ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ

0
1123

(መጋቢት  29፤2012 ፤አዲስ አበባ ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በሥነ ምግባር የታነፀ በሃላፊነት ስሜት ህዝብን የሚያገለግል ሚዲያ በሀገራችን  እንዲጎለብት የሚሰራ ተቋም ሲሆን በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍና በሀገራ አቀፍ ደረጃ የህዝቦች ስጋት የሆነው የኮቪድ 19 ወይም የኮሮና ቫይረስ እያደረሰ ያለውን ተጽእኖ ለመመከት ህዝብና መንግስት እያደረጉ ያሉትን  ርብርብ ይደግፋል፡፡

ሚዲያ በማናቸውም አስቸጋሪ ጊዜ ህዝባዊ አግልግሎታቸውን መስጠት ከማያቆሙ  ወሳኝ ተቋማት መሀከል አንዱ ነው፤ምክር ቤታችን  እነዚህን መገናኛ ብዙሃንን ያቀፈ ሲሆን ስለወረርሽኙ  ትክክለኛ ወቅታዊ መረጃዎችን እንደሚያስተላለፍ አካል ሀገራችን በአሁኑ ወቅት የገባችበትን አደጋ እንገነዘባለን፡፡

ይህንኑ አደጋ  ለማስወገድ መገናኛ ብዙሃን በዚህ ወቅት ህብረተሰቡ ስለ ወረርሽኑ ግንዛቤ ከማስጨበጥ አንስቶ እንዴት መከላከልና እያንዳንዱ ዜጋ ራሱን መጠበቅ እንዳለበት ጭምር ከመንግስት፤ ከህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት፣ከጤና ሚኒስቴር፤  ከዓለም ጤና ድርጅትና ከሌሎች ዓለም አቀፍና ተቋማት የሚተላለፉ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ በማቅረብ ግንዛቤው እንዲፈጠር እያደረገ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም    ስለ ኮሮና ቫይረስ አስከፊነት፣በፍጥነት መዛመትና መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ የሚመለከታቸውን የህክምና ባለሙያዎች በማነጋገር የወረርሽኙ የስርጭት ፍጥነት ከዚህ የከፋ እንዳይሆን ሙያዊ ሀላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡

በሀገራችን እስካሁን ድረስ ባለው የወረርሽኙ ስርጭት በቫይረሱ የተያዙ ወገኖች ቁጥር ከዚህ የበለጠ እንዳይጨምር የግንዛቤ መፍጠር ስራው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ በመሆኑም ጋዜጠኞች መረጃዎችን ከተረጋገጡ የመረጃ ምንጮች ብቻ መውሰድ  ይገባቸዋል፡፡ ከዚህ ውጭ ህዝብን የሚያሸብሩና ስጋት ላይ የሚጥሉ ዘጋባዎችን ላለማስተላለፍ ከፍ ያለ ሃላፊነት ያለባቸው ሲሆን በህግ ከሚያስጠይቁ የፈጠራ መረጃዎች  መራቅ አለባቸው፤ ተጨባጭ ያልሆኑ  የፍሬ ነገር ይዘቶችንና የመድሃኒት ግኝቶችን ከማስተዋወቅና የተስፋ ቃል ለህዝቡ ከማስተላለፍም ሊቆጠቡ ይገባል፡፡

የጋዜጠኝነት ሙያ እንደሌሎቹ ሙያዎች በቤት ውስጥ ተቀምጦ የሚሰራ ሳይሆን በየሰዓቱ በመንግስትና በሚመለከታቸው የጤና ስራ ሃላፊዎች የሚሰጡ መግለጫዎችን መከታታልና በትኩሱ ለህዝብ ማድረስ ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ጋዜጠኞች እንደማንኛውም የህብረተሰቡ አካል ለወረርሽኑ የመጋለጥ አጋጣሚው ያለባቸው በመሆኑ ሙያዊ ስራቸውን ሊያከናውኑ የሚገባው በቅድሚያ ስለወረርሽኙ በቂ ግንዛቤ በመያዝና የራሳቸውን ጥንቃቄ በማድረግ ነው፡፡

በመሆኑም ጋዜጠኞች  በስራ ላይ ለሚያጋጥማቸው ለወረርሽኑ የመጋለጥ አጋጣሚውን ለመቀነስ በቂ የሆኑ የመከላከያ ቁሳቁሶችን ማለትም ጓንት፤ማስክና የእጅ ማፅጃዎችን በአግባቡና በወቅቱ ማድረግ እንዳለባቸው በመገንዘብ ተቋማት እነዚህ የቅድመ ጥንቃቄ ቁሳቁሶች በማቅረብ ጥቅም ላይ መዋላቸውንም ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ በቃለ ምልልስ ወቅትም በቂ የሆነ ርቀት መኖሩን ማስተዋል ይገባል፤

በአሁኑ ወቅት ከወረርሽኑ  ስርጭት ጋር በተያያዘ መንግስት በወሰዳቸው የስራ እንቅስቃሴዎች ገደብ ሳቢያ ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖዎች እየታዩ ነው፡፡ በራሱ የማስታወቂያ ገቢ የሚተዳደረው ሚዲውም በማስታወቂያ ኢንዱስትሪው መቀዛቀዝ ሳቢያ ቀላል የማይባል የፋይናንስ እጥረት ላይ ወድቋል፤ ያም ሆኖ  መገናኛ ብዙሃን መቋረጥ የሌለበትን መረጃን በወቅቱ ለህዝብ የማድረስ ሀላፊነታቸውን በተቻለ መጠን እንዲያወጡ ጥሪያችን እናስተላልፋለን፡፡

የኮረና ቫይረስን ከዚህ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመከላከልና ህብረተሰቡን ለመጠበቅ መንግስትና የህክምና ባለሙያዎች ከሚደያርጉት ጥረት ጎን ለጎን  ተቋማትና ሌሎች ሙያዊ ማህበራት ለመገናኛ ብዙሃን መረጃን በማቅረብ ህዝብን የማስተማርና ግንዛቤ የመፍጠር ስራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የሁሉም አካላት ድጋፍና ትብብር አስፈላጊ በመሆኑ  ለአንደ ዓላማ የመንቀሳቀስ ሃላፊነታችንን በጋራ እንድንወጣ እንጠይቃለን፡፡

እጃችንን እንታጠብ! ርቀታችንን እንጠብቅ!  የጤና ምክሮችን እንተግብር!

 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ

መጋቢት 29 ቀን 2012 ዓ.ም

አዲስ አበባ

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here