የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ለ2012/13 የምርት ዘመን የሚያገለግል ማዳበሪያ በሚፈለገው መጠን ወደ ክልሉ እየተጓጓዘ አለመሆኑ ስጋት ላይ ጥሎኛል ሲል፣ የደቡብ ክልል በበኩሉ ማዳበሪያ በወቅቱ እየደረሰለት አለመሆኑን ገልፆ የበልግ ወቅት መድረሱን ተከትሎ አርሶ አደሮች ከፍተኛ ጥያቄ እያቀረቡ ነው ብሏል።
የአማራ ክልል ለቀጣይ የምርት ዘመን ከስድስት ነጥብ ኹለት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ የተመደበለት ሲሆን፣ ነገር ግን በማጓጓዣ እጥረት ምክንያት ለምርት ዘመኑ በተያዘው ዕቅድ መሰረት ወደ ክልሉ እየቀረበ እንዳልሆነ ገልጿል።
ማዳበሪያው በትክክለኛው የሰብል ዝግጅት ጊዜ እንዲደርስ በየቀኑ 44 ሺሕ ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ክልሉ መግባት ነበረበት ያሉት የክልሉ ግብርና ቢሮ የግብዓት አቅርቦት ኃላፊ አበበ መኮንን ናቸው። በየቀኑ 110 ተሳቢዎች መድረስ ነበረባቸው ያሉ ሲሆን፣ አሁን እየደረሱ ያሉት በቀን ከ80 የማይበልጡ ተሽከርካሪዎች በመሆናቸው ስጋት ውስጥ እንዳስገባቸው አስረድተዋል።
‹‹የማጓጓዙ ሥራ በኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት አማካኝነት የሚደረግ ነው። ክልሉ ከአገሪቱ ጠቅላላ የማዳበሪያ አቅርቦት 44 በመቶ የሚሆን ድርሻ ያለው በመሆኑ፣ መንግሥት ትኩረት አድርጎ የማጓጓዙን ሥራ ሊሠራ ይገባል›› ሲሉም ተናግረዋል።
ማዳበሪያውን የማጓጓዙ ሥራ ከተጀመረ ከአንድ ወር በላይ ያስቆጠረ ሲሆን፣ እስከ አሁን አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለአማራ ክልል ቀርቧል።
የምርት ዝግጅት ወቅቱ ከመድረሱ በፊት ቀሪውን ማዳበሪያ ለማጓጓዝ ከጂቡቲ ወደብ እስከ አዳማ በባቡር ለማጓጓዝ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ የተናገሩት አበበ፣ በዚህ መንገድም አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ለማጓጓዝ 20 ማራገፊያ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል።
ክልሉ ለቀጣይ የምርት ዘመን የግብርና ግብዓት አቅርቦት 10 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መድቧል። ከዚህ ውስጥም ለማዳበሪያ ግዢ 8 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር፣ ለማጓጓዣ ደግሞ 800 ሚሊዮን ብር የተያዘላቸው ሲሆን፣ ቀሪው ገንዘብ ለምርጥ ዘር እና ኬሚካል የሚውል ነው።
የደቡብ ክልል ኅብረት ሥራ ልማት ኤጀንሲ በበኩሉ ማዳበሪያ በወቅቱ እየደረሰለት አለመሆኑን ጠቁሟል። እንዲሁም የወቅቱን የበልግ ዝናብ ተከትሎ ከአርሶ አደሮች ማዳበሪያ እንዲቀርብላቸው በተደጋጋሚ ጥያቄ እያቀረቡ እንደሚገኙ ጠቅሷል።
የኤጀንሲው የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ባለሙያ ታመነ ጌታቸው ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ በክልሉ የሚገኙ መጋዘኖች ቦዶ ሆነዋል። የማዳበሪያ ዕጥረትም አለ። ምክንያቱ ግን ምን እንደሆነ ከክልሉም ይሁን ከፌዴራል መንግሥት የተገለጸልን ነገር የለም ብለዋል።
የባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት በበኩሉ የአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ የማጓጓዝ ግዴታ ተጥሎብኛል ያለ ሲሆን፣ የምርት ዝግጅት ጊዜው ሳያልፍ ለማድረስ በባህር፣ በየብስ እና ባቡር ትራንስፖርት አማራጮች ለማጓጓዝ ጥረት እያደረገ እንደሆነ አስታውቋል።
በአንዳንድ ክልሎች ለተከሰተው መዘግየት የኅብረት ሥራ ማኅበራት የመረከቢያ ቦታ አለማዘጋጀት፣ ተሽከርካሪዎች ጭነት ሳያራግፉ እንዲቆሙ ምክንያት ሆኗል የሚሉት የአገልግሎቱ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አሸብር ኖታ ናቸው። አገልግሎቱ የራሱን 400 ተሽከርካሪዎች እና የትራንስፖርት ማኅበራትን በማሳተፍ ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ማኅበራት ጨረታዎችን ካሸነፉ በኋላ ወደ ገጠራማ አካባቢዎች ተሽከርካሪዎችን ለማሰማራት ፈቃደኛ አለመሆናቸው በማጓጓዙ ሥራ ላይ እክል እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል።
የምርት ዘመኑ የዝግጅት ወቅት ሳያልፍ ማዳበሪያውን ለማድረስ የባቡር ትራንስፖርት አማራጭን በመጠቀም ላይ እንገኛለን ያሉ ሲሆን፣ እስከ አሁን ከ600 ሺሕ ቶን በላይ ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን አስታውቀዋል።
ማዳበሪያውን ወደ አገር ውስጥ የማስገባቱን ሥራ አገልግሎቱ ከሌሎች ሥራዎች ጎን ለጎን የሚያከናውነው መሆኑ ለውጪ ምንዛሬ እጥረት እና ለተደራራቢ ጫና እንደዳረገው አስታውቋል። የማዳበሪያ አቅርቦቱንም የምርት ዝግጅት ጊዜው ሳያልፍ ለኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ለማድረስ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ አሸብር ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በበኩሉ 21 የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ 34 ማራገፊያ ጣቢያዎችን በማዘጋጀት ሦስት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለመረከብ ዝግጅት አጠናቅቄአለው ብሏል። ከአጠቃላይ የማዳበሪያ ፍላጎቱም እስከ አሁን 24 በመቶ የሚሆነው ብቻ መቅረቡን አስታውቋል።
አማራ ክልል በ2011/2012 የምርት ዘመን 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ የተጠቀመ ሲሆን፣ አሁን በአንድ ሚሊዮን ኩንታል ጨምሯል። የአርሶ አደሮች የማዳበሪያ ፍላጎት መጨመር እና የሚያቀርቡት ተደጋጋሚ ጥያቄ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል።
በክልሉ ግብርና ዘርፍ ላይ የግል አልሚዎች ለመሳተፍ ፍላጎት እያሳዩ እንደሆነ የተነሳ ሲሆን፣ የክልሉ ግብርና ቢሮ ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ጋር በመተባበር የእርሻ እና የምርት አሰባሰብን ለማዘመን እየሠራ መሆኑ ተገልጿል።
ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012


