ዳሰሳ ዘ ማለዳ (የካቲት 26/2012)

0
485

 

አቤ ሳኖ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾሙ

አቤ ሳኖ በዛሬው እለት የካቲት 26/2012 የተሾሙት  በአምባሳደርነት የተሾሙትን የቀድሞውን የባንኩ ፕሬዚዳንት ባጫ ጊናን በመተካት ነው።

አዲሱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን በማገልገል ላይ እንደበሩ የተገለጸ ሲሆን ፕሬዚዳንቱ ከዚህ ቀደም ከጥር 1998 እስከ ታህሳስ 2001 ድረስ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በፕሬዚዳንትነት ማገልገላቸውም ተገልጿል። (ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት)

……………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

የሶማሊያው መሪ ዚያድባሬ ጦር በ1969 ዓ.ም ኢትዮጵያን ለመውረር የሞከረበትና ድል የተደረገበት የካራማራ ድል 45ኛ ዓመት በዛሬው ዕለት የካቲት 26/2012 ተከበረ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም (ዶ/ር) ለካራማራ ድል በዓል “ከዚያድ ባሬ መራሹ የሶማሊያ ወራሪ ኃይል ጋር በነበረን ተጋድሎ ወሳኝ ድል ላስመዘገብንበት የካራማራ ድል በዓል እንኳን አደረሳችሁ” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላፈዋል። ከኢትዮጵያውያን ጎን ተሠልፈው የተዋጉትንና ውድ ሕይወታቸውን የሠዉትን የኩባ እና የየመን ወታደሮችን ውለታ ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል ብለዋል። (ኢቢሲ)

……………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

ኢትዮጵያ የኩፍኝ እና የማጅራት ገትር በሽታ መከሰቱን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።በምዕራብ አርሲ ዞን በሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ፤ሻላ እና አጄ ወረዳዎች ብቻ እስካሁን 103 የሚሆኑ ህጻናት በበሽታው መጠቃታቸው ተገልጿል።ከተጠቁት ውስጥም 67ቱ የሚሆኑት ህክምና ተደርጎላቸው ወደ ቤታቸው መሄዳቸውን የዞኑ ጤና ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ግርማ ያዘው ተናረዋል፡፡በሽታው ከቅርብ ወራት በፊትም መከሰቱ መነገሩ የሚታወስ ነው።ይሁን እንጂ በሶስቱ አከባቢዎች ከባድ የተባለ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር በመኖሩ በሽታው መባባሱን ኃላፊው አስረድተዋል።(ኢትዮ ኤፍ ኤም)

……………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ሲቡ ስሬ ወረዳ ስሬ ከተማ በደረሰ የእሳት አደጋ በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገለጸ።የሲቡ ስሬ ወረዳ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት በእሳት አደጋው በ15 ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን አስታውቋል።በአደጋው ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች ውስጥ 3 ሰዎች ለህክምና ወደ አዲስ አበባ ሪፈር የተደረጉ ሲሆን፣ 2 ሰዎች ደግሞ ወደ ነቀምቴ ሆስፒታል እንዲሁም ቀሪዎቹ 10 ሰዎች ደግሞ በስሬ ሆስፒታል ህክምና እየተከታተሉ ይገኛሉ ተብሏል።(ኢዘ)

……………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የዶሮ ኮሌራ መድሃኒትን ሰርቶ ወደ አፍሪካ ገበያ እንዲገባ ማድረጉን አስታወቀ። ኢንስቲትዩቱ፣ የዶሮ ኮሌራ መከላከያ ክትባት ምርምርን በመደገፍ መድኃኒቱ ወደ ገበያ እንዲገባ ማድረጉንና የዶሮ ፈንግል በሽታን ለመከላከል የሚያስችል ምርምርም በማድረግ ተስፋ ሰጪ ውጤት እያሳየ መሆኑም ይፋ አድርጓል። (ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር)

……………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምንም እንኳን ግፊት ቢደረግበትም ወደቻይና የሚያደርገውን በረራ እንደማያቋርጥ በድጋሚ አሳወቀ።የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ  ተወልደ ገብረማሪያም እንደተናገሩት የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመቆጣጠር ወደ ቻይና የሚደረጉ በረራዎችን ማቋረጥ መፍትሄ አይሆንም ሲሉ ተናግረዋል።አክለውም በቫይረሱ ምክንያት ቻይናን ማግለል ፍትሃዊ አይደለም ብለዋል።(ዥንዋ)

……………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

በስርዓተ ምግብ ዙሪያ በተሰሩ ስራዎች ሀገር አቀፍ የመቀንጨር መጠንን ከ60% ወደ 37% የቀነሰ ቢሆንም የሚቀረው ስራ የበለጠ በመሆኑ ብዙ መስራት ይገባል ሲሉ በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህፃናት ዳይሬክተር መሰረት ዘላለም (ዶር) ተናግረዋል።የተሻለ አፈፃጸም ላሳዩ ከአማራ ክልል ለደሃና፣ ዝቋላና ጋዞ ከትግራይ ክልል ደግሞ አፍላና ቆላ ተንቤን በአጠቃላይ ለ5 ወረዳዎች ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።(ጤና ሚኒስቴር)

……………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

ጣሊያን ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለስራ ዕድል ፈጠራና ሌሎች ልማቶች የሚውል የአንድ ቢሊዮን 40 ሚሊዮን ብር ድጋፍና ብድር ለኢትዮጵያ ሰጠች። የድጋፍና የብድር ስምምነቱ ዛሬ የካቲት 26/2012 በገንዘብ ሚኒስቴር የተካሄደ ሲሆን ስምምነቱም  የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ አድማሱ ነበበ እና በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር አርቱሮ ሉዚ ተደርጓል።(ኢዜአ)

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here