የአማራ ክልል ከተሞች የተቃውሞ ሰልፍ

Views: 205

ከሰሞኑ በበርካታ የማኅበራዊ ድረ ገጾች መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች ተደርገዋል። በባሕር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ታቦር፣ ጎንደር፣ መርአዊ እና ሌሎች ከተሞች በርካታ ሕዝባዊ ሰልፎችን አስተናግደዋል።

ሰልፎቹ ላይ “በአማራ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ይቁም!”፣ “መንግሥት የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ያረጋግጥ”፣ ”የአማራ መደራጀት ቅንጦት ሳይሆን የኅልውና ጉዳይ ነው!”፣ “አማራን እረፍት አልባ በማድረግ የሚገኝ የፖለቲካ ጥቅም ይቁም!”፣ “አዴፓ ሥሙን ሳይሆን ግብሩን ይቀይር!” እና ሕገ መንግሥቱ የአማራን ሕዝብ እንደማይወክል የሚገልጹ መፈክሮች ተስተጋብተዋል። ሰሞኑን በቤንሻንጉል ክልል በተፈጠረው ግጭት የብሔሩ ተወላጆች መጠቃታቸውና መሞታቸው ለሰልፉ ዋና መቀስቀሻ ሆኗል።

ሰልፎቹን ያስተባበረው የአማራ ወጣቶች ማኅበር ሲሆን፤ የተቃውሞ ሰልፉም ምንም ዓይነት ችግር ሳይፈጠር በሰላም መጠናቀቁንም የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ አስተባባሪ ምክትል ኮማንደር መሠረት ላቀ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት አስታውቀዋል።

የተቃውሞ ሰልፎች በተለያዩ ከተሞች መካሔድ በጀመሩበት ቀን ሐሙስ ሚያዚያ 22/2011 በጎንደር ከተማ የክልሉን ርዕሰ መስተዳደር አምባቸው መኮነን (ዶ/ር) ያካተተ ከፍተኛ የባለሥልጣናት ቡድን ከነዋሪዎች ጋር ውይይት አድርጓል ። በዚህም ወቅት ክልሉን የሚወክለው ፓርቲ አዴፓ ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል ግልጽ አቋም እንዲኖረው እና ያስገነዘቡ ሲሆን፥ የሕገ መንግሥቱ መንሻፈፍ ለአማራ ክልል ሕዝቦች ስጋት እንደሆነም ከተሳታፊዎች በኩል ተነስቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com