ወረርሽኙ ጥላ ያጠላበት ምጣኔ ሀብትና የሚጠበቁ የመንግሥት እርምጃዎች

ኮቪድ-19 ኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ እንደ ጣልያን መዘናጋት የሚያስከፍለውን ዋጋ፣ እንደ ደቡብ ኮርያ በማስተዋል የሚወሰድ እርምጃ የሚኖረውን ጥቅም ከዚህ ቀደም አስቃኝተዋል። አሁን ደግሞ ቫይረሱ ስር የሰደደ ጫና እንዳያሳደርና ኢኮኖሚውን የከፋ ውድቀት ውስጥ እንዳይከት፣ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ በኩል የፖሊሲ ቅኝች ማደረግ ያስፈልጋታል ሲሉ የሚሞግቱት ሽመልስ አረአያ፣ ለዚህም በዋናነት የሚጎዱ የኢኮኖሚ ዘርፎችን እንደዚሁም የኅብረተሰብ ክፍሎችን መለየትም ዋናው ቁልፍ ሥራው ይሆናል ብለዋል።

የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ብዙ አሜሪካውያንን በማጥቃት እንደዚሁም በቀዳሚነት የብዙ ጣሊያናውያንና ስፔናውያንን ሕይወት በመቅጠፍ አሁንም መላውን ዓለም እያነጋገረ ይገኛል። እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት በአሜሪካ በቫይረሱ የተጠቁት በጠቅላላው ከዓለም ተጠቂዎች አንድ አራተኛው በላይ ሲሆን፣ ከተከታይዋ ስፔን ሦስት እጥፍ የሚያክል ታማሚ ተሸክማለች።

በአንጻሩ በኢትዮጵያ ይህ ጽሑፍ ለሕትመት እስከገባበት ቀን ድረስ ይፋ የተደረገው በቫይረሱ የተያዙ ታማሚዎች ቁጥር በኹለት አሃዝ የሚገለፅ ቢሆንም፣ እንደሌሎች አገራት መጠነ ሰፊ ምርመራ ቢካሄድ ቁጥሩ ከዚህ የበለጠ ሊሆን ይችላል የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ለማነፃፀሪያነት ኬንያ የመረመረቻቸውን ሰዎች ብዛት ይጠቅሳሉ።
የመገናኛ ብዙኀን (ማኅበራዊውም መደበኛውም) ቫይረሱ ስለደቀነው አደጋና ስለመከላከያ መንገዶቹ በመነጋገር ተመልተዋል። ስርጭቱን ለመግታት በዋናነት አካላዊ መራራቅንና የግል ንፅህና መጠበቅ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ለማመላከት ያለማቋረጥ እየተለፈፈ ይገኛል። ይሄ እጅግ ተገቢ በመሆኑ መዘናጋት እንዳይፈጠር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

በሌሎች አገራት እንደታየው የጤና ባለሙያዎቻችን ቁጥሩ የበዛ ታማሚ ቢከሰት ውስን በሆነው የጤና አገልግሎት አቅርቦታችን የተነሳ አገልግሎት ባለማግኘት ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ የሰጡትን የቅድመ-መከላከል ምክር መተግበር አሁንም እጅግ ወሳኝ ነገር ነው። በተያያዘም የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል እንዲያግዝ በአገር ደረጃ ለተቋቋመው ኮሚቴ በተለይም ከአገር ውስጥ ባለሃብት የሚደረገው የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍም ይበል የሚያሰኝ ነው።

ይህ ድጋፍ በአገር ውስጥ ብቻም ሳይወሰን በውጭም በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድም ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው። በዚህም ኢትዮጵያውያን እንደአገር ለተጋረጠባቸው አደጋ ምን ያክል እንደሚተባበሩና የጋራ ጠላትን ለማሸነፍ አሁንም ቢሆን በጋራ እንደሚቆሙ ለሚመለከታቸው መልዕክት ያስተላለፉበት ክስተት ሲሆን፣ ይህ የተጀመረው ድጋፍ የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

አገራት ስርጭቱን ለመከላከል የሕዝባቸውን ተለምዷዊ እንቅስቃሴ በሙሉ ወይም በከፊል እንዲገታ ከመምከር እስከ ማስገደድ እየተገበሩት ነው። ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ይህን ፈተና ለማለፍ በዘላቂነት ከቤት ባለመውጣት ብቻ እንገላገላለን ካልን የችግራችን ግዝፈትና ጥልቀት በሚገባ እንዳልተረዳ ይጠቁማል።
በመሆኑም ከሚተላለፈው ቅድመ መከላከል ማስጠንቀቂያዎች እንዲሁም መንግሥት የጤናውን ዘርፍ አቅም ለመገንባት ከ(ለዚሁ ዓላማ 5 ቢሊዮን ብር በጀት መመደቡ ይታወሳል) ሚያደርገው ጥረት ባሻገር፣ ቫይረሱ የሚያሳድረውን ተግዳሮት ለመቋቋም የሚያስችሉ አይነተኛ እርምጃዎችን ‹ሳይቃጠል በቅጠል› እንዲሉ፣ ሳይውል ሳያድር በሚችለው አቅሙ መተግበር አለበት። ምክንያቱም የቫይረሱ ስርጭት ፈተና የደቀነው የሰዎች ጤንነት ላይ ብቻ ሳይሆን ውሎ ሲያደር በፖለቲካ፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጤንነትም ጭምር ላይ ነው።

ከቫይረሱ የአደጋ ወሬ ቀደም ብሎ የአገራችን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መገለጫዎች እንደሚጠቁሙት በዋናነት በከፍተኛ አሃዝ የሚገለፅ ሥራ አጥነት፣ ኑሮ ውድነት፣ የሕዝብ ቁጥር እድገትና ስር የሰደደ ድህነት የተጫጫነን መሆኑን ነው።

በዓለማቀፍ ተቋማት መረጃ መሰረት ወቅታዊ የአገራችን ሕዝብ ብዛት ከ100 ሚሊዮን በላይ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ እስከ 2050 በእጥፍ ይጨምራል ተብሎ ተገምቷል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የኢኮኖሚ አቅም ባላቸው አገራት በእንዲህ ፍጥነት የሚጨምር የሕዝብ ቁጥር ዕዳ በመሆኑ፣ በራሱ የሚያስከትለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት ስጋት ጊዜውን ጠብቆ እንደሚፈነዳ ቦምብ የሚቆጥሩት ብዙዎች ናቸው።

እንግዲህ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት የብዙኀኑ ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ በሆነበት ሙሉ ለሙሉ የእንቅስቃሴ እገታ ተግባራዊ ቢደረግ በአብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እስከምን ሊደርስ እንደሚችል በቀላሉ መገመት ይቻላል። ለምሳሌ ህንድ ቫይረሱን ለመቆጣጥር ሁሉም በቤቱ እንዲከት በኃይል ጭምር እያስፈፀመችው ባለው ቁጥጥር የተነሳ፣ ቁጥራቸው ከ100 ሚሊዮን የሚልቁ በደኅናው ጊዜ ከኢመደበኛው የኢኮኖሚ ዘርፍ የእለት ጉርሳቸውን ለማግኘት የሚንከላወሱ ዜጎቿ ቤተሰባቸውን ምን እንደሚመግቡ ግራ መጋባታቸውን ለመገናኛ ብዙኀን በእምባ ገልፀዋል።

በተያያዘም በኢትዮጵያ በደኅናው ጊዜ እንኳን የኑሮው ሁኔታ አስቸጋሪ ለሚሆንባቸው ከቤት አትውጡ ቢባሉ ረሃብ ከቤት እንዲቀመጡ አያስችላቸውም። ለዚህም ይመስላል የአዲስ አበባ ከንቲባ ሙሉ ለሙሉ ከቆለፍን የማንወጣው ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ መግባታችን አይቀርም ሲሉ የተደመጡት።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ መረራ ጉዲና (ዶ/ር) በፓርላማ አባልነታቸው ወቅት ‹‹የሚበላውን ያጣ ሕዝብ መሪውን ይበላል” በማለት ባስተላለፉት መልዕክት የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ምላሽ ካላገኙ የሚደቅኑት የስርዓት አልበኝነት አደጋ የከፋ እንደሚሆን መክረዋል። እዚህ ላይ የአንዳንድ አገራት መንግሥታትም (ለምሳሌ የቻይና) ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ከሞላ ጎደል በመመለሳቸው የተነሳ (ምንም እንኳን የግለሰብ ነፃነት ባያከብሩም) የማኅበራዊና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት አደጋ ሲደቀንባቸው እምብዛም አይታይም።

በመሆኑም እንቅስቃሴ እንዳይኖር ሙሉ በሙሉ መቆለፉ ለተወሰኑ ቀናት ቢሠራ ከሳምንት ስለማለፉ ያጠራጥራል። ረሃብ አያስቀምጥምና በልጆቻቸው የዳቦ ያለህ ዋይታ ወላጆች ትዕዛዙን ጥሰው መውጣታቸው አይቀርም። በመሆኑም የተላለፈልን ቅድመ ጥንቃቄዎች አንዳችን ተግብረን ሌሎቻችን ባለመተግበር የወረርሽኙን ስርጭት ልንገታው አንችልምና፣ አሁን ከሚደረገው የበለጠ እንዲጠናከር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት መልዕክት እጅግ ተገቢም ወቅታዊም ነው።

በመሆኑም ከመንግሥት ኃላፊነቶች አንዱ በቫይረሱ ስርጭት የተነሳ ኑሯቸው በከፍተኛ ሁኔታ የተመሰቃቀለባቸው ሰዎች ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር የምግብ ዕርዳታ መስጠት ያስፈልጋል። እነዚህም በዋናነት የቀን ሠራተኞች፣ በጎዳና ንግድ ላይ የተሰማሩ፣ የንግድ እንቅስቃሴ በመቀዛቀዙ የተነሳ የዕለት ጉርሳቸውን ለተቀሙ ጫኝና አውራጆች፣ ወዘተ ዳቦ አፋቸው ላይ ማስቀመጥ ተገቢ ነው።

አልያም ጫናውም ለመቀነስ በዋናነት ብዙ የቀን ሠራተኛ የሚቀጥረው የኮንስትራክሽን ዘርፉ ሥራው እንዳይቋረጥ ማድረግ ሌላው መላ ይሆናል። ሙሉ ለሙሉ የሰዎች እንቅስቃሴ እንዲቆለፍ ማድረግም ዳፋው ብዙ ስለሆነ በተለይ ኑሯቸው ከእጅ ወደአፍ የሆኑ ወገኖች በዚህ ወቅት ለከፍተኛ የኑሮ ዋስትና ችግር ተጋላጭ ስለሚሆኑ፣ ይህም በመንግሥት ላይ ሌላ ተጨማሪ ሸክም ይደቅናል።

ክስተቱ ዓለማቀፋዊ እንደመሆኑ፣ ለጋሾች በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የተለመደው እገዛቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜ ሳያጠፉ ያቀረቡት ጥያቄ የሚያስመሰግን ሆኖ፣ መንግሥት በእጁ ያለውን ሀብት ተጠቅሞ በጊዜ ተፍ ተፍ ካላለ መዘግየት የበለጠ ዋጋ እንዳያስከፍል ያሰጋል። መንግሥት በግንባር ቀደምትነት ኃላፊነት ወስዶ ለእነኚህ ሰዎች የምግብ እርዳታ ማቅረብ ከተሳነው፣ የራበው ሰው ግንባሩን ለጥይት ለመስጠት እንደማያመነታ ልብ ማለት ያስፈልጋል።

የቫይረሱ ስርጭት በዓለም ኢኮኖሚ ላይ የደቀነው አደጋና ቀጣይ ስጋት በግልፅ እየታየ ሲሆን፣ አገራትም ከሚያሳርፍባቸው ዱላ ለማገገም እንዲያግዛቸው አጣዳፊ የፖሊሲ እርምጃዎች እየወሰዱ ይገኛሉ። በማንኛውም ጊዜ ኢኮኖሚያቸው ሃዲዱን ሳይስት እንዲጓዝ የሚጠቀሟቸው ቁልፍ የፖሊሲ እርምጃዎች በጥቅሉ በኹለት ሲከፈሉ፣ ይኸውም የበጀት እና የገንዘብ ፖሊሲ በመባል ይታወቃሉ።

እነኚህ ጥቅል የፖሊሲ አይነቶች የሚፈፀሙባቸው ዝርዝር ማስፈፀሚያ ቁልፍ መሣሪያዎች አሏቸው። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ቫይረሱ ክፉኛ የተሰራጨባቸው የበለፀጉት አገራት በሂደት ኢኮኖሚያቸው የኋሊት እንዳይንሸራተት ለማስተካከል እንዲረዳቸው እነኚህ ፖሊሲዎች ላይ ማሻሻያ በማድረግ በኢኮኖሚው ላይ ለተጋረጠባቸው አደጋ መላ ለማበጀት እየተጉ ይገኛሉ።

እንደ ዘ-ኢኮኖሚስት መፅሔት ዘገባ ጀርመን የወሰደችውን የፖሊሲ ማስተካከያዎች ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። የሚያስፈልጉት የጤና ቁሳቁስ ለማሟላት 156 ቢሊዮን ዩሮ ከመበጀት አልፋ 50 ቢሊዮን ዩሮ ደግሞ በቫይረሱ ስርጭት የተነሳ ሥራቸው ለሚስተጓጎልባቸው ለአነስተኛ አንቀሳቃሽ ተቋማትና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ከሥራ ለተቀነሱ ሠራተኞች ከመንግሥት ወጪ የሚከፈል በጀት አፅድቃለች። በአጠቃላይ ጀርመን በዚህ ቫይረስ ስርጭት አስገዳጅነት የተነሳ የተገበረችው የፖሊሲው ፓኬጅ 750 ቢሊዮን ዩሮ በላይ እንደመደበች መረጃዎቹ ይጠቁማሉ።

ሌሎች አገራትም እንደዚሁ ተመሳሳይ እርምጃ እየወሰዱ ጊዜያዊ ማነቃቂያ የበጀትና የገንዘብ ፖሊሲዎች በመተግበር ላይ ይገኛሉ። በዚህ ረገድ ትላልቅ ከሚባሉትም የአፍሪካ አገራት ከወሰዱት እርምጃ ሲነፃፀር አገራችን እስካሁን ይፋ ያደረገቻቸው የበጀትና ገንዘብ-ነክ የፖሊሲ እርምጃዎች ሲታዩ እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም።
በአገራችን ይፋ የተደረገው የቫይረሱ ተጠቂዎች አሃዝ ትንሽ ቢመስልም፣ የዓለም ንግድና ገበያ መቀዛቀዙን ተከትሎ በኢኮኖሚያችን ላይ ጠንከር ያለ በትሩን እንዳሳረፈ አመላካቾች አሉ። እንደአብነትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአብዛኛው የበረራ መዳረሻዎቹን ገበያ መቋረጥ ተከትሎ እስካሁን በይፋ በገለፀው መሰረት ከ190 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማጣት እንደተገደደ ተገልጿል።

ሲንከባለሉ የመጡ የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች
ለዐስርት ዓመታት እንደተመዘገበ በተነገረለት ባለኹለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የነበረው አከራካሪ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፣ የነበረውን እድገት ማስቀጠልና በሂደትም ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪው ሲጠበቅ ወደአገልግሎት ዘርፍ መፋለሱን የተገነዘበው መንግሥት ይህንን ለማስተካከል የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለመንደፍ እንደተገደደ ይታወቃል። ለእቅዱ ስኬትም ከውስጥና ከውጭ ሃብት በማፈላለግ በዋናነት በመንግሥት አማካኝነት በሚተገበሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ ማፍሰስ ተጀመረ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ወደሥልጣን መምጣትን ተከትሎ በተገለጠው ሪፖርት፣ እነዚህን ፕሮጀክቶች በመጠቀም የተፈፀመው የሀብት ምዝበራ እስከምን ድረስ እንደነበር በሰፊው ተገልፆአል። ብዙ ሃብት የፈሰሰባቸው እነዚህ ፕሮጀክቶች ካለመጠናቀቃቸውም በላይ በፋይናንስ እጥረት የተነሳ ወቅታዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንደተቀዛቀዘም መረዳት ተችሏል።

ሌላው በደኅናውም ጊዜ ለኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ምርት ዜጎቿን መመገብ እንደማይቻል ነው። በመሆኑም በአቅርቦት እጥረት የተነሳ የሚፈጠረው የምግብ ዋጋ ንረትን ለማስተካከል ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬ በመመደብ ስንዴ ከውጭ ለማስገባት እንደምንገደድ ተወስቷል። በመሆኑም በየዓመቱ በኢትዮጵያ የእህል ምርት ዕድገት እንደሚመዘገብ ቢገለፅም፣ ራሳችን መመገብ እንደቻልን ተደርጎ መውሰድ ስህተት እንደሆነና አሁንም የነፍስ ወከፍ ፍጆታችን ጉድለት የሚሸፈነው ከውጭ በግዢና በእርዳታ በሚገባ ምግብ ነው።

በየዓመቱ የወጪ ንግድ ገቢ ማሽቆልቆል አገሪቱ ለፈታኝ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደዳረጋትም ተገልጿል። በመሆኑም ከውጭ የሚገቡ ጥሬ ዕቃዎችን የሚጠቀሙ አምራቾች የውጭ ምንዛሬ ፍላጎታቸውን ማሟላት እንዳልተቻለም ተጠቅሶ ነበር። በዚህ የተነሳም በአብዛኛው የሸቀጦች ዋጋ ንረት እየተፈጠረ እንደሆነ የአደባባይ ሃቅ ነው። በወቅቱ ከወጪ ንግድ ይገኝ የነበረው ገቢ ማሽቆልቆሉን ተከትሎ አገሪቱ የነበረባትን ብድር የመክፈል አቅም ላይ ጫና በመደቀኑ፣ ተጨማሪ የልማት ብድር ለማግኘት እንዳልተቻለና በዚህም አገሪቷ የምትከተለው የፖሊሲ አቅጣጫ ጭምር ሊያስቀይራት እንደሚችል ተገለፀ።

በመሆኑም ለዓመታት የጠቅላላ ፍላጎት መጨመር መሰረት ተደርጎ ይመራበት የነበረው መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ትልቁን ሚና የሚጫወትበት አካሄድ በመቀየር ላይ ነበር። ወጪውንም በመቀነስ የግሉን ዘርፍ ማስፋፋት ማእከል ወዳደረገ አቅርቦትን መጨመር በሚያስችል ‹አገር-በቀል› በተሰኘ ፖሊሲ ተክቶ በትግበራ ላይ እገኛለሁ በሚልበት ወቅት ነው፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያልታሰበ ፈተና የደቀነው።

አሁን ከመንግሥት ምን ይጠበቃል?
በዚህ ወረርሽኝ ክፉኛ የተጠቁ አገራት ተሞክሮ የሚያሳየው፣ የአዳዲስ ተጠቂዎች ቁጥር እንዳይበዛ ከመከላከል ባሻገር ጊዜውን የዋጀ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ማድረጋቸው ነው። በመሆኑም ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት በወረርሽኙ ምክንያት በከፋ ሁኔታ የሚጎዱ የኢኮኖሚ ዘርፎችና የኅብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት የበጀትና የገንዘብ ፖሊሲ ማስፈፀሚያ ተግባራትን በመጠቀም በፍጥነት ማሻሻያ ለማድረግ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ጊዜ ላይ እንገኛለን።

በጀቱ በቫይረሱ ስርጭት የተነሳ በቀጥታ የተጠቁትን ተቋማትና የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመደጎምና አቅማቸውን ለማጠናከር የሚወጣ የመንግሥት ወጪ ነው። እንደዚሁም የገንዘብ ፖሊሲ በብሔራዊ ባንክ በኩል የተለያዩ ማስፈፀሚያ መሣሪያዎቹን ተጠቅሞ ገንዘብ ወደ ንግድ ባንኮች እንዲገባ ማስቻል ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም ደንበኞች ሂሳባቸው ከሚገኝበት ወጪ ሲጠይቁ እንደዚሁም ለሚቀርብ የብድር ማመልከቻ ባንኮች በዚህ ወቅት የጥሬ ገንዘብ ድርቅ እንዳይበረታባቸው በማድረግ በዚህም ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው እንዲገባ ለማስቻል ነው።

በመሆኑም በኮቪድ19 ስርጭት የተነሳ ከገበያ ውጭ የሆኑ አምራች ተቋማት (ለምሳሌ የአበባና የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች) ከታክስና ግብር ማሸጋሸግ፣ የባንክ ብድር መክፈያ ጊዜ እፎይታ እንዲያገኙ በማድረግ የዘርፉ ተወዳዳሪነት እንዲቀጥልና እንዳይወድቅም የተደረገ ቁልፍ ተግባር ነው። በተመሳሳይ የመስተንግዶ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ከገበያ ውጭ በመሆናቸው ደረጃ በደረጃ መደጎምም ሊያስፈልግ ይችላል።

እነዚህ ተቋማትና ድርጅቶች ለሠራተኞቻቸው ደመወዝ እንዲሰጡ የመንግሥት ድጎማ ዋስትና ካላገኙ ሠራተኞቻቸውን በቋሚነት ለማሰናበት ይገደዳሉ። በተመሳሳይም በኢ-መደበኛው የኢኮኖሚ ዘርፍ ተሰማርተው ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ይተዳደሩ የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከመንግሥት በጀት የሚቀርብ የምግብ ድጎማ ከላይ በተገለፀው መሰረት መደረግ አለበት። እነኚህ የኑሮ ዋስትና የሚመሰቃቀልባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመደገፍ ሌሎች አገራት በሚያደርጉት ልክ ለማድረግ የአቅም ውስንነት ቢኖር እንኳ፣ ለሌሎች ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆኑም ከሁሉ በማስቀደም መንግሥት በጀት በመመደብ በአስቸኳይ ምግብ ሊያቀርብላቸው ይገባል።
የተረጋጋ የፖለቲካ አየር በማይነፍስባት አገራችን ይህንን በፍጥነት ማስተካከል እንደሚጠይቅ እሙን ነው። እንዲህ ያለውን ድጋፍ ለማድረግ ለዘመናት ያከናወነው በመሆኑ ልምዱም አለን። የዓለም ምግብ ፕሮግራም መረጃ እንደሚጠቁመው፣ አንድ አምስተኛ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር በሴፍቲ ኔት ፕሮግራም በኩል በቋሚነት የምግብ እርዳታ ተቀባይ መሆኑ ይታወቃል።

ሌላው በብሔራዊ ባንክ በኩል ሊተገበር የሚችለው የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃ ሲሆን፣ ጥቅል ፋይዳው ብድር ለመውሰድ የሚከፈለው ወጪን መቀነስና መጠኑ ከፍ ያለ ገንዘብ ወደኢኮኖሚው እንዲገባ ለማስቻል ለባንኮች የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ ነው። በኢኮኖሚው ውስጥ የሚዟዟረው ገንዘብ እንዲጨምር ለማድረግ ጥቅም ላይ የሚውሉ ሦስት የፖሊሲው ማስፈፀሚያ መሣሪያዎች አሉ።

ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች የሚያበድርበትን ተመን መቀነስ፣ የባንኮችን አስገዳጅ የተቀማጭ ተመን መቀነስና በባንኮች እጅ የሚገኝን ሰነድ (ለምሳሌ የግምጃ ቤት ሰነድ) ግዥ በመፈፀም ደንበኛ ያሰባሰቡ ባንኮች የጥሬ ገንዘብ ችግር እንዳይገጥማቸውና በደንበኞቻቸውም በኩል ያገኙትን ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው እንዲረጩት ለማስቻል ነው። በዚህ ረገድ ለባንኮች በመንግሥት የተደረገ የገንዘብ አቅርቦት 15 ቢሊዮን ብር መሆኑ ተገልጿል። ይህ ድጋፍ ያንሳል ለማለት በመረጃ ላይ መመርኮዝ ይጠይቃልና፣ የድጋፉ ትሩፋትም እስከምን እንደሆነ ከሚያመጣው ውጤት ማየት እንችላለን።

ነገር ግን በሕክምና የታዘዘ መድኃኒት የጎንዮሽ ጉዳት እንደማያጣው ሁሉ፣ ወደ ኢኮኖሚው በሚረጨው የገንዘብ አቅርቦት የተነሳ የዋጋ ግሽበት እንደሚፈጠር ግልፅ ነው። እንደተለመደው የእቃዎች አቅርቦት መስተጓጎሉን ተከትሎ በተጠቃሚው ዘንድ የአቅርቦት እጥረት ይፈጠራል። በዚህም የዋጋ መወደድ ይከሰታል በሚል ስሌት በሽሚያ ግዢ በማካሄድ የሚያከማች ሲሆን፣ በእቃዎች ዋጋ (በተለይም ምግብ) ላይ ንረት መከሰቱ አይቀርም።

ሽመልስ አርአያ በአሁኑ ወቅት በጀርመን ሀገር ከሚገኘው ጊሰን ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪ እጩ ሲሆኑ ቀደም ብለው በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል በመምህርነት አገልግለዋል።
በaraya.gedam@gmail.com አድራሻ ማግኘት ይቻላል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here