ከ3 ሚሊዩን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ አገራዊ ጉዳት ያደረሰው ተከሳሽ ተቀጣ

0
645

ተከሳሽ ዓለሙ ዘለቀ ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለማግኘት በማሰብ ሕጋዊ ፍቃድ ሳይኖረው የባንክ ሥራ በመሥራት፣ ከሦስት ሚሊዩን ዶላር በላይ አገራዊ ጉዳት በማድረሱ ዐቃቤ ሕግ በመሰረተው ክስ በጽኑ እስራት እና በገንዘብ ተቀጣ።

የክስ መዝገቡ እንደሚያስረዳው፣ ተከሳሽ በአዋጅ ቁጥር 592/2000 ስር የተመለከተውን በመተላለፍ የባንክ ሥራ ለመስራት የሚያስችል ሕጋዊ ፍቃድ ሳይኖረው፣ እስከ ታህሳስ 03 ቀን 2007 ባለው ጊዜ በውጭ አገራት የሚገኙ የተለያዩ ግለሰቦች ገንዘብ በመቀበል ወደ ኢትዮጵያ አዘዋውሯል።

የሚላከውን የገንዘብ መጠን የሚላክለትን ሰው ሥም አድራሻ እና ስልክ ቁጥር ለጊዜው ያልተያዙና በውጪ አገራት ከሚኖሩ ግለሰቦች ተቀብሎ በስልክ በተለያዩ አገራት ለሚገኙ ገንዘብ ተቀባዮች በራሱ ሥም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቦምብ ተራ፣ ልደታ፣ ጎተራ፣ ቄራ እና ኮልፌ ቅርንጫፎች በኩል በድምሩ 3 ሺሕ 631 የኃዋላ መልዕክቶችን እንዲተላለፍ በማድረግ፣ በአጠቃላይ 58 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር አዘዋውሯል።

ገንዘቡ በሕጋዊ ገንዘብ አስተላላፊዎች በኩል ተልኮ ቢሆን ኖሮ፣ አገሪቱ ታገኝ የነበረውን የሐዋላ መልዕክት በተላከለት ወቅት ላይ በነበረው የውጭ ምንዛሬ ተመን ተመስርቶ ሲሰላ፣ 3 ሚሊዮን ዶላር የውጪ ምንዛሬ እንድታጣ ያደረገ በመሆኑ፣ በፈፀመው ያለፍቃድ የባንክ ሥራ መሥራት ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት ቀርቧል።

ዐቃቤ ሕግ ተከሳሽ የወንጀል ድርጊቱን መፈፀሙን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በማደራጀት ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል። ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን መርምሮ ተከሳሽን በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ ብሎታል።
የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 13ኛ ወንጀል ችሎት መዝገቡን መርምሮ የካቲት 30 ቀን 2012፣ በዋለው ችሎት ተከሳሽ በ11 ዓመት ጽኑ እስራት እና በአንድ ሚሊዩን አምስት መቶ ሺሕ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ እንደወሰነበት ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here