የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን እና ወቃታዊው የጋዜጠኝነት ፈተና

0
1020

የሕዝብ ዐይን እና አንደበት የሚባሉ ጋዜጠኞችና መገናኛ ብዙኀን በዓለም ዙሪያ ሥራቸውን እንዲሠሩና እውነትን እንዲያወጡ ቢተጉም፣ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ማለፋቸው አልቀረም። ይህም ስለታወቀ ነው ገለልተኛ አካላት አገራት በሚሰጡት የፕሬስ ነጻነትና የጋዜጠኞች መብት ዙሪያ ደረጃ ሰጥተው፣ ምስጋና እንዲሁም ወቀሳን የሚያቀርቡት። ኢትዮጵያም በዚህ ጉዳይ ከኹለት ዓመት ወዲህ እየተመሰገነች ሲሆን፣ አብርሐም ፀሐዬ ይህን በማንሳት ወደኋላ መመለስ እንዳይኖር ሲሉ ያይወቸውን ወደኋላ ሊመልሱ የሚችሉ ጉዳዮች አንስተዋል።

ታማኞቹን የሕዝብ ዘቦች ስናበረታታ አገር ትበረታለች፤ ትውልድም ይነቃል!!!
በአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1991 የ26ኛው የዩኔስኮ ኮንፈረንስ ላይ በተነሳው ሐሳብ አማካይነትና የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት፣ ከ1993 ጀምሮ በየዓመቱ ሚያዚያ 25 (May 3) የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን ሆኖ እንዲከበር ወስኗል።

ይህ የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን በተለይም የሚዲያ ነጻነቱ እምብዛም ባልዳበረባቸው አገራት የጋዜጠኝነት ሙያ በሥነ ምግባር የታነጸና ገለልተኛ እንዲሆን ወይም ከጫና ነጻ ሆነው እንዲሠሩ እንዲሁም አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው ያበረታታል። የየአገሩ መንግሥታትም የመናገር ነጻነትን ለመደገፍ ቁርጠኛ እንዲሆኑ በተለያየ መልኩ ሐሳብ ይሰጣል። የፕሬስ ነጻነት መርሆዎች ላይ ውይይትና ግምገማ ያደርጋል።

የዘንድሮው (2012/2020) አከባበር ጋዜጠኞች ለማኅበረሰቡ እየሰጡ ያሉትን ትልቅ አስተዋጽኦ ዋጋ እንስጥ የሚል እሳቤን ይዟል። ትኩረቱ ከግጭት ጋር በተያያዘ እየሠሩ ያሉትን የብዙኀን መገናኛ ባለሙያዎች የተመለከተ ሆኖ ‹ከስጋትና ከአድልዎ የራቀ ጋዜጠኝነት› የሚል መሪ ቃል አንግቧል። ለጋዜጠኝነት ሥራ ሕይወታቸውን የገበሩ ባለሙያዎችም ተገቢውን ክብርና ምስጋና እንዲሰጣቸው አስታውሷል።

እንደተለመደው አብዛዎቹ የአገራችን ብዙኀን መገናኛዎች ከተራ ዜናነት የዘለለ ትኩረት ባይሰጡትም ባሳለፍነው እሁድ ሚያዚያ 25 ይህ የዓለም አቀፉ የፕሬስ ነጻነት ቀን በብዙኀን መገናኛዎችና በማኅበራዊ ትስስር ገጾች በዓለም ደረጃ ተከብሯል። የዩኔስኮ ዳይሬክተር ጄነራል ኦውድሬይ ኧዞሌይ (Audrey Azoulay) እና የተባበሩት መንግሥታት (UN) ሴክሬተሪ ጄኔራል አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ያሉት አለ።

የኹለቱንም ሐሳብ በአጭሩ ሲጠቀለል፣ ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ የተፋለሰና አሳሳች መረጃዎች እየተዛመቱ ሕዝብ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሰለባ እንዳይሆን በሀቅ ላይ የተመሠረተና የተጣራ መረጃዎች እንዲያቀርቡ ሚዲያዎችን አደራ ብለዋል። እንደቫይረሱ ወረርሽኝ ሁሉ የመረጃ ወረረሽኝም (infodemic) አለ ሲሉም ገልጸዋል። ጉቴሬዝ ቀጥለው ‹‹አሁን ላይ ከገጠመን ወረርሽኝ ባልተናነሰ የተሳሳተ መረጃም ሌላኛው ወረርሽኝ ነው። በመሆኑም መገናኛ ብዙኀኑ የተረጋገጡ፣ ሳይንሳዊና እውነታ ላይ የተመሰረቱ ትንታኔዎችን ማቅረብ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው›› ብለዋል።

ክብርና ምስጋና ለጋዜጠኞች
ይህ የመረጃ ወረረሽኝ የአገራችንን ሕዝብም ትን እያስባለ ያለ በሽታ ነው። ከሙያው ጋር ተያይዞ ያሉትን ችግሮች እናነሳሳ ካልን ይጀመር ይሆናል እንጂ መጨረስ አይቻልም። የዳበረ የሙያ ስርዓት በመፍጠር ችግሩን መቀነስና መከላከል ይቻላል ብለን ተስፋ እናድርግ። የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን እንዳስገነዘበው በሙያቸው ላሉ ትጉህ ጋዜጠኞች ክብርና ምስጋና እንስጥ ያለውን እናስታውስና፣ ስለአገራችን የሙያ ክብር ጨረፍ እናድርግና እንለፍ።

በኢትዮጵያችን የሙያ ክብር እንዳልዳበረ እሙን ነው። በጋዜጠኝነት ሕይወታቸው ትውልድ ያነቁ፣ አገር ያዳኑ፣ በበሰለ መረጃ ጥበብን የሸመኑ ጋዜጠኞች ነበሩ፣ አሁንም አሉን። ለእነዚህ ታማኝና በልቶ ከማደር በላይ አገርን እና ሕዝብን ያገለገሉ የብዙኀን መገናኛ ባለሙያዎች ተገቢውን የክብር ምስጋና ስንሰጥ ሌሎች ሐቀኛ ጋዜጠኞችን እንፈጥራለን። ብዙ ክፍተቶችንም መሙላት እንችላለን።

የዘርፉ ምሁራን እንደሚነግሩን ጋዜጠኝነት ባለሦስት ዐይና ሙያ ነው። መንግሥት መንገድ እንዳይስት ይቆጣጠራል፤ ሕዝብ አቅጣጫ እንዳይለቅ ያነቃል። የጥፋት ዘብ፣ የመልካም ሥራም አፈ – ጉባኤ ነው። የተደበቁትን እየገለጠና እየመረመረ ወደ ሕዝብ ማዕድ ቶሎ ቶሎ የሚያቀርብ የመረጃ ‹ሼፍ›ም ነው። ሙያው ይህ ነው – ጠቀሜታው ደሞ ለሕዝብ!

ስለሆነም ታማኞቹን የሕዝብ ዘቦች ስናበረታታ አገር ትበረታለች፤ ትውልድም ይነቃል። ሙያውና ሙያተኞች በነጻነት የሚሠሩበትን ምቹ ሁኔታ እስካልፈጠርን ድረስ ግን ጉዳቱ በጥቂት ጉዳዮች ላይ ተወስኖ የሚቀር አይደለም።

ጋዜጠኝነትና ህልፈተ ሕይወት
ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል የሚባሉት ጋዜጠኞች ከሞት ጋር ቅርብ ለቅርብ የሚገናኙበት አጋጣሚም በርካታ ነው። ሰሞኑን ሞቃዲሾና ናይሮቢ ጋዜጠኞቻቸውን በሞት አጥተዋል። አንዱን ክስተት ብቻ እንይ። ኬንያ ከሥራቸው ጋር በተያያዘ 30 ጋዜጠኞችን አጥታለች። ባለፈው ዓመትም 56 ጋዜጠኞች ለህልፈት ተዳርገውባታል ብሏል፣ ካፒታል ኒውስ በዘገባው።

አንዳንዴ ጋዜጠኝነት ጠላትህን የማትለይበት ሙያ ነው። ወዳጅህም በዚያው መስመር ካንተ ጋር ጸንቶ አይቆይ ይሆናል። የጋዜጠኝነት ነገረ ሥራው አንድን እውነት ፈልቅቆ የማውጣት ጉዳይ እንጂ ለእገሌና እገሊት ብለህ የምትሠራው፣ እንዳሻህ የምትጠመዝዘው ሙያ አይደለምና ነው።

እውነቱ በጎርፍ እንደሚንገላታ ግንድ የት እንደሚያላትምህ አታውቀውም። ስለዚህም ነው አንድ ጋዜጠኛ ህሊናውና ልቦናው ብስል፣ ጥንቁቅና ሦስት ዐይና ይሁን የሚባለው። አለበለዚያማ መላተሙ ከሱም አልፎ ዳፋው ለሌላው ይተርፋል። ጋዜጠኝነት የሕዝብ ባላደራነት ነው። መንግሥት የመሆን ሌላው ገጽታ ነው። እንዲሁ ማንም የሚንቧችርበት ሙያ አይደለም። አልሆን ካለ ደግሞ ተብሎ ያለቀለትን፣ ተነግሮ የወጣለትን የዕለት ውሎ እየሰነቁ በሠላም ውሎ ማደርም ይቻል ይሆናል።

ሙያው ከሚፈቅደው ውጪ ቸል ያለ ተግባር!
‘ካፒታል ኒውስ’ እንዳስነበበው ተገዳዩ መሐመድ ሀሰን ማርጃን ኬንያዊ ጋዜጠኛ ነው። ከሥራ ወደ ቤቱ እየሄደ ሳለ ማንነታቸው ለጊዜው ያልታወቁ ሰዎች በጭካኔ ቀጥቅጠው ገድለውታል። የግድያ መንስዔውም እስከ አሁን በውል አልታወቀም። የኬንያው ሜዲካል ካውንስል ቢሮ እንደገለጸው፣ ኬንያ በሥራቸው ላይ ሳሉ 30 ጋዜጠኞችን በሞት ስታጣ ባለፈው ዓመት ብቻ ደግሞ በጥቅሉ 56 ጋዜጠኞች ለህልፈት ተዳርገውባታል።

ይህ ሟች ጋዜጠኛ የረመዳን ጾም እንደገባ በየምሽቱ ስለታላቁ ጾም ልዩ ዝግጅት እያቀረበ የነበረ ነው። ማርጃን እንዲህ ባለ የረመዳን ጾም ወቅት በልዩ ዝግጅቱ ምስጋናን ያተረፈ ታታሪና ተወዳጅ ባለሙያ ነበር ብለውለታል። የኬንያዋ ኪብራ ነዋሪዎች በሞቱ ክፉኛ አዝነዋል፤ የግዛቷን ፖሊሶች ቸልተኝነትንም አብዝተው ኮንነዋል።
እንዲህ ነው፤ ጋዜጠኛ መቼም መሣሪያ ያልታጠቀ ወታደር ነውና አንዳንድ ጊዜ ገፍቶ የመጣ ጠላት ከገጠመው የያዘው እውነት የማዳን ኃይሉ አንሶ ይገኛል። በዚህች ዓለም እውነት ፈጥኖ የማዳን ኃይል የላትም። የጋዜጠኝነት ፈተናውም ይህ ነው። ምናልባት ከሚያውቁት እውነት ሸሽቶ የመዘገብ አባዜ የሚስተዋለው ከዚህ የተነሳም ሊሆን ይችላል። አንድ አገር እንደጋዜጠኞች ላሉ ባለሙያዎቿ ጥበቃና ዋስትና የማድረግ ግዳጅ አለበት። በምንም አቋም ላይ ቢሆንም ሕዝብ ተኮር በሆነ ማንነት ላይ እስከቆመ ድረስ፣ ለጋዜጠኝነት ዋስትና ያስፈልገዋል፤ የሕዝብ አንደበት ስለሆነ!

ይህ ኬንያዊ ጋዜጠኛ ልምድ ያለው ሲሆን በናይሮቢ ደቡብ ምዕራብ በምትገኝ ኪብራ በተሰኘችው ልዩ ግዛት በፓሞጃ ኤፍ ኤም (Pamoja FM) ሬድዮ ጣቢያ ውስጥ ይሠራ ነበረ። በተለይም በምሽት አካባቢ ያለው ጥበቃ ልል እንደሆነ የሚነገርባት ኪብራ፣ የጋዜጠኛውን ገዳዮች ፖሊስ ፈልጎ ለፍርድ እንዲያቀርብ ነዋሪዎቿ አጥብቀው እየጠየቁ ነው። ፖሊስም አንድ ሰው ከግድያው ጋር ጠርጥሬ ይዣለሁ ሲል አሳውቋል።

የግዛቲቱ ምክትል ኮሚሽነር ጊዲዮን ኦምባጊ ፖሊስ በአስቸኳይ ምርመራውን እንደሚጀምር ለነዋሪዎቹ ገልጸውላቸዋል። የጋዜጠኛ ማርጃን እህት በማኅበራዊ ድረ ገጿ ላይ ‹‹እንደዚህ ያሉ ጨዋ ሰዎች ለምን እንደሚዘረፉና እንደሚገደሉ አይገባኝም›› ስትል በሀዘን ገልጻለች።

ያም ሆነ ይህ ማርጃን ሞቷል። ጋዜጠኛው የተገደለው ደሞ ዓለም የፕሬስ ነጻነቷን ባከበረችበት ማግስት ነው። ለጋዜጠኞች ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል ብሎ በተነገረበት፣ ከተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ እስከ ዩኔስኮ ዳይሬክተር ድረስ ጋዜጠኞች ያለስጋትና አድልዎ ሊሠሩ ይገባል እያሉ ባሳሰቡበት ጊዜ ላይ ነው። ይህ ዘመን ከምንጊዜውም በላይ የሚባለው ከሚሆነው ጋር ሲጣረስ የምናስተውልበት ዥጉርጉር ጊዜ ነው።

የኪብራ ግዛት ሕዝቦቿን ይዛ ‹ጋዜጠኛችን ምን ሆነ? ማን ገደለብን? ያ የኛን ሰው ምን አደረጉብን?› እያለች ነው። ሟቹ ሞርጃን ሰውኛ ሥራ ይሠራ ነበርና ሕዝቡ ስለሞቱ ዝም አላለም። ከመቃብር በላይ እገሌ በሚያስብል ሥራ ውስጥ ማለፍም አንድ ነገር ነው።

የ2019 ዓመት ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያና በአፍሪካ
በ2019 አዲስ አበባ የዓለም ዐቀፉን ፕሬስ ስብሰባ እንድታዘጋጅ ስትመረጥ ያለምክንያት አልነበረም፣ የጋዜጠኝነት ምህዳሩን አስፍተሻል በሚል ማንቆለጳጰስ እንጂ። በዚሁ ዓመት የፕሬስ ነጻነቱን አስመልክቶ ደረጃ ሲወጣ ኢትዮጵያ ከ180 አገራት መካከል የ110ኛ ደረጃን በመያዟ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር አበጀህ ተብሏል። ቀደም ካለው ዓመት አንጻር የተሻሻለው ደረጃ ቀላል አልነበረም፤ 40 አገራትን ወደታች ጥለን ወጥተናል።

በወቅቱ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ርዕዮቷን ወደሌላ ምዕራፍ እያሸጋገረች የነበረበት ጊዜ እንደመሆኑ የዓለም ዐይኖች ሁሉ ወደኢትዮጵያ ያተኮረበትና ጣልቃ ገብ የሆኑት ምዕራባውያንን ጨምሮ ሁሉም አገራት በሚመስል መልኩ ይሁንታን የቸሩለት ነበር። በወቅቱ የማንሸለምበትና የማንወደስበት ነገር አልነበረም፤ የጋዜጠኞች ብቻ ሳይሆን በእስር ያሉ ሁሉ ወደየ ቤታችሁ ሂዱ የተባለበት ይህ የመፈታት ዘመን ነው። ፕሬሱንም ነጻ አውጥቶት ነበር።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ተዘግተው የነበሩት የኢንተርኔት መስመሮች፣ በጽንፈኝነት የተፈረጁት ድረ – ገጾች ሁሉ ጥሩ የመጫወቻ ሜዳ አግኝተዋል። ከዚያ ወዲህም ተቀማጭነታቸውን በውጭ አገራት ያደረጉ እንደነ ቪኦኤና የጀርመን ድምጽ (ዴቼቬል) ያሉ ጣቢያዎች እኛው አገር ባሉት ኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያዎች የአየር ሰዓት ተከራይተው እስከመሥራት ደርሰዋል። በቢሲ አማርኛም ተጨምሯል። በመገናኛ ብዙኀኑ ዘንድ የነጻነት ነፋስ የታየ የመሰለበት ይህ ዘመን፣ በአጠቃላይ ሁሉንም ጉዳይ በአንድ የለውጥ ነፋስ ውስጥ አቅፎ የተነሳ አብዮት ስለመሆኑ ብዙዎች ምስክርነታቸውን ቢሰጡም አፍሪካ እንደመሆናችን ደግሞ ጥቂቶች በጥርጣሬ እያዩት ወደ 2020 አሸጋግሮናል።

ኢትዮጵያ በፕሬሱ ላይ ያስመዘገበችው ለውጥ ለአፍሪካም መልካም ዜና ሆኖ ተመዝግቧል። ከረጅሙ ዓመት ሥልጣነ መንበራቸው የተነሱትን የጋምቢያው መሪ ያህያ ጃሜህን ተከትሎ አገሪቷ ሠላሳ ደረጃዎችን አሻሽላ 92ኛ ደረጃ ማስመዝገቧ ተነግሮላት ነበር።

የዓለማቀፉ ድንበር አልባ የጋዜጠኞች ተቋም እንደገለጸው አፍሪካ ለሚዲያ ነጻነቱ የማትመችና በፖለቲከኞች የሚዘወር ፕሬስ የያዘች ሲል ይወርፋታል። መገናኛ ብዙኀኑና ጋዜጠኞች ያለፖለቲከኞች ይሁንታ በፈለጉበት ሙያዊ መንገድ እንዲጓዙ የማይፈቀድበት አህጉር ሆና ሳለ፣ ኢትዮጵያ ያሳየችውን ለውጥ እውቅና ሰጥቷል። የጋምቢያንም ተስፋ ሰጪ ስለመሆኑ ተናግሮ ነበር።

እዚህ ጋር ማንሳት የሚቻለው ሐሳብ በአፍሪካችን የጋዜጠኝነቱ ላይም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብትና የማኅበራዊ መሻሻሎች ለውጥ የሚታዩት በመንግሥት ለውጥ ብቻ መምሰሉ ነው።

2020 የአገራት ደረጃ – በፕሬስ ነጻነት
የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን በኮቪድ 19 ወረረሽኝ ምክንያት በተፈለገው መልኩ እንዲከበር ባያደርገውም የዓለም አገራትን ደረጃ አውጥቷል። ከመቶ ሰማንያ አገራት ኖርዌይ፣ ፊንላንድ፣ ዴንማርክ፣ ስዊድን፣ ኔዘርላንድስ ከአንድ እስከ አምስት ደረጃን ሲይዙ፣ ሥመ መልካም ያልሆኑትን አምስት አገራትም ደረጃው ላይ ሲታዩ ሰሜን ኮርያን መጨረሻ አድርጓታል። ጅቡቲ፣ ቻይና፣ ኤርትራ፣ ተርክሜኒስታንና ሰሜን ኮርያ ሆነዋል።

ኢትዮጵያችን አስራ አንድ ደረጃን አሻሽላ የዘጠና ዘጠነኛ ስፍራን ይዛለች። ዘንድሮ ጥሩ ደረጃ በማስመዝገብ አፍሪካዊቷ ሱዳን 16 ስድስት ደረጃዎችን ወደ ላይ ተሻግራ 159ኛ ስትሆን ሀይቲ ደግሞ ለኹለት ዓመታት ያለመረጋጋቷን ምክንያት ጋዜጠኝነት አድርጋ ነጻነት በመገደቧ 21 ወርዳ 83ኛ ሆናለች። በአፍሪካ ኮሞሮስ 19 ደረጃዎችን በማሽቆልቆል 75ኛ ስትሆን ቤኒን ደግሞ 17 አዘቅዝቃ 113 ላይ ተመዝግባለች።

ወቅታዊ የጋዜጠኝነት ፈተና በኮሮና ወረርሽኝ
ዓለማቀፉ የነጻው ፕሬስ ድርጅት ባለፈው ማርች 3/2020 አንድ አርጀንቲናዊ ጋዜጠኛ በቦነስ አይረስ ውስጥ በኮሮና ቫይረስ እንደተጠቃ ከተገለጸ ጊዜ ጀምሮ፣ በርካታ ጋዜጠኞች በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው እንዳለፈ አሳውቋል።

የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን ከመከበሩ አስቀድሞ መቀመጫውን ጄኔቫ ያደረገውና ለብዙኀን መገናኛዎች/ ጋዜጠኞች ተቆርቋሪ የሆነው በምኅጻረ ቃሉ ‘ፔክ’ (PEC – Press Emblem Campaign) የተባለው ድርጅት እንደተናገረው፣ ጋዜጠኞች የዓለማችንን ቀውስ አስመልክቶ መረጃ ለማድረስ ሲሉ ራሳቸውን ለቫይረሱ እያጋለጡ እንደሚገኙና እንዲጠነቀቁ አሳስቧል።

ይኸው ተቋም እንዳሳወቀው ባለፉት ኹለት ወራት ውስጥ ብቻ ቁጥራቸው 55 የሚሆኑ ጋዜጠኞች ሕይወታቸው እንዳለፈ ገልጿል። እነዚህ የ23 አገራት ጋዜጠኞች ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው እንዳለፈ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም፣ በአመዛኙ ግን ይኸው የቫይረስ ጣጣ መሆኑን አመልክቷል።

ድርጅቱ እንዳብራራው ጋዜጠኞች በተለይም ቫይረሱ በደንብ ባልተሰራጨበት ወቅት በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ የነበሩ ናቸው። በዚህ ጊዜ የቫይረሱ ስርጭትና ባህሪ እምብዛም ትኩረት ስላልተሰጠው ጋዜጠኞቹ በአመዛኙ መከላከያ ቁሳቁሶችን ባለመጠቀም እና ጥንቃቄዎችን ባለመተግበር ወደተለያዩ የሕክምና ተቋማት፣ የምርምርና ጥናት አጥኚዎች እንዲሁም ወደተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት ጋር ለዘገባ በሚሄዱበት ጊዜ ለጉዳት መዳረጋቸውን አሳውቋል።

በከፍተኛ ደረጃ ጋዜጠኞችን በሞት ያጣችው አገር ኢኳዶር ስትሆን፣ 9 ባለሙያዎቿን በሞት ተነጥቃለች። አሜሪካ 8፣ ብራዚል 4፣ እንግሊዝና ስፔን እያንዳንዳቸው ሦስት ጋዜጠኞችን አጥተዋል።

ይህ ጽሑፍ እስከታተመበት ጊዜ ድረስ በዓለማችን ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ሕዝቦች ያጠቃውና 250 ሺሕ በላይ ሰዎችን ሕይወት የነጠቀው ኮሮና ቫይረስ፣ በመገናኛ ብዙኀን እና ባለሙያዎቹ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳረፈ ይገኛል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ይኸው ፔክ የተባለው ተቋም ስጋቱን ገልጿል። ቫይረሱ ለዓለም ስጋት መሆኑ ከታወጀበ በኋላ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ አገራት ብዙኀን መገናኛዎቹን ሳንሱር የማድረግ፣ ኢንተርኔት የማቆራረጥ፣ ጋዜጠኞችን በማሰር፣ በባለሙያዎች ላይ የተለያዩ አካላዊና የቃል ጥቃቶችን በማድረስ እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥም የመረጃ ገደቦችን እያደረሱ ይገኛሉ ሲል አሳውቋል።
ድርጅቱ እንዳሳሰበው ‹‹በዚህ ወቅት ለሕዝቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚያስፈልገው ወቅታዊና የተጣራ መረጃ እንደመሆኑ ሚድያዎች በግልጽነት እንዲሠሩና የዓለም የጤና ቀውስ የሆነውን ቫይረሱን መከላከል እንዲቻል ብዙኀን መገናኛው ምቹ ሁኔታ ያስፈልገዋል›› ሲል አሳስቦ፣ ለዓለም ጤና ቀውስ ግልጽነት እጅግ አስፈላጊ እንዲሁም ሕይወት አድን የሆነ መላ ነው ሲል ቋጭቷል።

ጋዜጠኝነትና ፖለቲካ
ድንበር አልባው የጋዜጠኞች ተቋም መካከለኛው ምሥራቅና ሰሜን አፍሪካን ለነጻ ጋዜጠኝነት ምቹ ያልሆኑ አካባቢዎች ብሏቸዋል። ጅቡቲና ኤርትራንም የመረጃ ‘ብላክ ሆል’ ሲል የሚጠራቸው ናቸው። በተፈጥሮው ከፖለቲካው ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው የጋዜጠኝነት ሙያ በተለይም በአፍሪካ ጥሩ ሥም የለውም። መንግሥታቱ ወንበራቸው የተነቃነቀ ሲመስላቸው ግንባር ቀደም ተጠያቂ የሚያደርጉት ይህንኑ ሙያ ነው።

የፕሬስ ነጻነት ተቆርቋሪ ተቋም የሆነው ፔክ እንደሚለው፣ ጋዜጠኝነት የሕዝብ ነጻ አንደበት እንደመሆኑ መንግሥታት ተገቢውን ፖሊሲና ድጋፍ ሊያደርጉለት ይገባል። ሆኖም ይህንን በተግባር ተፈጻሚ ሲያደርጉ ግን አይታይም።

በ2019 ኢትዮጵያ ያሻሻለችው ደረጃ 40 ሲሆን ይህ የሆነውም በዐስር ዓመታት ውስጥ እስር ቤቶች ለመጀመርያ ጊዜ ታሳሪ ጋዜጠኛ እንዳልነበራቸው በመረጋገጡና ከዚሁ ጋር ተያይዞ በነጻነት የመናገር መብቶች የተከበሩ በመምሰላቸው ነው። ይህ የሆነውም የፖለቲካ ለውጥ ስለነበር ነው። ሱዳንን ብንመለከት 16 ደረጃዎችን አሻሽላ ለመመስገን የበቃችው የሱዳኑ የረጅም ዓመቱ ሰው ኦማር አልበሽር ከሥልጣን በመነሳታቸው የተፈጠረ ዕድል ነው።

ነገር ግን ከዚህ ቀደም የነበሩንን ልምዶች ካየን ይህ የፖለቲካ አዙሪት ተመልሶ ወደነበረበት መጥቶ ጋዜጠኝነቱን አይጫንም ማለት አንችልም ወይም ነጻ ሆኖ እንደሚቀጥል እርግጠኛ መሆን ይከብዳል። በአገራችን በዚህ ዓመት ውስጥ ጋዜጠኞችን የማሰር ምልክት አስተውለናል። የመገናኛ ብዙኀኑ የጀርባ አጥንት የሆኑት የአልኮል መጠጦች ከማስታወቂያ መታገድ ብዙኀን መገናኛዎቹን እያቀጨጨም ይገኛል።

የሕትመት መገናኛ ብዙኀኑ ማነስ አሁንም እንዳለ ነው። በመንግሥት ይዞታ ስር ያሉት የመገናኛ ብዙኀን ወደቀድሞ ዓይነት አሠራራቸው በመመለስ አንድ አቅጣጫ ውስጥ እየገቡ ነው። በተለይም ብሔርተኝነት ላይ የሚሠሩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጉልበታቸውን ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠናክረው እየሠሩ በመሆኑ ሕዝቡ አማራጭ በማጣት የሚያደምጣቸውና የሚመለከታቸው ሚዲያዎች እየሆኑ በመምጣታቸው ሰፋ ካለ ሐሳብ ይልቅ የአግላይ ፖለቲካ ሰለባ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ነጻ ሚዲያዎች የሚባሉትም ማኅበረሰብ ከማነጽ አንጻር በሳል ሥራ ለማቅረብ ብዙ ርቀት ይቀራቸዋል።

በተለይ በአሁን ሰዓት በፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ላለችው ኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ምህዳሩ የማኅበረሰቡን ሐሳብ ከማንሸራሸር ይልቅ ሚዲያውን ከሚመሩ አካላት በሚመጡ ሐሳቦች ብቻ ለሚታጠረው ሕዝብ ጉዳት አለው። በስተኋላ ላይ በየዘውጉ እየተሳበ በሚመጣ የተካረረ ልዩነት አማካይነት አቅጣጫ የሌለው መደናበር ውስጥ ይከታል። ስለሆነም የፕሬስ ነጻነቱን በአግባቡ በመቃኘት እየታየ የነበረውን የተሻለ አካሄድ በቀጣይነትና በተጠና አሠራር መደገፍና በዘላቂነት ማስቀጠል ይገባል።

አብርሃም ፀሐዬ የቢዝነስ አማካሪና ጋዜጠኛ ሲሆኑ በኢሜይል አድራሻቸው gerarame@gmail.com ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 79 ግንቦት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here