የጄቲቪ ጋዜጠኞች ሙሉ በሙሉ ተበተኑ

0
434

በድምጻዊ ዮሴፍ ገብሬ ባለቤትነት ስር ይተዳደር የነበረው ‹ጄ ቲቪ› የቴሌቪዥን ጣቢያ በሚያዚያ 29/2012 በስሩ ይሠሩ የነበሩትን ሠራተኞች የኹለት ወር ደሞዝ እንዲወስዱ በመወሰን መበተኑ ታወቀ።

ምንጮች ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ በጣቢያው ውስጥ ይሠሩ የነበሩ 40 የሚደርሱ ሠራተኞች ሐሙስ 29/2012 በነበራቸው ስብስባ፣ የኹለት ወር ደሞዛቸውን እንዲወስዱ እና ሥራ እንዲያቆሙ በመስማማታቸው የመልቀቂያ ፎርም መሙላታቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ የገቢ መቀነስ አጋጥሞኛል ያለው የቴሊቪዥን ጣቢያው፣ ይህንንም ለሠራተኞቹ መደበኛ ባልሆነ መንገድ አሳውቆ እንደነበር አዲስ ማለዳ ከሠራተኞቹ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። በዚህም መሰረት በጣቢያው በካሜራ ባለሙያነት ሲያገለግሉ የነበሩት ግለሰብ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ ከፍተኛ የገንዘብ ችግር አጋጥሞኛል በማለት በተደጋጋሚ አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር ሲሉ አስታውሰዋል። ጣቢያው ሥራ እንደሚያቆም ግን ምንም አይነት መረጃ አልተሰጠንም በማለት ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እንደ ሠራተኞቹ ከሆነ ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያ እንዳልተሰጣቸው እና ወደ ሥራ ለመግባት ሲሄዱ ቢሮው ተቆልፎ እንዳገኙት ለአዲስ ማለዳ ጨምረው ተናግረዋል።
እንደ አዲስ ማለዳ ምንጭ ሲናገሩ፣ ‹‹በሚያዚያ 16/2012 የደሞዝ ቅነሳ እንደሚኖር ሲያሳውቁን በዚህ ሰዓት የደሞዝ ቅነሳ ማድረግ ተገቢ አይደለም በማለት ተነጋግረን ነበር።›› ብለዋል።

ኮቪድ 19 የኮሮና ቫይረስ ወረርሽ በመግባቱ ምክንያት ሠራተኞችን መቀነስ እና የቅጥር ውል ማቋረጥን የከለከለ ሲሆን፣ ነገር ግን በአንዳንድ ተቋማት ላይ የሠራተኛ ቅነሳ መኖሩ እየተነሳ ነው። ከዛም በተጨማሪ እንደ ብሮድካስት ማኅበር ተቋም የሚዲያ አባል ያለበትን ደረጃ እና እንዴት እየቀጠለ እንደነበር እናውቅ ነበር ብለዋል።
ነገር ግን የሚዲያ ተቋሙ ተዘጋ ወይስ ቋሚ ላልሆነ ጊዜ ተቋረጠ የሚለው የተረጋገጠ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል። ቢሆንም የሳተላይት ክፍያ፣ የሠራተኛ ደሞዝ የመክፈል ሂደቶች ላይ ተቋሙ ችግር ላይ እንደነበር የብሮድካስት ማኅበር እንደሚያውቅ የብሮድካስተሮች ማኅበር ዋና አስተባባሪ እንዳሻው ወልደሚካኤል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እንደ ዋና አስተባባሪው ገለጻ፣ እየተስተዋለ ያለው ችግር የሚያመላክተው ወሳኝ ነጥብ የግል ሚዲያዎች ከባድ የሆነ የአቅም ችግር ውስጥ እንዳሉ እና ኹሉም የግል ሚዲያዎች በሪፖርታቸው ላይ ይሄን እያመላከቱን ስለሆነ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከዛም በተጨማሪ የብሮድካስት ማኅበር ዋና ዓላማው በሚዲያ ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞችን የማብቃት እና ሥልጠናዎችን የመስጠት ሥራ መሥራት ነው ያሉት እንዳሻው፣ አስተዳደራዊ ሥራው ላይ ግን እኛ ኃላፊነት የለንም ሲሉ እንዳሻው ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

የብሮድካስት ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ገብረጊዮርጊስ አብረሃ በበኩላቸው፣ ጄ ቲቪ ይዘጋ ወይም በሥራ ላይ የሚቆይ ይሁን መረጃው እንደሌላቸው ተናግረዋል። ነገር ግን ገብረጊዮርጊስ፣ አንድ ሚዲያ ሲዘጋ በተቋሙ ባለቤት ወይንም በፍርድ ቤት መዘጋቱን የሚገልፅ ተጨባጭ መረጃ ሲደርሰን ነው መዘጋት እና አለመዘጋቱ የሚታወቀው ብለዋል።

በተያያዠም የብሮድካስት ባለሥልጣን ሥራ አንድ ሚዲያ ተቋም ፍቃድ ሊወስድ ሲል ማሟላት ይገባዋል ብሎ ያወጣቸውን መስፈርቶች አሟልቶ መገኘቱን በማረጋገጥ ፈቃድ የሚሰጥ ተቋም ነው ብለዋል። በዚህም መሠረት የሥራ እቅዳቸውን በመመልከት በእቅዳቸው ውስጥ ምን ምን ተካተተ የሚለውን ተመልክቶ ዓላማውን መለየት፤ በመቀጠል ሚዲያ ተቋሙ የሚጠቀምበትን መሣርያ ዘመናዊነት መመዘን፤ ካፒታላቸውን እና የካፒታሉ መነሻ ምንጭ በዋነኛነት መገምገም፤ ከሚዲያ ጋር ያላቸውን ቅርበት እና ስለ ሚዲያ ያላቸው እውቀት፣ ከዛም በዘለለ እቅዳቸውን በመመልከት ያስቀመጡትን አቅጣጫ ምን አይነት ነው የሚለው ታይቶ እንደሚሰጥ አዲስ ማለዳ በ71ኛ እትሟ ላይ አስነብባ እንደነበር ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 79 ግንቦት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here