ዳሰሳ ዘ ማለዳ መጋቢት 14/2012

0
1030

ኮቪድ19 በ43 የአፍሪካ አገራት መከሰቱን የዓለም ጤና ድርጅት ገለጸ

በአፍሪካ እስካሁን ኮቪድ19 የተከሰተባቸው አገራት 43 መድረሳቸውን እና በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 1 ሺህ 396 መድረሱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

በቫይረሱ ከተያዙት ውስጥ በአሁኑ ሰዓት 122 ሰዎች ማገገማቸውን ድርጅቱ የጠቆመ ሲሆን ናይጄሪያ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የመጀመሪያውን ሞት ማስመዝገቧን ቢቢሲ የአገሪቱን የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል ጠቅሶ ዘግቧል።

በቫይረሱ ምክንያት ሕይወቱ ያለፈው እንግሊዝ ውስጥ የሕክምና ክትትል ሲያደርግ ቆይቶ ወደ ሀገሪቱ የተመለሰ አንድ የ67 ዓመት ግለሰብ መሆኑም ተነግሯል።(ኢቢሲ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኮቪድ19 ስርጭትን ለመግታት ሁሉም የአገሪቱ ድንበሮች ለሰዎች ዝውውር ዝግ መደረጋቸውን ገለጹ። የድንበር መዘጋቱ የሎጅስቲክስ አቅርቦት ለማዳረስ የሚደረገውን ጥረት እንደማያካትት የገለጹት ዐቢይ አሕመድ በዛሬው እለት መጋቢት 14/2012 የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በተገመገሙበት ዕለት ማህበረሰቡ ከንክኪ ተራርቆ እንዲንቀሳቀስ የተላለፈው መልዕክት ባለፉት ቀናት በአግባቡ እየተፈጸመ አይደለም ተብሏል። (ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

የጤና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ከተያዙ 11 ሰዎች መካከል ሁለቱ ጃፓናውያን ወደ ሃገራቸው መሸኘታቸውን ገለጸ። ሌሎች በቫይረሱ የተያዙ እና ከሰዎቹ ጋር ግንኙነት ነበራቸው የተባሉ ሰዎችም ክትትል እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ከዚህ ቀደም በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች መካከል አራቱ የህመም ስሜት ማሳየት ማቆማቸውን የጤና ሚኒስትሯር  ሊያ ታደሰ (ዶ/ር ) መግለጻቸው ይታወሳል። የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከልም ከዛሬ ጀምሮ ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ሰዎች በግዮን እና ስካይ ላይት ሆቴሎች ለ14 ቀናት ወደ ለይቶ ማቆያ ማስገባት ግዴታ ተጀምሯል። (የጤና ሚኒስቴር)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

አንበሳ የከተማ አውቶብስ፣ በተጠቃሚዎች ጥግግት ምክንያት ቫይረሱ እንዳይሰራጭ የአውቶብስ መቀመጫዎች ብቻ እንዲጭኑ ማድረጉን አስታወቀ። በዚህ የተነሳ የትራንስፖርት ችግር እንዳይገጥም የአውቶብሶችን የምልልስ ቁጥር እና አዳዲስ አውቶብሶች ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ማድረጉን አስታውቋል።(ሸገር ኤፍ ኤም)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

ከውጪ አገራት መጥተው ለለይቶ ማቆያ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ መሸፍን ለማይችሉ ኢትዮጵያዊያን የአዲስ አበባ መስተዳደር ወጪያቸውን እንደሚሸፍን አስታወቀ። የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ወደ ለይቶ ማቆያ ለሚገቡ ሰዎች የሚያስፈልገውን ወጪ እንደሚሸፈንላቸው በማኅበራዊ  ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።ምክትል ከንቲባው እንዳሉት “ለቆይታ ጊዜው ወጪያቸውን መሸፈን ለማይችሉ ዜጎቻችን ሙሉ ወጪያቸውን እኛ እንሸፍናለን።” ብለዋል ። (ቢቢሲ አማርኛ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተሳፋሪዎችን ቁጥር 50 በመቶ መቀነሱን ያስታወቀ ሲሆን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ስንታየሁ ወልደሚካኤል (ዶ/ር) እንዳሉት የተሳፋሪዎችን ቁጥር መቀነስ ያስፈለገው የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ነው። ከዚህ ቀደም የአንዱ የባቡር ፉርጎ በአንድ ጊዜ በአማካይ ይጭን ከነበረው 250 ሰው ከዛሬ ጀምሮ 128 ሰዎችን ብቻ እንደሚያስተናግድም ገልጸዋል።(ኢዜአ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………….

ኢትዮጵያ የኮቪድ19  ስርጭትን አደጋ ለመከላከል መንግሥት አምስት ቢሊዮን ብር መበጀቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ። ወረርሽኙ አሁን ላይ በ11 ሰዎች ላይ የታየ ቢሆንም በቀጣይ ስርጭቱ ሊስፋፋ ስለሚችል እያንዳንዱ ዜጋ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባልም ብለዋል። የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የአገሪቱ ሁሉም ድንበሮች ለሰዎች ዝውውር ዝግ መደረጋቸውንም ገልጸዋል። (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here