የግብፅን ፈላጭ ቆራጭ ሥነ-አመክንዮ በጋራ ክንድ እንመክት!

0
852

አሁን ላይ የዓለም አገራት ሁሉ ትኩረት ዓለም አቀፍ ስጋት በሆነው ኮቪድ19 ወይም ኮሮና ቫይረስ ላይ ሆኗል። ሌሎች አንገብጋቢና አወዛጋቢ ጉዳዮች በይደር የተቀመጡ ይመስላል። ዓለማየሁ ሞገስ በበኩላቸው ሌሎች አገራዊ ጉዳዮች መዘንጋት እንደሌለባቸው ለማሳሰብ፣ ይልቁንም በአባይ ጉዳይና በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ሊቆም ይገባል። የውሃ ሙሌቱ እንዲዘገይና ለዛም ኢትዮጵያ የካሳ ክፍያ እንድታገኝ በሚል የሚቀርቡ ሐሳቦችም ተቀባይነት ሊኖራቸው አይገባም ሲሊ ያሳስባሉ።

የግብፅ ገዥ መደቦችና ፖለቲከኞች ከፋራህ እስከ ሙርሲ፤ ከባሪያ ፈንጋይ ስርዓት እስከ 21ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ‹‹ግብፅ የአባይ ስጦታ ነች!›› የሚል ኋላ ቀር አመለካከት ሲያራምዱ ቆይተዋል። ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይም ሆነ የተፈጥሮ ሀብቷን በአግባቡ እንዳትጠቀም፤ መንግሥትና ሕዝብ ወደ ዘላቂ ልማት እንዳይገባ የፖለቲካ አለመረጋጋት በመፍጠር ድህነት አባባሽ አጀንዳዎችን ስትቀርፅልን መቆየቷ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ብሔርና ብሔረሰቦች በሚከተሉት የህዳሴና መደመር መስመር፣ የግብፅና ተባባሪዎቿን ዘመን ያለፈበት አጀንዳ በአራት ነጥብ ዘግተውታል። የኢትዮጵያ ሕዝቦች አሻራ ያረፈበትና 4.7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጭ የሚጠይቀው ታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ መጋቢት/2003 በታላቁ ዓባይ ላይ መሰረት ድንጋይ ከተጣለ በኋላ፣ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ብሎም የፊታችን ሰኔ 2012 ጀምሮ ግድቡን በውሀ የመሙላት ሥራ ተግባራዊ እንደሚሆን ተበስሯል።
ይህ ዜና በአባይ የላይኞቹ ተፋሰስ አገሮችና ለወንዙ ምንም አስተዋፅኦ ሳታበረክት የፈላጭ ቆራጭነት ሚና ለነበራት ግብፅ ታላቅ የኃይል ለውጥ ምክንያት ነው። ለውጡን ግብፅ ተቀበለችውም አልተቀበለችውም፣ የተዛባው የኃይል ሚዛን ተስተካክሎ እንዲቀጥል በር ከፍች ይሉታል፤ የዘርፉ ምሁራን።

ግብፅ 90 በመቶ የሚሆነውን ሕዝቧን የንፁህ መጠጥ ውሀም ሆነ የኃይል ተጠቃሚ ያደረገችው፣ ለአስዋን ግድብ 86 በመቶ ውሀ በሚያበረክተውና ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች በሚነሳው ጥቁር አባይ ነው። ኢትዮጵያ እጅግ እያደገ የመጣውን ኢኮኖሚዋን የሚሸከምና ከ70 በመቶ በጨለማ የሚኖረውን ሕዝቧን ጥያቄ ለመመለስ፣ ግድቡን ከአምስት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ መሙላትና መጠቀም ትፈልጋለች። ይህንንም ለማደረግ የሚያግደን ምንም ዓይነት ምድራዊ ኃይል የለም፤ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት።

ግብፅ የተዛባውን የቅኝ ገዥዎቿ የውሀ አጠቃቀም ስምምነት ጥላ ሁሉም የተፋሰሱ አገሮች ተጠቃሚ ወደሚያደርገው ስምምነት መግባት አልያም ደግሞ ኢ-ፍትሀዊ የውሀ አጠቃቀም የሚያስቀጥልላትን የአረብ ሊግን የመሳሰሉ ‘’የእብድ ገላጋይ’’ በመፈለግ መካከል፣ መንታ መንገድ ላይ ትባዝናለች። የኃይል እርምጃንም እንደ አማራጭ መውሰድ ሌላኛው እንደሆነ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ምሁራን ያስረዳሉ።

የላይኛው ተፋሰስ አገሮች በበኩላቸው፣ ነባሩን ጣል አድርጎ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በፍትሀዊነት ተጠቃሚ የሚሆንበትን /win- win approach/ መከተል አሁን በግብፅ ሥልጣን ላይ ለሚገኘው አል ሲሲ ጠረጴዛ ላይ የሚገኝ አማራጭ ነው ባይ ናቸው።

ኢትዮጵያን በተለመደው የግብፅ አካሄድ በፖለቲካ ማተራመስም ሆነ በወታደራዊ የኃይል እርምጃ መሞከር ወቅታዊ አጀንዳ አይሆንም። የኢትዮጵያ ሕዝብ አኩሪ ታሪክም ሆነ 21ኛው ክፍለ ዘመን ለፈላጭ ቆራጭ ሥነ-አመክንዮ /Authoritarian logic/ ዕድል አይሰጥም፤ አይፈቅድምም። እንደ ኢትዮጵያ የውጭና ደኅንነት ፖሊሲ ‹‹ጊዜና ፍትህ ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ጎን ቆማለች››

ግብፅ ነባሩን ጥቅሟን እንዲያስከብሩላትም ሆነ በግድቡ ውሀ አሞላልና አጠቃቀም ዙሪያ አሉኝ የምትላቸውን ወዳጆቿን ለሽምግልና በመጥራት በመባዘን ላይ ትገኛለች። ዓለም የታዘበው ነገር ቢኖር፤ የ21ኛ ክፍለ ዘመን የዴሞክራሲ መገኽሪያ የምትባለው አሜሪካ፣ ግድቡን ለመሙላት እስከ 21 ዓመት ይራዘምልኝ ጥያቄ ለምታቀርበው የግብፅ ፈላጭ ቆራጭ ሥነ-አመክንዮ የማዳላት ዝንባሌ ማሳየቷ ነው። ኢትዮጵያ ዝንባሌው ስላልተመቻት ድርድሩን በራሷ ፈቃድ ሰርዛለች። ታላቋ አገር አሜሪካ ጀምራው ሳይሳካ የተቋጨ ድርድር መሆኑ፣ የየካቲት ወር የዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኀን ቀለብ ሆኖ ቀርቷል።

ግብፅ ፍትሀዊነት ከጎደለው አባካኝ ውሀ አጠቃቀም ፖሊሲ ወጥታ ወደ ተስተካካለና ዘመናዊው፣ ሁሉንም የተፋሰሱ አገሮች አሸናፊ የሚሆኑበት ድርድር ትመጣ ይሆን? ወይስ ግብፅ የተለመደ ፈላጭ ቆራጭ ሥነ-አመክንዮ የሚደግፋትን ፍለጋ ትቀጥላለች? በሚለው ወሳኝ ጥያቄ የተለያዩ ምሁራን የግል አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

ቶቢያስ እና ጓደኞቹ በኔዘርላንድስ የዓለም ዐቀፍ ግንኙነት ተቋም የፒ.ኤች.ዲ ተመራማሪ ናቸው። ተመራማሪዎቹ በፌብሩዋሪ/2020 ‹‹ናይል – ከግጭት ወደ አውሮፓውያን አማራጭ!›› በሚል ርዕስ ለንባብ ባበቁት መጣጥፍ፣ ግብፅ አሁንም በሰጥቶ መቀበል የምታምን ሳይሆን ፈላጭ ቆራጭ ሥነ-አመክንዮዋን የሚደግፍ ፍለጋ ላይ መሆኗን የሚያመላክት ሐሳብ ሰንዝረዋል።

የተመራማሪዎች መጣጥፍ በግድብ ውሀ አሞላልና አጠቃቀም ዙሪያ አሜሪካ ስታከናውን የነበረችው ሽምግልና ያለምንም ፋይዳ መቋጨቱን በመጥቀስ ይጀምራል።
ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ መሙላት ከጀመረች ወዲህ ወደ ግብፅ መራሄ መንግሥትነት የመጡት አብዱል ፈታህ አልሲሲ፣ በውሀ አጠቃቀምና አመራር ዙሪያ የሚከተሉት ፖሊሲ ከፊተኞቹ እምብዛም የተለየ አይደለም፣ ተመሳሳይ ነው ባይ ናቸው፤ ምሁራኑ። እንዲያውም ‹አልሸሹም ዞር አሉ…› ዓይነት ነው የሚል አስተያየትም አክለዋል።

ኢትዮጵያ በያዘችው አጭር የጊዜ ገደብ፣ በህዳሴ ግድቧ ውሀ ሞላችም አልሞላችም፣ ለግብፅ ምንም ፋይዳ የለውም ባይ ናቸው፤ ቶቢያን እና ጓደኞቹ። ምክንያቱም ግብፅ እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ2025 ከፍተኛ የውሀ እጥረት እንደሚገጥማት የተባበሩት መንግሥታትን ጥናት ያመላክታል። ይህ የሚሆነው፣ አንደኛ ግብፅ በአሁኑ ወቅት የሕዝብ ቁጥራቸው በከፍተኛ ደረጃ እያደጉ ከሚገኙ የዓለም አገራት በዋነኛነት መገኘቷ ነው።

ይህ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እድገት፣ የአገሪቱ መንግሥት ዕድሜ ልኩን ከሚከተለው ፍትሀዊነት የጎደለው ውሀ አጠቃቀምና አባካኝ ፖሊሲ ጋር ተዳምሮ በሚፈለገው መጠን ያህል ንፁህ መጠጥ ውሀና ሀይል ለማቅረብ አስቸጋሪ ሊያደርግበት ይችላል ነው የተባለው።

ኹለተኛውና አሳሰቢው ጉዳይ ግብፅ በአልሲሲ መራሄ- መንግሥት፣ በዓለም ሦስተኛዋ የጦር መሣሪያ ሸማችና ወደ አገር ቤት የምታስገባ አገር ሆናለች። ይህ ደግሞ የታክስ ከፋዩን ሕዝብ ሀብት ያለ አግባብ በመመደብ ከፍተኛ ብክነት ላይ የምትገኝና የምትከተለው የውጭ እና ደኅንነት ፖሊሲም ለዘላቂ ልማት ቁብ የማይሰጥ አገር መሆኗን አመላካች ነው። ይህም የጸሐፊዎቹ እይታና አቋም ነው።

ከግብፅ የውሀ አባካኝ አጠቃቀም ልማድ ጋር ተያይዞ፣ ወደ ፊት የሚገጥማት ሌላው ጉዳይ አገሪቷ አሁን በርዕሰ- ከተማነት የምትጠቀምበትን ካይሮን በሌላ የመቀየር እቅዷን ይፋ ከማድረጓ ጋር የሚገናኝ ነው። ወደ ፊት ግብፅን በርዕሰ ከተማነት የሚያገለግለው አዲስና ምድረ በዳ ላይ የሚቆረቆረው ከተማ፣ 45 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ ይጠይቃል። የአዲሱ ከተማ ልማት፣ የግብፅን የውሀ ፍላጎት እጅግ እንደሚያንረው ይታመናል ሲሉ አጥኚዎቹ አትተዋል። በውሀ ሀብት አባካኝነቷ በእጅጉ ለምትታወቀው ግብፅ፣ የአዲስ ከተማ ግንባታ የውሀ ፍላጎት ተጨምሮበት አይደለም፣ አሁን ባለው አቋሟ፣ ከላይኛው ተፋሰስ አገራት ጋር ለሚጠብቃት ፍትሀዊ የውሀ አጠቃቀም ድርድር የጎን ውጋት ሆኖባታል።

የጥናት ቡድኑ አባላት በማስረጃ አስደግፈው ያቀረቡት፣ አብዱል ፈታህ አልሲሲ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ወደ ሥራ ያስገቧቸው ፕሮጀክቶችም ሆነ የኒኩሊየር ፓወር ግንባታው አንድምታቸውን የሚመለከት ነው። ይህም ምን ይሆን የሚለውን ጥያቄ ለአንባብያን በጣም ግልፅ ይመስለኛል። ጡንቻዋን ማፈርጠምና ነባር ፈላጭ ቆራጭ የውሀ አጠቃቀም ፍላጎቷን በኃይል የማስቀጠል ዝንባሌ ማሳያ ለመሆኑ ከማንም የተሰወረ አይሆንም።

በምሁራኑ የአስተያየት ማጠቃለያ፣ ግብፅ በጀርመን የሚመራና አውሮፓ ኅብረትን ሽምግልና የመላክ ጥያቄ ሐሳብ እንዳላት የሚጠቅሰው የቶቢያስና ጓደኞቹ መጣጥፍ ሽምግልናው ለየት ያለና ኢትዮጵያ ግድቡን ለመሙላት በፈለገችው አጭር የጊዜ ገደብ ባለመሙላቷ ምክንያት የምታጣውን ሀብት ወይንም በሥነ ምጣኔ ባለሞያዎች አባባል ‹‹calculating the opportunity cost›› ለመክፈል ዝግጁ መሆን ይጠበቅባታል የሚል የራሳቸው ምክረ-ሐሳብ የተካተተበት ነው።

እንደዚህ ጹሑፍ አቅራቢ አስተያየት ደግሞ፣ ኢትዮጵያ ልማታዊ አገር ሆና ግድቧን ውሀ ባለመሙላት ምክንያት የምታጣውን ኪራይ እንድትሰበስብ ዕድል የሚሰጥ የፖለቲካ ሥነ-ምህዳር የሌላት አገር ናት። በመሆኑም የምሁራኑ ምክረ-ሐሳብም ሆነ የግብፅ ፍላጎትና የጀርመን ሽምግልና ፍሬ አልባ መሆኑ የማይቀር ነው።
ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያ ዘላቂ ልማቷን አቁማ በካሳ ገንዘብ እየተቀበለች ግድቧን አትሙላ የሚል ምክረ-ሐሳብ በራሱ የአገሪቱን ሕዝብ ሥነ-ልቦናና የአገሪቱን መንግሥት ባህሪይ ካለመረዳት የሚመነጭ ምክረ-ሐሳብ ይመስላል። ሲጠቃለል ኢትዮጵያውያን ግብፅ ለረጅም ዘመናት የአባይን ወንዝ ጨምሮ በተፈጥሮ ሀብታችን ተጠቅመን ወደ ዘላቂ ልማት እንዳንገባ የውጭም የውስጥም ስልት በመንደፍ ለከፋ ድህነትና ስደት ምክንያት የነበረች መሆኗን ተገንዝበን፣ ከአምስት ዓመት ባነስ ጊዜ ውስጥ ግድባችንን ውሀ ሞልተን ብልፅግናችንን እናረጋግጥ! የግብፅን ፈላጭ ቆራጭ ሥነ-አመክንዮ በጋራ ክንድ እንመክት።
ዓለማየሁ ሞገስ ባህር ዳር

ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here