የሴቶች ጥያቄ እና የፌሚኒዝም አካሄድ በኢትዮጵያ

0
1586

የሴቶች ጥያቄ እና የፌሚኒዝም አካሄድ

በኢትዮጵያ

 

ስለሴቶች ስኬትና መልካም ዜና ከተሰማበት ጊዜ ይልቅ፣ ስለደረሰባቸው በደል የሚነሳበት ጊዜ ይልቃል። አንዳንዶች እንደውም፣ ‹የሴት ጥቃት የማይሰማበት ቀን ናፈቀን› እስኪሉ ድረስ ደስ የማይሉ ክስተቶች ይደመጣሉ። ይህ ስረዓት የጣሰ በደል ሆኖ፣ በመደበኛ ሕይወት ደግሞ ሴቶች ከእኩልነት መብት ተነጥለው፣ በመኖር ውስጥ ለሚያደርጉት እንቅስቃሴም ትግል እንዲኖርባቸው አድርጓል። ይህንንም ትግል ለመግፋት ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መካከል ‹ፌሚኒዝም› አንዱ ሲሆን፣ ይህ ተቀባይነት ከማግኘት ይልቅ እንደውም የሴቶች የመብት ጥያቄን እንዲገፋ አድርጎታል የሚሉ አሉ።

በብዙ ውዝግቦች መካከል ያለው ፌሚኒዝም፣ በለዘብተኛ እንዲሁም ጽንፍ በያዘና ከዛም ባለፈ ብዙ መልክ ባለው የተለያየ ጎኑ፣ አሻሚ የሆነባቸውም ጥቂት አይደሉም። ‹አዎን የፌሚኒዝምን ሐሳብ እቀበላለሁ፤ ግን ሁሉንም አይደለም› በማለት ለመሸራረፍ የተገደዱ መኖራቸውን ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ የሚታዘቡት እውነት ነው። የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ይህ የፌሚኒዝም ጉዳይ ለምን በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ተገኘ የሚለውንና በኢትዮጵያ አውድ ስላለው የፌሚኒዝም አቀባበል፣ ባለሞያዎችን በማነጋገርና መጻሕፍትንና መረጃዎችን በማገላበጥ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጋዋለች።

 

 

ትዳር አልመሠረተችም። ልጇን የምታሳድገው ብቻዋን ነው። የልጇን አባት የምታውቀውም እሷ ብቻ ናት። ‹ወላጅ አባቴ፣ እናቴ ላይ ብዙ በደል ያደርስ ነበር› በሚል የምትጠቀልለው የልጅነት ትዝታዋ ይሁን ወይም አንዴና ኹለት ጊዜ ጀምራ የፈረሰው የፍቅር ግንኙነቷ፣ የትኛው እንደሆ አታውቅም። ብቻ የምታወቀው አሁን ላይ ከልጇ በስተቀር ሌላ ወንድ በሕይወቷ ማስተናገድ እንደማትፈልግ ነው። ይህ ግን የእርሷ ፍላጎት እንጂ በልጇ ላይ ሊያደርስ ከሚችለው ማንኛውም አይነት ተጽእኖ አንጻር ያየችው እንዳልሆነ በእርግጠኝነት ትናገራለች።

ሥሟን መግለጽ ያልፈለገችው የአዲስ ማለዳዋ ባለታሪክ፣ ‹ልጄ ምን ይሆናል? እኔንም እናቴ ብቻዋን ነው ያሳደገችኝ› ስትል ልጇን ለብቻዋ ማሳደጓ ችግር እንደሌለው ማሳያ ታቀርባለች። ይህን አኗኗሯን አይተው፣ ዘመን አመጣሹ ‹ፌሚኒዝም› ያመጣው ጉዳይ ነው የሚሏት እንዳሉ አልሸሸገችም። እርሷም በበኩሏ ልጇን ለብቻዋ የማሳደግ ፍላጎት እንዳላትና ትዳር እንደማትፈልግ ከመናገር አትቆጠብም።

ይህ ፍላጎቷ ‹ፌሚኒዝም› ነው አይደለም ብላ ቀምራ የመረጠችው እንዳልሆነ እርግጠኛ ናት። ‹ፌሚኒዝም የሚባለው ነገር ገብቶኝ አያውቅም። አንዳንዱ ፌሚኒስት ነኝ ይላል፤ ሌላው ይቃወማል። የሴቶች መብት ጉዳይና ጥያቄ ከሆነ ጥሩ። እኔ ግን ልጄን ለብቻዬ ማሳደግን የመረጥኩት ፌሚኒስት ስለሆንኩኝ አይደለም። በቃ! ልጄን ለብቻዬ ማሳደግ ስለምፈልግና ባል ደግሞ ስለማልፈልግ ነው›› ስትል ስሜቷን ታስረዳለች።

ልጅሽ የአባት ፍቅር ጎድሎት ማደጉ ሊጎዳው አይችልም ወይ? አንቺ የአባት ፍቅር አጥተሸ ማደግሽ ያጎደለብሽ ነገር የለም ወይ? ስትል አዲስ ማለዳ ጠይቃታለች። ባለታሪኳ ወጣት ግን አሁንም ራሷ ያደገችበትን ሁኔታ ታስረዳለች። ‹እናቴ ትዳሯ ከፈረሰና ባሏ (አባታችን) ትቶን ከሄደ በኋላ እኔንና እህት ወንድሞቼን ለማሳደግ ብዙ ደክማለች። ግን እንደዛም ሆኖ ነጻነት ነበራት። የማናውቀው ነገር ሊጎድልብን አይችልም። እናታችንም ያጎደለችው ነገር አልነበረም። ስለዚህ ልጄም የሚጎድልበት ነገር እንዳይኖር አድርጌ ነው የማሳድገው›› ስትል መልሳለች።

ጉዳዩን ታድያ ከፌሚኒዝም ጋር የሚያገናኙት ጥቂት ሰዎች አይደሉም። በየትኛውም ጉዳይ ላይ ከተለመደው አኗኗር ወጣ ብላ ‹‹ስለምፈልግ ነው! መብቴም ነው!›› የምትል ሴትም፣ ሳትጠየቅ ‹ፌሚኒስት ናት›› የሚል መለያ ይለጠፍላታል።

 

ፌሚኒዝም ምን ይላል?

በሴቶች የእኩልነትና የመብት ጥያቄ ላይ ብዙዎች ይስማማሉ። አዎን! የወንዶች የበላይነት ለዘመናት ዓለምን ሲዘውራት ኖሯል የሚሉም ጥቂት አይደሉም። ይህንን ተከትሎ የሴቶችን መብት በማስከበርና እኩልነታቸውን በማረጋገጥ በሕግና አስተዳደር በኩል የሚወሰዱ እርምጃዎችን ይከታተላሉ፤ ይወቅሳሉ፣ ያደንቃሉ። ነገር ግን ሴቶች ለራሳቸው መብትና እኩልነት የሚታገሉበት ነገረ ‹ፌሚኒዝም› የተነሳ እንደሆነ፣ መስማት የሚፈልገው የዛን ያህል ብዙ ነው ማለት አይቻልም።

በወጣት ሴቶች ክርስትያናዊ ማኅበር የሴት ሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ተወካይ ቤተልሔም ደጉ፣ ፌሚኒዝም የሴቶች መብት ንቅናቄ መሆኑን ይናገራሉ። ‹‹እንደ ማንኛውም ጽንሰ ሐሳብ ፌሚኒዝም በውስጡ በርካታ አመለካከቶች አሉት›› ይላሉ። ይህም የሴቶችን የእኩልነት መብትን ወሳኝ እንደሆነ ሰብአዊ መብት በመጠየቅ ከመሟገት፣ ‹ያለወንዶች እንኖራለን› እስከሚል ጽንፍ የሚሄድ ነው።

እነዚህን አመለካከቶችን የመቀበልና ያለመቀበል ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፣ ፌሚኒዝም በራሱ ችግር ግን የለበትም፤ አንደ ቤተልሔም ገለጻ። አያይዘውም ይላሉ፣ ‹‹ብዙ ሰው ፌሚኒዝምን አልደግፍም ይላል፤ ግን ፌሚኒዝም ምን እንደሆነ በትክክል የተረዳው ጥቂቱ ነው።››

ቤተልሔም እንደውም የሰብአዊ መብት ጉዳይን የሚቀበሉ ነገር ግን ፌሚኒዝምን የማይቀበሉ ሰዎች ይገርሙኛል ሲሉ ትዝብታቸውን ይገልጣሉ። ‹‹ሰብአዊ መብት ብዙ ዓይነት መገለጫ እንዳለው ሁሉ ወይም ዴሞክራሲ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ከመምጣቱ በፊትም ብዙ መነሻ ሐሳቦች እንደነበሩ እናውቃለን። ፌሚኒዝምም እንደዛ በሂደት የመጣ ነው።›› ሲሉ ያስረዳሉ።

ታድያ የብቻ እናትነት በፌሚኒዝም ውስጥ የጽንፈኛውን ጠርዝ የሚይዝ ነው። ‹‹ይህ ግን የሁሉንም አስተሳሰብ አይቀርጽም›› ያሉት ቤተልሔም፣ የተለያየ ትንኮሳና ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ግን በዚህ ጽንፍ ላይ ሊገኙ እንደሚችሉ ያስረዳሉ። ‹‹የደረሰባት ጥቃት ነው ጽንፍ የሚያስይዘው። ከመሬት ተነስቶ የወንድ ጥላቻ አይኖርም። የሚዳብር ልምድ አለ›› ሲሉ ያስረዳሉ።

በግልጽና ለማስረዳት በማይቆጥቡት በቂ ምክንያት ‹ፌሚኒስት ነኝ› ከሚሉ ሰዎች መካከል ጋዜጠኛ እንዲሁም የመብቶችና ዴሞክራሲ ብልጽግና ማእከል ዳይሬክተር በፍቃዱ ኃይሉ አንዱ ናቸው። በፍቃዱ ‹የፌሚኒዝም ሀሁ›› በሚል ርዕስ ባስነበቡት አንድ ጽሑፍ ላይ፣ ፌሚኒዝም አባታዊ ስርዓትን አፍርሶ በሴት የበላይነት የሚተካ ንቅናቄ እንዳልሆነና ሴቶችን ከወንዶች እኩል መብት እና እኩል እድል እንዲያገኙ የሚጥር ንቅናቄ መሆኑን አንስተዋል።

በዚሁ ጽሑፍ ላይ ካነሷቸው ነጥቦች መካከልም የፌሚኒዝም ጽንፈኝነት አንዱ ሲሆን፣ ይህም ቢሆን ስጋት ሆኖ እንደማይታያቸው ጠቅሰዋል። በጽሑፋቸው እንዲህ ብለዋል፤ ‹‹የሚያስደነግጠው በአባታዊ ስርዓተ ማኅበር የሐሳብ አድማስ ውስጥ ቆመን ስለምናስበው ነው። ሲጀመር በትህትና ‹ወንድና ሴትን እኩል ማኖርና ማየት› ከሚለው ንግግር ይልቅ፣ ‹የወንዶች የበላይነትን ማፈራረስ› የሚለው ቃል ጽንፈኛ ቢመስልም፣ የኹለቱም ግብ የተንሰራፋውን ጾታዊ መድልዖን ማስቀረት ነው››

ይህም ብቻ ሳይሆን ፌሚኒዝምን የሚያቀነቅኑ ሴቶች በትዳርም ፈተና ሲገጥማቸው ይታያል። በወጣትነት እድሜ ልጆቻቸውንም ያለ አባት ድጋፍ እንዲያሳድጉ የተገደዱም አይጠፉም።

የሴታዊት ንቅናቄ ማኅበር መሥራች ከሆኑት መካከል ስኂን ተፈራ (ዶ/ር) ፌሚኒዝም ትዳርን ማናጋቱ አይቀርም ሲሉ ኤል ቲቪ ላይ ‹ሌላው ገጽታ› በተሰኘ መድረክ ባደረጉት ቃለመጠይቅ ተናግረዋል። አብዛኛው በኢትዮጵያ ያለ ትዳር በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አይደለም የሚሉት ስኂን፣ ይህንና ብዙ ሁኔታዎችን መጋፋት ትዳር ላይ ፈተና እንደሚሆን ነው የገለጹት።

ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ከሰጡት ሰዎች መካከል ሐናን (ሥማቸው የተቀየረ) ይገኙበታል። እንደ እርሳቸው እይታ ፌሚኒዝምን ለትዳር መፍረስ እንደ ምክንያት ማቅረብ የማይሆን ሰበብ መስጠት ነው። እንዲህም ሲሉ ይገልጹታል፤ ‹‹ሴት መብቷን ስላወቀችና መብቷን መጠየቋ እንደ ወንጀል መታየት የለበትም። እንደ እናቶቻችሁ ኑሩ ማለት ልክ አይደለም። በፊት በማን ጫንቃ ላይ ነበር ትዳሩ የሠመረው? በሴቷ እንደሆነ የታወቀ ነው።›› ሲሉ ያስረዳሉ።

መብትን መጠየቅ ትዳር የሚያፈርስ ከሆነም፣ መጀመሪያ ነገር ወንዶች አስተሳሰብና አመለካከት ላይ መሠራት ያለበት ጉዳይ አለ ሲሉ ይሞግታሉ።

‹‹የቤተሰብ ነገር በሕግ የተመሠረተ አይደለም። ማለትም በቤተሰብ ሕግ ላይ ያሉ ነጥቦች እንዳሉ ሆነው፣ ፍቅርና መተሳሰብ ላይ ነው የተመሠረቱት።›› ቤተልሔም እንዳሉት ነው። ታድያ በትዳርም ፍቅሩ ኖሮ፣ በተጓዳኝ አንዳንዱ ሰው ከሴቶች ባህላዊ የሆነውን ነገር ይጠብቃል። ይህ ያለውን ሁኔታ አለመረዳት የችግሩ መነሻ ይሆናል።

‹‹ፍቅሩ ነው የሚያሸንፈው። በእውቀት ብቻ ከሆነ እኔ ብቻ ለምን ይህን አደርጋለሁ? አንተስ ለምን አታደርግም? የሚል ጭቅጭቅ ይሆናል። በዚህ አለመስማማት ይነሳል።›› ያሉት ቤተልሔም፣ ይህ ነው እንጂ ፌሚኒዝም ከትዳር መፍረስ ጋር የማይገናኝ መሆኑን ያስረዳሉ። ፌሚኒዝም ለትዳር መፍረስ ተጠያቂ መሆን የለበትምም ይላሉ።

ይልቁንም የሴቷን መብት የማያከብርና ማንነቷን ያልተረዳ፣ አስተሳሰቧንም መቀበል ባልቻለ የትዳር አጋር ምክንያት ነው ትዳሩ ሊፈርስ የሚችለው። መብታቸውን እና የሚፈልጉትን የሚያውቁ ሴቶች ሲሆኑ፣ ያንን ተረድቶና ተቀብሎ ለመኖር የተዘጋጁ ብዙ ወንዶች የሉም ባይ ናቸው።

ለምሳሌ ‹‹ዛሬ ስብሰባ ስለማመሽ ራት አዘገጃጅተህ ጠብቀኝ›› የሚል መልዕክት ከባለቤቱ የደረሰው አንድ ባለትዳር፣ ያንን ያደርጋል ወይ? አሰናድቶ ለመጠበቅስ፣ እንደው የተዘጋጀን ለማቅረብ እንኳ ዝግጁነት ያለው ምን ያህሉ ባል ነው? ከዐስር አንድ ይገኛል? ቤተልሔም እንደሚሉት ከሆነ፣ አሁን ያለንበት ዓለም ይህን ጥያቄ ለመመለስ የደረሰ አይደለም።

ታድያ አስቀድሞ ነገር እኩልነትን በትክክል መረዳት ቢኖር፣ ፌሚኒዝምም ላያስፈልግ ይችል ነበር። ነገር ግን በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃትና ተጽእኖ እየባሰ እንጂ እየቀነሰ አለመሄዱ ጽንፍ መያዙን አበርትቶታል።

 

ቁጥሮች ምን ይላሉ?

የኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብና ጤና ዳሰሳ የ2016 ዘገባ እንደሚያሳየው፣ 6.3 በመቶ ሴቶች ፍቺ ፈጽመዋል። በአንጻሩ ትዳር መሥርተው የሚኖሩ ሴቶች 65 በመቶውን የያዙ ሲሆን፣ ያላገቡ ሴቶች 26 በመቶ ብቻ እንደሆኑ አትቷል።

በሚገርም ሁኔታ ታድያ ትዳር ካላቸው እና ጭራሽ ካላገቡት ይልቅ፣ ፍቺ የፈጸሙና ከትዳራቸው የተለዩ ሴቶች አልያም የትዳር አጋራቸውን በሞት ያጡ፣ ሥራ የማግኘት እድል አላቸው።

በአንጻሩ ደግሞ ለጋብቻም ሆነ ጾታዊ ግንኙነት ለመጀመርና ትዳር ለመመሥረት ሴቶች ከወንዶች በእድሜ ይቀድማሉ። በዚህ ላይ ትምህርት ያላገኙ ሴቶች ከተማሩት በ7.7 ዓመት ቀድመው የማግባት እድል አላቸው። 58 በመቶ ኢትዮጵያውያን ሴቶችም በ18 ዓመታቸው ያገቡ ሲሆን፣ በተመሳሳይ እድሜ ያገቡ ወንዶች 9 በመቶ ብቻ ናቸው። 38 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ትዳር በመሠረቱትበት እድሜ ማለትም 18 ዓመት እያሉ የመጀመሪያ ልጃቸውን ይወልዳሉ።

በሴቶች የመብትና የእኩልነት ጥያቄ ውስጥ የሚነሳው ሌላው ጉዳይ በሴቶች ላይ የሚፈጸም አካላዊ ጥቃትን የሚመለከት ነው። የኢትዮጵያ ሥነ ሕዝብና ጤና ዳሰሳ ባወጣው ዘገባ መሠረት ታድያ፣ 68 በመቶ ሴቶችና 28 በመቶ ወንዶች ባል ሚስቱን ቢመታ አግባብ ነው ብለው ያምናሉ። ለምን ይምታት ሲባል፣ ምግብ ብታሳርር፣ መልስ ለባሏ ብትሰጥ፣ ሳታሳውቅ ከቤት ብትወጣ፣ ልጆቿን ብትዘነጋ ወይም ባል ግንኙነት ማድረግ በፈለገ ጊዜ ፈቃደኛ ባትሆን ስትቀር የሚሉ ምክንያቶች ተጠቃሽ ናቸው።

በዚህ መሠረት ታድያ 23 በመቶ ሴቶች አካላዊ ጥቃትን አስተናግደዋል። ያገቡ ሴቶች ከሚደርስባቸው ጥቃት 68 በመቶውን በባል ወይም በትዳር አጋር የሚደርስባቸው ነው።

በዚህ ላይ የዘ-ጋርድያን ዘገባን እናክል። አዲስ ማለዳ ይህን ሐተታ በምታጠናቅርበት ጊዜ ዘ-ጋርድያን የተሰኘው የዜና አውታር አንድ ‹አስደንጋጭ› ዜና ለንባብ አብቅቷል። ይህም በ75 የዓለም አገራት ላይ የተደረገ የዳሰሳ ጥናት ሲሆን፣ ከዐስር ሰዎች መካከል ዘጠኙ በሴቶች ላይ አድልዖ የሚፈጽሙ ሆነው ተገኝተዋል ይላል።

ይህ ማለት 90 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች በሴቶች ላይ አድልዖ ይፈጽማሉ ማለት ነው። እነዚህ ጥናት የተደረገባቸው 75 የዓለም አገራት ለ80 በመቶ የዓለም ሕዝብ መኖሪያ የሆኑ ስለሆኑ፣ ጥናቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ መቀበል እንደሚያስችል ዘ ጋርድያን በዘገባው ጨምሮ ጠቅሷል።

የዚህ ጥናት ውጤት የሴቶች እኩልነትና የመብት ጥያቄ እንኳን ሊሻሻል እየባሰበት እንደሆነ ነው የሚጠቁመው። ለዚህ አንዱ ማሳያ ግማሽ የሚጠጋው ሕዝብ ወንዶች ከሴቶች የተሻሉና የበለጡ የፖለቲካ አመራሮች ናቸው ብለው ያምናሉ። 40 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በንግድ ሥራ ወንዶች የተሻለ እንደሚሳካላቸው እርግጠኛ ናቸው።

 

የእኩልነት መብት ጥያቄ ማለት…?

ቁጥሮቹና ጥናቶቹ አሁንም የሴቶች የመብት ጥያቄ መልስ እንዳላገኘና ይልቁንም ሌሎች ጥያቄዎች እንደተጨመሩ ማሳያ ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ፣ ብዙዎች የእኩልነትና የመብት ጥያቄን አደባባይ ወጥቶ ሥራ የመሥራት፣ ባለሥልጣን የመሆንና ዝናን መፈለግ ነው ይላሉ። ወንዶችን ሥልጣን የመካፈልና ኃላፊነትን የመጋራት ምኞት ያደርጉታል። ነገሩ ግን በአንጻሩ ነው። ሴት እንደመረጠችው እንድትሆን የማስቻል ጉዳይ ነው።

ቤት የመዋል ወይም አደባባይ ወጥቶ ሥራ የመሥራት ጉዳይ ብቻም አይደለም። ይህ ነጥብ በፌሚኒዝም በራስ ላይ እስከማዘዝ የሚደርስ ነው። ለምሳሌ መውለድ አለመፈለግ፣ ትዳር መመሥረት አለመሻት፣ ልጅን ለብቻ ለማሳደግ መምረጥ የመሳሰሉት ጎልተው ይስተዋላሉ።

ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ አስተያየት ሰጪ በዚህ ጉዳይ ላይ ብቻ ለአዲስ ማለዳ አስተያየት ሲሰጡ፣ ፌሚኒዝምን ወይም የእኩልነት መብት ጥያቄን የፈጠረው፣ መጀመሪያውኑ የወንድ አምባገነንነት ነው ይላሉ። በቤት ውስጥ የማስተዳደር ኃላፊነትን የበላይነት፣ የሴትን ታዛዥነትና ለቤቷ ነዋሪ መሆኗን ዝቅ አድርጎ መመልከት፣ ሴቶች ለመብታቸው እንዲሟገቱና ሲብስም ጽንፍ እንዲይዙ አድርጓል ብለው እንደሚምኑ ጠቅሰዋል።

ቤተልሔም ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ አንዲት ሴት በቤት ውስጥ ቤተሰቤን እያገለገልኩና ልጆቼን እየተንከባከብኩኝ ብቻ መኖር እፈልጋለሁ ካለች መብቷ ነው። የቤት ውስጥ ኃላፊነት ከውጪው ባልተናነሰ ዋጋ ያለው ስለሆነ። ከምንም በላይ ደግሞ ያቺ ሴት ዋጋ ስለሰጠችውና ዋጋ ለሰጠችው ነገር እንዳትኖር ማንም ሊከለክላት ስለማይችል ነው።

ይህ ግን ዝቅ አድርጎ የሚያሳያትና አደባባይ ወጥታ ከምትሠራው በታች ሊያቀርባት የሚችል አይደለም። ይልቁንም በአደባባይም እኩል እድልና እኩል መብት ማግኘት አለባት ነው።

ሐናን በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። ይህንንም የሴት ሥራ መዋል አልያም ቤት መዋል፣ ልጅ መውለድና ማሳደግ፣ ትዳር መመሥረትና አለመመሥረት የምርጫ ጉዳይ መሆን አለበት ባይ ናቸው። ሆኖም ብዙ ጊዜ በተለይም ቤት የመዋልና ከሥራ መቅረት፣ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ሴቷ ተገድዳ የምታደርገው ነው ይላሉ።

 

 

 

ለ‹ፌሚኒዝምና ፌሚኒስቶች› ያለው አመለካከት

አዲስ ማለዳ በመደበኛ መንገድ እንዲሁም በጨዋታ መካከል እያነሳች ካነጋገረቻቸው አስተያየት ሰጪዎች መካከል ናዖል (ሥሙ የተቀየረ) አንደኛው ነው። ናዖል ትዳር ባይመሠረትም እንደሚወዳትና አብሯት ሊኖር እንደሚፈልግ እርግጠኛ የሆነባት የፍቅር ጓደኛ አለችው።

ፌሚኒዝምን ከሥሙ ጀምሮ መስማት የማይፈልገው ጉዳይ እንደሆነ ይናገራል። ፍቅረኛህ ፌሚኒስት ነች ወይ ስትል አዲስ ማለዳ ጠይቃዋለች። ‹‹በራስ መተማመን አላት። የምታደርገውን የምታውቅና እንቶ ፈንቶ የማትወድ ቁምነገር ያላት ሴት ናት።›› ሲል ይገልጻታል።

‹‹እኔ ስለማልወድ ብላ ይሁን አይሁን ባላውቅም ፌሚኒስት ነኝ ብላ አታውቅም። ባትሆን ግን ደስ ይለኛል።›› ያለው ናዖል፣ ፌሚኒዝምን እንዳይቀበል ምክንያቴ ያለው ጭቅጭቅን መጥላት ነው። ‹‹በሁሉ ነገር ሴቶች ሴቶች እያሉ ሲያነሱ ሳይ ደስ አይለኝም።›› ይላል። ሆኖም ግን ሴቶች ከወንዶች ባላነሰ ራሳቸውን የሚያውቁ፣ ጠንካራና ስኬታማ መሆን እንደሚያስፈልጋቸው ያምናል።

ሐናን በበኩላቸው ፌሚኒዝም ተቀባይነት ያጣው ከወንዶች በተቃራኒ የቆመ፣ ወንዶችን ለማጥፋት የመጣ ተብሎ ስለሚታሰብ እንደሆነ ያምናሉ። ጥያቄውም የእኩልነት ሳይሆን የበላይነት የሚመስለው አለ። ይህም ከወንዶች በተቃራኒ የመቆም እንደሆነ እንዲታሰብ አድርጎታል።

ታድያ ሐናን እንደ ናዖል ያሉ ወንዶችን በቅርበት እንደሚያውቁና ሐሳባቸውንም እንደሰሙ ይናገራሉ። ‹‹ፌሚኒዝም ሲባል ብዙዎች በበጎ አያዩትም። ፌሚኒዝምን ከወንድ ጋር ላለመኖር ጦርነት የገጠሙ ሴቶች እንቅስቃሴ የሚመስላቸው አሉ። ጓዳኛ ሲመርጡ እንኳ ፊሚኒስት ከሆነች አንፈልግም ይላሉ። ምክንያታቸው ፌሚኒስቶች ሁሉንም የሚያዩት በሴትነት መነጽር ነው የሚል ነው›› ሐናን ያስረዳሉ።

እርሳቸውም የሚስማሙበት አንድ ሐሳብ አለ። ፌሚኒዝም ቃሉና እይታዎቹ ከአውሮፓ መሠረት የጣሉ ናቸው። ሐናን እንደሚሉትም ዓለማዊነት በጸናባቸው አገራት ላይ ፌሚኒዝምን ለማረዳት ባያስቸግርም፣ እንደ ኢትዮጵያ ሃይማኖትና ባህል መሠረት በሆነበት አገር፣ ጠቃሚም ቢሆኑ አንዳንድ አስተሳሰቦችን ለመውረስ በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረግ ነበረበት ባይ ናቸው።

‹‹ብዙዎች ስላልተረዱትና በዛም ላይ መሠረት ስለሌለው፣ ከባህል ለማፈንገጥ የምንጠቀመው  ይመስላቸዋል። ከባህል፣ ሃይማኖትና ማኅበረሰብ ወጣ ላለ እንቅስቃሴ ሽፋን አድርገው ይጠቀማሉ ተብሎ ነው የሚታሰበው። ፌሚኒዝምን ለአፈንጋጭነት ሽፋን መስጫ አድርገው ያስባሉ።›› ይላሉ። ይህም ሁሉ ታድያ ፌሚኒዝምን ካለመረዳት የመጣ ስለመሆኑ ይስማማሉ።

ቤተልሔም በበኩላቸው ከራሳቸው ልምድና እይታ በመነሳት፣ ፌሚኒዝምን የማይወድ ሰዎች ስለፌሚኒዝም በጥልቀትም ሆነ በመጠኑ እንኳ የማያውቁ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ ብለዋል። ‹‹ብቻ ሴቶችን አጉራ ዘለል እንዲሆኑና የተለየ መብት ለመስጠት የሚመስለው፣ ሴቶች የተለየ ጥቅም እንዲያገኙ የሚደረግ አድርጎ ነው ሰው የሚረዳው።›› ሲሉ ያስረዳሉ።

ነገር ግን ፌሚኒዝም እንደዛ ነው ወይ? አይደለም። ሌላው ቀርቶ የሚደግፉት እንኳ በአብዛኛው ዝርዝሩን ተረድተው እንዳልሆነ ነው ቤተልሐየም የሚያስረዱት።‹‹የአብዛኛው መረዳት ችግር አለበት። ስለምን እንደሆነ የሚደግፉትም በሚገባ አያውቁትም። ትንሽ በትምህትና ስርዓተ ጾታ እውቀት ያላቸው ናቸው የሚያውቁት። ግን ንቅናቄውን እደግፋለሁም አልደግፈውምም ከሚለው፣ ስለፌሚኒዝም በደንብ የሚያውቀው እምብዛም ነው።››

በፍቃዱ ኃይሉ ‹‹የፌሚኒዝም ሀሁ› በሚል ርዕስ ባስነበቡት ጽሑፍ፣ ለፌሚኒዝም በራሱ ያለው አመለካከት አንድም ‹መጤ ነው› በሚል ሐሳብ ላይ መሠረት ያደረገ ነው ይላሉ። በዚሁ ጽሑፋቸውም ላይ አስተሳሰብ ዘር እንደሌለውና ከየትም ይነሳ ከየት ዋናው ከሰው ልጅ የመጣ መሆኑ ጠቃሚ እንደሚያደርገው ይጠቁማሉ። ከዚሁ ጋር አያይዘው ነው፣ ትልልቅ አገራዊ እሴቶች የሚባሉ፣ ሃይማኖቶች ሳይቀር ከውጪ ወደ አገራችን የገቡ ናቸው ሲሉም ይሞግታሉ። እናም ሐሳቡን መጤ ነው በሚለው በፍጹም እንደማይስማሙ ነው የጠቀሱት።

ጸሐፊው ያነሷቸው ነጥቦች በሐሳብ ደራጃ በፌሚኒዝም በሚስማሙ ቅቡልነት ያለው ቢሆንም፣ ይህን ሐሳብ ተቀብሎ ፌሚኒዝምን መረዳት ባለመቻልና ሴቶች የእኩልነት መብታቸውን እውን ለማድረግ የገፉበት ርቀት ጫና እንደጨመረባቸው የሚያምኑ ጥቂት አይደሉም።

ቤተልሔም በሴቶች ላይ ጫና እና አላፈላጊ ሸክም ደርቧል ከሚሉት ወገን ናቸው። እንደ ቤተልሔም እይታ፣ ሴቶች በቤተሰብ ኃላፊነት ውስጥ ሆነውና የውጪ ሥራንም እየሠሩ ድርብርብ ኃላፊነትን ተቀብለዋል። ታድያ የቤቱንም አድምቀው ከአደባባዩም ሳይጎድሉ እየተንቀሳቀሱ ሳለ፣ እንደ ሰው የሚኖራቸው አንዲት መንገዳገድ ሳትቀር ከሴትነት ጋር ትያያዛለች። ‹አልቻሉም!› ባዩ ይበዛል።

‹‹ቤት ውስጥ ያላቸው ድርሻ ሳይቀነስ ውጪ ወጥተው እንዲሳካላቸው ነው የሚሠሩት። እንደውም እጥፍ ኃላፊነት ነው የሆነው።›› ይላሉ። እዚህ ላይ ነው ቤተሰብን ቅድሚያ በፍቅር መምራቱና የቀረውን እንዲከተል ማድረጉ፣ የእኩልነትና የመብት ጥያቄንም በሚገባ አስረድቶ ወደ መተጋገዝ ማቅናት ይቻላል ወደሚል ነጥብ የሚያደርሰው።

ሐናን በበኩላቸው ደግሞ ፌሚኒዝም መጀመሪያም በኢትዮጵያ የተዋወቀበት መንገድ ላይ ክፍተት አለ በማለት ይሞግታሉ። ወንዶችን አሳታፊ አለመሆኑንም ይወቅሳሉ። በአንጻሩ ከወንዶች በተቃራኒ የቆመ ተደርጎ መታሰቡ፣ የተማሩ የተባሉ ሰዎች ሳይቀር የወንድ የበላይነት መኖሩን ቢያምኑ እንኳ፣ ከፌሚኒዝም ጎን እንዳይቆሙ ያደረጋቸው ወንድ ጠል የሚመሰለው አስተሳሰብ እንደሆነ ያነሳሉ።

‹‹የሴቶች ጉዳይ ብቻ አደረግነው/አስመሰልነው። ለማንኛውም የእኩልነት እንቅስቃሴዎች ሁሉንም ማኅበረሰብ ማሳተፍ አለብን። የእኩልነት ጥያቄዎችን የወንድ ጉዳይ ማድረግ መቻል አለብን ብዬ አስባለሁ።›› ሲሉም ያስረዳሉ።

 

ፌሚኒስት እና ፌም – እንስት

ይህን ቃል ለአዲስ ማለዳ ያስተዋወቁት ሐናን ናቸው። ይህም የመጣው ‹ፌሚኒስት ነኝ› በማለት ነገር ግን ውስጡን ባለመረዳት ዝናን ለማግኘት የሚጠቀሙበት ስለመኖራቸው በማንሳት ነው። ‹‹ራስን መሸጫ አድርገው የሚያስቡት አሉ። እነዚህም የራሳቸውን ፕሮፋይል መሸጫ ነው ያደረጉት። ብዙ ጊዜ ጠብ የሚል መሬት ላይ የወረደ ነገር የላቸውም›› ሲሉ ያስረዳሉ።

ይህም በተለይ እንቅስቃሴያቸው ከተማ ላይ ብቻ ያተኮረ፣ የገጠሯን ሴት ጉዳይ የዘነጋ ነው የሚለውን ሙግት ያነሳሉ።

ፌሚኒዝምን በእውቀት ሳይሆን በመላምትና በመሰለኝ፣ በግምትና በተለመደ አስተሳሰብ መበየን ይታያል። ይህም በደንብ የሚያስረዳና ሐሳቡን ለማስረጽ የሚሞክር እንዳይኖር አድርጓል። የሚጠየቁ ሰዎች አሳማኝ ምክንያትና ማስረጃ አለማቅረባቸው፣ ከእነርሱ በሚገባ አለመረዳት የመነጨ ቢሆንም፣ የጽንሰ ሐሳቡ ድክመት ሆኖ እንዲታይ አድርጓል ብለው የሚሟገቱ አሉ።

ቤተልሔም በበኩላቸው ስለሴቶች መብት እንሠራለን ብለው ራሳቸው ሴቶችን የሚያንገላቱ አመራሮች ያሉባቸው ተቋማት እንዳሉ ይጠቅሳሉ። ‹‹እንደዛ ባሉ ተቋማት ሠርቼ አውቃለሁ። ከጥቅም ጋር ስለተሳሰረ ነው።›› ሱሉም ያስረዳሉ።

የሴቶች ጉዳይ ገንዘብ የሚገኝበት፣ ፌሚኒዝምን ማቀንቀንንም እንደ አንድ ዝናን ማግኛ ሆኖ ከመታሰቡ ጎን ለጎን ሥራዎች መሠራታቸው ግን አልቀረም። መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም የመንግሥት ተቋማትም ጨምሮ፣ በርካታ የሴቶች እኩልነት ጥያቄን የሚቀበሉ ተቋማት በየደረጃው አሉ። ሥልጠናና የአቅም ግንባታ ይሰጣል፣ ከፍተኛ ወጪ ይወጣል።

‹‹የቀረው ተግባር ነው፤ ጉዳዩ ሁሉም ጋር አለ። ገንዘብ አለበት፣ የሴቶች የእኩልነትና መብት ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ሳይገኝ የቀረውና ተግባር የጠፋው፣ ውጤታማም ያላደረገው አብዛኛው ለጥቅም የመጣ መሆኑ ይመስለኛል።›› የቤተልሔም እይታ ነው።

 

ሴትነት – በሃይማኖት

ኢትዮጵያን ለዘመናት ያቆያት የሕዝብ ትስስርና ሕዝብ ቦታ የሚሰጠው እሴት እንደ ቀላል ነገር የሚጣልና የሚተው ሳይሆን፣ መሻሻልና መዳበር ካለበት ጊዜ ሊሰጠውና በትዕግስት ሊስተናገድ የሚገባ ነው። ያ ሲሆን ብቻ ነው መሠረታዊ ለውጥ የሚመጣው ብለው የሚያምኑ አሉ። በዚህም ውጤቱ ብቻ ሳይሆን አካሄዱም ወሳኝ ነው የሚል ሙግት ይነሳል።

በአንጻሩ በመግፋትና ጫና በመፍጠር ለውጥን ማምጣት ይገባል የሚሉ ይገኛሉ። ይህም በምንም መንገድ ይሁን ወደ አንድ መፍትሔ ላይ የመድረስ ጉጉት የሚታይበት ነው። ታድያ አመለካከቶች መድረሻቸው አንድ ቢሆንም አካሄዳቸው ለየቅል ከሚሆንባቸው ሁኔታዎች መካከል አንዱ ይኸው የሴቶች የእኩልነትና የመብት ጥያቄ ነው።

በክርስትና እንዲሁም በእስልምና የየእምነቱ አስተምኅሮን በማንሳት ለሴቶች ያለውን ቦታ ደጋግመው የሚናገሩ ብዙ የሃይማኖት መምህራን፣ ያንንም ለማስረዳት የሚሞክሩ መጻሕፍት አሉ።

ኢስላማዊ የጥናት ማእከል ያሳተመውና ‹ማኀበራዊ ሕይወት በኢስላም› የተሰኘው መጽሐፍ፣ ስለሴቶች ጉዳይ አብራርቶ ባሰፈረበት የመጽሐፉ ምዕራፍ፣ በእውቀት ግብይት፣ በባህል እድገትና ሥልጠና ረገድ ኢስላም በወንዶችና በሴቶች መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት አላደረገም ይላል። የሴት ልጅ ሚና በቤት ውስጥ እንደሆነ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ያም ሆኖ በእውቀት ሊያሳድጓት የሚችሉትን ዘርፎች በማጥናት አመለካከትና እይታዋን እንድታሰፋ ማድረግ የግድ መሆኑን ተጠቅሶ ይገኛል።

‹‹ኢስላም በኹለቱ ጾታዎች መካከል የሥነ ልቦናና የሥነ ሕይወት ልዩነት መኖራቸውን መሠረት ያደረገ እይታ አለው። የእነዚህ ልዩነቶች መኖር ደግሞ ሴቶችና ወንዶች በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ሊኖራው የሚገባውን ሚና እንዲነጣጠሉ ያስገድዳል የሚል እምነት አለው›› ይላል፤ መጽሐፉ።

ለበርካታ ዓመታት የስምዐ ጽድቅ መጽሔት ዋና አዘጋጅ በመሆን ያገለገሉት ዲያቆን ማለደ ዋሲሁን፣ በክርስትና ሴቶች ስላላቸው ቦታ ሲያነሱ እንዲህ በማለት ይጀምራሉ። ‹‹ክርስትና በሴት ምክንያት ጠፋን ሲል የነበረውን ዓለም በሴት ምክንያት ዳንን ብሎ በማስተማር ስብከቱን የሚጀምር እምነት በመሆኑ ሴትን አንግሦ ጀምራል።››

ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ ክፍሎች ተጠቅሶ ይገኛል ያሉ ሲሆን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰበሰባቸው 120 ቤተሰቦች 36 ያህሉ ሴቶች እንደሆኑ፣ ማኅበረሰቡ ከሚንቃቸው በባህል ሥሪቱ ከሚገፋቸው መካከል ብዙዎቹን ሰብስቧቸው እንደነበር፣ ትንሣኤውን ለዓለም በመንገር ቀድመው አገልግሎት የጀመሩ ሴቶች እንደሆኑና ቤተ ክርስትያንም እጅግ ብዙ ቅዱሳን ሴቶች እንዳሏት ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን አስተዳደር ሴቶች በቤተክርስትያን ያላቸውን ሚና ከማስፋትና በአገልግሎት ከማሰማራት አንጻር ውስንነት ቢኖርም፣ ክርስትና ግን ሴቶች በአገልግሎት ሊሳተፉ የሚችሉበት ብዙ እድል ያመቻቸ እምነት ነው በማለት ያስረዳሉ።

ታድያ የሴቶችን የእኩልነት ጥያቄ በሚመለከት፣ እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጠር ‹ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው› ማለቱ፣ አንዱ ከአንዱ ልዩ መሆናቸውን ያሳያል። ወንድና ሴት የሆኑበትን የተፈጥሮ ልዩ ባህርያት ደግሞ በየራሳቸው ውስጥ ልዩ ሆነው እንዲታዩ አድርጓል ይላሉ።

ወንድም ሴትም፣ ሰውን ሰው ከሚያደርገው ሦስት ባህርያት ነፍስ እና አራት ባህርያተ ሥጋ ሳይጓደል እኩል ያላቸው፣ በሰብኣዊ ክብር ፈጽሞ አንዱ ከአንዱ ሳያንሱ የሚኖሩ ናቸው። ‹‹ልዩነታቸው አካላዊ አቅም/ችሎታ ብቻ ነው። ይህን ልዩነቱን ያመጣው ደግሞ ለሰው ልጅ ጥቅም/ሕለውና አስፈላጊ በመሆኑ ነው።›› ዲያቆን ማለደ እንዳሉት። ይህም የሰው ዘር እንዲቀጥል የሚረዳ የተፈጥሮ ልዩነት ነው።

‹‹በአካል ያላቸውን አንጻራዊ ልዩነት/እኩል/አለመሆን/ ግን ዓለምም የሚቀበለው ይመስለኛል። ዓለም አንኳን ሴቶችና ወንዶችን በአንድ ትራክ/ውድድር አያሰልፍም። ይህ አንጻራዊ ልዩነት ግን ሰብአዊ ክብርን ከአንዱ የሚያጎድልና ለሌላው አትርፎ የሚሰጥ አይደለም።›› ሲሉ አብራርተዋል።

 

ፌሚኒዝምን በሚመለከትስ…?

እንደ ዲያቆን ማለደ ገለጻ፣ ፌሚኒዝም ፖለቲካ ነው። የፖለቲካ ጥያቄ ተገቢውን መብት ለመጠየቅ የሚደርግ አንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ በተፈጥሮ፣ በባህልም የሚደረግ አመጽ ሊሆን ይችላል ይላሉ። ታድያ በዚህ አውድ ያነሱት ጽንፍ የያዘውን የፌሚኒዝም አመለካከት ነው።

‹‹ሴትን ሴት /female/ እንደሆነች የሚያይበትን የተፈጥሮ እውነታ ክዶ፣ ለተለየ ዓላማ ቅስቀሳ የሚያደርግ ሲሆን ፌሚኒዝም ተቀባይነት አይኖረውም። ነገር ግን ሴታዊ /Feminine/ የሚባሉ ተፈጥሮ /Nature/    ሳይሆን የሰው አመለካከት /Nurture/ የጫናቸውን ለሴቶች ጎጂ የሆኑ፣ ፈጣሪም ሊደሰትባቸው የማይችሉ፣ ለህሊናም የማይመቹ ነገሮች እንዲቀንሱ/እንዲቀሩ/እንዲገሩ ለማድርግ የሚደረግ አንቅስቃሴን ቤተክርስትያንም ልትደግፈው ትችላላች።›› በማለት ያስረዳሉ።

ታድያ በሃይማኖትና ባህል በተዋቀረችው ኢትዮጵያ፣ በዚህ ጽንፉ ፌሚኒዝም ስጋት ሆኖ ሊታይ እንደሚችል የሃይማኖት መምህራን ይናገራሉ። ነገሩ ሄዶ ሄዶ የተፈጥሮ ሕግን ወደ መጋፋት፣ ያንን ወደ ተቃረነ አስተሳሰብ /የማይገባ አእምሮ/ መድረስ ይሆናል ብለው ያምናሉ። ሴታዊ ብሎ ማኅበረሰቡ የሠራቸውን ነገሮች ለመቃወም በመነሳት፣ ተፈጥሯዊ የሆነውን ሴትነት ወደ መጋፋት መድረስ ጤነኝነት አይደለም ተብሎም ይወሰዳል፤ በሃይማኖቶቹ አስተምህሮዎች።

እናስ?

ቤተልሔም እንዳሉት በኢትዮጵያ የተወሰኑ ንቅናቄዎች ካልሆኑ በቀር የጠነከረ የፌሚኒዝም እንቅስቃሴ የለም። ‹‹በደንብ ተሠራ ማለትም አንችልም። በጣም እውቀት ይፈልጋል። እኔ መብቴን መጠየቄ ለሰዉ ቅብጠት ከመሰለው፣ አላወቀውም ማለት ነው። የሴቶች ጥያቄ የእኩልነት እንጂ ልዩ መብት አይደለም።›› ይላሉ።

ከዚህም ግን ሰው መጀመሪያ በእኩልነት ማመን አለበት። አሁን ላይ በተገለጠው የኢትዮጵያውያን ጠባይ መሠረት፣ በተለያየ ነገር ሕዝቡ እየተከፋፈለና አንዱ ራሱን ከፍ ሌላውን ዝቅ አድርጎ በሚያይበት ጊዜ፣ ራሱ የእኩልነትን ጽንሰ ሐሳብ መረዳትና ማስረዳት ይቀድማል፤ በቤተልሔም እምነት።

‹‹እኛ ስለፌሚኒዝም ማውራት አይደለም፣ ሰውና ሰው እኩል ነው የሚለው ላይ ራሱ ገና መሠራት ያለበት ደረጃ ላይ ነን። አሁን የተለያየ መከፋፈል ባለበት ጊዜ፣ ተጠቂ እየሆኑ ያሉት ደግሞ ሴቶች ናቸው።›› በማለት ሐሳባቸውን ገልጸዋል።

ሐናን በበኩላቸው የአኗኗር መቀየርን እያነሱ በፌሚኒዝምና በሴቷ ላይ መሳበብ የለበትም ይላሉ። ሆኖም ግን ፌሚኒዝምን የሚያቀነቅኑ ሰዎች በግልጽና ለማስረዳት በሚቻል መልኩ ማስቀመጥ፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ትግልና ወንዶችም የሚደግፉት እንዲሆን አስተሳሰብ ላይ መሥራት ያስፈልጋል ባይ ናቸው።

ዲያቆን ማለዳ በበኩላቸው፣ ሴትን መበደል ሰብአዊ ክብርን ማውረድ መሆኑን በክርስትና እንደሚታመንና፣ የወንድ ጭቆና ሆነው የሚታዩ አስተሳሰብና ድርጊቶችን ወይም ከዚህ አንጻር ያለ የባህል ጥቁር ገጽታ ተቀባይነት እንደሌለው ያስረዳሉ። ፌሚኒዝም በውስጡ ያለውን አይ-አዎ/Paradox/ እያሰፋ የመጣ አንቅስቃሴ በመሆኑ ግን፣ በልኩ መያዝ ያለበት እንደሆነ አስባለሁ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here