የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተላለፉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ግለሰቦች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈባቸው

0
986

በአማራ ክልል፣ ማዕላዊ ጎንደር ዞን በምሥራቅ ደምቢያ ወረዳ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍ ሰርግና ሌሎች ዝግጅቶችን ያከናወኑ ሁለት የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና አምስት ግለሰቦች ላይ  የቅጣት ውሳኔ ተላለፈ፡፡

የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት ከተላለፉ ውሳኔዎች አንዱ ከአራት በላይ ሆኖ መሰባሰብን መከልከል ነው፡፡ ይህም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተደንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም አዋጁን በመተላለፍ እንደ ሰርግ ያሉ በርካታ ሰዎች የሚሰባሰቡባቸውና ንክኪ የሚፈጥሩባቸው መሥተጋብሮች በድብቅና በገጠራማ አካባቢዎች ደግሞ በግልጽ እየተከወኑ ይገኛል፡፡ በምሥራቅ ደምቢያ ወረዳ የተከሰተውም ይህ ዓይነት ድርጊት መሆኑ ታውቋል፡፡

የአማራ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት እንደገለጸው የሥራ ኃላፊዎችና ግለሰቦች ቅጣቱ የተወሰነባቸው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሥርጭትን ለመከላከል ተብሎ የወጣውን አዋጅ በመተላለፋቸው ነው፡፡

እንደ የአማራ ብዙሀን መገናኛ ድርጅት ዘገባ 1ኛ ተካሣሽ አቶ መልካሙ ሲሳይ የቆላድባ ከተማ መሪ መዘጋጃ ሥራ አስኪያጅ ሚያዝያ 25 ቀን 2012 ዓ.ም ቆላድባ ከተማ ቀበሌ 02 ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ወንድማቸውን ለመዳር የቀለበት ሥነ ሥርዓት አካሂደዋል፡፡ በዕለቱም ከ50 ሰዎች በላይ በአንድ ቦታ አሰባስበው በመገኘታቸው በአዋጁ መሠረት በቀን 25/8/2012ዓ.ም ለምሥራቅ ደምቢያ ወረዳ ፍርድ ቤት ክሳቸው ቀርቦ ነበር፡፡ ተካሣሽም የቀረበባቸውን ክስ በዝርዝር በማመናቸው ፍርድ ቤቱ በ 10 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ መወሰኑ ታውቋል

እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ አቶ ሞገስ አደባ የምሥራቅ ደምቢያ ወረዳ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ናቸው፡፡ ሚያዝያ 25 ቀን 2012 አዋጁን በመተላለፍ ከመኖሪያ ቤታቸው ድግስ በማዘጋጀት በአንድ ቦታ በርካታ ሰው በማሰባሰብ ነው የተከሰሱት፡፡ ክሱን በማመናቸውም የምሥራቅ ደምቢያ ወረዳ ፍርድ ቤት በ10 ሺህ ብር እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል፡፡

በተመሣሣይም ሌላ አምስት የቆላድባ ከተማ ነዋሪዎች አዋጁን እና ደንቡን በመተላለፍ ሰርግ በማከናወናቸው ፍርድ ቤቱ ሚያዝያ 25 ቀን 2012 ዓ.ም በዋለው ችሎት ከብር 6 ሺህ እስከ 10 ሺህ ቅጣት እንደተላልፈባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ባሳለፍነው ሳምንት 4 ሺህ 737 ሰርጎች ከኅብረተሰቡ በተሰጠ ጥቆማ እና ከደጋሾች ጋር በመወያየት እንዲቋረጡ መደረጋቸውን መግለጹ ይታወሳል፡፡ 120 ደግሞ በእቢተኝነት ሰርጉን በማከናወናቸው ግለሰቦች በሕግ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እንደተጀመረባቸው ነበር ያሳወቀው ሲል አብመድ ዘግቧል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here