ጤና ቢሮው ከሦስት ሚሊዮን በላይ የቤት ለቤት የሙቀት ልየታ ማድረጉን አስታወቀ

0
711

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ በ18 ቀናት ውስጥ ሦስት ሚሊዮን 75 ሺሕ ሰዎች የቤት ለቤት የኮሮና ቫይረስ ምልክትና የሙቀት ልየታ ማድረጉን አስታወቀ። 935 ሺሕ 500 ቤቶች የልየታ ሥራው የተካሄደባቸው እንደሆነ ጤና ቢሮው ጨምሮ ገልጿል።

የከተማ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ ሚያዚያ 2/2012 የቤት ለቤት የኮሮና ቫይረስ የሙቀት ልየታ የጀመረ ሲሆን፣ በየክፈለ ከተማው ከተደረገው የ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ልየታ 925 ሰዎች የጉንፋን ዓይነት ምልክት ታይቶባቸው 21 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው ወደ ለይቶ ማቆያ መግባታቸውንና ቀሪዎቹ 904 ሰዎች በጤና ባለሙዎች ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሙሉጌታ እንዳለ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው ወደ ለይቶ ማቆያ ከገቡ 21 ሰዎች ውስጥ የስድስት ሰዎች የላብራቶሪ ውጤት የታወቀ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ የአምስቱ ሰዎች ውጤት ከቫይረስ ነፃ መሆናቸውን እና አንድ ሰው ቫይረሱ እንደተገኘባት ሙሉጌታ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። ቫይረሱ የተገኘባት ሴት የቂርቆስ ክፍል ከተማ ነዋሪ ስትሆን፣ ከተጠቂዋ ጋር ንክኪ የነበራቸው 22 ሰዎች ተለይተው ስድስቱ ወደ ለይቶ ማቆያ ገብተዋል፡፡ ቀሪዎቹ 16 ሰዎች በቤታቸው ራሳቸውን ለይተው ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ዶክተር ሙሉጌታ ተናግረዋል።

እንደ ምክትል ኃላፊው ገለጻ በአዲስ አበባ እየተደረገ ያለው የቤት ለቤት የሙቀትና ጉንፋን የሚመስል ነገር የሚታይባቸውን ሰዎች የመለየት ሥራ በዋናነት ዓላማው የቫይረሱ ስርጭት ከማኅበረሰቡ ውስጥ ገብቶ ከሆነ ለመለየት እና የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመግታት የታሰበ መሆኑን ጠቅሰዋል። ሙሉጌታ አክለውም ለልየታ የተሰማሩ ባለሙያዎች ከሙቀት ልኬት ጎን ለጎን ኅብረተሰቡ ስለ ቫይረሱ ግንዛቤ እንዲኖረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የልየታ ሥራው የእቅዱን 90 በመቶ ማሳካቱንም ምክትል ኃላፊው ለአዲሰ ማለዳ የተነገሩ ሲሆን፣ በልየታ ሥራው ላይ የተሳተፉ አካላት የጤና ባለሙያዎች፣ ፖሊሶች፣ መምህራን እና ሌሎችም በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተሳትፈዋል ተብሏል።

የጤና ባለሙያዎች እግረ መንገዳቸውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየሠሩ ቢሆንም ኅብረተሰቡ የተባለውን ሙሉ በሙሉ መከወን እንዳልቻለ ሙሉጌታ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ኅብረተሰቡ አንዱን ተግባራዊ አድርጎ አንዱን ተግባራዊ የማያደርግ ከሆነ ከቫይረሱ ከመጠቃት ለመዳን እንደማይቻል ሙሉጌታ ጨምረው አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ በከተማዋ የቤት ለቤት የኮሮና ቫይረስ ልየታ ለማካሄድ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንዲሠሩ ከስምንት ሺሕ በላይ የጤና ባለሙያዎችና በጎ ፈቃደኞች ማሰማራቱን ምክትል ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። ቢሮው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎችን የኮሮና ቫይረስ ልየታ ለማድረግ አቅዶ በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንዳለም ምክትል ኃላፊዉ ጠቁመዋል።

ነገር ግን በአዲስ አበባ እየታየ ያለው የኅብረተሰቡ ጥንቃቄ በእጅጉ አሳሳቢ መሆኑን መሉጌታ አንስተው፣ አሁን አሁን የመዘናጋት ሁኔታዎች በከተማው በስፋት እየታየ መሆኑን ያወሱት ሙሉጌታ፣ በተለይ በትራንስፖርት ላይ የሚደረጉ የሰልፍ መደራረቦች ኅብረተሰቡ ሊያስብበት እና ሊጠነቀቅ ይገባል ብለዋል።

አዲስ ማለዳ ለሕትመት እስከ በቃችበት ቀን ድረስ በአገር አቀፍ ደረጃ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ቁጥራቸው ይፋ የሆኑ 131 ሰዎች ሲገኙ፣ ከእነዚህ ውስጥ 3 ሰዎች ለሕልፈት ተዳርገዋል፣ 59 የሚሆኑት ያገገሙ ሲሆን 67 የሚሆኑት ደግሞ በቫይረሱ ተይዘው በለይቶ ማቆያ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው የሚገኙ እንደሆነ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 78 ሚያዝያ 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here