ልደቱ አያሌው የሽግግር መንግሥትን የሚመለከት አዲስ መጽሐፍ ጻፉ

0
718

ልደቱ አያሌዉ ‹‹ለውጡ ከድጥ ወደ ማጡ›› የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ ጽፈው የመጨረሻ ረቂቁን ማጠናቀቃቸው ታወቀ። የሽግግር መንግሥትን በሚመለከት ሰፊ ትንታኔ እና ገለጻ የያዘው አዲሱ መጽሐፍ፣ ‹ብሔርተኝነት፣ ጽንፈኝነትና የአመራር ድክመት የተቀየደች አገር” ሲሉ የመጽሐፋቸዉን ጽንስ ሐሳብ በንዑስ ርዕስነት ከፋፍለው አስቀምጠዋል።

በ104 ገጾች የተቀነበበው መጽሐፉ በዋናነት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ስለተፈጠሩ ኹነቶች ያነሳል።
አዲሱ የለውጥ ኃይል ተስፋ ላደረገው ሕዝብ የታሰበውን ያህል መፈጸም አልቻለም ሲልም ይጠቁማል።

‹‹በአሁኑ ወቅት በሥልጣን ላይ የሚገኘው የለውጥ አመራር የተጀመረውን የለውጥ ሒደት ስኬታማ አድርጐ አገራችንን ወደ መዋቅራዊ ዴሞክራሲ ለማሸጋገር የሚያስችል አቅምና ፍላጎት የለዉም›› የሚል ሐሳብ በሰፈረበት በዚሁ መጽሐፍ ላይ ልደቱ ይበጃሉ ያሏቸውን የመፍትሔ ሐሳቦችም አስቀምጠዋል።

በአገሪቱ እየታዩ ያሉትን ችግሮች በመጽሐፋቸው ነቅሰው ያወጡት ልደቱ ‹‹ከእንግዲህ ከህልውና አደጋ ወጥተን ወደ መዋቅራዊ ዴሞክራሲ ለመሸጋገር ያለን ዕድል እጅግ አስቸጋሪ ፈታኝ ቢሆንም፣ ያንን ለማድረግ የሚያስችለን አንድ ኹሉን ዐቀፍ የእርቅና የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ነው›› ሲሉ በመጽሐፋቸው አስቀምጠዋል።
በአዲሱ መጽሐፍ ልደቱ ስለመጪዉ ምርጫ በገለጹበት ክፍል ወደ አገራዊ ምርጫ መገባት ያለበት የለውጡን ጉዳትና ስኬታማነት አስቀድሞ ሲረጋገጥ ብቻ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።

በመጽሐፉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን መምጣት ጋር ተያይዞ፣ በአገራችን የተከሰተውና ከፍተኛ የሕዝብ ተስፋ ፈጥሮ የነበረውን የለውጥ ሂደት ወደ መክሸፍ አቅጣጫ እየሄደ ነው ሲሉ እንደመነሻነት አስቀምጠዋል።

ለውጡን ወደ ክሽፈት ያመሩት መሠረታዊ ምክንያቶች በኹለት መንገድ እንደሆነና እነሱም የመጀመሪያው መሠረታዊ የአገሪቱ የፖለቲካ ባሕል ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ኹለተኛው ደግሞ ከፖለቲካ አመራር ድክመት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ልደቱ በመጽሐፋቸዉ ጠቅሰዋል።

መጽሐፉ በዋናነት የዳሰሳቸውን ጉዳዮች የፖለቲካ ፅንፈኝነት (የፖለቲካ ፅንፈኝነት በኢትዮጵያ)፣ ብሔርተኝነት፣ ማንነት፣ የአመራር ድክመቶች፣ ምርጫ ምን ለመምረጥና ስርዓት በልካችን በሚሉ ንዑስ ርዕሶች ስር በዝርዝር አካትቷል። እንዲሁም ምርጫችን፣ ኢኮኖሚያችንና ውጭ ጉዳያችን የሚሉ ሐሳቦች ተካትተዋል። ጸሐፊዉ ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች በተጨማሪ በመጽሐፋቸው በእርቅና በሽግግር መንግሥት ላይ ትኩረት አድርገዋል።

ልደቱ በመጽሐፋቸዉ ለውጡ የከሸፈበትን ምከንያት ሲያስረዱ ‹‹በአንድ በኩል በአገራችን የበላይነት ባገኘው የጽንፈኝነትና የብሔርተኝነት ፖለቲካ ባህላችን ምክንያት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከመዋቅራዊ የፖለቲካ አመራር ድክመት በመነጨ ነው። የወቅቱ “የለውጥ አመራር” የእነዚህ መሠረታዊ ችግሮች ሰለባ በመሆኑ ምክንያት ሕዝቡ የጣለበትን ለውጡን ውጤታማ የማድረግ አደራ በታማኝነት ከመወጣት ይልቅ ወደ የእርስ በርስ ሽኩቻ ውስጥ በመግባቱ፤ ሕግና ስርዓትን በአገሪቱ በአግባቡ ማስከበር ባለመቻሉ ምክንያት የለውጥ ሒደቱን ውጤታማ ማድረግ የማይችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል›› ሲሉ አስረድተዋል።

‹‹ለውጡ ኹሉን ዐቀፍ በሆነ የሽግግር ተቋምና ከዚህ ዓይነቱ ተቋምና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር በመነጨ ፍኖተ ካርታ መመራት ሲገባው፣ በተጨማሪም አገር አቀፍ ብሔራዊ እርቀ ሰላም በማካሄድና መሠረታዊ የፖለቲካ ቅራኔዎቻችንን በተገቢ የሕግና የመዋቅር ማሻሻያዎች መፍታት በሚያስችል አግባብ መካሄድ ሲኖርበት፣ ገዢው ፓርቲ “እኔው አሻግራችኋለው” በሚል የተለመደ መታበይ ብቻውን ሊመራው በመፈለጉ አገሪቱን ከጥፋት ይታደጋታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የለውጥ ሂደት በተቃራኒው አገሪቱን ከድጡ ወደ ማጡ የማስገባት ስጋት ፈጥሯል›› በማለት ልደቱ የለውጡን መክሽፍና አገሪቱ ወደ ጥፋት እያመራች ነው በሚል ሙግታቸውን አኑረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 73 መጋቢት 19 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here