ኮቪድ19 ለመዋጋት – የደቡብ ኮርያን ዳና መከተል

ዓለም አሁን ያለችበት ሁኔታ

የኮሮና ቫይረስ ስርጭት አሜሪካን በግንባር ቀደምትነት አስቀምጦ የዓለምን ሕዝብ አሁንም ድረስ እያሸበረና እያመሰ ይገኛል። በየቀኑ በቫይረስ እንደተያዙ የተረጋገጡ አሜሪካኖች ቁጥር ከቀዳሚው ቀን በበለጠ ቁጥር ከፍ ማለቱን ሳያቋርጥ ቀጥሎበታል። በአግባቡ መቆጣጠር ካልተቻለ አሁንም የስርጭት ፍጥነቱ አሳሳቢ እንደሆነ ዘልቋል።

በቫይረሱ የተጠቁ አሜሪካውያን ቁጥር እየጨመረ ከመሆኑ በላይ ቁጥሩ የሚያድግበት መጠንም በጣም ትልቅ እንደሆነ በየቀኑ እየተለቀቁ የሚገኙት አሃዞች ይጠቁማሉ። ይህም ከጥቂት ቀናት በኋላ ከፍተኛ የሞት አሃዝ እንዲመዘገብ ሚና መጫወቱን ከጣሊያን ተሞክሮ በሚገባ ታይቷል። በዚህም የታይም መጽሔት በመጋቢት 28 እትሙ፣ ይህንን የአሜሪካውያን በቫይረሱ አዳዲስ ተጠቂዎች እለታዊ ቁጥር ያለማቋረጥ መምጠቁን በመተው ዘንበል የሚለው መቼ ይሆን ሲል ይጠይቃል።

የቫይረሱ ስርጭት እንዲህ ዓለምን አዳርሶ በሚያስጨንቅበት በዚህ ወቅት ኹለት አገሮች ብቻ የአዳዲስ በቫይረሱ የሚጠቁ ዜጎችን ቁጥር ከእለት ወደ እለት እየቀነሱ በዚህም ሕዝባቸውን ከተጋረጠበት የከፋ አደጋ እንደታደጉ እየተገለፀ ይገኛል። እነኚህ አገራት የቫይረሱ መነሻ የሆነችው ቻይናና ከሁሉም አገራት በመቅደም ከቻይና በመቀጠል በቫይረሱ ገፈት ቀማሽ ሆና የነበረችው ደቡብ ኮርያ ናቸው።

ከሳምንት በፊት የጣሊያን ሕዝብ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ከሚሰማው የተደበላለቀ መረጃ የተነሳ ግራ በተጋባበት ወቅት፣ መደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ በአግባቡ ወቅቱን በሚፈቅደው መጠን ባለመደረጉ የቫይረሱ የስርጭት ማእከል ከቻይና ወደ ጣሊያን ተዘዋውሮ ነበር። በየዕለቱም በቫይረሱ የሚያዙና ሕይወታቸው የሚያልፈው ጣሊያናውያን የዓለም ሕዝብ ትኩረት መሳቡንም የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባን መነሻ በማድረግ በሰፊው አስነብቤያችሁ ነበር።

በመሆኑም የመንግሥቱ እርምጃ የመውሰድና ህብረተሰቡም የሚጠበቅበትን ጥንቃቄ የማድረግ ዝንጋኤ ባስከተለው ዳፋ ጣሊያናውያን ምን ያክል ዋጋ እንዳስከፈላቸውና እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስም ጣሊያን በየቀኑ የሚመዘገቡት አዳዲስ ተጠቂዎቿ ልክ እንደ አሜሪካ ከቀደመው ቀን በበለጠ ቁጥር እየተመነደገ እንጂ እንደ ቻይናና ኮርያ ቀንሶ እንደማይታይ የአደባባይ ሃቅ ሆኗል።

ጣሊያን የአዳዲስ ተጠቂዎች ቁጥር ብቻ ሳይሆን የሟቾች አሃዝም በየዕለቱ ከባለፈው ቀን ጋር ሲነጻጸር እየጨመረ እንጂ ሲቀንስ ወይም ባለበት ሲቆም አይታይም። ‹‹ጣሊያን ሆይ መልካሙን ቀን ያምጣልሽ!›› ከማለት ውጭ አጋሮቿና ጎረቤቶቿ ሁሉ በራቸውን ከርችመው ከማየት ሌላ ያደረጉላት አንዳችም ነገር የለም። ከአውሮፓ አጋሮቿና ጎረቤቶቿ ይልቅ የቻይና፣ የኩባና የሩስያ እገዛ የተደረገላት መሆኑን እያየን እንገኛለን።

ምዕራባውያን ቻይናን ይህንን አጋጣሚ ተጠቅማ አውሮፓን ለመከፋፈል እየተጋች ነው በማለት እየከሰሱም ይገኛሉ። እኔም ታላቋ ጣሊያን መልካም ዜና የሚሰማበት ምድር እንድትሆን ምኞቴን እገልጻለሁ።

ዓለም ሁሉ የኮርያን ስኬት በመተግበር የዚህን አደገኛ ቫይረስ ስርጭት በሚገባ ሊገታው እንደሚገባ ሚዲያዎች እየተነተኑ ይገኛሉ። ኮርያን ለዚህ ተዓምራዊ ስኬት ያበቃት ምን እንደሆነ በዋናነት የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባን ጨለፍ በማድረግ፣ ለአገራችን ምን እንደሚፈይድላት ለማየት እንሞክራለን። በመሆኑም በዋናነት የዚህ ሐተታ ግብ በባለፈው ሳምንት ከጣሊያን ድክመት ምን እንማራለን በሚል እንደነበረው ሁሉ አሁንም ዋና ዓላማ አገራችን የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ለምታደርገው ጥረት ከኮርያ ምን ጥበብ ልትወስድ ትችላለች የሚለው ለማመላከት ብቻ ነው።

የደቡብ ኮርያ ተሞክሮ

ኮርያ ከሞላ ጎደል የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋ የሚያስተጓጉል ከቻይና በተቃራኒ አንዳችም የጠነከረ እርምጃ አልወሰደችም። ነገር ግን በጊዜው ጥበብና ብልሃት የተሞላበት መንገድ በመከተሏ ለዓለም ምሳሌነት በሚሆን መንገድ የቫይረሱ ስርጭት ከቁጥጥሯ ውጭ እንዳይሆን በመከላከሏ እየተወደሰች ትገኛለች። የታደለች ኮርያ! እስከ አሁን ባለው መረጃ መሰረት ለብዙኀኑ  ሽንፈት ለኮርያ ድል ተደርጎ ተወስዷል።

‹‹ቻይና የቫይረሱ ስርጭት ከቁጥጥሯ ውጭ እንዳይሆን ያስቻላት የፀጥታ ኃይሎቿ በሚገባ በመጠቀም እንደለመደችው የሕዝቧን ነጻነት በመግፈፍ ነው›› ብለው የሚሟገቱ አሉ። በአንጻሩ ዴሞክራሲ በሰፈነባቸው የዓለም አገራት (ጣሊያንና ሌሎችን እንደምሳሌ በመጥቀስ) ዘንድ በሚገባ የሚከበረው የግለሰብ ነፃነት መግፈፍ ከባድ በመሆኑ ቫይረሱ ተስፋፍቷል የሚል ሐሳብም ለማስተባበያነት ይቀርባል። ነገር ግን ከምዕራባውያን ተመሳሳይ የሆነ የዴሞክራሲ ባህል ባላት ኮርያ የተመዘገበው ስኬት፣ ይህን ሙግት ፉርሽ ያደረገ እንደሆነም በሰፊው እየተራገበ ይገኛል።

በፈረንጆቹ አቆጣጠር በየካቲት ወር በአገሪቱ ውስጥ አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከጥቂቶች ወደ መቶዎች ክዚያም ሺሕዎች ከፍ ብሎ ነበር። በዚህም በየካቲት 29 ብቻ የጤና ሠራተኞች ከዘጠኝ መቶ በላይ ተጠቂዎች በመመዝገባቸው ሃምሳ ሚሊዮን እንደሆነ የሚገመተው የአገሪቱ ሕዝብ በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ በመግባቱ፣ የመንግሥታቸውን ውሳኔ ለመተግበር በንቃት እየተጣባበቁ እንደነበር የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ አመልክቷል።

በመንግሥትና በሕዝቡ ትብብር በተወሰዱ ቀላል ነገር ግን ወሳኝ የሆኑ የቫይረሱ ስርጭት መቆጣጠሪያ እርምጃዎች የተነሳ ኹለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የአዳዲስ ተጠቂዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እንዲያሽቆለቁል ተደርጓል። በዚህም መሰረት ተዓምራዊ በሚያስብል መልኩ አዳዲስ በቫይረሱ እንደተያዙ የሚመዘገቡ ታማሚዎች ቁጥር ከቀን ወደቀን ቁልቁል እየተንደረደረ ሲሆን፣ በየዕለቱም ከቀደመው ቀን በግማሽ የሚቀንስ ሰው ብቻ የሚያዝ እንደሆነ እየታየ መሆኑን መረጃዎቹ ያመለክታሉ።

በዚህ ወቅት በሌሎች አገራት ዘንድ የአዳዲስ ተጠቂ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ ባለበት፣ ካለፈው እሁድ ጀምሮ በደቡብ ኮሪያ እለታዊ አዳዲስ ተጠቂዎች የሚያዙ ሰዎች በየቀኑ እያሽቆለቆለ ነው። እንዲሁም አገራ የሞት ቁጥራቸው በየእለቱ ሲጨምር፣ ኮርያ ግን በአንጻሩ በአንድ ቀን የተመዘገበባት ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር በጣት የሚቆጠር ብቻ ነው።

እናም ይህ ስኬቷ እንደ ቻይና መንግሥት በዜጎቹ ላይ በተተገበረው በፀጥታ ኃይሎች በታገዘ የኃይል እርምጃ አለመሆኑንና ኢኮኖሚዋም በወረርሽኙ እምብዛም አለመጎዳቱን ታሳቢ በማድረግ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ብዙዎች የምዕራባውያን መንግሥታት ልምድ ለመቅሰም አማትረው የሚመለከቷት የታደለች አገር ሆናለች፤ ደቡብ ኮርያ።

በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ ሁሉ በዚህ አደገኛ ገዳይ ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ወደ ሚሊዮን እየገሰገሰ ባለበት ሁኔታ፣ ኮርያን ለዚህ ስኬት ያበቋት በፍጥነት የተከተለቻቸውና የፈፀመቻቸው ተግባራት እምብዛም ውድ ያልሆኑ ናቸው። አልፎም ለማንኛውም አገር ትግበራ ተመጣጣኝ ይመስላሉ፤ እንደ ኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ።

ተግባራቱ አራት ናቸው። እነርሱም ቫይረሱን መቅደም፣ ብዙ ምርመራ ማካሄድ፣ የተነካካን በማሰስ በፍጥነት መለየትና የዜጎች ወሳኝ ድጋፍ መቀበል ተብለው ተጠቅሰዋል።

ተሞክሮ አንድ፡ አደጋ ከመደቀኑ በፊት መቅደም

ልክ የመጀመሪያውን የቫይረሱ ተጠቂ ነው ያሉትን በምርመራ እንዳረጋገጡ፣ የአገሪቱ ባለሥልጣናት የሕክምና ቁሳቁስ አምራች ተቋማት ተወካዮችን በአስቸኳይ በመሰብሰብ ቫይረሱን በፍጥነት ለመቆጣጠር እንዲያስችል የመመርመሪያ መሣሪያዎችንና ቁሳቁሶችን በገፍ እንዲያመርቱ አቅጣጫ አስቀመጡ።

አምራቾቹም በተላለፈላቸው አቅጣጫ መሠረትም መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የቫይረሱ ስርጭት በኹለት አሃዝ ባልበለጠበት ሁኔታ በሺሕዎች የሚቆጠር የመመርመሪያ ቁሳቁስ ወደተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በፍጥነት እንዲጓጓዝ ተደርጎ ነበር። በአሁኑ ወቅት ምርቱ ሳይቋረጥ እየቀጠለ ሲሆን፣ የአገር ውስጥ አዳዲስ ተጠቂዎች ቁጥር እያሽቆለቆለ በመሆኑ የእነኚህ ቁሳቁሶች ፍላጎት እምብዛም ሆኗል። ቢሆንም በሌሎች አገራት ግን ስርጭቱ በከፍተኛ ሁኔታ በመዛመት ላይ ስለሚገኝ፣ በዓለም ገበያ ፍላጎት መጨመሩን ተከትሎ፣ የአገሪቱ መንግሥት ስጋቱን በእድል ለውጦታል። ከሌሎች አገሮች ጋር በመነጋገርም በከፍተኛ መጠን ለውጪ ገበያ ለማቅረብ እየተሰናዳ መሆኑን እየተገለፀ ነው።

የኮርያ ባለሥልጣናት በተለመደው አኳኋን ለማስተካከል መሞከር እዳው ከፍተኛ እንደሆነ በፍጥነት በማመናቸው እንደሌሎቹ አገራት ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ለብዙዎች ሞት ምክንያት መሆን ከመጀመሩ በፊት ገና በጠዋቱ ስርጭቱን ለመግታት ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው መነሳታቸው ለለዚህ ስኬት እንዳበቃቸው ያስረዳሉ። ጣሊያን ይህን ሁሉ መከራ እየተጋፈጠች ያለችው ወቅቱን የጠበቀ ውሳኔ በመንግሥትም በሕዝቧም ዘንድ መዘናጋት ተፈጥሮ በተገቢው አኳኋን ማድረግ ባለመቻሏ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ቫይረሱ በዚህ መዘናጋት ወቅት በመላ አገሪቱ በማይታመን ሁኔታ መሰራጨቱን መረጃዎች ጠቁመዋል።

ተሞክሮ ኹለት፡ የምርመራ በፍጥነት መጀመርና ድግግሞሽ

ደቡብ ኮሪያ ከሌላ ከማንኛውም አገር ጋር ሲነፃፀር በበሽታው የተያዙ ሰዎች አነፍንፎ ለማግኘት ያደረገችው እንቅስቃሴ ብዙ ሰው በቫይረሱ ላለመያዙ እንደ ምክንያት ተጠቅሷል። በአገሪቱ በቫይረሱ እንደተጠቁ የተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር ከአሜሪካ አንጻር በዐስር እጅ የሚያንስ ቢሆንም፣ የመረመረቻቸው ሰዎች ቁጥር ግን አሜሪካ ከመረመረችው አርባ እጅ እንደሚልቅ ተነግሮላታል።

በዚህም እስከ አሁን ከሦስት መቶ ሺሕዎች በላይ የመረመረች መሆኑ ተመዝግቧል። ይህም በበሽታው የተያዙ ከተገኙ በአስቸኳይ ምልክቱ ሳይታይባቸው ከሌሎች በመቀላቀላቸው ያስተላልፉት የነበረውን እድል በመዝጋት በለይቶ ማቆያ በማስቀመጥ እንዲያገግሙ ተፈላጊው የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ባለሥልጣናቷ ይጠቅሳሉ።

የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደገለፁት ‹‹የተጠናከረ ምርመራ በማካሄድ ታማሚዎችን በቀላሉ ብዙ ጉዳት ሳያደርሱ ለመለይት ያስችላል። በዚህም የአዳዲስ ተጠቂዎች ቁጥር በፍጥነት ለመቆጣጠር እድል ሲሰጥ፣ የሞቱብንም ሰዎች አነስተኛ እንዲሆኑ በማድረጉ ላይ አይነተኛ ሚና ተጫውቶልናል›› ሲሉ ገልፀውታል።

ይኸውም ታማሚዎች ተገቢውን የሕክምና ክትትልና እርዳታ እንዲያገኙ አስችሏል። የምርመራ ተግባሩ የተሳለጠ ለማድረግ ሆስፒታሎች እና ክሊኒኮች ከመጨናነቅ ለማዳን ባለሥልጣናት በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎችን ለመመርመር የሚያስችሉ በፍጥነት የተቋቋሙ ከ600 የሚልቁ የምርመራ ማእከላትን በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች በመክፈት ብዙ ሰዎች ቶሎ እንዲመረመሩ ማድረግ መቻሉንና ባልተደራጀ መልኩ በሚደረግ የጥድፊያ ምርመራ የተነሳ ሊፈጠር የሚችል የባለሙያዎችም በቫይረሱ የመያዝ እድልም እንዲሁ መቀንስ መቻሉን የኒው ዮርክ ታይምስ ዘገባ ያመለክታል።

በሰፊው የመመርመር ነገር ሲነሳ በጣሊያን ባለሥልጣናት መካከል ለልዩነታቸው መነሻ ሆኖ እንደነበር መጠቀሱ ይታወቃል። የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስተር በጅምላ ምርመራ እያደረጉ የአገሪቷ ሃብት እንዲባክን ምክንያት ሆነዋል እያሉ በከፋ ሁኔታ በቫይረሱ የተጠቁት የሰሜኖቹ ክልል የሚያስተዳድሩትን ባለሥልጣናትን ሲከሱ፣ የአካባቢው ሹሞች ግን በገፍ ምርመራ ማካሄዱ ስርጭቱን ለመቆጣጠር አንዱ ቁልፍ መሣሪያ እንደሆነ በመጥቀስ እንዲያውም በዚህ ተግባር የሕክምና ተቋማት እንዲተነፍሱ አስችሎናል በማለት ይከራከሩ ነበር።

እንግዲህ የጣሊያን ባለሥልጣናትን ያላግባባው በገፍ የመመርመር ውሳኔ የቫይረሱ መስፋፋትን ለመቆጣጠር ቁልፍ ተግባር እንደሆነና ኮርያም ለዓለም ያበረከተችው መልካም ተሞክሮ ሆኖ ተጠቅሶላታል።

ተሞክሮ ሦስት፡ የተነካካን በፍጥነት በማደን መለየት

እንደዘገባው ከሆነ አንድ ሰው በቫይረሱ መያዙን በምርመራ እንደተረጋገጠ በጤና ሠራተኞች አማካኝነት በፍጥነት የቀደመ ግንኙነቱን በማሰስ (contact tracing) ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች ሁሉ በአስቸኳይ ለመሰብሰብ የተጠናከረ ሥራ ይሠራል። በዚህም የጤና ሠራተኞቹ የታማሚውን የቀደመ ውሎ በማሰስ ብዙም ጉዳት ሳይደርስ ሁሉም ሊያዙ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱት ተጠርጣሪዎች ምልክቱ እስኪያሳዩና በመርመራም እስኪረጋገጥ የለይቶ ማቆያ እንዲገቡ በማድረግ ሥራቸውን በሚገባ ፍጥነት አከናውነዋል።

ሁሉም ኮርያውያን ከግለሰብ ነፃነታቸው መጠበቅ ይልቅ በዚህ አስደንጋጭ ስርጭት የተነሳ ሊፈጠር የሚችለው ዘርፈ ብዙ ቀውስ የተነሳ የሚከሰት ለትውልድ የሚተላለፍ አካባቢያዊና አገራዊ ዳፋ ከግምት ውስጥ አስገብተዋል። ለዚህ ትልቅ ድል መሳካትም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳበረከቱም እንዲሁ በሰፊው ተወስቶላቸዋል።

በዚህ ረገድ አገራችን ሥራው በሚገባ ለማከናወን መልካም የሆኑ በቀደመው ጊዜ የተተገበሩ አስቻይ ሁኔታዎች ያሏት መሆኑን የቫይረሱን አደጋ ለመከላከል አስተዋፃኦ እንዲያበረክቱ መጠቀም አለብን። ይኸውም በቅርቡ ምርጫ ለማካሄድ በሚደረገው ዝግጅት የምርጫ ቦርድ የለያቸው የምርጫ ጣቢያዎችና ማእከላት ላይ በፍጥነት መረጃ በአግባቡ ከዋናው ማእከል የሚለዋወጥ አስተባባሪ የሆነ ባለሙያ በመመደብ እንደዚሁም የመመርመሪያ ቁሳቁስ በማሰናዳት በአገሪቱ በሞላ በሚገኙ ቀበሌያት ከተሰማሩ የጤናና የግብርና ልማት ጣቢያ (ኤክስቴንሽን) ሠራተኞች ጋር በቅንጅትና በተጠናከረ ሁኔታ በሰፊው የመመርመር ሥራውና ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ አላቸው የሚባሉትን ግለሰቦች ለማደን መሥራት ይቻላል።

እንደሚታወቀው ይህን ቫይረስ ለመቆጣጠር መከላከል ዋናው ተግባር እንደመሆኑ ላለፉት ዐስርት ዓመታት ይነስም ይብዛ በመከላከል ላይ ትኩረት ያደረገው የጤና ስርዓታችን አጋዥ ይሆናል። ሌላው የጤናና የግብርና ልማት ጣቢያ ሠራተኞችም በእነኚህ ቀበሌያት በቋሚነት ኗሪ በመሆናቸው በምርመራ ከተለየ የቫይረሱ ተጠቂ ጋር ግንኙነት ነበራቸው ተብለው መረጃ የተሰባሰበባቸው ሰዎች ወደሌሎች ሳያስተላልፉ ከአካባቢው ሚሊሻ ጋር በቅንጅት በመሥራት በቀላሉ ለመሰብሰብ የሚያስችል መሆኑን ነው።

ተሞክሮ አራት፡ የሕዝብ እገዛና ተባባሪነት

በሌሎች አገራት እንደታየው ቁጥራቸው በጣም ከፍተኛ የሆነ ሰዎችን ለመመርመር የጤና ሠራተኞችና የሠለጠኑ የሰውነት ሙቀት አንባቢዎች በብዛት ማሟላት ስለሚከብድ፣ ከየአገራቱ በጎ ፈቃድ ሰጪዎች ለዚህ አገልግሎት እየተመለመሉ እንደሆነ ይሰማል። በዚህም መሰረት ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ በፈቃደኝነት አገልግሎት ለመስጠት የሚሰለፉ ሰዎችን ማሳተፍ ስርጭቱን በሚገባ ለመቆጣጠር ሌላው ወሳኝ ጉዳይ ነው።

ደቡብ ኮርያም ይህንን በሚገባ አስተባብራ ለውጤት በመቀየሯ ልምዷ ለሌሎች አገራት ተሞክሮ እንዲሆን በመልካም ተግባርነት ተነስቷል። በዚህ ረገድ አገራችንም የብዙ ወጣት ባለቤት እንደመሆኗ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎችን ጊዜ ሳያልፍ ከላይ ለታይታ ብቻ መሆኑ ቀርቶ በሁሉም የአስተዳደር እርከኖች እስከ ቀበሌ ድረስ ወርዶ ዝግጁ እንዲሆኑ ከኹለት ቀናት ባልበለጠ ሁኔታ መተግበር ያሻል።

የኮርያ ባለሥልጣናት እንደሚገልፁት ቫይረሱን ለመቆጣጠር በየጊዜው ለዜጎች ወጥነት ያለው መረጃ ይቀርብ እንደነበረና በአገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ሰዎችም የተላለፈላቸውን የማስጠንቀቂያ መልዕክቶች ለመተግበር እንዲተባበሩ በሰፊው መሠራቱን ተናግረዋል። በቴሌቪሽን ፕሮግራሞች፣ በትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ማእከላት እንዲሁም በእጅ ስልኮች ሳይቀር ማድረግ የሚገባቸው የጥንቃቄ ድርጊቶች ግልፅና አጭር በሆኑ መልዕክቶች፣ አካላዊ መራራቅን የሚያስታውሱ ምልክቶችና የየቀኑ የቫይረሱ የስርጭትና የሟች አሃዞችን ይላክ እንደነበረም ይወሳል። ይህም ሕዝቡ የተደቀነውን አደጋ አሳንሶ እንዳያይና ከጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ እያንዳንዱ እጣ ፈንታው ሞት እንደሆነ ለማሳወቅ ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለብን ዝንጉነትና እርምት የሚፈልጉ ጉዳዮች መኖራቸውን ለመጥቀስ እፈልጋለሁ። እንደሚታወቀው በሁሉም ዘርፍ የመረጃ ልውውጥ እጅግ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ይታወቃል።

ሌላው በመንግሥት ደረጃ የአዳዲስ ተጠቂዎችና ሟቾች ቁጥር በፍጥነት ለሕዝቡ ያለማድረስ አሻጥር የሚመስል ነገር ነው። ይህ ቫይረስ ዓለማቀፋዊ እንጂ አገራችን በተከተለችው ፖሊሲ የተነሳ የተስፋፋ አይደለምና ሳትሸማቀቁ ትክክለኛው መረጃ ለጥንቃቄ ይረዳልና በፍጥነት ለሕዝቡ እንድታሳውቁት ከኮርያ ተሞክሮ መማር አለብን።

ሁሉንም ነገር ከሕዝብ የመደበቅ አመል አሁን አይሠራም። ሕዝቡ አውቆ እንዲፈራና እንዲጠነቀቅ በሰዓታት ውስጥ ለሁሉም እንዲደርስ መረጃው መለቀቅ አለበት። የሚተላለፈው መልዕክትም የጋራ ጠላት እንደተደቀነብንና ይህንንም ለማሸነፍ የግድ በጋራ መነሳት እንዳለብን የሚያሳስቡ ሆነው መታየት ነው ያለባቸው።

በዚህ ረገድ ኮርያውያን ለመንግሥታቸውና ለአገራቸው ታማኝነታቸው በተግባር ያሳዩበት እንደሆነም ተወስዷል። አንድ የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ባለሥልጣንም ‹‹ይህ የሕዝብ አመኔታ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የዜግነት ግንዛቤ እና የበጎ ፈቃድ ትብብር ውጤት አስገኝቷል›› ሲሉ ገልፀውታል።

እዚህ ላይ ከስድስት ዓመታት በፊት በአንድ ስብሰባ ላይ ተገኝቼ የሰማሁት ትዝ አለኝ። አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን ኢኮኖሚያችን ለማሳደግ ኮርያ የተከተለችው መንገድ ላይ ዐይናችን ሳንነቅል እየተከተልን እንገኛለን ይላል። ይህን የሰማና በስብሰባው ተሳታፊ የነበረ ግለሰብ እጁን ያወጣና፤

‹‹የኮርያን ሞዴል ለመከተል መወሰናችሁ እጅግ አደንቃለሁ። ልማታቸው እንዲፋጠንም ኮርያውያን ሁሉ ከመንግሥታቸው ጎን ተሰልፈው አገራቸውን ለዚህ ክብር አብቅተዋል። ነገር ግን የእኔ ጥያቄ የትኛውን ሕዝብ ይዘን ነው እንደኮርያ ለማደግ እየተሰናዳን ያለነው? የእኛ ሕዝብኮ በውጭ ብድር በተገኘ ገንዘብ የመንገድ መሰረተ ልማት ለማከናወን ቅያስ መውጣቱን ተከትሎ፣ ካሳ ለማግኘት ሲባል ከአካባቢ ባለሥልጣናት ጋር በመሞዳመድ ቤቱን አፍርሶና ወደተቀየሰው መንገድ አስጠግቶ አዲስ ጎጆ ቀልሶ የመሰረተ ልማት ዝርጋታው ከታቀደለት ወጪ በላይ እንዲወጣ የሚያደርግ ነው። ይህን ሕዝብ ይዘን እንዴት እንደኮርያ እናድጋለን ትሉኛላችሁ? የኮርያ ሕዝብ እኮ ሥልጡን ነው።›› አላቸው።

ወገን! ይህ አስቸጋሪ ወቅት ለአገራችን የወገብ ላይ ቅማል የምንሆንበት አይደለም። ይልቁንም እንደ ኮርያውያን ለአገራችን የሚከፈል መስዋዕትነት ለመክፈል የምንዘጋጅበት ጊዜ መሆን አለበት። የመኖርና የመጥፋት አማራጮች ከፊት ለፊታችን ተደቅነው ይገኛሉ።

ኒውዮርክ ታይምስ በዚህ ዙሪያ ባዘጋጀው መጣጥፉ፤ እውን የኮሪያን መልካም ተሞክሮ ማስፋት ይችላልን? ሲል ጥያቄ ያነሳል። ለሁሉም አገራት የደቡብ ኮሪያ ስኬቶች፣ ስልቶቹና የመቆጣጠሪያ መሣሪያዎች ውስብስብ ካለመሆናቸውም በላይ ከወጪም አኳያ ውድ አይደሉም ሲል ይጠቁማል።

ይኸውም አገሪቱ ከተጠቀመችባቸው ቁሳቁሶች (ለምሳሌ ጓንትና የፊት መሸፈኛ) በቀላሉና በርካሽ የተመረቱ ናቸው። በመሆኑም አገራት ከደቡብ ኮርያ ሊማሯዋቸው የሚገቡ ሦስት መሰረታዊ ነገሮችን አፅንኦት ሰጥቶ ይዘረዝራልል የኒው ዮርክ ታይምስ ዘገባ፤

አንደኛው የፖለቲካ ቁርጥኝነት ነው። ብዙ መንግሥታት ለቫይረሱ ስርጭት የተመቻቸ እድል የፈጠረለት ቸልተኝነትና መዘናጋትን አሳይተዋል። በዚህም የብዙ ዜጎቻቸውን ሕይወት እንዲያጡና እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስም በከፍተኛ ቁጥር የሚጨምር አዳዲስ የቫይረሱ ተሸካሚ ሰዎች እንዲበዙ ምክንያት ሆኗል። በዚህም ውሳኔያቸውን በከፍተኛ ፍጥነት ወደመሬት ባለማውረዳቸውና ወጥ የሆነ መረጃ ለሕዝባቸው ባለመልቀቃቸው አሁን ላይ ሁሉ ነገር የሩጫ ሆኗል፤ ብዙም ዋጋ እየከፈሉ ይገኛሉ።

ኹለተኛው የሕዝብ ትብብርና ፈቃደኝነት ነው። በደቡብ ኮሪያ ከሌሎች ብዙ አገሮች በተለይም የምዕራቡ ዓለም ዴሞክራሲ ከሚጨነቅለት ጋር ሲነፃፀር ሕዝቡ በራስ ተነሳሽነት ከግለሰብ ነጻነት ማቀንቀን ይልቅ ማኅበራዊ እምነቱ ከፍተኛ እንደሆነ ተወስቷል። በዚህም ሥነ ስርዓታቸው ከመጣው አደጋ ከሁሉም በመቅደም ዜጎች እራሳቸውን በመቀጠልም አገራቸውን መታደጋቸውን ዓለም መስክሮላቸዋል።

ሌላው ትልቁና ዋናው ጉዳይ ጊዜን መጠቀም ነው። ጊዜን በአግባቡና በፍጥነት አለመጠቀም የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የተከፈተ እድል ሁሉ እንደሚያስመልጥ ከጣሊያን ታይቷል። አንዴ ወረርሽኙ ከእጅ ካመለጠና ወደ ቀውስ ከተሸጋገረ፣ በኋላ የሚወሰድ እርምጃ ‹የዘገየ› ሊሆን ይችላል። እንጂ የሚወሰዱ መፍትሄዎች የሚፈለጉትን ውጤት አያስገኙም ሲሉ የደቡብ ኮርያ ባለሥልጣናት ያሳስባሉ።

የኮርያን ዱካ መከተል

ከኹለት ዐስርት ዓመታት በላይ አገራችን ግብርና መር የኢንደስትሪ ልማት ስትራቴጂ ስትከተል እንደነበር ደጋግሞ ከሚነገረው እንሰማ ነበር። ይህ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከሰሜን ምሥራቅ እስያ አገራት በዋናነትም ከኮርያ የዕድገት ምሳሌ የተቀዳ እንደነበር እንዲሁ ይወሳ ነበር። አሁን ባላውቅም በቀድሞው የኢሕአዴግ መንግሥት ጊዜ በየዓመቱ መጀመሪያ ወራት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ መምህራን መደበኛ የትምህርት መርሃ-ግብሩ ከመጀመሩ በፊት ለቀናት የሚቆይ ስብሰባ በማሳናዳት አገሪቷ በምትከተለው በተለያዩ የፖሊሲ ጉዳዮች በሚመለከት በከፍተኛ ባለሥልጣናት ለመምህራኑ ማብራሪያ መስጠት እየተለመደ እንደነበር በዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ዘንድ በሚገባ ይታወቃል።

በዚህም መሰረት እ.ኤ.አ. በ2014 ታዳሚ በነበርኩበት ስብሰባ ላይ በወቅቱ ገለፃ ሲያደርጉ የነበሩት አንድ ባለሥልጣን ‹‹ኮሪያዎች የረገጡትን ድንጋይ እየረገጥን በመጓዝ ላይ እንገኛለን›› የሚል ሐሳብ ይደጋግሙ እንደነበር አስታውሳለሁ።

እንግዲህ እንደለመድነው አሁንም ከኮርያ ተሞክሮ በሚገባ በመቀመር መንግሥት ተገቢ ሥራዎችን ብቻ በፍጥነት ቢያከናውን። እንዲሁ ከሞት ጋር መጋፈጣችን ለማይቀረው ግብግብ መፍትሔ የሚሆኑ ተግባራት ላይ ብቻ ቢያተኩር ማለትን እወዳለሁ። ቫይረሱ እኛ የድህነት ጠርዝ ላይ ላለነው ይቅርና በዘመኑ ቴክኖሎጂ ማማ ላይ የደረሱትን አገራት በመዘናጋታቸው አይቀጡ ቅጣት እየተቀጣ ይገኛሉ።

ስለዚህ የድርጊት መርሃግብር በሚገባ በመንደፍ ማከናወን በሚገባን ላይ ብቻ ትኩረት ብናደርግ ብዙ ነገሮችን ማስቀረት እንችላለን። ‹‹መድኃኒት ላመጣላችሁ ነው›› ሕዝባችን ተዘናግቶ አደጋው ቸል እንዲለው ስለሚያደርግ፣ ለሚፈጠርም ቀውስ ውሎ ሲያድር ከተጠያቂነትም አያድነንም። ያደጉት አገራትን ጨምሮ አንዳቸውም በዚህ ወቅት ስለመድኃኒትና ሕክምና ሲያወሩ አይስተዋልም።

ዜጎቻቸውን አሁንም ድረስ እየወተወቱ ያሉት ቤታቸው አርፈው እንዲቀመጡ ብቻና ብቻ ነው። ይህንንም ለማስፈፀም አሁን የፀጥታ ኃይላቸው እስከማንቀሳቀስም ደርሰዋል። እንግዲህ እኛ በተዓምር ካልሆነ በቀር በእንዲህ አይነት የመንግሥት አያያዝና ቸልተኝነት እንዴት እንደምንተርፍ ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው። እናም ለመሪዎቻችን የኮርያውያን ባለሥልጣናትን ልብ ይስጥልን ማለትን እወዳለሁ።

በመሆኑም ከኮርያ ስኬት አፈፃፀም በመነሳት መንግሥት የመሪነት ሚናውን ተጠቅሞ ኹለት ነገሮችን ማስፈፀም አለበት። ይኸውም አንደኛው አስፈላጊውን ቁሳቁስ ማሰናዳትና በፍጥነት ሳይረፍድብን የኮርያን ተግባራት መከወን ሲሆን ኹለተኛው ሁሉንም ዜጋ በዚህ በጋራ ጠላት ዙሪያ አንዲነሳ ማስተባበርና ማሰለፍ ነው።

በዚህም አስፈላጊ የሆኑት ቁሳቁሶች በፍጥነትና በሰፊው እንዲመረቱ ማድረግ ወይም በገፍ እየተመረተ ከሚገኝበት ኮርያ እንደሌሎቹ መንግሥታት በማስመጣት ለክልሎችና ምርመራው ለሚካሄድባቸው ማእከላት እንዲከፋፈሉ ማድረግ አለበት።

የታሪክ ምሩቅ ባለመሆኔ ዝርዝሩን ለዘርፉ ምሁራኖች እተዋለሁ። ነገር ግን በአጭሩ ሲገለፅ ኮርያውያን በጨለመባቸው ጊዜ ‘ጠላትሽ ጠላቴ ነው’ ብላ ሠራዊቶቿን አሰልፋ ከጎኗ የሆነችው የአገራችን ኢትዮጵያ ውለታ አለባት። እናም ያንን በማሳሰብ ብዙ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቀውን ከተትረፈረፈው ቁሳቁሶቿ ሲሆን ሲሆን በእርዳታና ስጦታ ካልሆነ እንደ ነዳጅ ግዢያችን በቀጣይ በሚከፈል የዱቤ ግዢ የምናገኝበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል። መንግሥት ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመጠቀም ጊዜ ሳይወስድ በፍጥነት መንቀሳቀስ አለበት።

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በተራችን ከጎናችን ካልሆነች በየዓመቱ የኮርያ ዘማቾችን ለማሰብ የሚደረገው ዓመታዊ ክብረ በዓል ጥቅሙ ፋይዳ-ቢስ ነው። አያቶቻችን እኮ ያን ያክል ርቀት ተጉዘው ሕይወታቸውን ሳይቀር ሳይሳሱ እንደሰጡም ጭምር መዘንጋት የለበትም።

የአገሪቱን ሕዝብ በሞላ መመርመር አይቻልምና የጤና ተቋማቶቻችን በአዳዲስ ተጠቂዎች ተጥለቅልቀው መፈናፈኛ እንዳያጡ ብዙኀኑ ከቤቱ ንቅንቅ እንዳይልም እንዲሁ ያዝ ለቀቅ በማድረግ ሳይሆን በተጠናከረ መልኩ መከልከል አለበት። በዚህ ወቅት የግለሰብ ነፃነት የምናከብር ነን ባይ አገራትም ጭምር እየተገበሩት ይገኛል። ይህንን የመንግሥት መመሪያ ተላልፎ በመንገዶችና በሰፈሮች የሚዟዟር የፀጥታ አካላትን በመጠቀም ወዲያውኑ ለሌላውም አስተማሪ የሆነ እርምጃ ለመውሰድ አሁኑኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመላ አገሪቱ መታወጅ አለበት።

ሌላው በዚህ ወቅት በፖለቲካ ልዩነት የተነሳ ጎል ለማስቆጠር የሚባል እሳቤ ነገር በፍፁም ስህተት እንደሆነ በማመን ሁሉም ከመንግሥት ጎን ሊረባረብ ይገባል። ምክንያቱም ብሔርንና ሃይማኖትን ያልለየ የሞት ፈተና ከፊት ለፊት ተደቅኖብናል። የጋራ ጠላት የሆነ ሞት እኛኑ ወይም የምንወደውን ሊነጥቀን የሁላችንም ደጃፍ ላይ ቆሞ እየተመለከተን ይገኛል። በመሆኑም ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች መንግሥት የሚያወጣውን ማንኛውንም ዓይነት መመሪያ ይከተለናል ብላችሁ በምታስቡት የኅብረተሰብ ክፍል ላይ በፍጥነትና በጥራት እንዲከናወን እንድታደርጉ በፈጣሪ ሥም ትለመናላችሁ።

ከሁሉም በላይ የወቅቱ የአገሪቱ መንግሥት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ትልቁን የመሪነት ሚና በመጫወት አገሪቷን እንዲታደግ ለዚህ ፈተና ታጭቷል። እኛም ዜጎች ከመንግሥት የሚተላለፉትን ወጥ የሆኑ የጥንቃቄ መረጃዎችን በፍጥነት እራሳችንን፣ ቤተሰባችንንና አገራችንን ለመታደግ ስንል በተጠንቀቅ ቆመን ይህን የመከራ ጊዜ ማለፍ አለብን። በዋናነት እንድናደርግ የምንታዘዘው ነገር ቢሆን፣ አሁን እያደረግን ካለው በበለጠ ከቤት ውጭ ከመዟዟር ተቆጥበን ቤታችን ውስጥ አርፈን መቀመጥ ብቻና ብቻ ነው።

መንግሥት የሚጠበቅበትን እስኪሠራ ድረስ እኛ እንደአገር ተረካቢ ወጣት ዜጋዎች ይህ እጅግም ያልተወሳሰበውንና በቀላሉን ለመተግበር የሚያስችለውን መንግሥታችንና አገራችንን ለማገዝ በዚህም የቁርጥ ቀን ልጆች መሆናችንን ዳግም ለማስመስከር ይህ የዘመኑ የጋራ ጠላታችን የሆነውን ለማሳፈር የሚናችንን እንወጣ እላለሁ። ምንድነው የምናደርገው ጥቅሙስ ምኑ ላይ ነው? የሚል ሐሳብ ሊነሳ ይችላል።

እንደተዓምር እየታየ ያለው ይህንን ወረርሽኝ ለማስቆም ብቸኛው መንገድ ባለሙያዎች የመከሩን ቫይረሱ የረሃብ ጠኔ እንዲመታው ምግቡን እንንፈገው ነው መልዕክቱ። አዎ! አሁን ንፉግ ሆነን ጠላታችንን ምግቡን ከልክለን እናስርበው። ምግቡ እኛ ነን። ስለዚህም ቁርስ፣ ምሳና እራት አድርጎ እንዳይበላን የረሃብ ጠኔ እንዲመታው እናድርግ።

በዓለም ዙሪያ ያሉ አገራት ለዜጎቻቸው እያስተላለፉ ያሉትም ማስጠንቀቂያ ይህን ለቫይረሱ ሕይወት መቀጠል እያደረግንለት ያለውን ድጋፍ በመግታት ድጋፉ ወደራሳችንና አገራችን እንዲሆን እናድርገው ነው። መቼም ሰው ለጠላቱ ድጋፍ አይሰጥም። ያውም የማይቆጠር ከንቱ መስዋዕትነት።

ከማንም በላይ እራሱን የማይወድ የለምና ለዚህ እርኩስ ቫይረስ የየሰዓት ምግቡን በመከልከል ለመቅጣት ጊዜ ሳናጣፋ የተባልነውን መተግበር አለብን።

ከምኖርበት አገር ከአገሪቱ ዜጎች ቀድሜ ውሎና አዳሬ ቤት ውስጥ ከሆነ ሶስት ሳምንታት ሆነዋል። በዚህም ከማነበው ለጥንቃቄ እንዲሆናችሁ እንደዚህ ዓይነቱን ጽሑፍ እንዳዘጋጅ ቫይረሱ እስከ አሁን ለእኔም እንደኮርያ ውለታ ውሎልኛል። ስለዚህም ሥራችሁን ከቤት ሆናችሁ ሥሩ ስል ካየሁት እመክራለሁ። ይህም ቀላሉ መንገድ ቫይረሱ ወደ እኛ እንዳይመጣ ለመገደብ እየተባሉ ያሉት አካላዊ መራራቅ (Physical distancing) እና ከመጠለያ ያለመውጣት የተላለፈው መመሪያ ለራሳችን ስንል በመተግበር ብቻ ነው የሚጠበቅብን።

እንግዲህ ሁሉም እንደታዘዘው ቫይረሱ እንዳይተላለፍ የሚረዱ የመከላከያ እርምጃዎች በመገንዘበ በፍጥነት ተግባራዊ ካደረገ የቫይረሱ ስርጭት ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ወረርሽኝ እንዳይከሰት በማድረግ አገራችንና ሕዝባችን ልክ እንደ ኮርያ መታደግ እንችላለን። ግቡም ከሌሎች ከበለፀጉት አገራት ጋር ሲነፃፀር ደካማ ከሆነው የጤና ስርዓታችን አቅም በላይ እንዳይሆንና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ወረርሽኝ እንዳይከሰት በመከላከል ሊሞቱ የሚችሉ ዜጎቻችን ቁጥሩ እጅግ በጣም ትንሽ እንዲሆን ለማድረግ ማገዝ ነው።

በዚህ ብቻ ነው የአዳዲስ ተጠቂ ቁጥር ታማሚዎችን በመቀነስ ወደላይ በየዕለቱ የሚምዘገዘግ ቁጥር ከቀደሙት ቀናት ጋር ሲነፃፀር ዘንበል እንዲል ማድረግ የምንችለው። ለዚህ ምሳሌ ከአውሮፓ ጀርመን እየተከተለች ያለውን መንገድ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በሺሕዎች ቢያዙባትም እንደጣሊያን ለብዙዎች ሞት ምክንያት ሲሆን ግን እምብዛም አይታይም። በቅርቡም ሁሉም አገር እንዲሁ የጀርመንን ተሞክሮ ለመመልከት የሚያማትርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።

ጠላታችን ልናሸንፈው የምንችለው የሚፈልገውን በመከልከል ወይም እንዲያጣው በማድረግ መሆኑን መገንዘብ አለብን ነው። ምርጫችን በሕይወት መቆየት ከሆነ የታዘዝነውን ምን የከበደ ቢሆን እንኳን ከመፈፀም ለሰከንድም መዘናጋት የለብንም። ‹‹እንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንደሚሉት የጤና ስርዓታችን በጣም ደካማ በሆነባት አገራችን፣ መንግሥት ሥራውን እስኪሠራ እኛም እንደዜጋ የሚጠበቅብንን አገርን ከጠላት የመከላከል ኃላፊነት ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት የለብንም። የትውልድና የአገር አደራ ለማስቀጠል ወቅቱ የሚፈልገውን ለመጋፈጥ በአርበኝነት መንፈስ ዝግጁ መሆን አለብን።

ምንም እንኳን በኢኮኖሚ አቅማችን ወደኋላ የቀረን ቢሆንም አያቶቻችን የማይቻለውን ለመፋለም በጦር አውድማ ለመገኘት ወደ አደባባይ ወጥተው እስከዛሬው በመላው ዓለም ለሚገኙ ጥቁሮች ሳይቀር ወገግ ብሎ የሚያበራውን በዘመናችንም ላሰበው ትንግርት የሆነውን ታላቅ ድል አስመዝግበው አንገታችን ቀና ብለን እንድንጓዝ አስችለውናል። የአሁኑ ውግያ ግን በአደባባይ ላይ በፉከራ የሚሆን አይደለም። ያሁኑ አርበኝነት በመሸሸግና በመደበቅ የሚመዘገብ ድል ነው።

‹‹ዘጠኝ ሞት ከደጅ ቆሟል ሲሉት አንዱን ግባ በለው›› አይነት ቀረርቶ አሁን አይሠራም። ወገኖቼ የአሁኑ ጀግንነት የሚለካው በመሸሽና በመሸሸግ ብቻ ነው። የአሁኑ ጥበብ ፍርሃት ነው። አዎ ፈርተን መሸሸግ አለብን። ጠላታችን የመጣው በጦር ሜዳ ባለን ጥንካሬ ሊገጥመን አይደለምና እጅግ ከባድ ጥንቃቄ ለመውሰድ እንትጋ። አያድርገውና ከጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ በሚፈጠር የጤና ቀውስ የተነሳ ስርዓት አልበኝነት ቢነግስ ባልሰከነው የፖለቲካ ሁኔታችን ላይ ተደምሮ አገራችን ለበለጠ ፈተና ስለምትዳረግ አሰፍስፈው ለመመልከት ለሚጠብቁን ጠላቶቿ ሰርግና ምላሽ እንዳይሆንም በጥበብ ማሰብ አለብን።

እርግጥ ቤት መቀመጥ እጅጉኑም ብርቅ የሚሆንባቸው ኑሮአቸውም ከእጅ ወደ አፍ የሆኑ ዜጎቻችን ቁጥር በጣም ብዙ እንደሚሆን አይጠፋኝም። በአፍሪካ አብዛኛው ሰው የሚንቀሳቀሰው ከመደበኛ ውጭ በሆነው የኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ እንደሆነ እሙን ነው። ረሃብም ጊዜ አይሰጥም። የራበው ግንባሩን ለጥይት ለመስጠት አያመነታም። ረሃብም ክፉ በሽታ ነው። ስለዚህ ፈተናው የጋራ መሆኑን በማመን ያለው ለሌለው ማካፈል አለበት። ምክንያቱም ወይ አብረን እንድናለን አልያም ተያይዘን መጥፋት ነው።

አንዳንዴ ሳስበው በመካከላችን ዘርተን ባሳደግነው የልዩነት አጥር እንደማይታደገን በማሳየት ፈጣሪ ሊያስተምረን የፈለገም ይመስለኛል። ስለዚህ ከሌላው ጊዜ በላቀ ሁኔታ መደጋገፍ አለብን። እዚህ ላይ ከዚህ ጋር በተያያዘ ግብፅ አገር የሆነውን ካነበብኩት ላካፍላችሁ። የቤት ሠራተኛቸው በሕዝብ ትራንስፖርት የምትገለገል በመሆኑ ልትጠቃ ትችላለችና ታስተላልፍብናለች ብለው የሰጉ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሚከፍሏትን ወርሃዊ ክፍያ ሳያቋርጡባት ነገር ግን ወደእነሱ እንዳትመጣባቸው አድርገዋል።

ይህ ትልቅ ጥበብ ነው። ቁሚ ተከፋዎች የሆንን ሰዎች ቤት ስንውል ክፍያችን አይቋረጥምና ከእኛ የሚቀበሉት ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ በሆኑት ላይ እንዲሁ ባለማቋረጥ ልንደግፋቸው ይገባል። በተለያዩ አምራች ተቋማት ተሰማርተውም የሚገኙ የግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሽ ኢንቨስተሮች በገቢ መቀነስ የተነሳ የቀጠሯቸውን ሠራተኞቻቸውን ቢበትኑ መልሶ ለመቅጠር የሚያስከትልባቸው  ወጪ ከፍተኛ መሆኑን አስልተው ሠራተኞቻቸው ከመበተን ቢታቀቡ ለራሳቸውም መልካም ነው።

በመግባባት መንፈስ የተወሰነ ተቀንሶም ቢሆን ለሠራተኞቹ ወርሃዊ ክፍያቸው እንዲያገኙ ማድረጉ ላይ መንግሥትም የተወሰነ ድጎማ በተለይ ብዙ ለቀጠሩት ለጨርቃ ጨርቅና አበባ አምራቾች በማቅረብ ይህንን አደጋ ለማለፍ መከፈል ያለበት ዋጋ ሁሉም ለመክፈል መዘጋጀት አለበት።

ለማጠቃለል እጣ ፈንታችን የጣሊያን ወይስ የኮርያ እንደሆነ የምንወስነው ራሳችን ብቻ እንደሆንን በሚገባ ማመን አለብን። የበዛ ጥንቃቄ ማድረግ እንጂ የድህነት መጠን እምብዛም ለከፋ ተጋላጭነት እንደማይዳርገን በማመን ጥንቃቄያችን ሁሌ ሊለየን አይገባም። የምንከፈለው መስዋዕትነት ከአያቶቻችን ከከፈሉት እጅጉኑ የሚያንስ ነው።

ይህን አስቸጋሪ ወቅት እስኪያልፍ ያለንን በከፍተኛ ቁጠባ እየተጠቀምን ቤት ውስጥ ተሸሽገን መቀመጥ ነው። እንቅስቃሴ ባለማድረግ ከሚመጣ ሌላ የጤና እክሎች ለመታደግም ግቢያችንን ሳንለቅ ከሌሎች ሰዎችም ሳንገናኝ ቀለል ያሉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ነው። ላለፉት ሦስት ሳምንታትም ለማደሪያ ብቻ እገለገልበት የነበረው ሦስት በሦስት የሆነው ክፍሌ ስፖርት ማዘውተሪያና ውሎ ማደሪያዬ ሆኖ ዘርፈ ብዙ ሚና እየተጫወተልኝ እንደሆነ እነግራችኋለሁ። በታዘዝነው መሰረት እጃችን በሚገባ በሳሙና ማፅዳትን ሳንዘነጋ።

ሌላው ይህ አደጋ አንዳችን ከውነን ሌላው ችላ ብሎት የምናመልጠው አይነት አይደለም። ሁላችንም መንግሥት በዘረጋው አስፓልት ላይ ያለማንም ከልካይነት እንደምንጓዘው ሁሉ አሁንም መንግሥት ለሚያወጣው መመሪያም ለመፈፀም ወደንም ይሁን ተገደን ዝግጁ የምንሆንበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው። ይህ ትውልድና አገር ለማስቀጠል የሚከፈል ትንሹ መስዋዕትነትም ነው። ይህን ካደረግን ምን ድሃ ብንሆን እንደልማዳቸው በአፍሪካ ምድር ተዓምር የሠሩ ጥቁር ሕዝቦች እየተባልን በታሪክ ዳግም እንታወሳለን።

ከመጣው መዓት ፈጣሪ አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን፣ ዓለምንም እንዲጠብቅልን በርትተን መፀለይ አለብን።

araya.gedam@gmail.com

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here