ኮቪድ-19 እና የአፍሪካ ግብግብ

0
1114

ኮሮና ቫይረስ ርእሰ ጉዳይ ሆኖ ሳምንታትን ተሻግሯል። ሉላዊነት በሠለጠነበት የዓለማችን ዘመን ላይ ከቻይና የተነሳ ተዋህሲ ዓለምን አዳርሷል። ‹አይመለከተኝም!› የሚል አንድ እንኳ እስከማይቀር ድረስ የሁሉንም ደጅ አንኳክቶ ፈትኗል። ኃያልን የተባሉ አገራትም በብልጽግና ከተሻገሯቸው ጥቂት መቶ ዓመታት በኋላ ችግርን ቀምሰዋል። በኮቪድ19 ኮሮና ቫይረስ ምክንያት።

ቫይረሱ ላደጉት አገራት ችግርን ያቀመሰ ቢሆንም፣ ለአፍሪካ ግን ‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ› እንዲሉ የተጫናት ተጨማሪ ሸክም ሆኗል። ቫይረሱ በተሰራጨባቸው የመጀመሪያ ሳምንታትም ‹አፍሪካ ወዮውላት! እንኳን ዘንቦበት እንዲያውም እንዲያ የሆነው የጤና ስርዓቷ ላይ ይህ ሲጨመር አበቃላት› ሲሉ የዓለም መገናኛ ብዙኀን ከተመራማሪዎቹ የሰሙትን አቀብለው ነበር።

አፍሪካ በቀልድ የተቀበለችው ኮሮና የልጅ እርምጃ ያህል በዘገየ ፍጥነት ዜጓቿን እየለከፈ ቢሆንም፣ የባሰ እንደሚመጣ ግን ሁሉም በስጋት እየጠበቀ ይገኛል። በአንጻሩ ‹አይበረታብንም›፣ ‹አፍሪካውያንን አይነካም› የሚልና መሰል በአኅጉሪቱ የሚነዙ ሐሰተኛ መረጃዎችና አስተሳሰቦች እንዲሁም አመለካከቶች ደግሞ ከቀጠሉ፣ ችግሩን የባሰ ያከፋዋል ተብሎም ተሰግቷል። የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ቫይረሱ በአፍሪካ ስላለበት ሁኔታ፣ ስላሉ የተለያዩ አስተሳሰቦችና ስለሚመከሩ ሐሳቦች ጭምር ከተለያዩ መገናኛ ብዙኀን፣ መዛግብትና ባለሞያዎች አንደበት መረጃ በመሰብሰብ፣ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጋዋለች።

በዛብህ ክብሮም የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው። እድሜያቸው ሰማንያዎቹን አልፏል። ጡረታ ከወጡ ከ20 ዓመት በላይ እንደሆነና በቤት ኪራይ ገቢና በልጆቻቸው ድጋፍ እንዲሁም በጥቂት የጡረታ ገንዘብ ኑሯቸውን እንደሚገፉ ለአዲስ ማለዳ ነግረዋታል። ሥራ የሌላቸው በመሆኑ እግራቸውን ለማፍታታት በሚል ከቤታቸው ወጣ ብሎ ከጓደኞቻቸው ጋር መጫወትን ያዘወትራሉ። በአቅራቢያቸው ባለ የቡና መሸጫ በረንዳ ላይ ሆነው ከእኩዮቻቸው ጋር ፖለቲካውንና ማኅበራዊ ሕይወትን በመተቸትና በመከራከር ሐሳብ እየተለዋወጡ መነጋገርንም ይወዳሉ፤ ቀኑንም የሚገፉት በዛ ነው።

‹‹አሁን ጉዳዩ ሁሉ ወረርሽኙ ሆኗል። ከነበርነው አምስት ጓደኛማቾች ውስጥም የለመድነው ቦታ መሄድ ያልተውነው ኹለት ብቻ ነን።›› ይላሉ። ቡና መሸጫ ሱቋ ምንም እንኳ ደንበኞቿ በእጅጉ ቢቀንሱም፣ የንግድ ሥራው ባለቤት ብቸኛ መተዳደሪያ በመሆኑ እንዳልተዘጋም ከትዝብታቸው ይናገራሉ።

‹‹ቫይረሱ በዜና እንደምንሰማው በውጪ አገር እንደተሰራጨው አይደለም እኛ ጋር የተሰራጨው›› የሚሉት አበበ፣ የዚህ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ግን ለመገመት እንደሚከብዳቸውና ከመገናኛ ብዙኀንም ግልጥ ያለ ነገር እንዳላገኙ ጠቅሰዋል።

‹‹አፍሪካውያን የመከላከል አቅማችን ከፍተኛ ስለሆነ ነው የሚሉ አሉ። በዛ ላይ በአገራችንም ወጣቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስለሆነና በሽታው ወጣት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ዝቅተኛ ስለሆነ ነው ሲባልም ሰምቻለሁ። ፈጣሪ ስለሚጠብቀንና ሃይማኖተኛ አገር ስለሆንንም ይሆናል። ምክንያቱን አላውቅም ወይም አልገባኝም መሰለኝ።›› ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል።

አፍሪካ በጤና ዘርፉ ካላት ድክመት በተጓዳኝ ሐሰተኛ መረጃዎች ለኮሮና ቫይረስ ስርጭት ድርሻ እንዳላቸው የሚናገሩ ጥቂቶች አይደሉም። እንደ በዛብህ በርካታ ሐሳቦችን በአእምሯቸው የሚያወጡና የሚያወርዱ ቢኖሩም፣ ያሰቡትን በልባቸው ከማቆየት አልፈው አደባባይ ላይ ማህተም እንደተመታለት እውነት የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም።

ይህም የተሳሳተ መረጃን ወልዶ ብዙ ኪሳራዎችን አምጥቷል። አገራት አንዳቸው ከሌላቸው በሚገባ ሳይማሩ ቀርተውም፣ በተመሳሳይ ጅራፍ እየተገረፉና ዜጎቻቸውም እንደ ቅጠል በአሳዛኝ ሁኔታ እየረገፉባቸው ነው። በቫይረሱ ምክንያት ለነገ የሚቀር ጥሪት መትረፉ አሳሳቢ የሆነበት ደረጃ የደረሱ አገራትም ጥቂት አይደሉም። ይህ ደግሞ በአፍሪካ ምንኛ እንደሚበረታ መገመት ቀላል ነው።

አፍሪካ – በቀደም እና ዛሬ
አፍሪካ ኮቪድ19 ኮሮና ቫይረሱን በሂደትና ቀስ ብላ ነው የተቀበለችው። ኒውዮርክ ታይምስ እንደዘገበው ከሆነ፣ የአውሮፓ አገራት የቫይረሱ ስርጭትና የፍጥነቱ ነገር አብዝቶ ባሳሰባቸው ሰዓት፣ በአፍሪካ የተለያዩ አገራት ግን ኮሮና የቀልድ ግብዓት ነበር።

‹‹ከቻይና የመጣ ቫይረስ ነውና አይበረክትም›› የሚሉና መሰል ቀልዶች ማኅበራዊ ሚድያውን ከፖለቲካውና ከሰላም ማጣቱ ፋታ ሰጥተው፣ የቀልድ አውድማ አድርገውት ነበር። እያደር ግን ፈገግታው እየደበዘዘ፣ ሳቁ እየቀነሰ ፍርሃትና ስጋት እየነገሡ ነው።

በአንጻሩ ቫይረሱ ገና ከቻይና ተነስቶ መሰራጨት ሲጀምርና ‹የዓለም ስጋት ነው ወይስ አይደለም› የሚል ክርክር የተጀመረ ጊዜ፣ ‹ወዮላት ለአፍሪካ! እንኳን ወረርሽኝ ደርሶባት በደኅነኛውም ጊዜ ያላማረባት!› ሲባል ነበር። ይልቁንም ከቻይና ጋር ያላትን የተሳሰረ ግንኙነት በማንሳት ‹ጉድሽ ነው አፍሪካ! ከወዲሁ ተዘጋጂ›› ሲሉ ቆይተዋል።

ኒውዮርክ ታይምስ በአፍሪካ አንድም በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው እንዳለ ሳይረጋገጥ በፊት ነበር፣ ይህን ስጋት በዘገባው ከባለሞያዎች አንደበት ተቀብሎ ያስነበበው። በጠቅላላው ለአፍሪካ በእጅጉ ተፈርቶላት ነበር፤ አሁንም ፍርሃቱ ሳይቀንስ እንዳለ አለ።

አልጀዚራ ይህን በሚመለከት በድረ ገጹ ባስነበበው አንድ ዘገባ፣ በማሳያነት በደቡብ አፍሪካ የታየውን ቸልታ ያነሳል። ቫይረሱ በደቡብ አፍሪካ መገኘቱ ይፋ ተደርጎ ሳይቀር፣ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከሌላ አገር (ከውጪ) የመጡ የተባሉ ሰዎችና ጥቂቶች ናቸው በሚል ነበር ቸልታ የበረታው። አሁንም ከቀን ወደ ቀን ቁጥሮች እያደጉም፣ ንቃቱም ከቸልታው በለዘበ አካሄድ እያዘገመ ይገኛል።

ሆኖም ቫይረሱ አሁን ባለበት ደረጃ ከአፍሪካ ይልቅ አውሮፓንና እነ አሜሪካን ያጠቃ ይመስላል። ታድያ ግን አፍሪካ ከዚህ ሁሉ ተርፋ አይደለም። ቢዘገይም አልቀረላትም። ከአንድ ወር ገደማ በፊት ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ በግብጽ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ የመጀመሪያ ሰው እንዳለ የተነገረው። ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ሰዓት ድረስ የቫይረሱ ስርጭት በአፍሪካ 49 አገራትን አዳርሷል፤ የተረፉትም አራት ብቻ ናቸው።

አሁን አፍሪካ በርካታ በሮቿን ዘግታለች። እንደ ሊብያ የአየር ክልላቸውን ሳይቀር የዘጉ ሲኖሩ፣ በማንኛውም አጋጣሚ ሕዝባዊ ስብሰባዎች እንዳይኖሩ ታግደዋል። ደቡብ አፍሪካ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስታውጅ፣ እርሷን ጨምሮ አገራቱ መሪዎች ግንዛቤ መስጠትን አማራጭ አድርገው ‹ተጠንቀቁ! ራሳቸሁን ጠብቁ!› እያሉ ይገኛሉ።
አፍሪካውያንን የማያጠቃና በነጮች ብቻ የሚነሳ መሆኑን በማሰብ ዘረኝነት ጥቃቶች ሲፈጸሙ ተሰምተዋል። ‹ነጮች ወደቤታችሁ ሂዱ› የሚሉ ማሳሰቢያዎችና የቃል ዘለፋዎች ነጮችን አስቸግሯቸው እንደነበርም ተነግሯል። በትራንስፖርት እንዳይሳፈሩ ማገድ፣ መሳደብና ድንጋይ መወርወር የታየ ክስተት ነው።

ድንበሮች ተዘግተዋል፣ ጉዞዎች ታግደዋል፣ ማቆያዎችም ተሰናድተዋል። አዳዲስ ሕጎችና መመሪያዎችም ተፈጸሚ እንዲደረጉ ከመንግሥት ወርደዋል። እንደ ኬንያ ማንም ኬንያዊ ያልሆነ የውጪ ዜጋ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ ከመከልከል ጀምሮ እንደ ኢትዮጵያ ከውጪ የሚገቡ ዜጎች ለ14 ቀናት በራሳቸው ወጪ በሆቴል ተገልለው እንዲቆዩ እስከማድረግ ድረስ ውሳኔዎችን አስተላልፈው ተፈጸሚ አድርገዋል።

አልጀዚራ በደቡብ አፍሪካ የተወሰደውን እርምጃ በማንሳት፣ ደቡብ አፍሪካውያን የአኗኗር ዘይቤአቸውን እንዲቀይሩ ከመሪዎቻቸው ተደጋጋሚ ምክረ ሐሳብ እየተለገሳቸው እንደሆነ ጠቅሷል። ኮሮና ለቀልድ ግብዓት መሆኑን ትቶም፣ በአፍሪካ ለሰላምታ አለመጨባበጥን እንዲሁም የአካላዊ ፈቀቅታ አስፈላጊነትን የሚሰብኩ ሙዚቃዎች እየተሠሩበትና እየተደመጡ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ለ1.2 ቢሊዮን የዓለማችን ሕዝብ መጠለያ የሆነችው አፍሪካ፣ ቫይረሱ አይነካኝም የሚል ሐሳብ ስታመላለስ ከመቆየቷ ባሻገር፣ ምሁራን ፈርተውላት የነበረው በኹለት ምክንያት እንደነበር የተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል። አንደኛው ያላት የጤና መሠረተ ልማት ደካማነት ሲሆን ሌላው ከቻይና ጋር ያላት ጥብቅ ግንኙነት ነው።

በምዕራብ አፍሪካ የተከሰተውን የኢቦላ ቫይረስ ተከትሎ፣ የበርካታ የአፍሪካ አገራትን የጤና አሠራር እንዳነቃ የሚናገሩም አልጠፉም። ኢቦላን ተከትሎ በአፍሪካ ኅብረት የተቋቋመው በአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማእከል በኢቦላ ምክንያት ተፈጥሮ ለነበረው ንቃት ማሳያ ይሆን ዘንድ የተረፈ አሻራ ነው። የማእከሉ ዳይሬክተር ዶክተር ጆን ኬንጋሶንግ ለኒውዮርክ ታይምስ በሰጡት አስተያየት፣ የኢቦላ መቀስቀስ አኅጉሪቱ በሕዝብ የጤና አጠባበቅና እንክብካቤ ስርዓት በጠቅላላ ደካማ መሆኑን ያሳወቀ ነው ብለዋል።

ኹለቱ ሰበቦች፤ ቻይና እና ድህነት
አፍሪካና ቻይና በርካታ በሆኑ ዘርፎች ይገናኛሉ። ይህንንም ግንኙነታቸውን በብድር አስረው ይዘውታል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት የቻይና እዳ አልያም ውለታ ያለባቸው ናቸው። አፍሪካ ውለታና ብድሯን ሳትረሳ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን እያወቀች ራሱ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሉ ተቋማት መንገደኞችን ያለመታከት ስታደርስና ስትመልስ ነበር።

በአፍሪካ ቻይናውያን ሠራተኞች ብዙ ናቸው። እንደ ኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ፣ በአፍሪካ 200 ሺሕ በላይ ቻይናውያን በቋሚነት የሚኖሩ ሲሆን፣ ኹለት ሚሊዮን የሚጠጉ ደግሞ ከአፍሪካ ቻይና በተለያየ ምክንያት የሚመላለሱ ናቸው። በተጓዳኝ ከ81 ሺሕ በላይ አፍሪካውያን ደግሞ በቻይና ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው። በእርግጥ የመጀመሪያው በኮሮና ቫይረስ የተያዘ አፍሪካዊ ሰው የ21 ዓመት ካሜሮናዊ ተማሪ ሲሆን ትምህርቱን በሁቤይ ግዛት በሚገኝ ያንግዝ ዩኒቨርሲቲ የሚማር ነበር።

ይሁንና አፍሪካ ከቻይና ጋር እንዲህ የጠበቀ ግንኙነት ያላት ቢሆንም፣ ቫይረሱን ወደ አፍሪካ ያመጡት ግን የተፈሩት ቻይናውያን አልነበሩም። ይልቁንም በአፍሪካ በሚገኙ አየር መንገዶች ሲገቡ መነሻቸው ቻይና ስላልነበረች ‹እለፉ› ተብለው የታለፉ አውሮፓውያን ነበሩ።

በተጓዳኝ ወረርሽኙን ለአፍሪካ አስጊ ያደረገው ድህነቷ ነው። በአፍሪካ የጤና ዘርፍ በቂ በጀት የተመደበለት አይደለም። ከዚህ በላይ ደግሞ አፍሪካ እንደ አኅጉር ጥግግት የበዛበት የአኗኗር ሁኔታና የንጽህና ጉድለት ተዳምረው፣ ለቫይረሱ ስርጭት አቅም ሊሆኑት እንደሚችሉ የባለሞያዎች ስጋት ነው። ኒውዮርክ ታይምስም ይህንን ስጋት ነው በገጹ ያስነበበው።

አሁን ኮቪድ19 ኮሮና ቫይረስ በአፍሪካ ዙሪያ 6 ሺሕ 473 ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ ተረጋግጧል። 229 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል።
አፍሪካውያን በድህነት የተነሳ በአንድ ቤት ውስጥ ብዙ ሰው ሲገኝ፣ ከተሞች የበለጠውን መጨናነቅ ያስተናግዳሉ። ቫይረሱ ታድያ እንዲህ ጥግግት ወደሚበዛባቸው ከተማዎች ከዘለቀ፣ የሚያደርሰው ጥፋት ከፍተኛ ሲሆን ማቆሚያም በእጅጉ ያጥራል።

ቫይረሱ በሁሉም እድሜ ያሉትን ሰዎች የሚያጠቃ ቢሆንም፣ ሌላ ተደራቢ በሽታ ላለባቸውና በእድሜ ለገፉ የከፋ ይሆናል። በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን በኮቪድ 19 የተያዙ ሰዎች በተመዘገቡባት ደቡብ አፍሪካ፣ ኤች.አይ.ቪን ጨምሮ ሌሎች በሽታዎች ተስፋፍተው ይገኛሉ። ነገሩም ‹አልሸሹም ዞር አሉ› እንዲሉ ይሆናል።
አልጀዚራ ይህን በተመለከተ በዘገባው እንዲህ ሲል ጠቅሷል፣ ‹ደቡብ አፍሪካን አብዝቶ የሚያሳስባት ሰባት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎቿ ኤች አይቪ በደማቸው ያለ ከመሆኑ ሌላ፣ ኹለት ሚሊዮን የሚሆኑት ሕክምና እየተከታተሉ ባለመሆኑ ነው።››

ይህ የአንዲት የደቡብ አፍሪካ እውነት ብቻ ሳይሆን የብዙ የአፍሪካ አገራት መራራ ሃቅ ነው። በደቡብ አፍሪካ ማሳያነት አፍሪካ ስትቃኝ፣ አሁን ባለው የጤና ስርዓት ብቻ ቫይረሱን መቆጣጠር እንደማይቻል ነው።

ከዚህ በተጓዳኝ በጤና መስኩ በቂ አቅምና ቁሳቁስ አለመሟላት ትልቅ የአፍሪካ ችግር ነው። ለዚህ ሁሉ ችግር አሁን ላይ ድንገቴ መፍትሔ የሚገኝ ባለመሆኑ፣ ሁሉም አፍሪካዊ ጥንቃቄን እንዲታጠቅ አደራ እየተባለ ነው። በተለይም ከተለመደው የአኗኗር ባህል አንጻር፣ ማሳሰቢያውም ጠንከር ብሎ እየተሰማ ነው። ሆኖም አሁንም በቸልታ የተለመዱ ክዋኔዎች መካሄዳቸው አልቀረም።

ኮሮና ለአፍሪካ ዘገየ?
ኮቪድ19 ስርጭታቸው ፈጣን ከሆነና ከማይገመቱ ወረርሽኞች የመጀመሪያው ሆኗል። ዓለምንም በፍጥነት ሊያዳርስ ችሏል። በሌላ በኩል ቫይረሱ ወደ አፍሪካ ለመምጣት ዘግይቷል፣ በብዛት በቫይረሱ የተያዙትም ሰዎች አፍሪካዊ ያልሆኑና ከአውሮፓ የመጡ ናቸው የሚል እይታ አለ። ነገር ግን ያ ሳይሆን መመርመሪያው በአግባቡ ተደራሽ ስላልሆነ ነው የሚሉ አልጠፉም። እንጂ በነቂስ ተወጥቶ ምርመራ ለማካሄድ እድሉ ቢገኝ፣ በቫይረሱ የተያዙ በመቶዎችና ከዛም በላይ ሰዎች ሊገኙ ይችላሉ ተብሏል።

ዘ-ጋርድያን በአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማእከል ዳይሬክተር ዶክተር ጆን ባነጋገራቸው ጊዜ እርሳቸው እንደገለጹት፣ ምርመራ ለማድረግ ያለውን አቅም ማሳደግ ቢቻል ‹ይዞኛል› ብለው የሚጠረጥሩ ሰዎች እንዲመረመሩ ያግዝ ነበር ብለዋል። እናም ብዙ በቫይረሱ የተያዙ አፍሪካውያን አሁን ላይ ያልተመዘገቡት በመመርመሪያ ቁሳቁስ እጥረት ሊሆን ይችላል ብለዋል።

በተመሳሳይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም፣ ምርመራ ባለመካሄዱ እንጂ በርካታ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ሊገኙ ይችላሉ ሲሉ ስጋታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን ያካፈሉትና በግሩም ጠቅላላ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶክተር ብሩክ ዓለማየሁ፣ የአፍሪካ አገራት እየሄዱ ባለበት አዝጋሚ ሂደት ይሄዱ የነበሩ አገራት እንዳሉ ጠቁመዋል። ይህንንም የቫይረሱን ስርጭት በቀረበበት ስዕላዊ ገለጻ (ግራፍ) ስርጭቱ ሲጀምር ዝግ ያለ ሆኖ ለተወሰኑ ሳምንታት ሊቆይ ይችላል ይላሉ።

ለምሳሌ አሜሪካ የጠቀሱ ሲሆን፣ በአሜሪካ ቫይረሱ ለመሠራጨትና መቶ ሺዎችን ለማዳረስ ሦስትና አራት ሳምንታ ወስዷል። ታድያ ይህ አንድም እንደሚመረመረው ሰው ብዛት ሊለይ ይችላል ብለዋል። በአንድ ጎንም ምርመራ በስፋት አለመኖሩ እንቅፋት ይሆናል ያሉ ሲሆን፣ ነገር ግን አካሄዱ ልዩና ያልታየ ሳይሆን በሌሎች አሁን የቫይረሱ ስርጭት በተበራከተባቸው አገራትም የተስተዋለ ነው በማለት ያስረዳሉ።

‹‹የእኛ ልዩ ነው ብሎ ማሰብ ትክክል አይደለም።›› የሚሉት ብሩክ፣ የተረጋጋው ክፍለ ጊዜ ረዘም ያለ ሊሆን ቢችልም፤ ቁጥሮች ግን መጨመራቸው አይቀርም ብለዋል።

በጥቅሉ አሁን ቫይረሱ በአፍሪካ ‹እያሟሟቀ› ነው እንደማለት ነው። ምርመራ በስፋት አለመደረጉ ደግሞ በሰዎች መካከል ተደብቆ ቆይቶ በድንገት የከፋ አደጋ እንዳይጥል በሚል እንዲፈራ አድርጎታል። ‹‹እንጂ መጨመሩ አይቀርም›› የሕክምና ባለሞያው አስተያየት ነው።

በዚሁ ጨምረው በሌሎች አገራት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እድገቱ በቶሎ በቶሎ የሚታየው ምርመራ በስፋት ስለሚሠራ እንደሆነ ያነሳሉ። ‹‹ፈጣን መሆኑ ጥቅም አለው፤ ቶሎ ቶሎ ወደተግባር ለመግባት ያግዛል።›› በማለት ያስረዳሉ። የእርሳቸው ስጋት ታድያ፣ የቫይረሱ ስርጭት የደረሰበትን ደረጃ ለማወቅ አለመቻልና፣ ተስፋፍቶ ቆይቶ በድንገት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው የሕክምና ማእከላቱን እንዳያጨናንቅ የሚል ነው።

‹‹የከፋው ነገር ገና ከፊት ነው ብሎ ማሰቡ ነው የሚያዋጣው ብዬ አስባለሁ።›› ሲሉም አክለዋል።

ሐሰተኛ መረጃ
ለአፍሪካ ከደረሱ ሐሰተኛ መረጃዎች መካከል ቀዳሚው ቫይረሱ አፍሪካውያንን የማይዝና የጥቁሮች ደም ቫይረሱን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም እንዳለው ነው። ዶክተር ብሩክ እንዳሉት በእርግጥም በዘርና ትውልድ ምክንያት ለይተው የሚያጠቁ ቫይረሶችን ዓለም አስተናግዳለች። አንዳንድ በሽታዎችም በነጮች ላይ ሲበረቱ በጥቁሮች ላይ ጫናቸው ዝቅተኛ ሆኖ ይገኛል። ይህ ጉዳይ ግን ጥናት የሚፈልግ ከመሆኑ በላይ፣ ዛሬን በተመለከተ ‹እንዲህ ነው› ብለው በእርግጠኝነት ለመናገር እድል የሚሰጥ አይደለም ሲሉ አስረግጠው አሳስበዋል።

ቫይረሱ ጥሬ ስጋ በመብላት ምክንያት የመጣ ነው በሚል መላምት የአመጋገብ ልምዳቸውን የቀየሩ ነበሩ። በማኅበራዊ ሚድያዎችም ሐሰተኛ መረጃዎች ሰዎችን መወናደብ ውስጥ ሲከታቸውም ተስተውሏል። ይህ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓ አገራትም የታየ እውነት ነው። ጣልያን ትልቅ ዋጋ እንድትከፍልና ኮሮና በተነሳ ቁጥር ከቻይና ይልቅ ሥሟ እንዲነሳ ያደረገው፣ አንድም የመረጃ ክፍተትና ግራ መጋባት ነበር።

ኒው-ዮርክ ታይምስ በዘገባው ይህን ሲያነሳ፣ በአንጻሩ ትክክለኛ ለሆነ መረጃ ደግሞ ሰው መዘናጋት አሳይቷል ይላል። እጅ ታጠቡ፣ አትተቃቀፉ፣ አትጨባበጡ የሚሉ መረጃዎችን ሰዎች ሊረዱ እንደሚገባም ባለሥልጣናት እያሳሰቡ ይገኛሉ ሲል ጠቅሷል።

ዶክተር ጆን ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ ከጋዜጠኛው የቀረበላቸው አንዱ ጥያቄ ከዚህ ጋር የሚገናኝ ነበር። ወረርሽኙን ለመከላከል ተግባቦትና መተማመን ወሳኝ ሆኖ ሳለ ሐሰተኛ መረጃዎች በሚሰራጩበት ሁኔታ ያንን እንዴት ማድረግ ይቻላል ይላል ጥያቄው። የማእከሉ ዳይሬክተር ዶክተር ጆን መልስ ሲሰጡ፣ ‹‹የተሳሳተ መረጃ የፈጠረውን የፍርሃት ደረጃ አይተናል። ከዛ መረጃ ውስጥ አንዳንዱ በማኅበራዊ ሚድያ በኩል የቀረበ ነበር። ከወረርሽኙ በተጓዳኝ የዚህ ሐሰተኛ መረጃ ነገርም አንዱ ስጋታችን ነው።

ይህን ለመቋቋም ከተለያዩና ከሁሉም የመገናኛ ብዙኀን ጋር አብረን መሥራት ይኖርብናል። ያለበለዚያ የማኅበረሰቡን እምነት ማግኘት ከባድ ነው። እንደሚታወቀው ትግሉን ለማሸነፍ ማኅበረሰቡ ከጤና ባለሞያዎች ጋር ተጣምሮ እንዲሠራ ይጠበቃል።›› ብለዋል።

ዶክተር ብሩክ በበኩላቸው ሐሰተኛ መረጃ አፍሪካን እንዲሁም ኢትዮጵያንም በጣም ጎድቷል ብለው ያምናሉ። ይህ ታድያ በማኅበረሰብ ደረጃ ብቻ አይደለም። እርሳቸው እንደሚሉት ከመንግሥትና ባለሥልጣናት ጀምሮ ነው።

እንዲህ ሲሉ ገለጹት፣ ‹‹አይረድሰብንም የሚል ስሜት ነበር። ይህም ከጎደለው ዝግጁነት አንጻር የሚታይ ነው። በቂ የሥነ ልቦና ዝግጅት አልነበረም። እንደማይመጣ ተደርጎ ለምን እንደታሰበ አላውቅም። ግን በአመራር ደረጃ ያሉትም ላይ ተጽእኖ ፈጥሯል።›› ብለዋል።

በዚህም ብቻ አይደለም። ‹‹እንደ ባለሞያስ ምን ያህል ተዘጋጅተናል የሚለውን ብናይ፣ የመዘናጋቱ ነገር በመንግሥትና በግል የጤና ዘርፍም በማኅበረሰብም የመዘጋጀት ሂደቱን አቀዝቅዟል።›› ሲሉ በሕክምና ባለሞያዎችና ተቋማት ሳይቀር ‹ቢመጣስ!› የሚል ሐሳብ ዝር አለማለቱን በአግራሞት ያነሳሉ።

አሁንም ታድያ እየዘገመ እየሄደ ያለውን የቫይረሱን ስርጭት መጠቀም ይገባል ሲሉ ያሳስባሉ። ‹‹ይህ የዘገመ አካሄድ እድል ሊሰጠን ይችላል። አሁን ላይ ትክክለኛ አካሄድ መሄድ ከቻልን ነው ጥሩ ነገር ሊፈጠር የሚችለው።›› ብለዋል።

ታድያ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አገራት የተነሱ ወረርሽኞች ኢትዮጵያ ስላልተከሰቱ፣ ‹አይደርስብንም› የሚል የልቦና ውቅር በሂደት ተገንብቷል ብለው ያምናሉ። ‹‹አሜሪካ የሚኖሩ ጥቁር ሰዎች ሳይቀሩ የማይነኩ ነው የሚመስላቸው። ጥቁር መሆናቸውን ጠቀመን የሚሉም አሉ። ሐሰተኛ መረጃ ዝግጁነታችን አዘግይቶታል ብዬ አስባለሁ።›› ሲሉም የነበረውን ጫና አውስተዋል።

ኮሮና በኢትዮጵያ
ሰባት የአፍሪካ አገራት ነበሩ የተፈራላቸው። እነዚህም በተለይ ከቻይና ጋር ከፍተኛና ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሲሆን፣ ናይጄሪያ፣ ሱዳን፣ አንጎላ፣ ታንዛንያ፣ ጋና እና ኬንያ ካሉበት ከዚህ ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያም ተቀምጣ ነበር። የዓለም ጤና ድርጅትም ከቻይና ጋር በሚያደርጉት በረራና ግንኙነት ምክንያት ቫይረሱን ወደ አፍሪካ ያስገባሉ ብሎ የሰጋባቸው አገራት እነዚህ ናቸው።

ኢትዮጵያ የመጀመሪያው በኮቪድ19 ኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው እንደተገኘ ይፋ እንዳደረገው ነበር የሕክምና መስጫ ማእከላትን ወደማሰናዳት ያቀናችው። ለዚህም ታስቦ የየካ ኮተቤ ሆስፒታል የተሠየመ ሲሆን፣ የሆስፒታሉ ታማሚዎችን የማስተናገድ አቅም ከ500 አስከ 600 እንደሆነ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኤባ አባተ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ገልጸው ነበር።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸውም በቫይረሱ የተያዘውን የመጀመሪያ ሰው ይፋ በተደረገበት መግለጫ፣ ቫይረሱን ለመቆጣጠርና ለመከላከል 300 ሚሊዮን ብር መበጀቱን ጠቅሰዋል። ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆንም ተጨማሪ በጀት ለማፈላለግ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል።

ይህም የማፈላለግ ሥራ ስኬታማ የሆነ ይመስላል። በ444 ላይ በአጭር የጽሑፍ መልእክት እየተሰበሰበ ካለው ገቢ በተጨማሪ ባለሀብቶችና በጎ አድራጊዎች ያላቸውን ሲለግሱ፣ ግለሰቦች ቤታቸውን ለሕክምና መስጫነት እንዲውል ቃል ሲገቡና ሲያስረክቡ፣ ‹ቅድሚያ ለሰብአዊነት› በሚል እንቅስቃሴም አስፈላጊን ቁሳቁስ በማዋጣት ለችግር ጊዜ ከወዲሁ መዘጋጀቱ ጠንክሮ ታይቷል።

ቫይረሱ በዓለም አገራት ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም የካቲት 21/2012 ባካሄደዉ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ፣ ቫይረሱን ለመከላከል በጤና ሚኒስቴር የሚመራ ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራውን እያከናወነ ይገኛል። ኮሚቴው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እየሠራ ያለውን ሥራ በየጊዜው ያቀርባሉ።

ታድያ ከመጀመሪያውም አንስቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቫይረሱ ላይ የሚደረገውን መዘናጋት ትቶ መዘጋጀት አስፈላጊ ነው ሲሉ አሳስበዋል። በቫይረሱ ምክንያትም በአዲስ አበባ ሊደረጉ የታሰቡ ዓለም ዐቀፍ ጉባኤዎች ተሰርዘዋል። ይህም ብዙ ወጪና ኪሳራ የሚያስከትል ቢሆንም፣ የሚታገሉት እንጂ የሚታደሉት ጉዳይ አልሆነም።

ስለምን ይዋሻል?
በአውሮፓ ካሉ የጤና ዘርፍ ተመራማሪዎችና በአውሮፓ እንዲሁም በቻይና ቫይረሱ ካሳየው ስርጭት አንጻር፣ በአፍሪካ አገራት የቫይረሱ ስርጭት ዘገምተኛ መሆኑን ከሚያነሱት ጎን ለጎን ‹ዋሽተውናል› የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም።

የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ፣ ምንም ያህል ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ቢሆን አሳውቁኝ ሲል አሳስቧል። አገራትም መረጃዎችን እንዲያካፍሉ አደራ ብሏል።
ዶክተር ብሩክ በግላቸው በቫይረሱ የተያዘና የተደበቀ ጉዳይ አለ ወይ ብባል፣ እየተደበቀ ነው ብዬ አላምንም ብለዋል። በማኅበራዊ ሚድያዎች የሚናፈሱት ሐሰተኛ መረጃዎች እንዳሉ ሆነው፣ ይህ የሆነው በቂ መረጃ ከስር ከስር ባለመሰጠቱ ነው ባይ ናቸው። ይህን ክፍተት ለመሙላት የጤና ሚኒስቴር እንዲሁም የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃዎችን ከስር ከስር መስጠትና ትክክለኛ መረጃን ማቀበል ይኖርባቸዋል ብለዋል።

መደበቅ ግን በጣም አደጋ አለው፤ በእርግጥ ተደብቆ ከሆነ። ‹‹የእኛ ማኅበረሰብ እንደውም እየተጠነቀቀ አይደለም። ሰዎች እንደማይደርስባቸው ነው የሚያነሱት። ጥቂት ሰው ብቻ ነው ያለን እያሉ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራንፕ ሲያቃልሉ ቆይተው አሁን ላይ ደርሷል።›› ሲሉ በአሜሪካ የሆነውን በማንሳት ‹‹መንግሥት ቁጥርና መረጃ በመደበቁ ሊጠቀም የሚችለው ነገር አለ ብዬ አላስብም።›› በማለት የግል እይታቸውን አካፍለዋል።

በተመሳሳይ የተለያዩ የሕክምና ባለሞያዎችም ከጥንቃቄ አንጻር ብቻ ሳይሆን ሊገኝ ከሚችለው ድጋፍ አኳያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች እንዳልተያዙ ተደርጎ ይደበቃል ብለው እንደማያምኑ ሲገልጹ ይስተዋላል። ጉዳዩ ግን ሐሰተኛ መረጃም ይሁን አልያም ስጋትና ፍርሃት የፈጠረው፣ በግልጽነት መረጃዎችን በመስጠት መፍትሔ መስጠት ይቻላል።

አፍሪካና የተዘረጉ እጆቿ
የዓለም ስጋት ሆኖ የቀጠለው ኮቪድ19 አገራት እንዲረዳዱና እንዲደጋፊ ምክንያት ሆኗል። ደግሞም መደጋገፍ አማራጭ የሌለው መንገድ እንደሆነ ሁሉም ያምናል። አገራት አንዳቸው ያለሌላቸው መዝለቅ እንደማይችሉና ሉላዊነት ምን ያህል እንዳስተሳሰራቸውም የተገለጠላቸው ይመስላል። አስፈላጊ የቫይረሱን መከላከያና ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶችንም እየተቀባበሉ ይገኛሉ።

አፍሪካ በተጓዳኝ ትሰጠው ብዙ ባይኖራትም እርስ በእርስ ከመደጋገፍ በላይ ከሌሎች የምትቀበለው ብዙ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት በአፍሪካ ለ13 አገራት ይልቁንም ከቻይና ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸው ላላቸው ድጋፍ አድርጓል። በተለይም ሰፊ የሆኑ ምርመራዎች እንዲካሄዱና ቤተሙከራዎችም ምርመራ እንዲያከናውኑ በማድረግ በኩል ይህ ድጋፍ ድርሻ ሊወስድ ችሏል።

ተስፋና ስጋት
አፍሪካ አሁን ላይ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በተስፋና በስጋት ውስጥ ታጥራ ትገኛለች። በአንድ ወገን ወጣት ኃይል የሚበዛባት መሆኑ ጉዳቱን ሊቀንሰው ይችላል ቢባልም፣ ይህ ተማምነው የሚደገፉትና እቅድ የሚነድፉበት ሁኔታ አይደለም። የግሩም ሆስፒታሉ ዶክተር ብሩክም፣ በአፍሪካ ወጣቶች መብዘታቸውና ቫይረሱ ወጣቶች ላይ ጉዳቱ አነስተኛ ነው በሚለው ተስፋ ላይ እቅድ ማውጣት አይቻልም ይላሉ።

ምክንያቱ ደግሞ ወጣት ሽማግሌ የሚል ከቫይረሱ ጋር የተገናኘ መረጃ የተሰጠው በቻይና የሆነውን በማየት ነው። ‹‹አፍሪካ ላይ ያለው የቫይረሱ መገለጫ ሌላ ሊሆን ይችላል። ጣልያን ጠንከር ያለ ሕመም ያላቸው ወጣቶች እንዳሉ ታይቷል። እና በአፍሪካ የተጠና መረጃ ስለሌለን እቅድ ማውጣት አንችልም።›› ሲሉ አስረድተዋል።
በአፍሪካ ደረጃ ደግሞ ድህነትና የምግብ እጥረት የበለጠ አጋላጭ ይሆናሉ ያሉ ሲሆን፣ በዚህ ምክንያት የባሰ በሽታም ሊመጣ ይችላል፣ ከአድሜ ውጪ ያሉ ሌሎች ለቫይረሱ ስርጭት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ ሁኔታዎችን መርሳት የለብንም በማለት አሳስበዋል።

‹‹የእኛ ጤና ስርዓት በደኅናው ጊዜም ችግር ያለበት ነው። ውጪ አገር በማሽን እጥረት ሰዎች ሊሞቱ አይችሉም። አሁን ግን ከአቅም በላይ ሲሆን በማሽን ማጣት ምክንያት ሰው እንዲያጡ ግድ ብሏቸዋል። እኛ ግን በደኅናውም ጊዜ ማሽን በማጣት ሰው ሲሞት ስለነበር፣ የእኛ መሠረትም ችግር ነው።›› ያሉ ሲሆን፣ አያይዘውም የአፍሪካ አቅም ስለሚፈተን ተስፋ ሰጪ ነገሮችን ብቻ ይዞ በፍጹም መረጋጋት አያስፈልግም፤ የዶክተሩ ሐሳብ ነው።

ስጋቱ ጸንቶ አለ። ቀስ በቀስ እያዘገመ ቢሆንም በአፍሪካ በኮሮና የተያዙ ሰዎች ቁጠር ከእለት ወደ እለት እየጨመረ ይገኛል። አሁንም ባለሞያዎች በአፍሪካ ያሉ ሰዎች የቫይረሱን አደገኝነት ሊገነዘቡ ይገባል እያሉ ነው።

ወደከፋው እንዳንደርስ
ቫይረሱ ከጸናባቸው የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ በሆነችው ናይጄሪያ፤ የሳይንስ አካዳሚ የቪርጎሎጂ ፕሮፌሰር ኦዬዋሌ ቶማሪ ‹‹የሚያሳስበን አደጋ እሱ ነው። በቻይና የሆነው እንዲደገም መጠበቅ የለብንም።›› የሚል አስተያየት ለሲኤንኤን ሰጥተዋል።

ዶክተር ጆንም በተመሳሳይ፣ ቫይረሱ ያለባቸውን ሰዎች መለየት እንዲሁም ቫይረሱን መቆጣጠር መቻልን በሚመለከት አፍሪካ ልትጋፈጠው የምትችለው ፈተና እንደሚሆን ከሲኤንኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል። በአፍሪካ ፍጥነቱ ከፍተኛ አለመሆኑና ረጋ ማለቱ ሊያዘናጋ እንደማይገባና፣ አሁንም ቢሆን በቫይረሱ እየተያዙ ያሉ ሰዎች ስለመኖራቸው ጠቅሰው፣ የሞት ፍጥነቱ ኹለት በመቶ ቢሆንም እንኳ፣ ያም ቢሆን ብዙ ቁጥር ያለው ሕዝብ ነው ብለዋል።

ከፋርማሲ የሚገኙት ሳይሆኑ ማንኛውም ሰው ሊያደርግ የሚችላቸው ማኅበራዊና አካላዊ ፈቀቅታ፣ ቤት ውስጥ መቆየትና አለመውጣት፣ እጅን መጣጠብና ንጽህናን መጠበቅ አሁን የቀሩ የመፍትሔ ሐሳቦች ናቸው። እነዚህም ስርጭቱን የበለጠ ሊያጓትቱት ይችላሉ፤ እንደ ዶክተር ጆን ገለጻ።

ዶክተር ብሩክ በበኩላቸው፣ ምርመራዎችን ሳይንቁ ማድረግ ተገቢ ነው ሲሉ ይሞግታሉ። በውጪ አገራት የስርጭቱ የመጀመሪያ ሰሞን በትንሽ ጥርጣሬም ሰዎች ሲመረመሩ የሚስተዋል ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ግን ቢያንስ ሳልና ትኩሳት ያላቸውን ሰዎች የመመርመር እድል አልተመቻቸም። ለዚህም ‹ድርቅ› ያለ አሠራርና አካሄድ ምክንያት ሆኗል።

ምልክቶች አይተናል ብለው የሚያሳውቁ ሰዎችን ሁሉ ለመመርመር አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ሁኔታዎችን አይቶ አስፈላጊ ለሆነው ምርመራውን ማካሄድ ይገባል። ከውጪ አገር የመጣ ሰው መሆን አለመሆን ወይም ከውጪ ከመጣ ሰው ጋር ንክኪ አለ የለም ከሚለው ባሻገር፣ አንድ ጊዜ ቫይረሱ ገብቶ ከሆነ፣ እርስ በእርስ ቅብብሉ በፍጥነት የሚቀጥል ስለሆነ፣ የትኛውም ጉዳይ ቸል ሊባል አይገባም።

እንደ ዶክተር ብሩክ፣ ሌላው የመመሪያ አስፈላጊነት ነው። 8335 ነጻ የስልክ መስመር ላይ ከመደወል ባሻገር ማድረግ የሚገባውን ጥንቃቄ በመንግሥት ደረጃ የተሰጠ መመሪያ የለም ይላሉ። ቫይረሱ በበረታባቸው አገራት እንደ ጉንፋን ያለው የቫይረሱ ምልክት ከታየባቸው በቤታቸው ሆነው ሊያደርጉ ስሚገባው ጥንቃቄ መመሪያ ስለተሰጣቸው አልከበደም። በኢትዮጵያም በተመሳሳይ ማድረግ ቢቻል መልካም ነው ሲሉ ባለሞያው ሐሳባቸውን ሰጥተዋል።

ከምንም በላይ ግን ስርጭቱ እንዳይከፋ ሕዝብ የሚሰበሰብባቸውን ማኅበራዊም ሆነ ሃይማኖታዊ እንዲሁም የተለያዩ ክዋኔዎችን መቀነስ ተገቢ ነው ብለዋል።
ሌሎች እንዳይረሱም ሲሉ አሳስበዋል። እርሳቸው አገልግሎት እየሰጡ ባሉበት ግሩም ሆስፒታል፣ ቫይረሱን በሚመለከት ሰዎችን ለማስተናገድ እንዲያስችላቸው በር ላይ ካለው ልየታ በተጨማሪ ራሱን የቻለ ቡድንና ክሊኒክ አሰናድተዋል። ከውጩ ጉዞ ለመጡና የቫይረሱ ምልክት ለታየባቸው፣ ክሊኒክ መደራጀቱንና ከሌሎች ታካሚዎች ጋር መደበላለቅ ሳይኖር ሕክምና ለመስጠት እንደሚያግዝም አንስተዋል።

‹‹ቫይረሱን የሚከታተል የራሱ የሆነ ቡድን ተደራጅቶ አለ። ይህ ቡድን በሁሉም አቅጣጫ እንዲመራና መረጃ መቀባበል ላይ እንዲመራ ተደርጓል። እንደ አንድ ተቋም ጥሩ እየሠራን ነው። መቀናጀት ያስፈልጋል። ከግል ሆፒታሎች ጋርም እየተነጋገርን ነው። ልምድም እየተለዋወጥን እንገኛለን። ግን የከፋው ጊዜ ከፊታችን ነው እያልን ስለሆነ፣ ገና ብዙ ይጠበቅብናል።›› ሲሉ አሳስበዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 74 መጋቢት 26 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here