የኮሮና ጫና በርዕዩተ ዓለሞች እና እውነታዎች ላይ

0
1106

ባለፉት ሦስት ወራት መነጋገሪያ ሆኖ ከቆየ በኋላ በአሁኑ ጊዜ የሁሉንም ቤት እያንኳኳ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የጤና ችግሮች ብዙ የተባለላቸው ቢሆንም በሰፊው ተቀባይ በሆኑ ርዕዮተ ዓለሞች እና ዓለማቀፋዊ ሂደቶች ላይ ያለው ጫና ዘላቂ እንደሚሆን ይገመታል። በዚህም መሠረት ወረርሽኙ በኒዮሊብራሊዝም፣ በሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) እና በምዕራብ ዘመሙ የዓለም ፖለቲካ ላይ ሊኖሩት የሚችሉትን ተፅዕኖዎች እናያለን።

ኮሮና እና ኒዮሊብራሊዝም
ከአስራ ኹለት ዓመት በፊት ዓለም ከአሜሪካ በተነሳ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ በነበረችበት ጊዜ የአገሪቱ ፌዴራል ሪዘርቭ የተባለው ማእከላዊ ባንክ ሊቀመንበርነታቸውን ከለቀቁ ኹለት ዓመት ያልሞላቸው እና የፋይናንስ ዘርፉ ጣኦት ተደርገው ይወሰዱ የነበሩት አለን ግሪንስፓን ‹‹ይህ ቀውስ የገበያ ኃይሎች ምክንያታዊ (ራሽናል) ያለመሆናቸውን ያሳየ ነው›› ብለው ነበር።

ይህንንም ያሉት በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አዋጭነቱን እና ቀጥሎ የሚያመጣውን ችግር ባላገናዘበ መልኩ ብድር ሲሰጡ መቆየታቸውን ካረጋገጡ በኋላ ነው።

በውጤቱም እንደታየው የአሜሪካ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ኃላፊነት የጎደለው ሥራ ለዓለም ተርፎ እንደ ግሪክ፣ ፖርቹጋል፣ አይስላንድ፣ አየርላንድ እና ስፔን ያሉ አገሮች መንግሥታት ለሕዝብ አገልግሎት የሚያውሉትን ወጪ በእጅጉ በመቀነስ (ኦስቴሪቲ) ለእዳ ከፈላ አውለውታል። አገራቱ በእንደዚህ ዓይነቱ ችግር ውስጥ ለዓመታት የማቀቁ ሲሆን ችግሩ የሰዎችን ኑሮ እጅጉን ከማክበዱም በተጨማሪ የአገሮቹን ሉዓላዊነት የገረሰሱ እርምጃዎችን ያመጣም ነበር።

እነዚያ ትላልቅ የአሜሪካ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶችን ለማዳን በመፍትሔነት ቀርቦ ተግባራዊ የተደረገው ነገር ደግሞ መንግሥት ከግብር ከፋዩ እና በኢኮኖሚ ቀውሱ ከተጠቃው ሕዝብ የሰበሰበውን ገንዘብ በመቶ ቢሊዮኖች በሚቆጠር ዶላር ለእያንዳንዱ ድርጅት መስጠቱ ነበር። በዚህም ተጠቂው ሕዝብ ጥፋት ያደረሰውን አካል ክሷል። ይህ ፍተሃዊ ያልሆነ ተግባር የድርጅቶቹ መውደቅ አጠቃላይ የአሜሪካ ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው ተፅዖኖ ከባድ ስለሆነ ለወድቁ አይገባም በሚል ምክንያት ተሰጥቶታል።

ማንም ሰው ሊገምተው እንደሚችለው እና ብዙ ሰዎችም በጊዜው እንደተከራከሩት በመቶ ቢሊዮኖች ሰጥቶ ያተረፋቸው መንግሥት በገንዘቡ በድርጅቶች ውስጥ ተመጣጣኝ ድርሻ ሊይዝ ይገባ ነበር። የገበያ ኃይሎች ምክንያታዊነታቸውን ጥሰው ራሳቸውን ለማጥፋት መንቀሳቀሳቸው እና መንግሥት በነጻ መስጠት ሳይጠበቅበት በዚያ ገንዘብ በድርጅቶቹ ሊገዛ ይገባ እንደነበር ግምት ውስጥ በማስገባት ነበር አለን ግሪንስፓን ዘመኑ የነጻ ገበያ ስርዓት ማብቂያ መሆኑን የጠቆመው።

ምንም እንኳን ሰውየው ይህንን ቢልም የነጻ ገበያ ስርዓት ግን በሌላ እንዲተካ አልተደረገም። ይልቁንም ኃያላኑ አገራት ባለፉት አስራ ኹለት ዓመታት በዓለም እጅጉን እንዲሰፋ ሠሩ እንጂ። በመሆኑም የነጻ ገበያ አስተሳሰብን በውስጡ ያካተተው የመንግሥትን ሚና ቀንሶ በግሉ ዘርፍ አካላት መካከል ያሉ ኮንትራቶችን የሚያፈራርም እና ሲጣሉ የሚዳኝ አካል የሚያደርገው ኒዮሊብራሊዝም እየሰፋ መጥቷል።

ከአስራ ኹለት ዓመታት በኋላ ግን አሁንም ዓለምን የሚንጥ አንድ ጉዳይ ተከስቷል። ይህም የኮሮና ቫይረስ ዓለም አቀፍ ስርጭት ነው። እያየነው እንዳለውም ቫይረሱ ኃያላን የሚባሉትን መንግሥታት አንድም ሳያስቀር አቅማቸው እንደሚገምቱት ያህል እንዳልሆነ እያሳየ ነው። እነ አሜሪካ፣ ቻይና እና የአውሮፓ አገራት የወረርሽኙ ዋነኛ ተጠቂ መሆናቸው እና ሕዝባቸውን ከስቃይ ሊያስጥሉ ያለመቻላቸው የሰው ልጅን ሳይንስ መር በሆነ መንገድ እንዲያስብ ብዙ ለጣሩት ኃይሎች መጥፎ ዜና በመሆን አምላክ አለ የሚለው አስተሳሰብ እንዲጨምር ማድረጉን ከሰሞኑ የመገናኛ ብዙኃን ሪፖርት ሰምተናል።

ለዚህ ከባድ ዓለም ዐቀፍ ችግር ምላሽ ለመስጠት በመዋቅርም ደረጃ ሆነ በሀብት ደረጃ ጥሩ አቋም ላይ ያሉት መንግሥታት መሆናቸውን ከዓለም ተሞክሮ እያየን ነው። መንግሥታት የዜጎችን የመንቀሳቀስ መብት በመገደብ፣ ባለሙያዎችን በማስተባበር፣ ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ሆስፒታሎችን በፍጥነት በመገንባት፣ ለሕክምና የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ አገራት በማስገባት ችግሩን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየተንቀሳቀሱ ነው።

የግሉ ዘርፍ ይህን ችግር ለመቅረፍ ያለው ሚናም ከፍተኛ ነው። እንደ እንግሊዝ ባሉ አገሮች የግል ድርጅቶች እጥረት እየታየበት ያለውን የቬንቲሌተር ማምረት ሥራ የሚያግዙ አዳዲስ አሠራሮችን አምጥተዋል። ለበሽታው ክትባት የሚፈልጉ የግል ላቦራቶሪዎች እና የጥናት ማእከላትም ተስፋ ሰጪ ውጤት እያስመዘገቡ ይገኛሉ።
ነገር ግን ችግሩ ከቬንቲሌተር ማምረት እና ክትባት ከመፈለግ እንቅስቃሴዎች እጅጉን የከፋ ነው። እነዚህን ዓይነት ትርፍ ሊሠራባቸው የሚችሉ ጉዳዮች የግሉን ዘርፍ የሚስቡ መሆናቸው ግልጽ ቢሆንም፣ ቫይረሱ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ያሳየው ግን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጫናው ከፍተኛ መሆኑን ነው።

መንግሥት የዜጎችን እንቅስቃሴ ሲገድብ ኢኮኖሚው እንደሚጎዳ፣ ራሳቸውን በዚያን ጊዜ ሊመግቡ የማይችሉ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ፣ እንደማኅበረሰብ በጋራ የሚታለፍ ችግር መሆኑን ግምት ውስጥ አስገብቶ ነው። ምንም እንኳን እነዚህ ተግባራት የሰዎች እና የድርጅቶች አቅም ላይ ችግር የሚያመጡ ቢሆኑም፣ እንደ አገር ይህን ችግር ለማለፍ ከትርፍ በዘለለ የማኅበራዊ ትስስርን እሴቶች መጠቀም እና ሰውን ማዳን እንደሚቀድም ግምት ውስጥ የከተቱ ናቸው።

በአሁኑ ጊዜ ቫይረሱን ለመቋቋም አገሮች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ስፋት መንግሥታት በማኅበረሰብ ውስጥ ያላቸው ከፍተኛ ሚና ማምረት እና አገልግሎት በመስጠት ላይ በተሰማሩ ድርጅቶች ብቻ እንደማይተካ ያሳየ ነው። በገበያ የሚመራ ስርዓት በእንዲህ ዓይነቱ የችግር ወቅት የሕክምና ግብዓቶች ዋጋ ንሮ የሚታይበት ይሆን ነበር። ይህም ማስኮች፣ ጓንቶች እና ሌሎች የንፅህና መጠበቂያ ዕቃዎች እና ይጠቅማሉ የተባሉ መድኃኒቶች ላይ በተለያዩ አገሮች በታየው የዋጋ ጭማሪ የተደገፈ ነው።

ፍላጎት ሲጨምር ዋጋ ይጨምራል ይላል ሳይንሱ በቀላሉ። ነገር ግን የመንግሥታት ጣልቃ ገብነት እነዚህ ግብዓቶች በነጻ ወይም በተመጣጣኝ ዋና እንዲቀርቡ በማድረግ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ሕዝብ እንደታደገ ማየት ችለናል። ኒዮሊብራሎች ከአስራ ኹለት ዓመት በኋላ የመንግሥታትን ጥቅም እንደገና የተጎነጩነበት አጋጣሚ በኮሮና ቫይረስ ተፈጥሯል ማለት ይቻላል።

ኮሮና እና ሉላዊነት
ቀዝቃዛው ጦርነት ካበቃበት ጊዜ ጀምሮ በአሸናፊነት ዓለምን በሊብራል ካፒታሊዝም መንገድ ሲመሯት የኖሩት ምዕራባዊያን ኃይሎች ባራመዷቸው ፖሊሲዎች ሉላዊነት እየተጠናከረ የመጣ ሒደት ሆኗል። ይህም ፅንሰ ሃሳብ ከአገራዊ ብሔራዊነት ጋር እየተነጻጸረ የሚሔድ ሲሆን የሉላዊነት መጠናከር አገራዊ ብሔርተኝነት በምዕራባዊያን መገናኛ ብዙኋን እና ልሒቃን እንደ ስጋት እንዲታይ አድርጎት ቆይቷል።

ከአራት ዓመታት በፊት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ሲመረጡ ያሳዩት ከፍተኛ የሆነ የአገራዊ ብሔርተኝነት ስሜት የሕዝበኝነት መስፋፋት የሥልጣን ጫፍ ድረስ እንደሚደርስ ያሳየ ነበር። አሜሪካ ትቅደም ብለው የተነሱት ቢሊዮነር ድንበር የለሽ እየሆነ እንዲመጣ ይታሰብ የነበረውን ዓለም በአጥር በመክፈል ልዩነቶችን እንደሚያጎሉ ቃል በመግባት ነበር ወደ ሥራ የገቡት። ይህም ሉላዊነትን የሚቀናቀኑ አስተሳሰቦች በአውሮፓም እንዲጠነክሩ በማድረግ በሉላዊነት ላይ አዲስ ተግዳሮች ጨምሮበታል።

የኮሮና ቫይረስ ከተከሰት ጊዜ ጀምሮ መንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ዜጎች እንዳይንቀሳቀሱ ሲከለክሉ እና ድንበራቸውን ሲዘጉ ታይተዋል። ይህም ድንበር የለሽነትን ለሚሰብከው ሉላዊነት የማይረዳ እንቅስቃሴ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ እንደ ጣልያን እና ስፔን ያሉ በቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠቁ ያሉ አገሮች በሉላዊነት መንፈስ ኢኮኖሚያቸውን እና ድንበራቸውን ከፍተው እንዲሁም ገንዘባቸውን አንድ አድርገው ከሚንቀሳቀሱበት ከአውሮፓ ኅብረት ምንም እርዳታ ያለማግኘታቸው ታይቷል። ለእነዚህ አገሮች ብቻ ሳይሆን ለሌሎቹም አባል አገራት የአውሮፓ ኅብረት እዚህ ግባ የሚባል ትብብር ያለማድረጉ በግልጽ የታየ ነው። በዚህም መሠረት እንደ ጣልያን ያሉ አገሮች እርዳታ ከራሽያ እና ኩባ ያገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህም የአህጉራዊ ህብረቶች ጥቅም ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።

ሉላዊነትን ተከትሎ የማምረት እንቅስቃሴዎች ተከፋፍለው የአንድ ምርት ክፍሎች በተለያዩ አገሮች ተመርተው ሌላ ቦታ የሚገጣጠሙ ሲሆኑ፣ ይህም በዓለማቀፋዊ የአቅርቦት እና ስርጭት ሰንሰለት ውስጥ የተካተተ ነው። ለምሳሌ የአንድ መኪና ሞተር፣ ሻንሲ፣ ወንበር እና ሌሎችም ክፍሎች በተለያዩ አገሮች የሚሠሩበት እና አንድ ሌላ አገር የሚገጣጠሙበት ሁኔታ በሉላዊነት ዘመን እየጎለበተ መጥቷል።

የኮሮና ቫይረስን ለመቋቋም የሚደረጉት እንቅስቃሴዎች እንዳሳዩት ግን ይህ ዓይነቱ የምርት ሒደት ጊዜ እና ገንዘብ ቆጣቢ ሆኖ አልተገኘም። በመሆኑም አገሮች በዚህ ጊዜ በራሳቸው አቅም ምርቶችን ሙሉ በሙሉ ወደ ማምረት መግባት ጀምረዋል። ይህም በኢኮኖሚያዊ ሉላዊነት ላይ የሚያደርሰው ጫና ከፍተኛ ነው።
በአጠቃላይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አገሮች በተለያዩ ምርቶች ራስን እንደመቻል ዘላቂ መፍትሔ እንደሌለ እንዲያዩ በር የከፈተ በመሆኑ የፖለቲካው አገራዊ ብሔርተኝነት በኦኮኖሚው ዘርፍም እንዲደገም እድል እየፈጠረ ነው። ይህ አካሔድ ደግሞ ለሉላዊነት መቀዛቀዝ የራሱ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል።

ኮሮና እና ምዕራብ ዘመሙ የዓለም ፖለቲካ
ምዕራባዊያን አገሮች የሚከተሏቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ፖሊሲዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድሩ ይታወቃል። በዓለም ዐቀፋዊ የገንዘብም ሆነ የመንግሥታት ድርጅቶች በኩል ምዕራባዊያን የሚያራምዷቸው ፖሊሲዎች ተግባራዊ የሚደረጉ ሲሆን፣ ከዚያ ውጭ ያሉ ደግሞ በተለያየ መንገድ ሲወገዙ ይታያል። በመሆኑም ምዕራባውያን ለተቀረው ዓለም አመራር እንደሚሰጡ ተደርገው ይታዩ ነበር።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከመጣ ጊዜ ጀምሮ ግን ምዕራባዊያን ለዓለም አመራር መስጠታቸው ጠፍቶ ራሳቸውም ችግሩን ለመቋቋም ተስኗቸው እየታዩ ነው። አሜሪካም ሆነች የአውሮፓ አገራት በቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠቁ ሲሆን ለአብዛኞቹ ክፉው ቀን ገና ከፊታቸው ነው። በመሆኑም አገራቱ በተናጠልም ሆነ በጋራ ለሌላው ዓለም ጥሩ ተሞክሯቸውን የሚያካፍሉበት እና እርዳታ የሚያደርጉበት ሁኔታ ላይ አይደሉም።

ይልቁንም አገራቱ እንደ ቻይና እና ደቡብ ኮሪያ ካሉ የምሥራቅ እስያ አገሮች እርዳታ ሲጠይቁ እና ሲቀበሉ ነው የሚታዩት። ይህም ዓለማቀፋዊ ተግዳሮቱን የማሸነፍ ሥነ-ልቡና ከምሥራቅ ኃይሎች ጋር እንዲሆን እያደረገ ሲሆን፣ የተቀረው የዓለም ሕዝብም ለምክርም ሆነ ለእርዳታ ፊቱን ወደ ምሥራቅ እንዲያዞር ጋብዟል። ምዕራባዊያኑም አሁን ባለው ሁኔታ በምሥራቅ ኃይሎች ብልጫ የተወሰደባቸው ይመስላል።

ይህ ግንዛቤም ዘላቂ የሆነ ውጤት ሊኖረው ይችላል። በመሆኑም ምንም እንኳን የዓለም የኃይል ሚዛን ከምዕራብ ወደ ምስራቅ ይዞራል ተብሎ ባይጠበቅም የምስራቅን አቅም ጨምሮ የምዕራብን በመቀነስ ልዩነታቸውን ሊያጠብ ግን ይችላል።

ቅጽ 2 ቁጥር 73 መጋቢት 19 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here