‹‹ከቤት አትውጡ የሚል ማሰታወቂያ እየተነገረ ነው›› የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች

0
1153

ዛሬ መጋቢት 20/2012 በአዳማ ከተማ ባሉ ጎዳናዎች ‹‹ከአሁን ሰዓት ጀምሮ በከተማው ውስጥ አንገብጋቢ ካልሆነ በስተቀር እንቅስቃሴ ማድረግ ተከልክሏል›› የሚሉ ማስታወቂያዎች እየተነገሩ መሆኑን ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።

የከተማ አስተዳደሩ ትልልቅ የድምጽ ማጉያዎችን በጫኑ መኪኖች በአማርኛ እና በኦሮሚኛ ቋንቋዎች በዋና ዋና ጎዳናዎች ማስታወቂያውን እያሰራጨ መሆኑን ገልጸዋል።

‹‹በየሰፈሩ የበሽታው ምልክቶች የታየበት ሰው የሚጠቆምበት ትስስር ተዘርግቷል፣ ጥቆማ ሲኖርም አንቡላንሶች በፍጥነት ይመጣሉ›› ያሉት አንድ ነዋሪ ‹‹ተጠርጥረው ማቆያ ከገቡ ሰዎች ጋር ግንኙነት የነበራቸው ጓደኞቼም ራሳቸውን አግልለው ቆይተዋል ብለዋል። ‹‹የተገለሉት ሰዎች ነጻ መሆናቸው እንደተነገረ ነው ከቤታቸው የወጡት›› ሲሉም አክለዋል።

በከተማው ባሳለፍነው ሳምንት እጅ መታጠብ እና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ የተመከለቱ ማስታወቂያዎች ሲነገሩ መቆየታቸውን የገለፁት ሌላኛው ነዋሪ ከዛሬ ጀምሮ ግን ከቤት አትውጡ የሚሉ መልክቶች መነገር ጀምረዋል ብለዋል። እኚሁ ምንጫችን እንደገለፁት ከተማዋ ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል የመዝጋት ውሳኔዎች ባይኖሩም እቅስቃሴዎችን ለመቀነስ የታሰበ ይመስላል ሲሉ ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ወደ ከንቲባ ጽህፈት ቤት በተደጋጋሚ ብትደውልም ሳይመለስ ቀርቷል፡፡ በአዳማ ከተማ ሶስት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን የጤና ሚኒስቴር መግለፁ ይታወሳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here