365 ሺሕ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴው ግድብ በየቀኑ አንድ ብር ማዋጣት ጀመሩ

0
492

ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ይውል ዘንድ በ8100 አጭር የጽሑፍ መልእክት ቋሚ ተመዝጋቢ በመሆን በየቀኑ አንድ አንድ ብር ለመክፈል የተመዘገቡ ኢትዮጵያውያን ቁጠር 365 ሺሕ ደረሰ።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በይፋ ያስጀመሩት 3ኛው ዙር የሕዝብ መዋጮ፣ በ8100 A አጭር የሞባይል መልዕክት በመላክ እና በመመዝገብ በየቀኑ የሚቆረጥ ሲሆን፣ ደንበኛው ማቋረጥ እስከሚፈለግበት ጊዜ ደረስ የሚቀጥል ይሆናል።

የግድቡ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ኹለት ነጥብ ኹለት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ዘመናዊ አውቶሞቢል እና ሌሎች ሽልማቶች ማዘጋጁተን ለአዲስ ማለዳ ገልጿል። የገቢ ማሰባሰቢያ ተሳትፎው ለስድስት ወራት የሚቆይ ሲሆን፣ 20 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን የሕዝባዊ ተሳትፎው አስተባባሪ ምክር ቤት የሕዝብ እና የሀብት ፕሮጀክት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ተካ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እንደሰለሞን ገለፃ ሕዝቡ እያሳየ ያለው መነቃቃት እና ከፍተኛ ተሳትፎ፣ እቅዱን ወደ 100 ሚሊዮን ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ገልፀዋል።
ለገቢ ማሰባሰቢያውም ኢትዮ ቴሌኮም እና ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ቀዳሚ አጋሮች መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ኢትዮ ቴሌኮም ለ8100 ፍቃድ በመስጠትና ጠቅላላ ከተሰበሰበው ገንዘብ ላይ 40 በመቶ ያገኝ የነበረውን የኮሚሽን ክፍያ በነፃ በማድረጉ ከፍተኛ የገቢ መጨመር እንደሚኖርም ሰለሞን ገልፀዋል። ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትም ያለ ክፍያ ማስታወቂያዎችን በማስተላለፍ እያገዘ እንደሆነ አብራርተዋል።

የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራው በጀመረበት የመጀመሪያ ሳምንት፣ በ8100 አጭር የጽሑፍ መልእክት መላኪያ ላይ የቴክኒክ ችግር እና ከአቅም በላይ የመጨናነቀ ችግሮች ተፈጥረዉ ምዝገባውን እያካሄደ እንዳልነበር ሰለሞን ገለፀዋል። በህዳሴ ግድቡ ላይ የተነሳውን ውዝግብ አስመልክቶ፣ ኅብረተሰቡ ያሳየውን ቁጭት ግድቡ እንዲጠናቀቅ በ8100 የበኩሉን አስተዋፆ በማድረግና ድጋፉን በማጠናከር ቁጭቱን መወጣት እንዳለበት ሰለሞን ገልጸዋል።

ሰለሞን ኅብረተሰቡ የህዳሴ ግድቡ ቤተሰብ ለመሆንና ለመደገፍ በፈቀደዉ ልክ 8100 ላይ ተመዝገቦ በአንድ ቀን አንድ ብር በህዳሴ ግድቡ ለግሶ ሲበቃው ማቆም እንደሚችል አስረድተዋል። የ8100 ተመዝጋቢዎች ለምዝገባ መልዕክት ሲልኩ ከአንድ ጊዜ በላይ መላክ እንደሌለባቸውና፣ ተመዝጋቢዎች ደጋግመው በመላካቸው ተጨማሪ የሚቆረጥ ገንዘብ አለመኖሩን አንስተዋል። አንድ ሰው አንድ ጊዜ ከተመዘገበ በቀን አንድ ብር ብቻ ይቆረጣል። ደጋግሞ በመላክ የሚያጋጥመውን የመስመር መጨናነቅ መቀነስ ያስፈልጋልም ሲሉ አክለዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ በ2003 ተጀምሮ ዘጠኝ ዓመቱን ሊደፍን ቀናቶች ይቀሩታል። ግንባታው ሲጀመር በአምስት ወይም በስድስት ዓመታት ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል ተብሎ እንደነበር ይታወሳል። ነገር የግድቡ ግንባታ በተለያዩ መሰናክሎች እስከ አሁን ሳይጠናቀቅ እንዲቆይ ሆኗል።
በሌላ በኩል አሁን ላይ በግድቡ ዙሪያ በግብጽ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ መካከል በተለይም በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረውን የውሃ ሙሌት ልዩነት ለመፍታት አሜሪካ በአደራዳሪነት ጣልቃ ገብታ ለግብጽ በመወገኗ፣ በሦስቱ አገራት መካከል የሚደረገው ድርድር ተቋርጦ ይገኛል።

ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here