ኮዓለም በኮቪድ-19 የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትና በሽታው እያስከተለው ባለው ሞት በተጨነቀች ሰዓት፣ ሌሎቹን ጉዳዮቿን ሁሉ ቆዩኝ ያለቻቸው ይመስላል። ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የተለመዱ ጉዳዮቿ በይደር ሊቆይዋት የሚችሉ ቢሆንም፣ በጤና ዘርፉ የሄደችበትን ርቀት ወደኋላ ሊመልስ የሚችል መሆኑ ግን ልትጋፋው የማትችለው መራራ እውነት ሆኗል።
ወረርሽኝ በሚከሰት ሰዓት ሌሎች የጤና እክሎች ታግሰው የሚጠብቁ አይደሉም። እናም እንዲህ ባለ ወረርሽኝ የሁሉንም ሐሳብ ሰርቆ በያዘበት ሰዓት፣ ሌሎች የጤና እክሎች ቀላል የማይባል ጉዳት ያደርሳሉ። ተላላፊ የሆኑ እንዲሁም ያልሆኑ በሽታዎችም ትኩረት ስለሚነፈጉ፣ ላልተወሰነ ጊዜ ርዕሰ ጉዳይ በሆነው ወረርሽኝ ተጋርደው ጥፋት ማድረሳቸው የማይቀር ነው። እነዚህም በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የጤና ዘርፉ ዳዴ በሚልባቸው አገራት ጉዳታቸው የከፋ ይሆናል። ይህንን ጉዳይ በማንሳት፣ የተለያዩ የጤና ባለሞያዎችን በማናገር፣ ጥናታዊ ሥራዎችና ጽሑፎችን በማገላበጥ የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጋዋለች።
ዓለምነሽ አየለ (ሥማቸው የተቀየረ) በየካቲት እንዲሁም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎች ተመላላሽ የጤና ክትትል ያደርጋሉ። ይህን ክትትላቸውን ለዓመታት አቋርጠው እንደማያውቁና በጤናቸው ላይ ለታዩና ለሚታዩ የየእለት መሻሻሎችም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ይጠቅሳሉ። ‹‹አሁን ግን ከኹለት ሳምንት ወዲህ ቀጠሮዎቼ ሁሉ ተራዝመዋል፤ ሄጄ አላውቅም።›› በማለት የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ያስከተለባቸውን ተጽእኖ ያስረዳሉ።
‹‹ቀዶ ጥገና ካካሄድኩ ጥቂት ጊዜ ነው። ፈጣሪዬን የምለምነው ይህ ክፉ ጊዜ እስኪያልፍ ድረስ ሕመሜ እንዳይቀሰቀስ ነው።›› በማለት ስጋታቸውን ከወዲህ ገልጸዋል። ቢሆንም በዚህ ጊዜ ሆስፒታል መሄዱ ወረርሽኝ ሆኖ ለተከሰተው ኮሮና ቫይረስ ሊያጋልጣቸው ስለሚችል፣ ከነስጋታቸውም ቢሆን ትክክል ነው ብለው እንደሚያምኑ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ዓለምነሽ ለሦስት ወራት የሚያገለግላቸውን መድኃኒቶች ገዝተዋል። ከሚታከሙባቸው ጤና ማእከላትም መድኃኒቶችን እንዲወስዱና ጤናቸውን በቤት ውስጥ በደንብ እንዲጠብቁ እንደተነገራቸው ያስታውሳሉ።
እንደ ዓለምነሽ ያሉ በርካታ ሰዎች መደበኛ ሕክምናቸውን እንዲያቋርጡ ተገደዋል። ይህም የሆነው በኮሮና ቫይረስ ስርጭት ምክንያት የሕክምና ማእከላት ትኩረታቸውን ሁሉ በቫይረሱ ላይ በማድረጋቸው ነው። በተጨማሪም ታካሚዎች ለቫይሩሱ ተጋላጭ የሚሆኑበትን አጋጣሚ መቀነስንም ታሳቢ ያደርገ ነው። ይህም መደበኛና ድንገተኛ የጤና እክሎችን ብቻ ሳይሆን፣ አስቀድሞም ቤተኛ የነበሩትን እንደ ኩፍኝ፣ ኮሌራ፣ አተት እና ወባ ያሉ ወቅትና ጊዜ ጠብቀው የሚከሰቱ ወረርሽኞችን ለመቆጣጠር ከባድ ፈተና መሆኑ አይቀሬ ነው።
ወረርሽኞች ትኩረት፣ አቅም፣ የሰው ኃይልና ሀብትን የመውሰድ አቅም አላቸው። ይህም አሁን ላይ በኮሮና ምክንያት እየታየ ሲሆን፣ ቀደም ባሉ ጊዜያት ያሉ ልምዶችም ለዚህ ምስክር የሚሆኑ ናቸው። እንደ ማሳያ እየተጠቀሱ ካሉት ውስጥም አንደኛው በቅርቡ በምዕራብ አፍሪካ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ሲሆን፣ ያንን ተከትሎ ሥነ ተዋልዶን ጨምሮ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት የተዘነጉ የጤና እክሎች ለበርካቶች ሞት ምክንያት ሆነዋል።
ነባራዊ እውነት…ምን ታጎለ?
የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስን መከሰትና መሰራጨት ተከትሎ፣ ኢትዮጵያም አሻግራ ስታየው የኖረችው ስጋት እያደር የየእለት እውነትና ዘገባዋ ሆኗል። የቫይረሱ ስርጭት ቅድመ መደበኛና መደበኛ እንዲሁም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲዘጉ፣ አገልግሎት ሰጪ የንግድ ተቋማትም ሥራ እንዲያቆሙ አድርጓል። ይህም ብቻውን ስርጭቱን ለመቆጣጠር አቅም ይሆናል ተብሎ ስላልታሰበ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።
የቫይረሱ ስርጭት ከቀጠለና ከበረታ ሕክምና ለመስጠትም የሕክምና ተቋማት እንዲዘጋጁ ጥሪ ተላልፎ ያም ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የወጣ መግለጫ እንደሚያሳየውም፣ ቫይረሱ ኢትዮጵያ እንደገባ በታወቀ ጥቂት ቀናት ውስጥ ከተሰናዳው የሕክምና እና የለይቶ ማቆያ ማእከላት በተጨማሪ፣ 180 ለይቶ ማቆያዎች እንደተጋጁ ተጠቅሷል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክረተርያት ንጉሡ ጥላሁን ይህን መረጃ ይፋ ሲያደርጉ፣ እነዚህ 180 ተቋማት ከ180 ሺሕ በላይ ሰዎችን የማስተናገድ አቅም እንዲኖራቸው ተደርገው ተዘጋጅተዋል ብለዋል። እንዲሁም የሰው ኃይልን በማጠናከር እንዲሁም አስፈላጊ የሚባሉ ቁሳቁሶችም ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እነዚህ ታድያ ከሕክምና ተቋማት ውጪ በበጎ ፈቃደኞች የተሰጡ ሆቴሎችና አገልግሎት ሰጪዎች የተገኙ ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶችና የሃይማኖት ተቋማት መሆናቸውን ገልጸዋል። ይህም ከውጪ የሚገቡ ሰዎችንም የሚያስተናግድ ሲሆን፣ አጠቃላይ ስፍራዎቹ በፖሊስ ጠንካራ ጥበቃ እየተደረገላቸው ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ከዚህም በተጓዳኝ የተለያዩ የገንዘብ ድጋፎች እንቅስቃሴውን ለማገዝ እየተለገሱ መሆኑን አንስተዋል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ደጋፍ ተደርጓል። ይህም የጤና ዘርፉን ከማገዝ ጎን ለጎን በሚኖሩ የእንቅስቃሴ ገደቦች ጉዳት ለሚደርስባቸው ወገኖች ተደራሽ ለመሆን ያግዛል ተብሎ ይጠበቃል።
አሁን ላይ ታድያ ነገሮች እንደ ቀድሞው አይደሉም። የደም ባንክ እንደወትሮው ብዙ ሰዎችን እያስተናገደ አይደለም። ከኹለት ዓመት በፊት ጀምሮ በወራት ልዩነት ደም ትለግስ የነበረችው ሕይወት ፈለቀ (ሥሟ የተቀየረ) አሁን ደም ለመስጠት ወደ ቀይ መስቀል መሄድ ስጋት ስለፈጠረባት ከመስጠት ተቆጥባለች። ለአዲስ ማለዳም ሐሳቧን ስታካፍል ምን ያህል ደም መለገስ ደስ የሚያሰኝ ተግባር እንደሆነ ግን በሙሉ መተማመን የተናገረችው ነው።
‹‹ደም መስጠት [መለገስ] እንደሚያስፈልግ አውቃለሁ። ደም ሲወስዱም ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ እርግጠኛ ነኝ። ግን ደግሞ ቫይረሱ ትንሽ አጋጣሚ ነውና የሚፈልገው፣ ደፍሬ መሄዱን ፈርቻለሁ።›› ስትል ሐዘን በተቀላቀለበት ስሜት ታስረዳለች። እንደ ሕይወት ሁሉ ብዙዎች ቀድሞ ደም የለገሱና ይለግሱ የነበሩ አሁን በራቸውን ዘግተዋል። ይህም ወረርሽኙ የፈጠረው ስጋት ነው።
ይሁንና በጎ ፈቃደኞች ደም ልገሳቸውን እንዲቀጥሉና ስጋት ሊሰማቸው እንደማይገባ የጤና ባለሞያዎች ሲናገሩ ተሰምቷል። የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰም፣ ቫይረሱን ለመቆጣጠር የተደረጉ እንቅስቃሴዎችን በማንሳት አስፈላጊና ተገቢነታቸው ላይ ሐሳብ አካፍለዋል።
ነገር ግን የበጎ ፈቃድ ደም ለጋሾች ቁጥር መመናመን አሳሳቢ መሆኑን ሳይጠቅሱ አልቀሩም። ‹‹በዚህ የወረርሽኝ ጊዜ የደም አቅርቦትን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው። በድንገተኛ አደጋ እንዲሁም በወሊድ ጊዜ ደም የሚያስፈልጋቸው የነበሩ አሁንም ደም ያስፈልጋቸዋል። ደም መለገስን መቀጠል ያስፈልጋል።›› ሲሉ መልእክታቸውን በማስተላለፍ ኅብረተሰቡ በዚህ ረገድ እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።
ለዚህም ተገቢው ጥንቃቄ በባለሞያዎች በኩል እንደሚደረግ፣ የደም ባንኮች በየቦታው በመንቀሳቀስ በጎ ፈቃደኞች ካሉበት በመገኘትም ደም የመሰብሰብ ተግባር የማከናወን እንቅስቃሴ ላይ እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
ዶክተር ትንሣኤ ዓለማየሁ የሕጻናት ሕክምና ዘርፍ ላይ ያገለግላሉ። የደም ልገሳን በሚመለከት ባስነበቡት ጽሑፍ፣ የዓለም የጤና ድርጅትን ሪፖርት ጠቅሰዋል። በሪፖርቱ መሠረት በአንድ አገር ከሚኖሩ ከእያንዳንዳቸው አንድ ሺሕ ነዋሪዎች ውስጥ፣ ከፍተኛ ገቢ ባላቸው አገራት በዓመት 32.6 የደም ዩኒት፣ ከአማካይ ከፍ ያለ ገቢ ባላቸው 15.1 ዩኒት እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገራት በዓመት 4.4 ዩኒት ደም ይለግሳሉ።
ታድያ ከሪፖርቱ ተገኘ ባሉት መረጃ መሠረት፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት ከሚለገሰው ደም ውስጥ ግማሹ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ላሉ ሕፃናት የሚሰጥ ነው።
አልፎም ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ አገራት ዘጠና በመቶ የደም ልገሳዎቻቸው ከበጎ ፍቃደኞች የሚሰበሰብ ነው። እናም ይህ የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ቁጥር መቀነስ ምን ያህል አሳሳቢ ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም።
ዶክተር ቃልኪዳን ካሳዬ ‹የጤና ወግ› የተሰኘው ድረ ገጽ ላይ ይህን በሚመለከት ያነሱት ሐሳብ ነበራቸው። በተለይም ወረርሽኙ የሁሉን ትኩረት በብቸኛነት መሳቡ ምን አስከተለ፣ ምንስ አስታጎለ ለሚለው ጥቂት ነጥቦችን ዘርዝረዋል። ለምሳሌ በአዲስ አበባ በርካታ ሆስፒታሎች ድንገተኛ ያልሆኑ ቀዶ ጥገናዎችን ላልተወሰነ ጊዜ ማቆማቸውን ጠቅሰዋል። የተመላላሽ ሕክምና ክፍሎች በቀን ውስጥ የሚያዩትን የታማሚ ቁጥር ሲገድቡ፣ የአስተኝቶ ማከም ክፍል ውስጥ የአልጋ ቁጥሮችን ቀንሰዋል።
ሌላው የሰው ኃይል ሲሆን፣ በከፍተኛ ቁጥር መቀነስ ታይቷል ይላሉ። የሕክምና ባለሞያዎች፣ በሥራ ላያ ያሉት እንዲሁም ትምህርት በመከታተል ላይ የሚገኙት ጭምር ለወረርሽኝ ጉዳዮች ተመድበዋል።
አስተማማኝ የጤና ስርዓት?
የኢትዮጵያ የጤና ስርዓትና አሠራር እንኳን በከፋ ወረርሽኝ በመደበኛው አገልግሎትም ፈተና ያለበት ነው። አስተማማኝ የሆነ የጤና ስርዓት አለመኖሩም፣ እንዲህ ባለ የወረርሽኝ ጊዜ ወረርሽኙንና መደበኛ የጤና ዘርፍ አገልግሎቱን ለመስጠት ፈታኝ ይሆናል።
ባለሞያዎችና ተመራማሪዎች እንደሚናገሩት፣ የጤና ስርዓት አስተማማኝ የሚባለው ድንገተኛ ክስተቶችን ቀድሞ መተንበይ የሚችልና ሲደርስበትም የሚቋቋም ሲሆን ነው። ለዚህም የ2013 እስከ 2016 የዘለቀው የኢቦላ ወረርሽኝ የአስተማማኝ የጤና ስርዓት አስፈላጊነት በጉልህ የታየበት አጋጣሚ ነበርም ይላሉ። እናም በመፈረካከስ ላይ የነበሩ የጤና አገልግሎቶች በዚህ ወቅት የባሰ አዘቅት ውስጥ ይገባሉ በማለት ይገልጻሉ።
የተለያዩ የዓለም አገራት ቀደም ባሉ ጊዜያት ለተፈጠሩ ወረርሽኞች ዝግጁ አልነበሩም። እናም እነዚህ በሠለጠኑ አገራት ያሉ የጤና ዘርፎች ሳይቀር መደበኛ አገልግሎታቸውን እንኳ መስጠት አልቻሉም ነበር።
እናም ታድያ የእነዚሁ አገራት ባለሞያዎች ለአስተማማኝ የጤና ዘርፍ የተለያየ ትርጓሜ ይሰጣሉ። በአንድ በኩል የነበረውን የጤና ዘርፍ ለማጠናከር የሚደረግ እንቅስቃሴ ጋር የሚዋሐድ አድርገው የሚቆጥሩት አሉ። ይህም ቀድሞ ሁኔታዎችን ተረድቶና ገምቶ ቅድመ ጥንቃቄዎች እንዲደረጉ የሚያደርግና በቶሎ ድጋፍ እንዲሰጥ የሚያበረታታ ነው ተብሎ ይገመታል።
ይህም አስፈላጊ ከሆኑ ግብዓቶች ጋር የሚገናኝ ሲሆን፣ መሠረተ ልማትንም ያካትታል። በተለይም የሕክምና ተቋማት ግንባታን የሚመለከት ነው። ሀብትና ገንዘብ አጠቃቀም ላይም በተመሳሳይ ቅድሚያ ዝግጅት የሚፈልጉና መታሰብ ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ በጉዳዩ ላይ ትንታኔ የሚሰጡ ባለሞያዎች ያስረዳሉ።
በወረርሽኝ የተደበቁ ‹ወረርሽኞች›
በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ፣ ሰዎች እርስ በእርስ በሚፈጥሩት ግጭትና አገራ ባካሄዷቸው ጦርነቶች ሕይወታቸውን ካጡ ሰዎች ይልቅ በወረርሽኞች የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው። ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ የተከሰቱ ወረርሽኞችም የአዳጊ አገራትን ብቻ ሳይሆን ያደጉ አገራትን የጤና ዘርፍ መፈተናቸውና እግር በእግር እየተከተሉ ለውጥ እንዲያደርጉ ማስገደዳቸው አልቀረም።
ወረርሽኝ የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ ግብረ መልስ የሚፈልግ ነው። ያም ብቻ ሳይሆን የግል ሆፒታሎችና ኪሊኒኮችም ሸክሙን በማገዝ በኩል የራሳቸው ሚና ይኖራቸዋል፤ ሊኖቸራውም ይገባል።
እንደሚታወቀው የሕክምና ተቋማት ከድንገተኛ ሕክምና በተጨማሪ የተመላላሽ ሕክምና፣ የክትትል ክፍል፣ የአስተኝቶ ማከም፣ የቀዶ ጥገና፣ የወሊድ እንዲሁም የክትባት አገልግሎት ይሰጣሉ። እናም እንደ ዓለምነሽ ተመላላሽ ክትትል ያላቸውን ጨምሮ የተለያየ የጤና አገልግሎት ያገኙ የነበሩና የታጎለባቸው ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም።
የሕክምና ባለሞያዎችና ተቋማትም የቫይረሱ ምልክት ካታየባችሁና የከፋና አጣዳፊ ሕመም ካልሆነ በቀር በቤታችሁ ራሳችሁን አስታሙ፣ ጤናችሁንም በቤታችሁ ጠብቁ ብለዋል።
‹የጤና ወግ› የተሰኘው ድረ ገጽ በመረጃ እና በምርምር የተደገፉ፣ ጤና ነክ መረጃዎችን በተለያየ ቋንቋ፣ በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተዘጋጁ ጽሑፎችን የሚያደርስ ገጽ ነው። ከሰሞኑም ጉዳዮን ሁሉ በኮሮና ላይ ያደረገ ሲሆን፣ ወረርሽኙ ከተለያየ አንጻር ስለሚያሳድረው ተጽእኖና ሰዎች በጉዳዩ ስላላቸው ጥያቄ የተለያዩ ሞያዊ አስተያየቶችን አኑረውበታል።
ከዚህም መካከል በዚህ ጉዳይ ላይ ሐሳባቸውን ያካፈሉት ዶክተር ቃልኪዳን ካሳዬ፣ የኮቪድ19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመቋቋም የሕክምና ተቋማት የተለያዩ ጥረቶችን እያረጉ ይገኛሉ በማለት ይጀምራሉ። አያይዘውም ዋናው ወረርሽኙ ቢሆንም፣ ከወረርሽኙ ባልተናነሰ መልኩ ከባድ ፈተና የሚሆነው ከዚህ ውጪ ያሉ ሕመምተኞች ክትትል ነው በማለት ይጠቅሳሉ።
ለዚህም ማሳያ የሚሆን በ2015 የተሠራን ጥናታዊ ጽሑፍ አጣቅሰዋል። ይህም ወረርሽኞች በተከሰቱ ሰዓት ሰዎች በበሽታው እንዳንያዝ በማለት ወደ ሕክምና ተቋማት አለመሄዳቸው ሲሆን ሆስፒታሎችም በአዲስ በሽተኞች መጣበባቸው ነው ይላሉ።
አያይዘውም ወረርሽኙ ሌሎች አገልግሎቶችን የሚያዳክምበት ምክንያት ነው ያሉትን ዘርዝረዋል። አንደኛ ያሉትም በቫይረሱ የመያዝ ስጋት ሲሆን፣ በዚህ ምክንያት ታካሚዎች ወደ ሕክምና ማእከላት አለመሄዳቸው ነው። በተያያዘም ራሳቸው የሕክምና ተቋማት ለወረርሽኝ ዝግጅት ሲባል ብዙ ክፍሎቻቸው አገልግሎት ማቆማቸው ነው።
ይህ መሆኑ ምን ያስከትላል ለሚለው የሕክምና ባለሞያዋ ምላሹን በጽሑፋቸው አስፍረዋል። በምሳሌነትም በምዕራብ አፍሪካ ተከስቶ የነበረውን የኢቦላ ወረርሽኝ የጠቀሱ ሲሆን፣ ወረርሽኙ በቀጥታ ካመጣው ሞት በተጨማሮ ከ11 ሺሕ በላይ ሰዎች የሕክምና ክትትል በማጣት ሕይወታቸው አልፏል በማለት አውስተዋል።
አያይዘውም የስኳር እና የደም ግፊት ሕመምተኞች በየጊዜው ክትትል ካላደረጉ አደገኛ ለሆኑ እንደ ስትሮክ እና የድንገተኛ የልብ አደጋ አልፎም ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ ያስረዳሉ። ተገቢ የወሊድ ክትትል አለማድረግም እናቶች በወሊድ ጊዜ የሚገጥማቸውን ችግሮች በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ሲሉ አሳስበዋል።
የልጆች በጊዜው ክትባት አለማግኘት ለተለያዩ ሕመሞች ተጋላጭ የሚያደርጋቸው መሆኑ፣ የኤች አይ ቪ ሕመምተኞች መድኃኒት ካቋረጡና በአግባቡ ካልወሰዱ ለሌሎች በሽታዎች ተጋላጭ መሆናቸውን ወዘተም አያይዘው አንስተዋል። እነዚህም ሁሉ ዋና ርዕሰ ጉዳይ በሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ውስጥ ያልታዩ ወረርሽኞች ሆነው ሊመዘገቡ የሚችሉ ናቸው።
ኮሮና በእናቶችና በሕጻናት ላይ
በውጪ አገራት ልምድ መሠረት፣ በተለይ የኮሮና ቫይረስን መከሰት ተከትሎ የአዋላጅ ሐኪሞችና ነርሶች እጥረት እንደተከሰተ የሚያነሱት ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን ያካፈሉት ዶክተር ኤልያስ ገብሩ ናቸው። የጅማ ዩኒቨርሲቲ የጤና ማእከል የሥነ አእምሮ ክፍል ስፔሻሊቲ ትምህርት ተከታታይ የሆኑት ኤልያስ፣ እንዲህ ያለ ስህተት በኢትዮጵያ ግን መደገም የለበትም ሲሉ ያሳስባሉ።
አያይዘውም በተለይ ከሥነ ተዋልዶና ከሕጻናት ጤና ጋር በተገናኘ፣ በወሊድ ጊዜ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ የነበሩ አካሄዶችን ወደ ኋላ ይጎትታል የሚል ስጋታቸውን ጠቅሰዋል። ይህም የጨቅላ ሕጻናትን ሞት ጭምር ከፍ የሚያደርገው ነው።
ዶክተር ትንሣኤ በዛው በጤና ወግ የሕክምና ባለሞያዎች ገጽ ላይ ባጋሩት ጽሑፍ፣ የወረርሽኙ ተጓዳኝ ጉዳት ብቻ ሳይሆን ራሱ ቫይረሱ በሕጻናት ላይ ሊያደርስ ስለሚችለው ተጽእኖ ጠቃቅሰዋል። ቫይረሱ በሕጻናት ላይ ስላለውና ስለሚኖረው ተጽእኖ በከፊል አስረድተዋል። በዚህም እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት እና አዳጊዎች ከዓለም ሕዝብ ውስጥ 29.3 በመቶ ድርሻ እንደሚይዙ አስታውቀዋል።
አሁን ያለው የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ በጽንስ ወቅት ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፉ ነገር ይህ ነው የተባለ ጥናት የተደረገበት አይደለም። ይሁንና በተመዘገቡ ጥቂት ነፍሰጡር የነበሩ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች መሠረት ሲታይ፣ የወለዷቸው ልጆች ከቫይረሱ ነጻ ሆነው እንደተወለዱ ዶከተር ትንሣኤ ጠቅሰዋል።
በአገራችን ከተመዘገቡ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መካከል የዘጠኝ ወር ልጅ እንደሚገኝበት ይታወሳል። ይህም ቫይረሱ ልጆችን ሊይዝ እንደሚችል በቅርብ የታየ አንዱ ማረጋገጫ ነው። ታድያ በቻይናም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 72 ሺሕ በነበረበት ሰዓት፣ ከዛ ውስጥ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የነበረው 965 እንደሆኑ ሲጠቀስ፣ አንድ ልጅ ብቻ ሕይወቱ አልፏል።
ምን ይደረግ?
በግሩም አጠቃላይ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶክተር ብሩክ ዓለማየሁ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በሚሠሩበት ሆስፒታል ያለውን አሠራር ለማስቃኘት ሞክረዋል። በሆስፒታሉ ለኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ክትትልና ቁጥጥር ብቻ ቡድን ተቋቁሟል ብለዋል። ይህም ከተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነትና ቅንጅት ጨምሮ ስለቫይረሱ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ነው።
ይህ የተደረገው መደበኛ የጤና አገልግሎቶችን መስጠት እንዳይታጎልና እንዳይቀር ለማስቻል ነው ብለዋል። በሆስፒታሉ የደም ካንሰርና የኩላሊት እንዲሁም መሰል የጤና እንክብካቤ አገልግሎቶች የሚሰጡ መሆኑን ጠቅሰው፣ እነዚህ ሰዎች ሕክምና እያገኙ ካልቆዩ በሕይወት መቆየት አይችሉም ሲሉ ጠቅሰዋል። እናም ወረርሽኙን ለመከላከል የተለየ ቡድን መዋቀሩ እነዚህንም መደበኛ ታካሚዎች ለመከታተልና ሕክምና እንዳያቋርጡ ለማድረግ ይረዳል ብለዋል።
ይህን እንደ አንድ የሕክምና አገልግሎት መስጫ ተቋም አደረጉት እንጂ፣ እንደ መንግሥት ግን ቻይና የተጠቀመችውን መንገድ መጠቀም ጠቃሚ ነው ሲሉ ያስረዳሉ። ‹‹በአገራችን አሁን ላይ ሁሉም ሆስፒታሎች ለቫይረሱ ተዘጋጁ ተብለዋል። በዚህ መልክ ግን ሊሆን አይችልም። የተወሰኑ ሆስፒታሊች በዚህ ላይ ተለይተው መቀመጥ አለባቸው። የኩላሊት እጥበት ታካሚዎችና አጣዳፊ ቀዶ ጥገና የሚፈልጉ ሰዎች በመሃል ሊጎዱ ስለሚችሉ፣ አዲስ አበባ ላይ እንዲሁም በክልል ከተሞች የተወሰኑትን ለይቶ፣ እነዛ ቦታዎች ነባሩን አገልግሎት እንደውም አካክሰው የሚሠሩበት መንገድ ቢኖር ጥሩ ነው።›› ሲሉም ምክረ ሐሳባቸውን ለግሰዋል።
እንደ ብሩክ ገለጻ ከሆነ በሌሎች በሽታዎች የጤና እክል ላይ ያሉና የሕክምና ክትትል የሚፈልጉ ሰዎች፣ከኮሮና ቫይረስ ጉዳት ባልተናነሰ አደጋ ላይ ይወድቃሉ የሚል ስጋት አለን ብለዋል።
‹‹እነዚህ ሰዎች እድል ላያገኙ ነው እያልን እንጨነቃለን።›› ሲሉም ስጋታቸውን አካፍለዋል። ሐሳቡንም ለመንግሥት እንዳቀረቡና ተግባራዊ በማድረግ በኩልም እንቅስቃሴዎች እየተጠበቁ ስለመሆናቸው አስረድተዋል።
ምን ይተርፈናል?
ከወራት በፊት ነበር የሕክምና ባለሞያዎች ድምጻቸውን ሲያሰሙ የነበረው። ይህም ለሕክምና ባለሞያዎች ሊደረግ ከሚገባው ድጋፍ አንስቶ ለዘርፉ የሚመደበውን በጀት የሚያጠይቅ ነበር። ይህንንም የሚያስታውሱት ዶክተር ኤልያስ፣ ለጤና ዘርፍ የሚመደበውን በጀት ይተቻሉ።
‹‹ለጤና የሚሰጠው በጀት ከጠቅላላው አምስት በመቶ በታች ነው። በዓለም ጤና ድርጅት ግን ቢያንስ 15 በመቶ የአገር በጀት ጤና ላይ እንዲመደብ ይታዘዛል።›› ሲሉም ጠቅሰዋል። በዚሁ አያይዘው የኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ብዙ የሚቀረው አለ ያሉ ሲሆን፣ አሁን በታየው የኮሮና ቫይረስ እንኳ ሌላው አገር በአንድ ሆስፒታል ያለው የቬንትሌተር መጠን በኢትዮጵያ ግን እንደ አገር አለ የሚባል ከ‹ብዙ› የሚቆጠር መሆኑን በሐዘኔታ ይጠቅሳሉ።
‹‹ይህ ለሕዝብ ማንቂያ ደወል ነው መሆን ያለበት። በምን እየታከመና እንዴት አገልግሎት እየሰጠን እንደሆነ ማወቅ አለበት።›› በማለት ያክላሉ። ይህም ወረርሽኝ ለዘርፉ ተጨማሪ በጀት እንደሚያስፈልግ፣ ጤና ከምንም በላይ መቅደም ያለበት ጉዳይ እንደሆነና በመሠረተ ልማትም ሆነ በቁሳቁስ መሟላት የሚቀረው ብዙ ነገር እንዳለ፣ አስተማማኝ የጤና ሥርዓት አለመኖሩና አስፈላጊ መሆኑ ላይ ማረጋጋጫ የሚሰጥ ጉዳይ ይሆናል።
ይህ ምንአልባት እንደ ኤልያስ ያሉ የሕክምና ባለሞያዎች ይኖራል ብለው የሚጠብቁት ከወረርሽኙ ማለፍ በኋላ የሚጠበቅ የአመለካከት ለውጥ ነው። እርግጥ ነው! አንድ ወረርሽኝ ተከስቶ ካለፈ በኋላ ብዙዎች ላይ የማይሽር ጠባሳ ከማሳረፉ በላይ ዓለምን እያደር አስተምሯታል። ይሁንና የጤና ዘርፉ ግን እንኳን በደሃይቱ አገር ኢትዮጵያ በሠለጠኑት አውሮፓውያን እነጣልያን እንዲሁም በኃያሏ አገር አሜሪካም የተማሩትን ሲተገብሩ አልታየም።
በአንጻሩ የኢቦላ ወረርሽኝ በተለይም ለአፍሪካ የጤናው ዘርፍ መነቃቃት እንደፈጠረ ይነገራል። ይህም ካስከተለው የብዙ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ጎን ለጎን፣ በኋላ ላይ ለመንግሥትና ለሕዝብ ያቆየው ትምህርትና ያስጨበጠው ግንዛቤ ወሳኝ ነው። ለኢትዮጵያ እንደዛ የሆነላት ባይሆንም፣ ዶክተር ብሩክ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት አስተያየት የታየው ትብብር የሚደነቅ ነው ብለዋል። ተቋማት፣ የመንግሥት፣ የግል ሆስፒታሎች ጋር የተወሰነ መደማመጥ ታይቷል። ይህ ግን አሁንም የሚቀረውና ሊጠነክር የሚገባ ነው፤ እንደ ባለሞያው አስተያየት።
ዶክተር ኤልያስ ያነሱት ተያያዥ ነጥብ የታዩ መልካም ተግባራትን እንዲሁም የፈጠራ ሥራዎችን ነው። በአንድ ጎን የታዩ በጎ አድራጎቶች ሲሆኑ፣ በተጓዳኝ የፈጠራ ሥራዎች ተበራክተዋል። ከዚህም መካከል ቬንትሌተር የሠሩ ወጣቶችን አንስተዋል። ‹‹ይህ ጥሩ ነው። ግን ከጤና የሚበልጥ ነገር እንደሌለ ከዚህ በላይ የሚያስተምር ነገር አይመጣም። እና በኢኮኖሚም በፖለቲካውም ተጽእኖ ይፈጥራል። በዚህም ለውጥ ያመጣል ብዬ አስባለሁ።›› ብለዋል።
ምን ይበጃል?
አሁንም ቢሆን የሕክምና ባለሞያዎች የሚመክሩት፣ ማኅበረሰቡ ግንዛቤ ሊኖረውና ሊሰጠው ይገባል የሚለው ላይ ነው። በተለይም ከቫይረሱ ጋር የተገናኘ አልያም በጣም አጣዳፊ የሆነ ሕመም ካልሆነ በቀር፣ ወደ ሕክምና ማእከል ከመሄድ እንዲቆጠቡ ነው። ‹‹ቀለል ያሉ በሽታዎችን ላናክም እንችላለን። ይህን ማኅበረሰቡ ማወቅ አለበት። ለሕይወት አስጊ የሆነ ሲሆን ነው ወደ ጤና ማእከላት መሄድ ያለባቸው።›› በማለትም አስረድተዋል።
ይህ ካልሆነ ግን በአንድ ወገን ባለሞያዎችን ስለሚያዋክብና ሥራ ስለሚጨምር አልፎም ለሕክምና የሄደን ሰው ለኮቪድ 19 የኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ ስለሚያደርግ፣ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።
ዴሎይት የተሰኘ የሕክምና ጉዳይ ላይ የተሠሩ ጥናታዊ ወረቀቶችንና ምክረ ሐሳቦችን የሚያቀብል ድረ ገጽ፣ ባለድርሻ የሚባሉ በጤና ዘርፉ ላይ የሚገኙ አካላት ይህን ልብ ሊሉ ይገባል ሲል የተለያዩ ነጥቦችን ይጠቅሳል። አንደኛው እንደ ወረርሽኝ ያሉ ድንገተኛ አደጋዎች የሚስተናገዱበትን ስርዓት መፍጠር ወይም ማሻሻል ነው።
ለሁሉም ነገር ‹ሠርገኛ መጣ› ከማለት፣ ቀድሞ ተሰናድቶ ቢመጣም ባይመጣም መጠበቅ እንደማለት ነው። ይህም የክስተቱን አሉታዊ ተጽእኖ እንዳይበረታና በትኩሱ ለመያዝ የሚረዳ ነው ተብሎ ይታመናል። ይህም ኃላፊነትና ሥልጣንን እንዲሁም ድርሻን ለመለየት፣ ያለውን ሀብት ለማስተባበር ያግዛል።
ለወረርሽኞች በቂና ተገቢ ምላሽ ሰጥቶ እንዲሁም መደበኛውን ሥራ ለማከናወንም የሕክምና ተቋማት ተከታዮቹን አካሄዶች እንዲጠቀሙ ሲል ምክረ ሐሳብ ያቀብላል። አንደኛው በመደበኛ አሠራር አስፈላጊ የሆኑትን የጤና ግብዓቶች ሁሉ በተለያየ የአደጋ መጠንን ግምት ውስጥ በማስገባት ዝግጁ ማድረግ ነው። ሌላው ደግሞ ለሕክምና አስፈላጊ የሆነ ግብዓት አቅራቢዎች ጋር ዘላቂ ግንኙነት መፍጠርና ያንን ማጽናት ነው። የግል የጤና ተቋማት ከመንግሥት ጋር ጥብቅ ግንኙነትን መቀጠል ያስፈልጋቸዋልም ተብሎም ይመከራል።
ታይለር ስሚዝና ባልደረቦቻቸው በሠሩትና የሕክምና ተቋማትን በወረርሽኞች መካከል ጤናማ አድርጎ ማቆየትን የተመለከተው ጥናታዊ ጽሑፋቸው፣ በዋናነት ለአንድ ወረርሽኝ ተብሎ በሚደረግ እንቅስቃሴና በመደበኛ የጤና አጠባበቅና ክትትል አገልግሎት መካከል ያለውን ግንኙነት ላይ ያጠነጥናል።
በእነዚህ በኹለቱ መካከል ያለው ግንኙነት፣ ለማሳለጥ የተለያዩ ጥናቶች ለዘመናት ተካሂደዋል ይላሉ፣ አጥኚዎቹ። ታድያ ውጤታማ የሆነ የበሽታ ወይም የሕመም ቁጥጥር ለማድረግ፣ የጤና ግብዓቶች በጠቅላላ፣ በአግባቡ መሟላትና ጥቅም ላይ መዋል አለባቸው። ይህም ከገንዘብና በጀት ፍሰት ተነስቶ የመሠረተ ልማትና ግንባታ፣ የግብዓት አቅርቦት፣ አያያዝና ከአመራር፣ ከሰው ኃይልና አቅም ጭምር ጋር ግንኙነት ያለው ነው። በመጨረሻም እነዚህን የማስተባበርና የማስተሳሰር አቅም ይጠይቃል ይላሉ።
ዶክተር ቃልኪዳን በበኩላቸው ሌላው የጤና ዘርፍ በአስገዳጅ ሁኔታ ቸል መባሉና ‹ይቆየን› የሚል መልእክት መተላለፉ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን መሠረት አድርገው ያነሳሉ። በኢትዮጵያም በዚህ ሰዓት ይህ እንዳይፈጠር ምን ማድረግ እንችላለን በሚል ምክረ ሐሳባቸውን አካፍለዋል። በዚህም መሠረት ጤና ጣቢያዎች የቆየ ሕመም ያለባቸውን ታካሚዎቻቸውን በስልክ ከሐኪም ምክር እና ክትትል የሚያገኙበትን አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።
‹‹በዚህ ረገድ ለምሳሌ እንደ ጥቁር አንበሳ ባሉ አንዳንድ አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ ሆስፒታሎች በተለያዩ ክትትል ክፍሎች የስልክ መስመር ተዘጋጅቶ ታካሚዎች እየደወሉ ሕክምናቸውን እንዲያገኙ ተደርጓል።›› በማለትም ነባራዊውን ሁኔታ ያስረዳሉ። እንዲሁም መድኃኒቶችን ረዘም ላለ ጊዜ በማዘዝ የታካሚዎችን ምልልስ መቀነስ፣ ታካሚዎች በራሳቸው ቤታቸው ውስጥ የደም ግፊታቸውን እና የስኳር መጠናቸውን እንዲለኩ ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል፣ በተጨማሪ የሰጡት ሐሳብ ነው።
እንደ ቀደሙት የሕክምና ባለሞያዎች እርሳቸውም ከኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ውጪ ያሉ ታካሚዎች ለብቻ አገልግሎት የሚያገኙባቸውን ተቋማት መለየትና ዝግ የሆኑ ትምህርት ቤቶችን ሙሉ በሙሉ ወረርሽኝ ለመከላከል የሚችሉ ተቋማትን ማድረግ ተገቢ እንደሆነ መክረዋል።
ዶክተር ኤልያስም በተመሳሳይ ይህን የተለያየ ድረሻ የማከፋፈል ሥራ ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ብለዋል። እርሳቸው አሁን ላይ አገልግሎት እየሰጡበት ባለው በጅማ ሆስፒታል በኮሮና ብቻ አተኩሮ የሚሠራ ቡድን መቋቋሙንም አውስተዋል። ‹‹ከ200 በላይ አልጋ ተዘጋጅቷል። ለጊዜያዊ ማቆያ የተዘጋጀም አለ። በጅማ ዩኒቨርስቲም ደረጃ በትብብር እየተሠራ ነው። ሳኒታይዘር ማከፋፈል ሥራም እየተሠራ ነው። ግን ይህ ይበቃል ማለት አይደለም። ሁሉም በትኩረት መዘጋጀት ነው ያለበት።›› ብለዋል።
በድርሻ ክፍፍሉ ወረርሽኙ ላይ የተወሰኑ ባለሞያዎች በሙሉ ትኩረት እንዲሠሩ ማድረግና የተቀሩት መደበኛውን አገልግሎት በመጠኑም ቢሆን እንዲሰጡ ማድረጉ ላይ አሁንም ትኩረት ያስፈልጋል ብለዋል።‹‹እና ይህን ጤና ሚኒስቴር ቢያዘጋጅ፣ የተወሰነ ዶክተር ተለይቶ አንገብጋቢ በሽታዎች ባሉበት ሰው መመደብ ይቻላል።›› የኤልያስ አስተያየት ነው።
ዶክተር ትንሣኤ የደም ልገሳ ነገርን አንስተዋል። ይህንንም መሠረት አድርገው ባሰፈሩት ሐሳብ እንዲህ ይላሉ፣ ‹‹በአጠቃላይ የመተንፈሻ አካላት ሕመሞችን የሚያመጡ እንደ ኮሮና ያሉ ቫይረሶች በደም ንክኪ አይተላለፉም። እስከ ዛሬም በደም ንክኪ የተላለፈ የኮቪድ 19 ሕመም ሪፖርት አልተደረገም።››
እናም በዚህ ድንገተኛ ወረርሽኝ ጊዜ ደም መለገስ ጤናን ይጎዳል ወይ ብሎ ለሚጠይቅ፣ ደም እንዳይለግሱ የሚከለክል ሌላ የጤና ሁኔታና እክል እስከሌለ ድረስ ያለጉዳት መለገስ ይቻላል ብለዋል። በአጠቃላይ ደም ልገሳ እንዳይቀንስም የኢትዮጵያ የደም ባንክ አገልግሎት የቤት ለቤት የደም ልገሳዎችን ከበጎ ፍቃደኞች መሰብሰብ ይችላል፣ የሚድያ ተቋማትም ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እና ማስተማር አለባቸው ሲሉ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።
የኢትዮጵያ የደም ባንክ አገልግሎትም በጎ ፍቃደኞች ለመለገስ ሲቀርቡ የኮቪድ 19 ቫይረስ ሕመም መከላከያ ሥራዎች ማሟላት አለበት ብለዋል። በተያያዘም ቫይረሱ ከእናት ወደ አራስ ሕፃናት እንዳይተላለፍ፣ ተገቢውን ሁሉ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
‹‹በኢትዮጵያውያን ባህል አንዲት እናት በምትወልድ ጊዜ በተለይ የመጀመርያዎቹ ኹለት ወራት ላይ ብዙ ጠያቂዎች ቤቷ ይመላለሳሉ። ስለዚህም በዚህ ወቅት አራስ ሕፃናት የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ሕመም እና ሌሎችም የመተንፈሻ አካላት ሕመሞች ካለው ጠያቂ ሕመም እንዳይጋባባቸው ኹለት ዋና መንገዶችን መጠቀም ይቻላል።›› ሲሉ ጠቅሰዋል።
አንደኛ ያሉት ጠያቂዎች በርቀት እንዲቀመጡ ማድረግ ነው። ይህም የዓለም የጤና ድርጅት ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው እንዳይተላለፍ የአንድ ሜትር ርቀትን ሲጠቁም፣ የአሜሪካው የበሽታ መከላከያ እና ቁጥጥር ተቋም ኹለት ሜትሮችን ይጠቁማል። በዚህ ርቀት መሆን ተገቢ ሆኖ ሳለ፣ ከተቻለ ግን በተለይም አራስ ሕፃናት ወደተኙበት ክፍል ውስጥ ከናካቴው ጠያቂዎች እንዳይገቡ ማድረግ ያስፈልጋል።
ሌላውና ኹለተኛ ብለው የጠቀሱት እናቶች እና አራስ ሕፃናት የሚተኙበትን ክፍሎች በቂ የአየር ዝውውር እንዲያገኝ ማድረግን ነው።
ቅጽ 2 ቁጥር 75 ሚያዝያ 3 2012