ዳሰሳ ዘ ማለዳ (መጋቢት 09/2012)

0
799

 

በአዲስ አበባ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች ላይ ጥቃት እየተሰነዘረ መሆኑን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ ገለጸ

በአዲስ አበባ የውጭ አገራት ዜጎች ሲንቀሳቀሱ ኮሮና አመጣችሁብን፣በእናንተ ምክንያት ነው በቫይረሱ የተጠቃነው በሚል ነዋሪዎች ጥቃት እያደረሱ ነው ሲል ኢምባሲው በድረገጹ ላይ አስታወቀ።

ጥቃቱ በድንጋይ መምታት፣ታክሲ ውስጥ እንዳይገቡ መከልከል፣ መስደብ እና ሌሎች ድርጊቶች በነጮች ላይ እየተፈጸመ መሆኑን በመግለጽ አሜሪካዊያንን ጨምሮ ሁሉም ነጭ ዜጋ በቤታቸው እንዲቆየ ኤምባሲው መክሯል።

……………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

 

የጋምቤላ፣ የምዕራብ ወለጋ፣የደቡብ ሱዳን እና የአሶሳ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ባልታወቁ ታጣቂዎች ታግተው ተወሰዱ የተባለው መረጃ ከእውነት የራቀ እንደሆነ ተገለጸ።አቡነ ሩፋኤል በአሁን ወቅት በጥሩ ጤንነት ላይ መሆናቸውንም የተለያዩ ሰዎችን እና የሊቀ ጳጳሱን ሾፌር በማነጋገር ለማወቅ መቻላቸውን የጋምቤላ እና የደቡብ ሱዳን አገረ ስብከት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አባ ቲቶ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በአሁን ወቅትም በደንቢዶሎ በተለመደው መንፈሳዊ ሥራቸው እንደሚገኙም ለማረጋገጥ መቻላቸውን ጠቁመዋል።(አዲስ ማለዳ)

……………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በመጋቢት 7 ቀን 2012 ከጣልያን ሮም በአዲስ አበባ በኩል በመሻገር (transit) ወደ ናይሮቢ ጉዞ ያደረገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ሁለት ጣልያናውያን፤ አባት እና ልጅ የያዘ ሲሆን ግለሰቦቹ የናይሮቢ መንግስት ከጣልያን የሚመጡ ማንኛውንም ተጓዦች አልቀበልም በማለት ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ አድርጎም ነበር።

ተሳፋሪዎቹ ቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ በሚገኙት የጤና ባለሞያዎች የህክምና ምርመራ ተደርጎላቸው ምንም አይነት የበሽታው ምልክት እንዳላሳዩ ለማረጋገጥ መቻሉንም ኢኒስቲቲዩቱ አስታውቋል።(የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት) ……………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

 

በቤት ልማቱ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ለቤት ልማት ብቻ የሚያገለግል ብሄራዊ የቤቶች ልማት ፈንድ ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስታወቀ። በሚኒስቴሩ የከተማ ልማትና ቤቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ መስፍን አሰፋ በከተማ ቤት አቅርቦት ስትራቴጂ ላይ አማራጭ መንገዶችን ማስቀመጥ አለመቻል ትልቅ ክፍተት መሆኑን ያነሱ ሲሆን የህብረተሰቡን የቤት ፍላጎት ለማሟላት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን አብራርተዋል። (ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት)

……………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድ ሠራዊቱ ራሱን ከኮሮናቫይረስ እንዲጠብቅ ዛሬ መጋቢት 09/2012  በሰጡት መግለጫ አሳሰቡ። የሠራዊቱ አባላት ላልተወሰነ ጊዜ ከካምፕ ውጭ ያለ ሥራ መንቀሳቀስ እንደሌለባቸው ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ማሳሰቢያ የሰጡ ሲሆን በሽታውንም ለመከላከል በሁሉም ካምፖች በቂ የሆነ የውሃ አቅርቦት እንዲኖር ጥረት እንደሚደረግ ኢታማዦር ሹሙ ተናግረዋል። (ኢዜአ)

……………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

ከጅቡቲ ወደብ ተጓጉዞ በኢንዶዴ እና በአዳማ የባቡር ጣቢያዎች የሚገኘው የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ በፍጥነት እንዲደርስ ትራንስፖርት ሚኒስቴር መመሪያ ሰጥቷል፡፡አቅጣጫውን የሰጠው የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አወል ወግሪስ የተመራ ቡድን በማዳበሪያ አገባብ እና ሥርጭት ዙሪያ በስፍራው ተገኝቶ የመስክ ምልከታ ባደረገበት ወቅት ነው።

በጉብኝቱ ላይ ከኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት  እና ከኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ድርጅት አመራር እና ባለሞያዎች መሳተፋቸውንም ተነግሯል።(ትራንስፖርት ሚኒስቴር)

……………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በዛሬው ዕለት መጋቢት 09/2012  ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 37 የበርበሬ መሸጫ ሱቆች መታሸጋቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ።ከነዚህ ሱቆች በተጨማሪም ደረጃውን ያልጠበቀ የፊት መሸፈኛ ማስክ በከፍተኛ ዋጋ ሲሸጡ የተገኙ እና በውሃ ማሸጊያ ፕላስቲክ (ሃይላንድ) ክዳን ፌጦ በ10 ብር ስትሸጥ የነበረች ግለሰብ ተይዘው ምርመራ እየተጣራ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።በከተማችን ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ጋር ተይዞ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ እያደረገ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል። (የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን)

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here