መድን ድርጅት ለግዮን ሆቴል የመድን ክፍያ ከለከለ

0
818

ግዮን ሆቴል ኅዳር 23/2012 ሳባ በተሰኘው የስብሰባ አዳራሹ ላይ የደረሰበትን የመፍረስ አደጋ ተከትሎ ለኢትዮጵያ መድን ድርጅት ያቀረበው የካሳ ጥያቄ ውድቅ ተደረገ።

ሆቴሉ ከመድን ድርጅቱ የእሳትና የመብረቅ አደጋ ዋስትና የገዛ ሲሆን፣ ይህንን ተከትሎ በአዳራሹ ላይ የደረሰውን የመፍረስ አደጋ መሸፈን አይገባኝም በማለቱ ክፍያ መከልከሉን የግዮን ሆቴል ሥራ አስኪያጅ ገብረጻድቃን አባይ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ነገር ግን መድን ድርጅት ግዮን ሆቴል የረጅም ጊዜ ደንበኝነቱን ከግምት ውስጥ በመክተት የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ የወደመውን ንብረት እያጠና መሆኑንም ተናግረዋል። ሆቴሉም ጉዳዩን የሚከታተል ኮሚቴ አቋቁሞ እየሠራ መሆኑን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ገልጸዋል።

በአዳራሹ መፍረስ የወደመው ንብረት አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር የሚገመት ሲሆን፣ የመድን ድርጅት ከፍተኛ አመራሮች በወሰኑት መሰረት በእርዳታ መልክ እንዲሰጥ መወሰናቸውን የጠቅላላ መድን ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍክሪ አብዱልመጅድ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

‹‹ደንበኝነቱን ላለማጣት እና ከሆቴሉ ወደፊት የሚገኘውን ትርፍ በማሰብ የተወሰነ ውሳኔ ነው›› ሲሉ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው አስታውቀዋል። ‹‹የባለሙያ ቡድን አዋቅረን ጥናት እያስጠናን ሲሆን በጥናቱ ውጤት መሰረት እስከ አሁን ሲደረግ እንደነበረዉ የአጠቃላይ የጉዳት መጠን የተወሰነውን ልንሸፍን እንችላለን›› ብለዋል።

ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ግዮን ሆቴል ከመድን ድርጅት የገዛው መድን የመደርመስ እንዳልሆነም ጠቅሰዋል። መድን ድርጅት ለግዮን ሆቴል ኢንሹራንስ አልከፍልም አለማለቱን አያይዘው አንስተዋል። ‹‹መክፈል እንፈልጋለን›› ሲሉም ፍክሪ ጠቁመዋል። ነገር ግን የድጋፍ ክፍያው መቼ እንደሚከፈልና ምን ያህል እንደሚከፈል እንዳልተወሰነ ጠቅሰዋል።

የፌዴራል የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ግዮን ሆቴል የራሱ አስተዳደር ስላለው ከመድን ጋር የሚያደርገው የድጋፍ ስምምነት ላይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በጉዳዩ ጣልቃ እንዳልገባና ስለጉዳዩ እንደማያውቅ ገልጿል። የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወንዳፍራሽ እንደገለፁት፣ ችግሩን ሆቴሉ ለብቻው ያስተዳድረዋል።

የግዮን ሆቴል ሥራ አስኪያጅ ገብረጻድቃን ለአዲስ ማለዳ በሰጡት አስተያየት፣ የስብሰባ አዳራሹ በእድሜ ብዛት መፍረሱን ተናግረው ያለበቂ እድሳት ማገልግል ከሚገባዉ ጊዜ በላይ በመቆየቱ የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዲዛይን እና ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በባለሙያ አረጋግጦ ማስረጃ እንደሰጣቸዉ ገልጸዋል።
ሳባ የመሰብሰቢያ አዳራሽ 73 ዓመት እንደሆነው የተናገሩት ገብረፃድቃን፣ የፈረሰውን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለማሠራት ጨረታ መውጣቱን ጠቁመዋል።
የመድን ድርጅት ለታማኝ ደንበኞቹ እና ግለሰቦች ከገባው የኢንሹራንስ ውል ውጭ ለደረሰባቸዉ ጉዳት፣ የችግሩን ምንጭ እየገመገመ እንደየ ሁኔታው ድጋፍ እንደሚያደርግ ፍክሪ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here