መነሻ ገጽሕይወት እና ጥበብኪን/ጥበብዶክተር ካትሪን ሐምሊን በልግስና የተኖረ ሕይወት

ዶክተር ካትሪን ሐምሊን በልግስና የተኖረ ሕይወት

‹‹እኔ እንኳን ብሞት በኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ሴቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚደርስባቸው ህመም እና ስቃይ ጨርሶ እስከሚወገድ ድረስ፣ የጀመርነው ዘመቻ መቋረጥ አይገባውም!›› ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን።

ስለሴቶች መብት ተሟጋች ነን ከሚሉ እልፍ ሰዎች መካከል የእርሳቸውን ሩብ እንኳ ያደረገ ማግኘት ከባድ ነው። ዶክተር ካትሪን ሐምሊን እድሜያቸውን፣ ሕይወታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ኑሯቸውን ሁሉ ለኢትዮጵያውያን ሴቶች፣ ይልቁንም ደራሽና ረዳት አጥተው ለነበሩት የሰጡ መልካም ሴት ናቸው። የሰውነትን ክቡርነት ከፍታ ማሳያ የሆኑት እኚህ ሴት፣ በልግስና ኖረዋል። ኢትዮጵያም ውለታቸውን እስከመቼውም የምትረሳው አይሆንም።

ትውልድና እድገት
ኤሊኖር ካትሪን ሐምሊን ሙሉ ሥማቸው ነው። የተወለዱት አውስትራሊያ በአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር መስከረም 24/1924 ነው። ያደጉት ደግሞ ሲድኒ ከተማ። የከፍተኛ የትምህርት ተቋም ገብተው መደበኛ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፣ በሲድኒ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርታቸውን ተከታትለው በ1946 ተመርቀዋል።

የመጨረሻ ዓመት የሕክምና ተማሪ ሳሉና በልምምዳቸው ወቅት በቅዱስ ዮሴፍ ሆስፒታል አገልግሎታቸውን ሰጥተዋል። ይህን ካጠናቀቁ በኋላ በተለያዩ የሕክምና ማእከላት ያገለገሉ ሲሆን፣ ‹ክራውን ስትሪት› የተባለ የሴቶች ሕክምና ማእከል በማህጸን ሕክምና ዘርፍን ተቀላቅለዋል።
ካትሪን በ1950 ነበር የትዳር አጋራቸው ሆነው ለበርካታ ዓመታት ከቆዩት ሬጂናልድ ሐምሊን ጋር ትዳር የመሠረቱት።

ወደ ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ መንግሥት ‹ዘ ላንሴት› በተባለ የሕክምና ጥናት መጽሔት ላይ አንድ ማስታወቂያ አውጥቶ ነበር። ይህም በ1958 የሆነ ሲሆን፣ ማስታወቂያው ኢትዮጵያ የማኅጸንና የማዋለድ ሐኪም እንደምትፈልግና ይህም ዓላማው የአዋላጅ ነርሶች ትምህርት ቤትን ለመክፈት ታስቦ እንደሆነ የሚገልጽ ነው። ይህም ትምህርት በወቅቱ የልዕልት ፀሐይ መታሰቢያ ሆስፒታል ለመስጠት ታስቦ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ካትሪን ከባለቤታቸው ጋር በመሆን የ6 ዓመት ልጃቸውን ሪቻርድን አስከትለው ወደ ኢትዮጵያ መጡ። ወደ ትምህርት ቤቱ እንደደረሱ በርካታ ፊስቱላ ያለባቸው ሴቶችን ተመለከቱ። ጥንዶቹ ከዛ ቀደም ፊስቱላን በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ በትምህርት፣ ሲያተማሩም በዛው ደረጃ እንጂ በሕመሙ የተያዙ ሴቶችን ለማግኘት አጋጣሚ አልነበራቸውም።

ምክንያቱ ደግሞ ይህ የፊስቱላ ችግር ከአሜሪካ በ1895 ጠፍቶ ስለነበር ነው። የመጀመሪያው የፌስቱላ ሆስፒታልም በአሜሪካ ኒውዮርክ በሩን የዘጋው በ1925 ነው።
እናም ግን ለሦስት ዓመት ሥራ ወደ ኢትዮጵያ ያቀኑት ጥንዶች፣ ፊስቱላ ማከም የሚችልና በዚህ ላይ ብቻ ያተኮረ ሆስፒታል ለመክፈት ወሰኑ፤ አደረጉትም። ከ15 ዓመታት በኋላ፣ በ1974 አዲስ አበባ ላይ ‹የአዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታል›ን መሠረቱ። ይህም ሆስፒታል ዛሬም ድረስ ብቸኛውና በፊስቱላ ላይ ብቻ የሚሠራ የሕክምና ተቋም ሆኖ ተመዝግቧል።

ውለታቸው
ትውለደ አውስትራሊያዋ ዶክተር ካትሪን፣ ‹‹ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ›› የተባለ ግብረሰናይ ድርጅት በማቋቋም ከስልሳ ዓመታት በላይ የፊስቱላ ሕክምና ሲሰጡ ቆይተዋል። ሐምሊን ታድያ ቀድሞ አዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታል በኋላ ሥሙን ቀይሮ ሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል በተባለው የሕክምና መስጫ ማእከል ቅጥር ጊቢ ባሠሩት አነስተኛ ጎጆ ውስጥ ኑሯቸውን አድርገዋል።

በዛም ፍቅርና በስስት ከሚያይዋቸው፣ ውለታ ከብዷቸው የሚያደርጉላቸውን ከተቸገሩ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ጋር አንድ ጊቢ ተጋርተው ነበር የሚኖሩት። ይህም በየቀኑና በየሰዓቱ ለታካሚዎቻቸው ቅርብ አድርጓቸዋል። እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ባለቤታቸው ዶክተር ሬጂናልድ ሐምሊንም በሆስፒታሉ እንቅስቃሴ ውስጥ እስከ እለተ ሞታቸው ድረስ ሳይታክቱ ሲሳተፉ ነበር።

የኢትዮጵያ ሴቶች ይልቁንም ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱት፣ በለጋ እድሜያቸው ተድረው ለከባድ ኑሮ ሲታጩ፣ በወሊድ ጊዜ የሚገጥማቸው የማህጸን መሰንጠቅ (ፊስቱላ) ችግር በአገር ውስጥ መድኃኒት የተገኘለት አልነበረም። እነዚህ ሴቶች በማኅበረሰቡ፣ በትዳር አጋርና በቤተሰባቸው ጭምር ተገፍተው ይተዋሉ። በራሳቸው ጥፋት ያደረጉት አንዳች በደል ያለ ይመስል፣ እንዲገለሉ ይገደዳሉ። የማኅበረሰቡን አፍ መፍራትና መሸሽም ሕይወታቸውን በሰቀቀን ይመላዋል።
ይህ አካላዊ ጉዳት ብቻ አይደለም። ይህ ሥነ ልቦናዊ ሕመምም አለበት። ዶክተር ካትሪን እነዚህን ሴቶች ሳይጠየፉ፣ ሳይንቁና ሳይጠሉ፣ ምን አገባኝ ቢሉ የሚፈርድባቸው ባይኖርም፣ ከሕግም ከፍቅርም በላይ ሆነው፣ ሰብአዊነትን ከሙያቸው ጋር አክብረው የእነዚህን ሴቶች ሕይወት ቀይረዋል። በየቀኑ ድና የምትወጣን አንዲት ሴት ፈገግታ ግብ አድርገውም፣ ፊስቱላን ከኢትዮጵያ ገጽ ለማጥፋት የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል።

የሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል በ1966 ከተመሠረተ ጀምሮ ነፃ ሕክምና ሲሰጥ የቆየ የሕክምና ተቋም ነው። ማእከሉ በባህርዳር፤ በመቀሌ፤ በይርጋለም፤ በሐረርና በመቱ አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት በየዓመቱ አራት ሺሕ ሕሙማን ሕክምናውን እያገኙ ነው። ባለፈው ዓመት የወጣው ዘገባ እንደሚመለክተው ታድያ፣ 39 ሺሕ የሚደርሱ እናቶችና ሴቶች አሁንም በፊስቱላ የጤና ችግር ውስጥ ናቸው።

ሽልማቶች
ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን በሕይወት ዘመናቸው ላበረከቱት አስተዋፆኦ በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል። ከዚህ መካከል በአውስትራሊያ፣ ኢንግሊዝ እና አሜሪካ የሕክምና ማኅበራ የክብር አባልነትን ተቀብለዋል።በአውስትራሊያም ከፍተኛ የሚባለውን የክብር ሽልማት ያገኙ ሲሆን፣ ይህም የማህጸን ሕክምናን በሚመለከት በአዳጊ አገራት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የተበረከተላቸው ነው።

ዶክተር ካትሪን የጻፉት ‹The Hospital by the river: A Story of Hope› የተሰኘ መጽሐፋቸው በሽያጭ ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቦላቸዋል። ይህንንም ተከትሎ ‹የዘመናችን ማዘር ትሬዛ› የሚል መጠሪያ ሥም በኒውዮርክ ታይምስ መጽሔት ተሸላሚ ጸሐፊ ተሰጥቷቸዋል። ይህንንም ዓለም ሳያንገራግር የተቀበለው ሥያሜያቸው ነበር።

ኹለት ጊዜ ለኖቤል ሽልማት የታጩት ዶክተር ካትሪን፣ ከኖቤል ሽልማት ተጓዳኝ የሆነውን <Right Livelihood Award› የተሰኘ ሽልማት ተቀብለዋል። ሐምሊን ግን ለተበረከተላቸው ሽልማት ምስጋና ሲያቀርቡ፤ ‹‹እኔ የምሠራው መሥራት የምወደውን ነው። ከእነዚህ ሴቶች ጋር በኢትዮጵያ መሥራት ለእኔ ከባድ አይደለም›› ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ባለውለታን በቁሙ ባለማመስገን ብትታማም፣ ዶክተር ካትሪንን ግን በተወሰነ ደረጃ በሕይወት እያሉ ማመስገን ተችሏል። አንደኛው የበጎ ሰው ሽልማት ነው። አዲስ ማለዳ ይህን ጽሑፍ ለማዘጋጀትም የበጎ ሰው ሽልማት 2009 መጽሔትን ያጣቀሰች ሲሆን፣ ዶክተር ካትሪን በ2009 ለኢትዮጵያ መልካም የሠሩ የውጪ አገር ዜጎች ዘርፍ ተሸላሚ ሆነው ነበር።

ባለፈው ዓመት ግንቦት 22/2011 በአዲስ አበባ ጦር ኃይሎች አቅራቢያ በሚገኘው ራሳቸው ባቋቋሙት ሆስፒታል የመታሰቢያ ሃውልት ተሠርቶላቸዋል። በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ለዶ/ር ሃምሊን ላበረከቱት አስተዋፅኦ የወርቅ ሜዳሊያና የእውቅና የምስክር ወረቀት አበርክተውላቸዋል።
የኢፌዴሪ መንግሥት ዶክተር ካትሪን ሐምሊን ‹‹በኢትዮጵያ ባለፉት 60 ዓመታት በጤናው ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋፅኦ ነው›› ሲል ያበረከተላቸውን ሽልማት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ከእኔ ዘር ውጪ አላይም ባይ በበዛበት ጊዜ፣ ከዘር፣ ከቀለም፣ ከጾታ በላይ ሰውነትንና ሰውን ማዳን ያሳዩ እናት ናቸው። ሕዝቡ ከእርሳቸው ተግባር መማር ይገባዋል። እኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትም እንደዚህ ዘመን የማይሽረው ለትውልድ የሚጠቅም አሻራ ለማስቀመጥ መሥራት ይጠበቅብናል› ሲሉ ተናግረዋል።

- ይከተሉን -Social Media

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥለው ይህን ነበር ያሉት፣ ‹‹ዶክተር ካትሪን ኢትዮጵያ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ስልሳ ዓመታት ከስልሳ ሺሕ በላይ እናቶችንና ሴቶችን መታደግ ችለዋል። ይህ ደግሞ ‹ስልሳ ሺሕ ተገድሎ በሚጨፈርበት አገር ስልሳ ሺሕ ያዳኑ የድሀ እናት› የሚያስብላቸው መልካም ሥራቸው ነው››
ዶክተር ካትሪን ቀደም ሲልም በሙያቸዉ ያገለገሏት የኢትዮጵያን የክብር ዜግነት አግኝተዋል። እርሳቸውም ካገኙት ከተሰጣቸው ሽልማት ሁሉ በላይ ይህ እንደሚበልጥባቸው ደጋግመው ይናገሩ ነበር። እኚህ ሴት እርግጥም የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ወዳጅ ነበሩ።

ስንብት
የወደዳቸውና ግብራቸውን ያየ ሁሉ የልቡን ሥም ሲሰጣቸው ነው የኖረው፤ ለዶክተር ካትሪን። ‹‹ተአምረኛዋ ሴት፣ ጻዲቋ ዶክተር፣ የብዙኀኑ እህቶች እናት፣ የእግዚአብሔር መልእክተኛ፣ የዘመናችን ማዘር ትሬዛ …ወዘተ›› ይባሉ ነበር።
‹‹ይህን መልእክት የምናሰፍረው እጅግ ከበረታ ሐዘን ጋር ነው። የሃምሊን ፊስቱላ መሥራች ዶክተር ካትሪን ሐምሊን፣ አዲስ አበባ በሚገኘው ሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል በሚገኘው ቤታቸው አርፈዋል።›› ይላል የመጀመሪያው መልእክት።

ይቀጥላል፤ ‹‹ይህ ለካትሪን ቤተሰቦች፣ ለታካሚዎቿ፣ ለሥራ ባልደረቦቿ እና በዓለም ላይ ለሚገኙ ብዙ ሺሕ ደጋፊዎቿ የሐዘን ጊዜ ነው። በዚህ ሐዘን ጊዜ፣ ሕይወቷንና የኖረችውን ኑሮ ደግሞ እናደምቀዋለን። በዓለም ላይ በጣም ተጋላጭ ለነበሩ ሴቶች የሰጠችው ሥጦታ ነውና፣ እናመሰግናለን እናከብራታለን።
ፊስቱላን ከኢትዮጵያ በማጥፋት ለሚያግዟት ሁሉ ካትሪን በብዙ ታመሰግን ነበር። የእኛ ሥራ አካል ስለነበሩ እናመሰግናለን። ያለእናንተ የካትሪን አስደናቂ የሕይወት ሥራ የሚቻል አይሆንም ነበር።››

ይህን ዜና የሐምሊን ፋውንዴሽን በገፁ ማልዶ ነበር ያስነበበው። እልፍ ዓመት ቢኖሩና ሲመሰገኑ ቢቆዩ የሚያንስባቸው ሰዎች ጥቂት በመሆናቸው፣ የካትሪን ሞት የብዙዎችን ልብ የነካና ያሳዘነ፣ ከምንም በላይ ደግሞ ውለታቸውን ብዙዎች አስታውሰው እንዲያመሰግኗቸው ያደረገ ነበር።
ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን ‹‹የኢትዮጵያ እናት አርፈዋል!›› ሲል ነበር ዜናውን ያሰማው። ‹‹ሰው መሆን ከድንበር የዘለለ መሆኑን ያሳዩን ታላቅ እናት (ለኢትዮጵያ የኖሩ ታላቅ እናት) ካትሪን ሃምሊን – በ1916 ተወለዱ። በዕለት ረቡዕ፣ መጋቢት 9 ቀን 2012፣ በሚወዱት የፊስቱላ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ባለችው ደሳሳ ጎጆ በ96 ዓመታቸው በክብር አረፉ።

በወላጅ፣ በጎረቤት፣ በትዳር አጋር መገለል የደረሰባቸውን ሴቶች ገመና የሸፈኑ እናት ናቸው። ለበርካታ ሴቶች ፊስቱላ ጋር ተያይዞ ለሚመጣ የሥነ ልቦና ጫና ፈውስ ሆነዋል። ዶክተር ካትሪን ሃምሊን ከልባቸው ለውጥ ማምጣት የቻሉ የበጎነት ተምሳሌት ናቸው። እህቶቼን አድነውልኛልና አመሰግንዎታለሁ።›› ይላል።
የዶክተር ካትሪን ድንገተኛ ኅልፈት ብዙዎችን ነው ያስደነገጠው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይህ ዜና መሰማቱን ተከትሎ፣ ‹‹በዶክተር ካትሪን ሐምሊን ሕልፈተ ሕይወት ጥልቅ ኀዘን ተሰምቶኛል። ከ60 ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ክብራቸው የተነጠቀባቸውን በሺሕዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ሴቶች ዳግም ቀና ብለው እንዲራመዱ ለፍተዋል። እኚህን ብርቅዬ ጌጥ ኢትዮጵያ አጥታለች” ሲሉ የሀዘን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ምስጋና
‹‹መልካም ተግባር ሁሌም ከመቃብር በላይ እንደሆነ የኢትዮጵያ እና የሴት ልጆቿ የክፉ ቀን ባለውለታዎች የሆኑት ዶ/ር ካትሪን እና ሟቹ ባለቤታቸው ዶ/ር ሪግራንድ በተግባር አስመስክረዋል። ለሦስት ዓመታት የሥራ ኮንትራት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከስድሳ ዓመታት በላይ ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውን እና ሕይወታቸውን ጭምር ለኢትዮጵያ እና ለልጆቿ በገጸ በረከት አበርክተዋል።›› የጌጡ ቃል ነው።
ለአጭር ጊዜ ቆይታ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እድሜና ሙሉ ሕይወታቸውን የሰጡት ዶክተር ካትሪን፣ ኢትዮጵያውያን ነፍሰ-ጡር እናቶችንና የፊስቱላ ሕመምተኛ እህቶችን ለመርዳት ቆርጠው በተግባር አሳይተዋል። ከልጅነት ጀምሮ እስከ መጨረሻዋ እለት ድረስ ለቃላቸው ታምነው፣ በሙያቸው በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እናቶችን ሕይወት ታድገዋል።
ልጅ ወልዶ መሳም በሕመማቸው ምክንያት ዳግም የሚታሰብ ያልመሰላቸው፣ በዶክተር ካትሪን መልካምነት ውስጥ ነገን አይተዋል።

ምስክርነት
‹‹በኢትዮጵያ ብዙ መልካም የሆኑና መልአክት የመሰሉ ሰዎችን አግኝቻለሁ። ከእነሱም አንዷ ዶክተር ካትሪን ሐምሊን ናቸው። ለኢትዮጵያ ሴቶች በርካታ ሥራዎች ሠርተዋል።›› የዴንማርኳ ንግሥት ሜሪ
‹‹ይህ እርስዎ የሚሠሩት ሥራ በምድር ላይ የሚገለጥ የእግዚአብሔር ሥራ እንደሆነ አምናለሁ። ሥራዎ የሴቶችን ጤና እና ክብር የሚያስመልስ ትልቅ በጎ ተግባር ነው›› ኦፕራ ዊንፍሬይ
‹‹ሃምሊን በቀላሉ አስደናቂ ሴት ናቸው። በሚገርም ቁርጠኝነት የሰው ልጆችን ለማገልገል የተፈጠሩና ሕይወታቸውን የሰጡ ሰው ናቸው›› የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድኀኖም
አዲስ ማለዳ በዶክተር ካትሪን ሐምሊን ዙሪያ ያነጋገረችው ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ስለ ካትሪን ሐምሊን ሲናገሩ፣ በኢትዮጵያ የሠሩት ሥራ የቅድስና ሥራ ሊባል የሚችል እንደሆነ ይገልጻሉ። ለሠሩት ሥራም ኢትዮጵያ የሚገባቸውን ክብር እንደሰጠቻቸው እንደሚያምኑም ነው የጠቀሱት። ይህም በቀላ የሚታይ ተግባር አይደለም ባይ ናቸው።

‹‹ነገር ግን ሥራቸው ብዙ ማስተማሪያ ይሆን ነበር። እዚህ ላይ ግን አልተጠቀምንባቸውም። የሠሩት ሥራም ለዝና ወይም ለገንዘብ ሳይሆን፣ እንደውም የቅድስና ሥራ ማለት ነው ይቻላል።›› ብለዋል። ይህም ብዙዎች ሊታዘቡት የሚችሉት እውነት ነው። ካትሪን በዘመናቸው ይህንን ሠርቻለሁ፣ ያንን አድርጌአለሁ ብለው ልታይ ልታይ ኣላሉም። ሥራቸው ግን አፍ አውጥቶ ስለእርሳቸው ይመሰክር፣ ይናገርም ነበር።

- ይከተሉን -Social Media

ጥበቡ እንዲህ ሲሉ ይናገራሉ፤ ‹‹እንደውም የሚያስቆጨው ወጣቱ እርሳቸውን በደንብ አያውቃቸውም። እንጂ እርሳቸው ሥራቸውን ከሚገባው በላይ ሠርተዋል።››
ከትውልደ ኢትዮጵያዊ በላይ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ተቆርቋሪና ሠሪ የነበሩት ዶክተር ካትሪን ሐምሊን፣ ኢትዮጵያዊ ሳይሆኑ የሠሩት ሥራ ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት ሳይገድበው እና ሳይለየው የሴቶችን ችግር እንደራሳቸው ችግር በመመልከት ብቻ ነበር። ይህም ነው ‹ኢትዮጵያዊ ሳይሆኑ› የሚል ቃልን በእርሳቸው ላይ መጠቀምን አስጨናቂ የሚያደርገው። እንደ ጥበቡ ገለጻም፣ ‹‹ሰው ሆነው ሰውነትን የሰበኩ ናቸው››

ሐውልታቸው በተመረቀበት እለት በቦታው እንደተገኙ የሚያታውሱት ጥበቡ፣ በዚያን እለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ንግግር አድርገው ነበር ይላሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካትሪን ሐምሊንን በደንብ ነው የገለጿቸው ሲሉም እንዲህ ያስታውሳል፤
‹‹ጀግንነት ሰው መሆን ነው። ጀግንነት ሰው ማዳን ነው። ለተረሱት ዜጎቻችን ቅንነትን ያስተማሩን ካትሪን ሃምሊን ናቸው። እኛ ወገኖቻችን ዝቀ ብለን ልናገልግል ሲገባ፣ በብሔርና በሃይማኖት እንዲሁም በጎሰኝነት ተከፋፍለን አንዳችን ለአንዳችን እንደጠላት በምንተያይበት ወቅት፣ እርሳቸውን ፈጣሪ አስነስቶ ለሰው መሥራት ክብር ነው ብሎ የእኛን እብሪት እና ጉራ ያስተነፈሱ ሰው ናቸው››

‹‹በመሆኑም…›› ይላሉ ጥበቡ ‹‹በመሆኑም እኚህ ብርቱ ሴት ብዙ ጥሩና መልካም ሥራ ሠርተው በክብር አልፈዋል። ሁሌም ሰው ሲዘክራቸው ይኖራል።››
ታድያ ጥበቡ እንደሚሉትና ከዚህ በኋላ መሆን አለበት ሲሉ ባካፈሉት ሐሳብ፣ እንደ በጎ ሰው ዓይነት ሽልማቶችን ከፍ ማድረግ እና ማሳደግ ተገቢ ነው። መገናኛ ብዙኀን እንዲህ ያሉ ሰዎች የሠሩትን በጎ ሥራ ለማጉላት የበለጠ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ዶክተር ካትሪን ለሠሩት ሥራም እርሳቸውን ሊዘክር እና ሥራቸው ሕያው እንደሆነ ለትውልድ አቆይቶ የሚያሳይ፣ ተቋማትን በሥማቸው መሰየም ያስፈልጋል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የዶክተር ካትሪን ሐምሊን የቀብር ስነ ስርዓት ሰኞ መጋቢት 14/2012 ከቀኑ 7፡00 ላይ በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተክርስትያን እንደሚፈጸም ቢቢሲ አማርኛ አስነብቧል። አዲስ ማለዳ በዶክተር ካትሪን ሐምሊን ሞት የተሰማትን ጥልቅ ሐዘን ስትገልጽ፣ ሥራቸው ከመቃብር በላይ ሆኖ ሲጠሩና ሲመሰገኑ እንደሚኖሩ በማመንና ለኢትዮጵያውያን ሴቶች ላደረጉት መልካም ነገር ሁሉ በማመስገን ነው። ለቤተሰባቸው፣ ለሥራ አጋሮቻቸውና ለወዳጆቻቸው፤ በበጎ ሥራቸው ሕይወታቸው ለተቀየረ፣ ለመላው ኢትዮጵያንም ሁሉ መጽናናትን ተመኛለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች