ጊዜውን ባላገናዘበ ሁኔታ ፈቃዳችን ተሰርዞብናል ሲሉ ባለሃብቶች ቅሬታ አሰሙ

0
370

ጋምቤላ ክልል በእርሻ ዘርፍ መሬት ወስደው ያላለሙ የ285 ባለሃብቶችን የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰረዙ ተገቢ ያልሆነና ጊዜውንም ያላማከለ ነው ሲሉ በክልሉ በእርሻ ዘርፍ ተሰማርተው የነበሩ ባለሀብቶች ቅሬታቸውን ገለፁ።

የባለሀብቶቹ የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰረዙን ተከትሎ በጋምቤላ ኢንቨስተሮች ማኅበር ሊቀ መንበር ጊዜውን የጠበቀ ውሳኔ አይደለም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በእርሻ ኢንቨስትመንት ካለፈው አራት ዓመታት ወዲህ በተደጋጋሚ ውይይት ሲደረግበት የነበረ ጉዳይ ነው የሚሉት የማኅበሩ ሊቀመንበር የማነ ሰይፉ፣ ነገር ግን እንድንሠራ እድሉን እና ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ይልቅ ወከባ በዝቶበታል ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ሊቀመንበሩ አያይዘውም የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት በፊት ይሄን እርምጃ ሊወስዱት አስበው ተወያይተን ቀርቶ ነበር የሚሉት የማነ፣ ነገር ግን ይህን ለመወያየት እና ወደ ሚመለከተው አካል ቅሬታ ማቅረብ የማይቻልበትን ጊዜ ጠብቀው ውሳኔ ማስተላለፋቸው ተገቢ እንዳልሆነ አስታውቀዋል።

አዲስ ማለዳ ከማኅበሩ ያገኘችው መረጃ እንደሚያመላክተው ከሆነ መጀመርያ ማኅበሩን ተቀላቅለው ከነበሩት 650 የሚሆኑት ባልታወቀ ምክንያት 300 የሚደርሱት ከማኅበሩ እንዲወጡ መደረጉን እና አሁን ባለው ሁኔታ በቋሚነት ብድሩንም ተበድረው እየሠሩ ያሉት 46 እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

‹‹ከዛም በተጨማሪ ከልማት ባንክ ተወስዶ ባለ መመለሱ ምክንያት 36 ባለሀብቶችን የኢንቨስትመንት ፈቃዳቸው መሰረዙን የክልሉ መስተዳድር መግለፃቸው ስህተት ነው›› የሚሉት የማነ፣ በጉዳዩ ውሳኔ ሊሰጥበት የሚገባ ትክክለኛው አካል ልማት ባንክ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ‹‹ለዚህም ከልማት ባንክ ጋር በተደጋጋሚ የክፍያ ግዜው እንዲራዘም እየጠየቅን ነበር›› በማለት አስታውሰዋል።

ከዛም በተጨማሪ የነበረው ስርአት ሥራዎችን የተፈለገውን ያህል ለመሥራት የተመቻቸ አልነበረም ያሉት ሊቀመንበሩ ‹‹ከትርፉ ይልቅ ኪሳራው የጎላበት ሂደት እና የብድር ስርዓት ነበር›› በማለት ገልፀዋል። እንደ እርሳቸው ገለፃ ከሆነ በጋምቤላ ክልል በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ መሬት ወስደው ያላለሙ ተብለው 285 ባለሀብቶችን የኢንቨስትመንት ፈቃዳቸው መሰረዙን የክልሉ መስተዳድር መግለፃቸውን ተከትሎ፣ ውሳኔው ትክከለኛ እና ጊዜውን ያልጠበቀ ከመሆኑም በላይ ‹‹ምክንያቱ ላይ ውይይት ሳይደረግ እና ለባለሀብቶቹ ሳይነገር መደረጉ ከተጠያቂነት ለመዳን ተብሎ ነው›› ብለዋል።

ከዛም በተጨማሪ የኢንቨስትመንት ፈቃዳቸው ከተሰረዘባቸው ባለሀብቶች መካከል 36 የሚደርሱት ከልማት ባንክ ብድር የወሰዱ ናቸው የተባለውም መሥርያ እድሉ የተመቻቸ ሁኔታ ባለመሟላቱ እና በክልሉ ያለውም የሰላም ሁኔታ ሥራው በተገቢው መንገድ ተከናውኖ ብድሩ እንዳይመለስ ሆኗል ብለዋል። ከዛም በተጨማሪ ‹‹የብድር ስርአቱ 30/70 እንደሆነ ነገር ግን ቅድሚያ ብድሩን ለማግኘት ባለሀብቱ በራሱ ወጪ የእርሻ ቦታውን ለማስተካከል እና ለልማት ቀሪውን ብድር ለማግኘት እንድትችሉ በሚል 30 በመቶ ያህሉን ወጪ በማውጣት የቅድመ ሥራዎች እንቅስቃሴ እንድንጀምር አድርገው ነበር›› የሚሉት ሊቀ መንበሩ ከዛ በኋላ ግን የብድር ስርአቱ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ ነበር እንዲደርስ የተደረገው ብለዋል።

በዛም ምክንያት ባለሀብቱ ኪሳራ ውስጥ እንደገባ እና የያዘውን ቦታ ለልማት ማስቀጠል አለመቻሉን ተናግረዋል። በዛም ምክንያት በተደጋጋሚ ከክልሉ እና ከልማት ባንክ ጋር በተደጋጋሚ ውይይት ተደርጎ ነበር። የክፍያ ጊዜ ለተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ተጠይቆም ነበር ሲሉ የማነ ሰይፉ የጋምቤላ ኢንቨስትመንት ማኅበር ሊቀ መንበር ገልፀዋል።

አዲስ ማለዳ የተፈጠረውን ጉዳይ በሚመለከት ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ መረጃ ለማግኘት ሙከራ ያደረገች ሲሆን፣ ጉዳዩ እየተጣራ እንደሆነ እና ሌላው በሕግ የተያዘ ጉዳይ በመሆኑ ዝርዝር መረጃዎችን ከመስጠት ለጊዜው መቆጠባቸውን በባንኩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ፍሬው መኳንንት በኩል ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 78 ሚያዝያ 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here