻን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ከቤተሰብ ሕጉ ውስጥ የወጡት ኹለት አንቀጾች ናቸው። አንቀጽ 193 ጉዲፈቻ አድራጊው የውጭ ዜጋ ሲሆን የሕጻናትን ደኅንነት ለመከታተል ሥልጣን የተሰጠው አካል ለፍርድ ቤት የሚሰጠውን አስተያየት እና 194 ንዑስ አንቀጽ 3 የፍርድ ቤት ሥልጣን ናቸው። እነዚህ አንቀጾች አንደኛው የሕጻናትን ጉዳይ እንዲከታተል ሥልጣን ለተሰጠው አካል በጉዲፈቻ አድራጊዎች ላይ የሚሰጠውን አስተያየት እና ለፍርድ ቤት ሕጻኑ (ጉዲፈቻ ተደራጊው) በአገር ውስጥ የሚያድግበት አማራጮች መኖር አለመኖራቸውን እንዲያረጋግጥ ተሰጥቶት የነበረውን ሥልጣን ነው።

የእነዚህ ድንጋጌዎች መቅረት/መሻር የውጭ ጉዲፈቻውን ያስቀራል ወይስ አያስቀርም? የትኛውም ጉዲፈቻ የሚደረገው በውል ነው፣ ፍርድ ቤት የሚቀርበው ይኸው የጉዲፈቻ ውል ይጽደቅልኝ ጥያቄ ነው። ስለሆነም ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የጉዲፈቻ ተቀባይ ላይ ይሰጥ የነበረውን አስተያየት ሕጉ ስለተሸረ ይቀራል እንጂ ፍርድ ቤቱ ወይም ማሳደጊያው ድርጅት ይህን ማድረግ ይችላሉ። ለፍርድ ቤት ተሰጥቶት የነበረው ሥልጣን ሕጻኑ በአገር ውስጥ የሚያድግበትን አማራጭ መኖር አለመኖሩን እንዲታይ/ማየት የሚያስችለው መብት ያሰጠዋል። እንጂ እንዴት ጉዲፈቻውን ያስቀረዋል? ስለሆነም የውጭ ጉዲፈቻ ቀርቷል ቢባልም በእውነት ቀርቷል የሚያስብል ነገር አለው ወይ? እነዚህን ጥያቄዎች ለሚመለከታቸው አካላት በመተው ሐሳቤን እቋጫለው። ቸር እንሰንብት!!!!
ሙሉጌታ በቀለ በኢ-ሜይል አድራሻቸው bmulugeta852@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here