2 ሺሕ አረጋዊያንን ከጎዳና ላይ ለማንሣት ጊዜያዊ ተገጣጣሚ ቤቶች ሊገነቡ ነው

0
721

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ 2 ሽ ሕ ለሚሆኑ የጎዳና ተዳዳሪ አረጋዊያን መጠለያ የሚሆን ተገጣጣሚ ቤቶች በመቄዶንያ የአረጋዊያንና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማእከል ሊገነቡ ነው።

ቤቶቹ የሚገነቡት በከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስተባባሪነት ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በዓለማችን እንዲሁም በአገራችን የተከሰተውን ኮሮናቫይረስ የመከላከል ጥረት ለማገዝ መሆኑም ተገልጿል።

የመቄዶንያ የአረጋዊያንና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማእከል ምክትል ሥራ አስኪያጅ ተወካይ አሰፋ ባልኤር፣ በማእከሉ ውስጥ ከ2500 በላይ አረጋዊያን እና የአእምሮ ሕሙማን እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ብዛት ያላቸው አረጋዊያንና የአእምሮ ሕሙማን በአንድ ቦታ ተሰባስበው መኖራቸው ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ የመሆን ዕድላቸውን ከፍ እንደሚያደርገው አቶ አሰፋ ገልፀው ችግሩን ለመቅረፍ በከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተለያዩ ኮንትራክተሮችንና ባለሀብቶችን በማሳተፍ ጊዜያዊ ተገጣጣሚ ቤቶችን ለመገንባት ቦታውን የመጥረግ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ለማእከሉ ተረጂዎች ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ቁሳቁሶች ማበርከቱንም ጠቅሰዋል።
አክለውም፣ በማእከሉ የሚገኙ ተረጂዎች በማንኛውም እንቅስቃሴ የሰዎችን እርዳታ የሚጠይቁ በመሆናቸው እና እነዚህን ወገኖች በተንቀሳቃሽ ስልካችን 8161 ላይ በመደወል ok በማለት ልንደግፍ ይገባል ብለዋል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ላቀዉ አበጀ በሚኒስቴር በስሪያ ቤቱ አስተባባሪነት እየተገነባ ያለዉ ተገጣጣሚ ቤት ጊዜያዊ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡ ላቀው አክለዉም በመቄዶንያ የአረጋዊያንና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማእከል እና በሚኒስቴር መስሪያቤቱ አስተባባሪነት የሚገነባዉ አረጋዊያኑ ተቀራርበዉ ስለሚኖሩ ለኮረና ቫይረስ ተጠቂነት ተጋላጭ እንዳይሆኑ በመስጋት ነዉ ብለዋል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 75 ሚያዝያ 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here