የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚደረገውን ድርድር በተያዘው አመት ለማጠናቀቅ ከሚፈልጓቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል መሆኑን እና ኢትዮጵያም በድርድሩ ላይ የታየውን መጣደፍ ባለመቀበል በስክነት ለማየት መምረጧን አስታወቀች።
አሜሪካ ሃያል አገር ናት ያሉት የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ገዱ አንዳርጋቸው ከቀናት በፊት ‹‹የሶስትዮሽ ድርደሩ ሳያልቅ ግድቡ መሞላት የለበትም›› ማለቷን ራሷ አሜሪካ ታርመዋለች ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
‹‹በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ፣ ከታችኛው ተፋሰስ አንድ ኩባያ ውሃ ሳንወስድ፣ በራሳችን ገንዘብ እንዲሁም ከኢትዮጵያ በሚፈሱ ወንዞች የሚገደብ ግድብ ስለሆነ የግድቡ ሙሉ ባለቤት ኢትዮጵያ ብቻ ናት›› ብለዋል። ‹‹ነገር ግን ረጅም ርቀት ሄደን የታችኛውን ተፋሰስ አገራትን ጥቅም ለማስጠበቅ እየሰራን ነው ይህንንም እንቀጥልበታለን›› ብለዋል ገዱ።
በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያለው አማራጭ አንድ ነው እርሱም ተነጋግሮ መስማማት ብቻ ነው ያሉት ገዱ ኢትዮጵያም የቱ ሃያል አገር ከጎኔ ይቆማል ብላ ሳይሆን የህግ እና የሞራል እውነት ስለያዘች ግድቡን በሙሉ ልብ ታከናውናለች ሲሉም ገልፀዋል።
የሱዳን መሪዎችም አሁንም ከኢትዮጵያ ጎን ናቸው ያሉት ገዱ ‹‹የአባይን ወንዝ የመቆጣጠር ፍላጎት ያላት ግብፅ እንጂ ሱዳን በፍትሃዊ ተጠቃሚነት ታምናለች›› ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
ዛሬ ከሰአት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በሰጡት መግለጫ ላይም ኢትዮጵያ የመጨረሻው የድርድር ጉባኤ ይራዘም አለች እንጂ ድርድሩን አቋርጣ ያለመውጣቷን እና ድርድሩም ጠቃሚ ሆኖ እስተገኘ እንደሚቀጥል የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒቴሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገልፀዋል።
ስለሺ እንዳሉት የህዳሴ ግድብ በመጪው የክረምት ወራት ሙሌት ለመጀመር የተያዝው እቅድ ላይ ለውጥ እንደሌለ እና ከዚህ በፊት የተፈረሙ ስምምነቶችም ይህንን እደማይከለከሉ አስረድተዋል።
ገዱ አሜሪካ ከራሷ በሚፈሱ ወንዞች ላይ የማታራምደውን አቋም በኢትዮጵያ ላይ ለማራመድ ትሞክራች ብለን አናስብም የሁለቱ አገራት ግንኙነትም በአንድ ፕሮጀክት ላይ የተመሰረተ ስላልሆነ ይሻክራል ብለው እንደማያምኑ ገልፀዋል።



