ስለ ‹ራስነት› ከተነሳ…

0
369

ሐሳብ በመለዋወጥ ውስጥ አንዳንዴ የተሻለ ሐሳብ ሌላ ጊዜ ደግሞ የተለየ ሐሳብ ይገኛል። ቀጣዩን ሐሳብ በአንድ ቤተሰብን ባሰባሰበ ክዋኔ ላይ ከወዳጆቼ ጋር በተገናኘንበት ያገኘሁት ነው። ላካፍላችሁ ወደድኩ፤

በአገራችን ታሪክ ሥልጣንን መያዝ ከኃላፊነት ይልቅ የራስን ክብር ማግኛ ሹመት ሆኖ ይቆጠራል። አገር የሚመራ ሰው አገርን የሚያህል ትልቅ ኃላፊነት ከመሸከሙ ይልቅ፣ እንደ አገር የሚያስዋኝ ሥልጣን ያገኘ ያህል ይሰማዋል። ምንአልባት ስሜቱ እንደዛ ይሁን አይሁን ደርሼ ባላውቀውም፤ የሚታዩ የባለሥልጣናት እንቅስቃሴ ያንን የሚያሳብቁ ናቸው። ከዚህ ባለፈ ደግሞ ባለሥልጣናቱ እንኳ ያንን ባያስቡ፣ እኛ…ሕዝብ የሆንን ሰዎች ያንን ሳናስብ አንቀርም።

እናም የበላይ መሆንን፣ ራስነትን፣ ኃላፊነትን የመበላለጫ መስፈርት እናደርገዋለን። ይህ ነገርና እሳቤ ነው አሁን ላይ በብሔሮች መካከል ለሚታይ የሥልጣን ፍጭትና የ‹ባለተራ› ትርክት ያበቃን። አንዱ ራስ ሆነ ማለት፣ ኃላፊነት ተሰጠው ማለት ወይ ኃላፊነት አለበት ማለት፣ የበላይና የሚበልጥ እንደሆነ ይታሰባል፤ ይቆጠራል።
በቤት ውስጥ የየግል ኑሯችንም ታድያ ይህ የአገራችን ገጽታ ቁልጭ ብሎ ይታያል። በተለይም ‹ወንድ ልጅ የቤቱ ራስ ነው› በሚል ሐሳብና ጉዳይ ላይ ወደኋላ ያዝ የሚያደርገን ነገር አለ። የቤት ራስ መሆን የበላይነትና የመብለጥ መገለጫ ነው ወይ? ወይም ራስ ሆኖ መሾም ኃይልንና ጉልበትን ማሳያና የበላይነት መግለጫ አውድ ነው ወይ?

በዚህ ላይ በሴቶችም ሆነ በወንዶች በኩል ያለው እይታ ቢስተካከል ነገሮች በተወሰነ መልኩ መስመር የሚይዙ ይመስለኛል፤ በተለይ በጾታዊ ግንኙነት አልያም በትዳር ውስጥ። አንደኛ ወንድ የቤቱ ራስ መሆኑን ለመታበይ መጠቀም የለበትም። በዚህ ላይ ከዚህ ቀደም በዚሁ በሲቄ አምድ ላይ ሐሳቡን ማንሳታችንን አስታውሳለሁ። አዎን! ማንም ራሱን የፈጠረ፣ ዜግነትና ቀለሙን ወይም ጾታውን የመረጠ የለምና፣ በነጻ በተሰጠው ጾታ ሊታበይና የበላይ ነኝ ሊል አይችልም፤ ቢልም ሞኝነት ነው።
እናም ወንድ የቤቱ ራስ መሆኑን ሴቷን በመርገጥ፣ በመግፋትና አሳንሶ በማየት አልፎም እሷን ራሷን አሳንሳ እንድታይ በመግፋት መገለጥ የለበትም። የተሰጠውን ኃላፊነት ማክበር ይገባዋል፤ አለበትም። ይህንንም በልመድ ሳይሆን በማስተዋልና በመጠንቀቅ ሊፈጽመው ይገባል። ይህ ማስተዋልና መጠንቀቅ ሲበዛ ልምዱ መሆኑ ስለማይቀር፣ ያኔ የማንነቱ አካል ይሆናል።

በሌላ በኩል ወደ ሴቶች ላማትር። ወንድ የቤቱ ራስ ነው ማለት ሴት ዝቅ ተደርጋ ትታያለች ማለት አይደለም። ነገር ግን ለቤቱ ባለው ኃላፊነት ትዕግስተኛ፣ አስተዋይ፣ ብልህና ጠንቃቃ መሆን እንዳለበት ማሳሰቢያው ነው። አንድ ወንድ ሚስቱን ወይም ሴትን ልጅ በአካልም ይሁን በመንፈስ ጥቃት የሚያደርስባት ከሆነ፣ ያ የሆነው ወንድ የቤቱ ራስ ነው ስለተባለ ወይም ስለሆነና ያ ሰው መሆኑን ስለተገነዘበ አይደለም። ስብእና ስለራቀውና ማስተዋል ስለጎደለው ብቻ ነው።

ግን ከሁሉ ከሁሉ በመተሳሰብ፣ በጋራና በፍቅር የሚደረግ የትኛውም ነገር አንዱ ከፍ ሌላው ዝቅ የሚልበት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በምድር ላይ የተለያየ ቋንቋና ቀለም፣ ብሔርና ሐይማኖት ይኑር እንጂ፣ ኹለት ዓይነት ጾታ ብቻ ነው ያለው፤ ሴት እና ወንድ። ኹለቱ እኔ ነኝ ራስ፣ አይ እኔ ነኝ ራስ ብለው ቢነታረኩ ማብቂያ አይኖረውም።

ራስ ምን ማለት እንደሆነ በመረዳት ግን፣ ወደ አንድ የጋራ ነጥብ መምጣት ይቻላል። ይህ ሲሆንና መደማመጥ ሲጀመር ነው፣ የሴቶችን ጉዳይ የሰዎች ጉዳይ እንደሆነ ያለጥርጥር ለወንድሞች ልናስረዳ የምንችለው።
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here