የኮሮና ወረርሽኝ እና የሥነ ልቦና ጫናው

0
1016

ረዳት ፕሮፌሰር ማጂ ኃይለማርያም በሥነ አዕምሮ ጤና ኤፒዲሞሎጂ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን የማስተርስ ዲግሪያቸውንም በሶሻል ወርክ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተቀብለዋል።

ማጂ ኃይለማርያም በአሁኑ ወቅት በአሜሪካን አገር ሚችጋን ግዛት በሚችጋን ስቴት ዩኒቨርስቲ ውስጥ የፖስት ዶክቶራል ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን፣ በዛው ዩኒቨርስቲ ውስጥ በከፍተኛ አጥኚነት እና ተመራማሪነት እያገለገሉ ይገኛሉ።

ማጂ ኃይላመሪያም (ረ/ፕ) በኢትዮጵያ በገጠራማው ክፍል በአዕምሮ ጤና ረገድ ሰፋ ያለ ምርምር ያካሔዱ እና ጠለቅ ብለው ከተሠሩ ጥናቶቻቸው የተነሳ ጠንካራ ግኝቶችንም ይፋ ማድረግ ችለዋል።

በሦስተኛ ዲግሪያቸው መመረቂያ ጽሑፋቸውን በሚያጠናቅሩበት ወቅትም የአዕምሮ ሕክምና ለግፉአን እንዴት ይዳረሳል በሚል ጠለቅ ያለ ምርመራ አድርገዋል።
የአዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ ከማጂ ኃይለማሪያም (ረ/ፕ) ጋር አሁን የተከሰተው የኮሮና ኮቪድ 19 ቫይረስ በሥነ ልቦና ላይ ስላለው ተጽእኖና ተያያዥ ጉዳዮች በማንሳት ተከታዩን ቆይታ አድርጓል።

ቤት ውስጥ ብቻ በመዋልና ከሰዎች ጋር በአካል መራራቅ፣ በዚህ የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት የሚመከከር ተግባር ሆኗል። በአንጻሩ ከቤት ውጪ በሥራና በእንቅስቃሴ ተጠምዶ መዋልን የለመደዱ ሰዎች፣ ይህን ጊዜ እንዴት ቢያሳልፉት ይመከራል?
ማኅበራዊ ፈቀቅታ ትልቅ ለውጥ ነው። ከተለመደው ወጣ ያለና ያልተጠበቀ ነገር ድንገት ሲከሰት ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ የተለያየ የሥነልቦና ምላሾች ይኖራሉ። በዚህም ፍርሀትና ጭንቀት፣ ውጥረት እንዲሁም ንዴትና ግራ መጋባት ይኖራል። በጣም የተለያዩ ዓይነት ግብረ መልሶች ይኖራሉ። እነዚህ ስሜቶች እውነት ነው። ለምን እንዲህ ተሰማኝ መባል የለበትም። ትክክለኛ የሆነ ስሜት ነው። አሁን በዓለማችን ባለፉት 100 ዓመታት ያልተከሰተ ዓይነት ችግር ውስጥ ነው እያለፍን ያለነው።
ይህ ነገር በግለሰብም ሆነ በማኅበረሰብ ደረጃ ብዙ ነገር ያቃውሳል። ቤት ከመዋል አንጻር ያለው የሥነ ልቦና ችግር ስናነሳ፣ ቤት መዋል ብቻ ሳይሆን መውጣት አለመቻልም ጭምር ነው። በፊት ከሰው ጋር ለመገናኘት ባይሆን እንኳ በፈለገን ሰዓት የምወጣበትን፣ ለምሳሌ ሱቅ ሄዶ መምጣት ዓይነት ነገሮች ጭምር ናቸው የቀሩት። ከተማውም ጭር ያለ ነው፤ ዝር የሚል ሰው አይታይም።

ብዙ መገለል አለው። በዚህ ሁሉ ነገር ውስጥ መልካም ነው ብዬ የማስበው ነገር፣ በአካል ነው እንጂ የምንራረቀው በሌሎች ማኅበራዊ ገዱይ ላይ አብረን መቆም እንችላለን። መደዋወልና መጠያየቅ እንችላለን። ከከተማ ውጪ የሚኖረው ጋር ኔትወርክ አለ፣ ሞባይልም እንደዛው።

ቤት ውስጥ መዋል አሁን አዲስ ነገር መልመድ ነው። ያ ማለት ቤት ስለምውል እንደፈለግሁ እተኛለሁ እንዳሻኝ እነሳለሁ ወይም ደስ እንዳለኝ እበላለሁ፣ እጠጣለሁ ማለት አይደለም። ቢቻል የተለመደ የሥራ ሰዓትን በጠበቀ መልኩ ቤት ውስጥ ያሉ ሥራዎችን በመሸንሸን መንቀሳቀስ፣ ልክ ቢሮ እንደሚሄድ ሰው በጠዋት ተነስቶ መዘጋጀት፣ ከአልጋና ከመኝታ ልብስ በጠዋት መውጣት፣ ልብስ መቀየር። አመጋገብን ማስተካከል፣ ራስን መጠበቅ ያስፈልጋል።

ሥራን መሥራት ባለብን መሥራትና ማቆም ባለብን ሰዓት ማቆም ሊኖርብን ይችላል። የተለያዩ የመቋቋሚያ መንገዶችን በተለይ ደግሞ እያንዳንዱ ሰው የየራሱ መንገድ አለውና፣ ከዚህ ቀደም ጤነና የሚባሉና ‹ለእኔ ይሄ ያስኬደኛል› ብለን የምናስበውን ነገር በዚህ ጊዜ አለመተው ያስፈልጋል።

ቫይረሱ አሁን የደረሰበትን ደረጃ ያሉ እውነቶችን በየቀኑ መረዳት ማወቅ ተገቢ ነው። ግን ሙሉ ጊዜን በዛ ላይ አተኩሮ ማድረግ የሚፈጠር የሥነ ልቦና ተጽእኖ ይኖራል?
እንደ ሰዉ ይለያያል። አንዳንድ ሰው በጣም ዜና ከማንበብ የተነሳ የተለያየ የሥነ ልቦና ጭንቀት ወይም ውጥረት ሊገባ ይችላል። ከተለያየ የዜና ምንጭ ከተለያዩ አገራ የሚወጣው ዜናም አስፈሪና አስደንጋጭ ነው። ለምሳሌ ትላንትና ብቻ (መጋቢት 23/2012) በአሜሪካ ኒውዮርክ 748 ሰው ሞተ የሚል ዘገባ አይቻለሁ። እናም ይህን የሌሎችን ሞት ስታይ፣ አንተ የተለየህ እንዳልሆንክና ለአንተም ቅርብ እንደሆነ ያሳይሃል።

ሰው ነንና ያም የተለያየ ስሜት ሊያጭር ይችላል። መፍራትና መጨነቅ እንዲሁም ማዘን አለ። እና የጤና ባለሞያዎች የሚሉት፣ የአሜሪካ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማእከል እንዳስቀመጡት፣ በቀን ውስጥ ከ30 ደቂቃ በላይ ዜና ባንሰማ ነው። ማለትም በቀን ምን ያህል ሰዓት ዜና አያለሁ የሚለውን መወሰን ያስፈልጋል። ለምሳሌ ጠዋትና ማታ ማየት የምፈልግ ከሆነ፣ ጠዋት 15 ደቂቃ እንዲሁም ማታ 15 ደቂቃ መስጠትና መገደብ።

በተጨማሪ መረጃዎች አስጨናቂ የሚሆኑት፣ በጣም የተለያየ የመረጃ ምንጭ በመኖሩ ነው። የትኛውን ነው የምንከታተለው? በቫይረሱ ላይ የተለያየ ጽንሰ ሐሳብ ይነሳል፣ ያንንም ይዘው ወጥተዋል። እናም ትክክለኛውን የዜና ምንጭ ማግኘት ተገቢ ነው። ለምሳሌ በኢትዮጵያ ከኢትዮጵያ ኅብርተሰብ ጤና ተቋም ወይም ከጤና ሚኒስቴር የሚወጡትንና የሚነገሩትን ብቻ መከተል፣ ከተለያዩ ትክክለኛ ካልሆኑ ምንጮች የሚመጣውን ውጥረት ለመቀነስ ይረዳል። የዜና አጠቃቀማችንን በሰዓት መገደብ አስፈላጊ ነው ብዬ ግን አምናለሁ።

ቀድሞ እንዳነሳው ቤት ውስጥ መቀመጥ የግድ በሚልበት ጊዜ ሰዎች ማኅበራዊ ሚድያን አንዳች አዲስ ነገርን ፍለጋ ሲያስሱ ነው የሚውሉት። የሚገኙበት ጭንቀትም የታወቀና ግልጽ ስለሆነ፣ በሚከታሏቸው ማኅበራዊ ገጾች ላይ ተደማጭ የሆኑ ሰዎች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?
ሰው በኹለቱም መንገድ ታዋቂ ነው። ትክክለኛ መረጃ የማይሰጡትም ምንጮች በጣም ታዋቂ ናቸው። አይተን ከሆነ፣ ብዙ ተጻጻሪ ሐሳቦችን የሚያኘሱ ገጾች በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሏቸው ናቸው። እንደ እኔ እምነት የምንከተላቸውን ገጾች ማወቅ ከውጥረት ያድነናል። ምክንያቱም አንድ ገጽ ብዙ ተከታይ አለው ማለት ገጹ የሚሰጠው መረጃ ትክክል ነው ማለት አይለደም። እናም ገጾቹ መረጃቸውን ከየት እንደሚያመጡ ማወቅ ነው።

ሌላ ደግሞ ሶሻል ሚድያ እንደምትከተለው ሰው ወይም ሐሳብ፣ ጥሩም ነው መጥፎም ነው። አንዳንድ ሰዎች የሚቀርቡትና የሚጽፉት ነገር የሚረብሽና የሚያስጨንቅህ ከሆነ፣ ከዛ መውጣትና አለመከተል ያስፈልጋል። ትክክለኛ የሆኑ የምትከተላቸውን ዘገባዎችን መምረጥ፣ ከማን ምንድን ነው የማየው የሚለውን መለየትና መወሰን ያስፈልጋል።

እንደተባለው ተጽእኖ ፈጣሪ የሚባሉና ብዙ ተከታይ ያላቸው ሰሰዎች አሉ። እነዚህ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች ሲያጋሩና በገጻቸው ሲያካፍሉ፣ የገጹን ትክክለኛነትና የመረጃ ምንጭን በሚመለከት ማጣራት ይኖርባቸዋል፤ ምክንያቱም የሚከተላቸው ብዙ ሰው ስላለ።

ሌላው በተለይ ከተማ ላይ ላሉ ሰዎች፣ ለወጣቱ ማኀበራዊ ሚድያ ወሳኝ የመረጃ ምንጭ ነው። እና የመንግሥት አካላት ወይም በዚህ ጉዳይ ላይ ባለሞያዎች የሚመክሩትን በገጻቸው እንዲታይ ለሌሎች እድል መስጠት ይኖርባቸዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንተርኔት ተደራሽነቱ ዝቅተኛ ነው። አብዛኛው ሰው የኢንተርኔት አገልግሎት አያገኝም። እና እነዚህ ሰዎች ‹ኦን-ላይን›ም ‹ኦፍ-ላይን›ም ያላቸውን ተሰሚነት መጠቀም አለባቸው። በተለይ ደግሞ የሚታወቁ የራድዮን የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ጥያቄ ማንሳትና መጠየቅ፣ ጫና መፍጠር ቢኖርባቸው ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም ይህንን ማድረግ፣ መረጃ ከማድረስ በዘለለ ሌሎች አካላት ላይ ግፊት ማሳደርና ተጽእኖ መፍጠር የሚችሉበትን እድልን መጠቀም ይኖርባቸዋል።

ይህ ወረርሽኝ ኢኮኖሚው ላይ ጫና መፍጠሩ ግልጽ ነው። የደከመውን ኢኮኖሚ የበለጠ ያደቀዋል። ከዚህ ጋር በተገናኘ ጭንቀቱ ለአእምሮ አለመረጋጋት ይዳርጋል። እስኪስተካከል ድረስ የአእምሮው ሁኔታ እንዲሁ ይቀጥላል ማለት ይሆን?
ይህን በኹለት መልኩ አየዋለሁ። እንደሚታወቀው አብዛኛው ሰው ውስን በሆነ የገቢ ምንጭ የሚኖር ነው። ከወር እስከ ወር ወይም በየቀኑ ወጥተው ካልሠሩ ጊቢ የማያገኙ ሰዎች አሉ። ይህ ማት ኢኮኖሚው ላይ ካለው ተጽእኖ ባለፈ፤ ለምሳሌ አስቀድሞ የአእምሮ ጤን ችግር ያለባቸውና በሕክምና የሚታከሙ ሰዎች፣ እንደሚታወቀቀው ከኪስ ነው የሚከፈለው። ለዛ የሚሆን ገቢ አለማግኘት ይኖራል። እና አብዛኛው ሰው መድኃኒት ሊያቋርጥ ይችላል። ከዚህ ቀደም ተሽሏቸው የነበሩ ምልክቶች ተመልሰው ሊመጡ ይችላል።

ቤት ውስጥ መዋልንም አስቀድሞ አንስተን ነበር። ቤት መዋል ብቻ ሳይሆን ደግሞ ቤት ውስጥ ከማን ጋር ነው የምትውለው የሚለው አለ። በተለይ ደግሞ የኢኮኖሚው ጫና የአእምሮ ጤና ችግር ላይ ሲታከል፣ አንዳንድ ሰዎች ለተለያየ አካላዊና ወሲባዊ ጥቃት ተጋላጭ ይሆናሉ። የኢኮኖሚ ጫና ነገሮችን ከባድ ያደርጋል።

በተለይ ደግሞ የሕክምና ፍላጎት ላላቸውና ታማሚ የሆኑ፣ መድኃኒት የሚያስፈልጋቸው ሰዎች፣ መግዛት የማይችሉበት ሁኔታ ሊከሰት ይችላል። እኛ አገር ሕክምና በብዛት ያለው ከታ አካባቢ ነው። ክፍለ አገር የአእምሮ ጤና ያለው ትልልቅ ከተሞች ላይ ነወ። ወደሚቀጥለው ሐኪም ቤት እስክትሄድ ድረስ፣ ለመሄድም መሄጃ ገንዘብና ትራንስፖርት የለም። አገልግሎት ሰጪዎችም ቅድሚያ ለይሰጡ ይችላሉ።

የኢኮኖሚ ተጽእኖው አንደኛ ቀድሞ የነበረ የአእምሮ ችግርን ያባብሳል። ኹለተኛ ደግሞ ከኢኮኖሚ ተጽእኖ የተነሳ አብዛኛው ሰው የሚያጋጥመው የአእምሮ ጤና ችግር ይኖራል። ድኅነቱ የሚያመጣው የአእምሮ ጤና ችግርና የነበረው የአእምሮ ጤና ችግር ላይ ድህነቱ የሚያሳድረው ተጽእኖ መታየት አለበት።

ብዙ ጊዜ ባደጉ አገራት ድባቴ ወይም ዲፕሬሽን አለ ይባላል። የተነጠለ ኑሮ የሚኖሩና በአብሮነት በሚኖሩ ሰዎች መካከልም የሥነ አእምሮ ችግር ልዩነት አለ ይባላል። እኛ አገር ‹ይህኛው የአእምሮ ችግር በስፋት ይስተዋላል› ብለን መለየት እንችል ይሆን?
እኛ አገር ከማንኛውም አገር የተለየ የአእምሮ ጤና ችግር የለም። ኢትዮጵያዊ ስለሆንን ለአእመሮ ችግር አንጋለጥም ማለት አይደለም ወይም ከሌላው የባሰ ተጋላጭ ነን ማለት አይቻልም። ልዩነቱ ሕመሙን ማወቅና ሕክምና መፈለግ ላይ ነው። ለምሳሌ ድባቴን ብንወስድ፣ ሌላው አገር ውስጥ አብዛኛው ሰው ለዚህ ብቻ ምርመራ ይካሄዳል።

ለምሳሌ በአሜሪካ ለአካላዊ ጤና ምርመራ ስትሄድ የአእምሮ ጤናህንም ይመለከታሉ። እኛ አገር ካለው ጫና እና የባለሙያ ቁጥር አንጻር፣ ከአንዱ በሕመምተኛ ወደ ሌላው ለመሄድም ባለሞያዎች ውጥረት ላይ ናቸው። በዚህ ምክንያት ድባቴ ላይ እንደዛ ያለ ክትትል አይኖርም። ስለዚህ ሕክምናው ስላተዳረሰና ብዙ ሰው ስላልታከመ፣ ችግሩ ትንሽ ነው ማለት አይቻልም። ከማንም ያነሰ ወይም የሚበዛ ቁጥር የለውም።

የአእምሮ ጤና ምን ያህል ትኩረት ተሰጥቶት ተጠንቷል፣ ተለይቷል ማለት ይቻላል? ማኅበራዊ ግንኙነታችንስ በዚህ ላይ ምን ሚና ይኖረዋል?
በመጀመሪያ ሰው ስለሆንን ለየትኛውም የአእምሮ ጤና ችግር ተጋላጭ ነን። ለምሳሌ በኢትዮጵያ አኗኗራችን ማኅበራዊ ቅርበት አለው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት የጠበቀ ማኅበረሰባዊ ግንኙነት ያላቸው ከድባቴ የተጠበቁ ናቸው የሚሉ ሰዎች ነበሩ። ያንን የሚጻረር በኢትዮጵያ ውስጥ የተደረገና የታተመ ጥናት አለ።

በዚህም መሠረት እንደውም ማኅበራዊ መረብ በሰፋ ቁጥር ከተለያየ መረብ የሚመጣ ውጥረትና ጭንቀት ተጋላጭ ያደርጋል። እና ይህ አብሮ መኖሩና ማኅበራዊ ትስስሩ ከአእምሮ ጤና ችግር አይጠበቅም። ስጋት የሚፈጥርም ሊሆን ይችላል። ስለዚህ በጥንቃቄ መታየት አለበት። እኛም አገር ያጠናናቸው ጥናቶችና ያሳተምናቸው ወረቀቶች አሉ። በዛ መሰረት እኛ አገር ከሌላው አገር የተለየ የጤና አእምሮ ተጋላጭነት የለም።

ገጠር ላይ የተጠና አንድ ጥናት ነበር። ይህም በ2014 ቡታጅራ ከተማ ያጠናነው ነው። 1 ሺሕ 497 ሰዎችን ያሳተፈ ጥናት ነበር። በዛ ለማየት የሞከርነው የድባቴ፣ የአልኮልና ራስን ማጥፋት ወዘተ የመሳሰሉ የተለመዱ አእምሮ ችግሮችን ልናይ ሞክረን ነበር። የአንድ ወር ተጋላጭነቱን ስናይ፣ ቀላል መካከለኛና ከባድ በሚባለው ውስጥ፣ ከ14 በመቶ እስከ 5 በመቶ ሰዎች፣ ማለትም 14 ሰው ቀላል የሆነ የአእምሮ ችግር ገጥሞታል። ወደ 9 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ መካከለኛ በሚባል ሁኔታ እንደ ድባቴ ያሉ የአእምሮ ጤና ችግሮች ገጥመዋቸዋል።

አልኮል አጠቃቀምን ስንወስድ፣ 22.4 ያህል ሰው ከባድ የአልኮል ተጠቀሚ ነበር። ወንዶች ከሴት ይልቅ የአልኮል ተጠቃሚ ነበሩ። 41 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ከባድ የሆነ የሕይወት አጋጣሚ ባለፉት ስድስት ወራት የገጠማቸው ሰዎች ብዛት ነው። ይህም ሥራ ማጣት ወይም ሞትና ትዳር መፍታት፣ ከባድ የሆነ ችግር ገጥሟቸዋል። ስለዚህ ይሄ የትኛውም ሕዝብ ውስጥ ሊገጥም የሚችል ዓይነት ቁጥር ነው።

ይህ እንደምሳሌ ያነሳሁት ነው። ይህ ጥናት ኅብረተሰብን መሠረት አድርጎ ቤት ለቤት የተደረገ ጥናት ነው። ጤና ተቋማት ውስጥ ያለ የድባቴ ጥናቶችን ስታይ፣ ቁጥሩ ከዚህ ይበዛል። ምክንያቱም አንደኛ አስቀድሞ ያለ የጤና ሁኔታ ድባቴን ሊያባብሰው ይችላል። ኹለተኛ የድባቴ ሕመም አካላዊ ሕመም ሊኖረው ይችላል። አብዛኛው ሰው ድብርት ውስጥ ሲሆን ያመኛል ብለው ማስረዳት በማይችሉት ምክንያት ሐኪም ጋር በተደጋጋሚ ሊሄድ ይችላሉ። እና ተጋላጭነቱን ማኅበረሰብ እንዲሁም በተቋት ላይ ያለውን ሁኔታ መሠረት አድርገን ስናይ እንኳ፣ የተለያየ ነው።

በተለይ ደግሞ የአገልግሎት አቅርቦትም ውስን ነው። ለምሳሌ ከባድ የአእምሮ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ከ10 ሰው አንድ ነው ሐኪም ጋር የሚሄደው። ከባድ የአእምሮ ሕመም ያለው 90 በመቶ ሰው፣ የአገልግሎት ተጠቃሚ አይደለም። የሕክምና ልዩነቱ ሰፊ ነው።

በ2009 የታተመ ወረቀት ይህን አሳይቷል። በዚህም ዐስር በመቶው ብቻ ያውም ከኪሱ ከፍሎ እንደሚታከምና ለዛም ከተማ መሄድ እንደሚጠበቅበት ይጠቅሳል። ለዚሁም ብዙ የመድኃኒት አማራጮች የሉትም። እዚህ ላይ ወረርሽኝ ሲጨመርበት፣ የጤና ተቋማት ምን ያህል ውጥርት ውስጥ እንደሚገቡ፣ ያሉት ባለሞያዎችም በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሠርተው እንደሚያልፉ ስታስብ፣ ከአብዛኛው ሰው በላይ የአእምሮ ሕመምተኞች በዚህ ጊዜ ተጋላጭ ይሆናሉ። ከዛ በተረፈ ኢትዮጵያዊ ስለሆንን ከማንም ሰው ያነሰና የበዛ ተጋላጭነት ይኖረናል፣ ማኅበራዊ አኗኗራችን ጥብቅ ስለሆነ እንሻላለን ብሎ ማሰብ ዘበት ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 74 መጋቢት 26 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here