በ700 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ትምህርት ቤት ተመረቀ

0
720

ሊድስታር የማኔጅመንት ኮሌጅ 700 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ መሰናዶ የሚያስተምር ትምህርት ቤት አስገንብቶ ለመጪው የትምህርት ዘመን ማዘጋጀቱን አስታወቀ።
እድሜያቸው ከሦስት እስከ 18 ዓመት የሚሆኑ ተማሪዎችን ያስተናግዳል የተባለው ይህ ትምህርት ቤት፣ 200 የመማሪያ ክፍሎች እና አራት የተማሪዎች መጽሐፍ ቤቶች ያሉት ሲሆን የጂምናዚየም፣ የቴሌቪዥን እና የሙዚቃ ስቱዱዮ ያለው መሆኑ ተገልጿል። የእንግሊዝ የትምህርት ሥርዓትን የሚተገብረው እና ‹‹ካምብሪጅ አካዳሚ›› የሚል ሥያሜ የተሰጠው ይህ ትምህርት ቤት፣ ግንባታው ተጠናቆ በኢትዮጵያ በ2013 የትምህርት ዘመን ትምህርት እንደሚሰጥም ታውቋል።

የካምብሪጅ አካዳሚ ባለቤት የሆኑት ቄስ ገመቺስ ደስታ (ዶ/ር)፣ ትምህርት ቤቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ታስቦ መገንባቱን በመግለጽ፣ ዓለም ዐቀፍ ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ለማፍራት እንሠራለን ብለዋል።

ገመቺስ እንደገለጹት፣ ትምህርት ቤቱ ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ ተማሪዎቹን ከመገናኛ ብዙኀን ጋር ቅርበት እንዲኖራቸው ለማድረግና በቀላሉ ነገሮችን ለማስረዳት የሚያስችላቸውን የቴሌቪዥን ስቱዲዮ የመገንባት አስፈላጊነት አስረድተዋል።

ትምህርት ቤቱ በአዲሰ አበባ፣ ቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ሰሚት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በ25 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ የሰፈረ ሲሆን፣ ሦስት ሕንጻዎች አሉት።
እንዲሁም ለተማሪዎች የኦንላይን ዲጂታል ቤተ መጸሕፍት ያለው ሲሆን፣ የጂምናዚየም እና የስፓርት መጫወቻ ሜዳ እንዳሉት አክለዋል።

ተማሪዎችን በቋንቋ ብቁ ለማድረግ ብሎም በአገር እና ዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ፣ ከአማርኛ በተጨማሪ አፋን ኦሮሞ፣ ፈረንሳይኛ፣ አረብኛ እና እንግሊዝኛ እንዲማሩ ዓለም ዐቀፍ የቋንቋ ማስተማሪ ማእከል እንዳለው ገመቺስ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ እንደመሆኗም፣ ለተለያዩ ዲፕሎማቶች፣ ለውጭ አገር ዜጎች ልጆቼን የት አስተምራለሁ ብለው እንዳይጨነቅ ለማድረግ ትምህርት ቤቱ ጉልህ ሚና እንዳለውም ገመቺስ ጠቁመዋል። በቀጣይም በኦሮሚያ ክልል ነቀምቴ ላይ እንዲሁም በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል ላይ ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት እንቅስቃሴ ላይ ነን ብለዋል።

ተማሪዎች ላይ የእንግሊዝ አገር ተፅዕኖ እንደማይኖረው የገለጸው ተቋሙ፣ ኢትዮጵያ ያላትን እውቀት ሰጪ እና ተቀባይ አገር መሆን አለባት ብሎ እንደሚያምን እንዲሁም በሮቿን ዝግ ማድረግ አይገባትም የሚል አቋም እንዳለው ገልጿል። ‹‹ኢትዮጵያ ለዓለም የምታበረክታቸው የራሷ ድርሻ አላት። በመሆኑም የትምህርት ስርዓቱ የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ምንም የሚያሳድረው ተጽእኖ የለም›› ሲሉ ጠቁመዋል።

የትምህርት ቤቱ መምህራንም ቢሆኑ 70 በመቶ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ 30 በመቶው የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው መምህራን ናቸው። ይህንን ቀስ በቀስ ግን ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን መምህራን ለመተካት ይሠራል ተብሏል።

የአስተዳደር ሥራው ካምብሪጅ አካዳሚ ኤስ.ኤስ.ቲ. ከሚባል በእንግሊዝ እና አየርላንድ አገሮች ከሚሠራ ተቋም ጋር በጋራ እንደሚሠሩ ታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here