በልጅነታቸው ከወላጅ አባታቸውና ከአባታቸው ጓደኞች አንደበት የሚወጡትን የፖለቲካ ወሬዎች ይሰሙ ነበር። ሻሸመኔ ‹ኩየራ› ልጅነታቸውን ያሳለፉት ኤፍሬም ማዴቦ፣ ሐዋሳ ከተማ እስከ ስምንተኛ ክፍል ተከታትለዋል። ቀጥሎ በመጣላቸው ነጻ የትምህርት እድል ባቀኑበት ደብረዘይት ኢቫንጀሊካል ትምህርት ቤት፣ ከ14ቱም ክፍለ አገር የመጡ ተማሪዎች ነበሩ። ያኔ ነው ኤፍሬምም የኢትዮጵያን ምስል ያገኙት።
‹‹ናሽናሊስት የሆንኩት ያኔ ነው። ኤርትራውም ጀበሐ፣ ወለጋውም ኦነግ ብሎ ስለሚጽፍ ከኤርትራውም ከወለጋውም ጋር እጣላለሁ። ያ ነው የፖለቲካ መሠረቴን የጣለው።›› ይላሉ። ‹ደርግን አናገለግልም› ብለው አባታቸው ቤት ተመለሱ እንጂ እድገት በኅብረት ሄደዋል። ኢሕአፓም ገብተዋል። በጊዜው የኢትዮጵያና የሶማሌ ጦርነት ጀምሮ ነበርና፣ ባላቸው የአገር ፍቅር ምክንያት ግን ‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው› የሚል ንግግር ከሰሙበት ኢሕአፓ ሳይውሉ ሳያድሩ ወጡ።
ይልቁንም ስለ ሊብራሊዝም ያነብቡ የነበረው ነገር ይበልጥ ስቧቸዋል። ነጻነትን ማሰብንም ምርጫቸው አደረጉ። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሲወጡ ወደ ኤርትራ አቅንተው በዛው ወደ ሥራ ዓለም የተቀላቀሉት ኤፍሬም፣ ብሎገር ሆነዋል፣ በግንቦት ሰባት የትጥቅ ትግል ኃላፊነት ተረክበው አገልግለዋል። የ59 ዓመቱ ጎልማሳ ኤፍሬም ማዴቦ፣ በ1997 ምርጫ እንዲሁም በግንቦት 7 አመሠራረት፣ አልፎም አሁን ላይ በኢትዮጵያ ባለው የፖለቲካ አየር ዙሪያ ከአዲስ ማለዳው ተወዳጅ ስንታየሁ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።
ግንቦት 7 ከመመሥረቱ በፊት በ1997 ምርጫ የነበረውን ድባብ እንዴት ያስታውሱታል?
ያኔ ውጪ ነበርኩ። አገር ውስጥ የነበረው መንፈስ እዛ (ውጪ) ለነበርነው አይታይም። እዛ በሚድያ ነው የምንሰማው። ከሞላ ጎደል ከዛ በፊት ከነበሩት ምርጫዎች የተሻለ እንደነበር በደንብ እናውቅ ነበር። ምክንያቱም የፖለቲካ ድርጅቶች መነቃቃት ያሳዩበት፣ ተወዳድረን ድምጽ እናገኛለን ብለው ያመኑበት ጊዜ ነው። በተለይ የተለያዩ ድርጅቶች ቅንጅትን ከፈጠሩና ቅንጅት በሰሜን አሜሪካ ዋሺንግተን ንግግር አድርገው የሰውን ቀልብ ከሳቡ በኋላ፣ በዛ (ሰሜን አሜሪካ) በኖርኩበት ዓመታት ዐይተን በማናውቀው መንገድ ድጋፍ የታየበት ነው፤ ጥቂት ተቃዋሚ መኖሩ ግን አይቀረም።
ኅብረቱ ከቅንጅት በፊት ነው የተፈጠረው፣ ኅብረቱ ሲመሠረት ነበርኩኝ። አመራር ሲመጣ ነው ኹለቱ የተለዩት። ሰው በአብዛኛው የቅንጅት ደጋፊ ነበር። ፖለቲካ ውስጥ የቆዩ የኅብረቱ ደጋፊዎችም ነበሩ። ትልቅ መነቃቃት ነበር። በገንዘብ እርዳታም በኩል ኹለቱ ድርጅቶች ከፍተኛ ገንዘብ በአጭር ጊዜ ማሰባሰብ ችለው ነበር። ቅንጅትም ኅብረትም በተቻለ መጠን ተጠጋግተው ይሠሩ ስለነበር፣ በተለይ የምርጫ ክርክሩ ከተጀመረ በኋላ ውጪ ያለ ሰው ሐሳቡ ወደ ኢትዮጵያ ነበር።
እንደውም ቅንጅት ሥልጣን የሚይዝ ከሆነ ወደ ኢትዮጵያ እንዴት ነው የምንሄደው፣ ሄደን ምን ልንሠራ እንችላለን የሚለውን ስናስብ ነበር። በጊዜው የፖለቲካ ፓርቲ አባል አልነበርኩም፣ የኅብረቱ፣ ከዛም የደቡብ ኅብረት ደጋፊ ነበርኩኝ።
ያኔ መደበኛ የመገናኛ ብዙኃንን ብቻ ነበር የምንሰማው። እንደ ዛሬ ማኅበራዊ ሚድያዎች አልነበሩም። በአብዛኛው እዚህ (ኢትዮጵያ) ካለ ሰው ቀጥታ በስልክ ነበር የምንገናኘው። በሰዓቱ እኔም ብሎገር ነበርኩኝ።
የ97ቱ ምርጫ እስከ መጨረሻ ጊዜ አካባቢ ድረስ ትልቅ ተስፋ የታየበት ምርጫ ነበር። መጀመሪያ ቅንጅት አዲስ አበባን አሸነፈ ሲባልና ከዛ በኋላ መንግሥት ኃይለኛ መሆን እስኪጀምር ድረስ ትልቅ ተስፋ ነበረን።
ለእኔ ያኔ የነበረው ትልቅ ተስፋ ቅንጅት ሥልጣን ይይዛል የሚለው አይደለም። ይህቺ አገር ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ልታደርግ ነው የሚለው ነው። እሱ ነበር ለእኔ ትልቅ ነገር። በትክክለኛ ምርጫ ሕወሓት አሸንፎ ቢሆን እንኳ እሱም ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ነበር የሚሆነው። አንደኛው ምርጫ ላይ በእውነተኛና በትክክለኛ ምርጫ ካሸነፉ፣ በቀጣይም ትክክለኛ ተመሳሳይ እውነተኛ ምርጫን ነው የምትጠብቀው። በእውነተኛ ምርጫ አንድ ፓርቲ ብቻ ሊያሸንፍ አይችልም፣ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ እስካለ ድረስ።
እሱ ሂደት ኢትዮጵያ ውስጥ ይፈጠራል የሚል ግምት ስለነበረን፣ ማስተባበርና ሰዎች እንዲደግፉ ማድረግ ጀመርን። ኅብረትና ቅንጅት የሚባል ነገር ልዩነት እንዳይፈጠር ጥረት እናደርግ ነበር። ኹለቱ አንድ ላይ የሚሠሩበት ጊዜ እንጂ አሁን እንደሚታየው በድጋፍ መከፋፈል እንዳይኖር ከፍተኛ ጥረት አድርገን ነበር። ውጤቱ ግን ሲወጣ ሁሉ ነገር ተቀለበሰ። ሰዉ እልህ ውስጥ ገባና እንደገና መደራጀት ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ሰዎች ተገደሉ፣ እሱም የባሰ ሰዎችን እልህ አስገባ። የቅንጅት መሪዎች ታሰሩ። ዋሺንግተን ትልልቅ ሰላማዊ ሰልፎች ነበሩ።
እንደገና በልዩ መልክ መደራጀት ተጀምሮ ነበር። እሱ እንዳለ ደግሞ ጭራሽ ቅንጅት ራሱ ተከፈለ። ይህም የባሰ ችግር ይዞ መጣ። ያ ጊዜ ከፍተኛ የትግል ጊዜ ነበር። የምርጫው ቀን ስለተፈጠረው ነገር ያለዎት ስሜት ምንድን ነው?
ያኔም አገር ውስጥ አልነበርኩም። እንደ አሜሪካ ምርጫ በራድዮን ወይም በቲቪ የምትከታተለው ዓይነት ምርጫ አይደለም። የኢትዮጵያ ምርጫን አስመልክቶ መጀመሪያ ያገኘሁት መረጃና ትዝ የሚለኝ ቅንጅት አዲስ አበባን አሸነፈ የሚል ነው። ኢትዮጵያም ውስጥ በየቦታው እየመራ ነው የሚለውን መረጃ ሰማን። ቅንጅት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻውን መንግሥት የሚያሸንፍበትን መቀመጫ ያገኛል ወይ የሚለው ነገር፣ ቅንጅት የሚወዳደርበትን ወንበር አውቃቸው ነበር። የማይወዳደርባቸው ነበሩ። እነዚህ ማለት ገዢው ፓርቲ ያለ ተቃውሞ የሚወስዳቸው ናቸው።
ስለዚህ ቅንጅት ብቻውን ያሸንፋል የሚል ግምት አልነበረኝም። ይልቁንም ከኅብረቱ ጋር ሆነው ጥምር መንግሥት ይመሠርቱ ይሆናል የሚል ግምት ነበር። ጥምር መንግሥት ቢፈጠር ኖሮ እነ መለስ ዜናዊ እንደፈለጉት የማይሆኑበት መንግሥት ይፈጠር ነበር።
ቅንጅት አዲስ አበባ ላይ ማሸነፉን ስንሰማ ምሽት ነበር። እየነጋ ሲሄድ ኮሮጆ ተወስዷል፣ ተሰርቋል ወዘተ የሚል ነገር ተሰማ። ምርጫውን እንዳጭበረበሩ ይታወቃል፤ ምን ያህል እንደሆነ ነው የማይታወቀው፣ እነሱ ናቸው የሚያውቁት። ግንቦት 8 ላይ ብዙና የተለያየ ዓይነት መረጃ ነው የተሰማው። ትክክለኛ ነው ብለህ የምታምነው መረጃ አታገኝም። ቅንጅት አሸንፏል ግን ድምጽ ሰርቀው ራሳቸው አሸነፉ የሚል መረጃ ነው የወጣው። ግንቦት 8 እስከ ቀጣይ ሳምንት ድረስ በጣም የሚያስፈራ ጊዜም ነበር።
ቅንጅት በከተሞች አካባቢ ጥሩ ድምጽ አግኝተው እንደነበር ጥርጥር አልነበረውም። መኢአድም ጠንካሮች እንደነበሩ እሰማለሁ።
ያኔ ሰው በጣም ተነሳስቶ ትልቅ ነገር ጠብቆ ነበር። ቅንጅት ፓርላማ አንገባም ወደሚለው ውሳኔ ከሄደ በኋላ ሰውም የጠበቀውን ስላጣ ከፖለቲካው ራሱን እንዲያወጣ ያደረገ ክስተት ነበር። ፓርላማ ቢገቡ ይሻል ነበር ብለው ያስባሉ?
ኹለቱም ፓርቲዎች አንገባም የሚል ውሳኔ አሳልፈዋል። ግን ለምንድን ነው ቅንጅቶች ወደ ፓርላማ አንገባም ያሉት ስንል፣ ‹መቼ ነው አንገባም ያሉት፣ ደጋፊዎቻቸው ከተገደሉ በኋላ ነው ሳይገደሉ በፊት?› የሚለው ሲታይ፣ እሱ ውሳኔ (ፓርላማ አንገባም የሚለው) ሰዎች ከተገደሉ በኋላ የመጣ ነው። ፓርላማ ላለመግባት የወሰኑበት የራሳቸው ምክንያት እንዳለ ሆኖ፣ ምርጫው ተጭበርብሯል። አንደኛው ነጥብ እሱ ነው። ያልተመረጡ ሰዎቻቸው (የኢሕአዴግ) እንዲመረጡም ሆነ ብለው አድርገው ነበር። ሑለተኛ ደግሞ ለምን ተጭበረበረ ሲባል ብዙ ሰው ሞቷል።
ያንን ትግል ወደኋላ የመለሰው የቅንጅት ፓርላማ አለመግባት አይደለም፣ ያንን ተስፋ ወደኋላ የመለሰው መለስ ዜናዊ ነው። በአገራት ውስጥ ዴሞክራሲ እንዲለመልም፣ ከነበረበት ተነስቶ ወደሚቀጥለው ምዕራፍ እንዲሄድ ፓርቲዎችና ምሁራን የሚያደርጉት ሚና እንዳለ ሆኖ የአንድ ሰው ሚና ትልቅ ነገር ነው።
በናይጄሪያ እና ማሊ መሪዎች በወሰዷቸው እርምጃዎች የዴሞክራሲ ሽግግር አይተናል።እነዚህ መሪዎች ያደረጉትን ነገር በ1997 መለስ ዜናዊ አድርጎት ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ የመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽ ሄደን ነበር ፎቶ የምንነሳው። የኢትጵያን ዴሞክራሲ መሠረት የጣለ ብለን እናነሳው ነበር። ዛሬ ፋውንዴሽኑ ይዘጋ ነው የምለው፣ ማየትም አልፈልግም።
የሱ ሥልጣንና እሱ የሚመራው ሥልጣን እንዳይነካ ነው ያሰቡት። ‹እኛ በጠመንጃ ያመጣነውን ሥልጣን የከተማ ውስጥ አውደልዳይ ሊወስድ ነው እንዴ› የሚሉትን ሰምተናል። መለስ የ1997 ምርጫ ጭላንጭል እንዲያሳይ አድርጓል፣ ያ ጭላንጭል ለሱ እንደማይሆን ሲያውቅ አጨለመው። የኢትጵያን የዴሞክራሲ ተስፋ ያጨለመው ይሄ ነው። ግን ጨልሞ እንደማይቀር የሚያውቁ ሰዎች ተስፋ ሳይቆርጡ ትግሉን ቀጠሉ። ጥቂት ሰዎች ተነስተው ነፍስ እየዘሩ ቀጠሉ። የተለያየ አገር ሆነው ጥረታቸውን ቀጥለው ወደ በረሃ እስከመግባት ደረሱ።
እርስዎ ወደ ፖለቲካ እንዴት ገቡ?
ያኔ ብሎገር ነበርኩኝ። ብሎግ ማንበብ አይከለከልም ነበር። ‹እንሰት› የሚባል ብሎግ ነበረን። ሦስት ሆነን ነው የፈጠርነው። በሳምንት ሦስት ጊዜ እንጽፍ ነበር። በጣም ብዙ ሰው ያነበው ነበር። ከዛ በፊት ለተለያዩ ብሎጎች ጽፈን እንሰጥ ነበር፣ ግን ቆራርጠው የፈለጉትን ሲያወጡ ያልፈለጉትን ያስቀራሉ። በዚህ ምክንያት የራሳችንን ጀመርን፣ በጣም ተወዳጅም ሆነ። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ሚድያ ሁሉ ከእኛ እየወሰደ ማውጣት ጀመረ። ሰዎች ይጋብዙንም ነበር። ያኔ በውሸት ሥም ሰው ሲጽፍ እኛ በሥማችን ነበር የምንጽፈው።
በዚህ መካከል ቅንጅቶች ሲፈቱ ሰሜን አሜሪካ መጡ። ያኔ የኢትዮጵያ ሚሊኒየም ነበር፣ ሀዋርድ ዩኒቨርስቲ ትልቅ የጥናት መድረክ ነበር። ኹለት ቀን ነው የተካሄደው። አንድ ቀን ንጉሤ መንገሻ ደወለልኝ፣ ከአሜሪካ ድምጽ ራድዮን። ብሎግህን እናነባለን፣ በአውደ ጥናቱ ላይ አንድ ጽሑፍ እንድታቀርብ አለኝ። የቅንጅት መሪዎች ተፈትተው መጥተው ዋሺንግተን ብዙ ሰው በነበረበት መድረክ ተሳተፍኩ። አቀረብኩኝ።
አንዴ ካሊፎርኒያ እያለሁ ብርሃኑ ነጋ ደወለልኝ። የደቡብ ልጆች ከሳንዲያጎ መጥተው ላናግራቸው እንደምፈልግ ስነግራቸው የአንተን ስልክ ሰጡኝ አለኝና ሲመጣ ተገናኘን። ብዙ ነገር አውርተን ተለያየን። ሌላ ጊዜም ደወለልኝ። ብሎግ ላይ እየጻፍኩኝ እንደሆነ ስነግረው፣ ‹የብቻ ትግል አያስፈልግም፣ ከእኛ ጋር ታገል አለኝ።
ግንቦት 7 የሚባል ድርጅት መፈጠሩን ነገረኝ፣ ሰምቼ ነበር። በአሜሪካም ጉዳዩ ትልቅ ዜና ነበር። ያንን ዜና ከመስማቴ ቀናት በፊት የትጥቅ ትግል ከሰላማዊ ትግል ጋር መቀላቀል ያስፈልጋል የሚል ነገር ጽፌ ነበር። እና በሐሳቡ ተስማማሁ። በኤርትራ ጉዳይ ላይ ግን መነጋገር አለብን አልኩኝ። ብርሃኑ ነጋ እና አንዳርጋቸው ጽጌ መጥተው ብዙ አውርተን ተግባባን። አማራጭ ብንፈልግ አጣን። ሶማሌ በዛን ጊዜ አይሆንም፣ ጅቡቲና ኬንያ ዘመድ ነው። ደቡብ ሱዳን ገና ነጻ አልወጣም።
ኤርትራን እንደ አማራጭ የወሰድነው ከዛ መታገል እንችላለን በሚለው ሐሳብ ብቻ አይደለም፣ ሕወሓትን እንደሚጠሉ እናውቃለን። የምንጠላበት መንገድ ሊለያይ ይችላል፣ ግን እንጠላለን። ኹለታችንም እነሱ እንዲወገዱ እንፈልጋለንና ተስማማን። ከዛ በኋላ የግንቦት 7 ትግል ተጀመረ።
የሕዝብ ግንኙነት ውስጥ ነበር የምሠራው። ከዓመት በኋላ ዲሲ እነ ብርሃኑ መጥተው ነገሩኝ። ድርጅቱ መሥራች ጉባኤ በመረጣቸው ሰዎች ነበር ሲመራ የቆየውና፣ ከዚህ በላይ በዛ መሄድ ስለማይገባ በተመረጡ ሰዎች መመራት ያስፈልጋል አለኝ። በተሰጠ ጥቆማም ሥምህ አለ አለኝ። እና ለማሰብ ትንሽ ጊዜ ወስጄ እገባለሁ አልኩኝ፣ ገባሁ።
የሚገርመው ደግሞ ስመረጥ ከአንዳርጋቸውና ከብርሃኑ ቀጥሎ ከፍተኛ ድምጽ አገኘሁ። ሰዎች አውቀውኝ አይደለም፣ በብሎግ ነበር የሚያውቁኝ። ከዛ ጊዜ ጀምሮ አርበኞች ግንቦት 7 እስኪመሠረት ድረስ የንቅናቄው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ነበርኩኝ። አርበኞች ግንቦት ሰባት ሲመሠረት ግን እኔ አልመረጥም አልኩኝ። ውህደቱን አልፈለኩትም ነበር።
ለምን ነበር ያልፈለጉት?
ሁለቱ ድርጅቶች በጣም ከፍተኛ ልዩነት የነበራቸው ናቸው። አርበኞች ግንባር መሳሪያ ብቻ ለውጥ ያመጣል ብሎ የሚያስብ ነገር ግን በመሳሪያውም ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የማያደረግ ቡድን ነበር። ለግንቦት 7 ደግሞ የመሳሪያው ትጥቅ ትግል የፖለቲካ ዓላማ ማሳኪያ እንጂ በእራሱ ግብ አይደለም። ግንቦት 7 ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ የኢትዮጵያን ፖለቲካ የተከታተሉ እና የመሩ እንዲሁም በ97 ምርጫ ከፍተኛ ሥራ የሰሩ በመሳል ፖለቲከኞች የተሰባሰቡበት ነው። አርበኞች ግንባር ደግሞ በአብዛኛው በገበሬዎች የተዋቀረ ነው። በድርጅታዊ ባህላችን የተለያየን ነበርን። በረሀ ውስጥ አርበኞች ግንባር፣ ደሚት፣ የሲዳማ ድርጅት፣ የኦሮሞ ድርጅት፣ የአፋር ድርጅት፣ የጋምቤላ ድርጅት፣ የቤኒሻንጉል ድርጅት የሚባሉ ነበሩ። እነዚህ ድርጅቶች ተራ በተራ ከስመው አንድ ድርጅት ለማውጣት ነበር ትልቁ ዓላማችን። በእርግጥ እሱን ወደ በረሀ ሔደን ስናየው ምንም የሚሆን ነበር አይደለም።
የትጥቅ ትግል ከተጀመረ በኋላ እርሶስ እንዴት ኤርትራ ተመለሱ?
ኤርትራ ከድርጅቱ መመሥረት በኋላ ነው የገባሁት። መሪነቴ የከተማ ውስጥ ነበር። በዛ መካከል አንዳርጋቸው ታሰረ። እስከዛ ድረስ ኤርትራ አልሄድኩኝም። ለፔንታጎን እየሠራህ እንደልብ መንቀሳቀስ አትችልም። ኤርትራ እሄዳለሁ ካልኩኝ ለምን እንደሆነ መናገር አለብኝ። እንኳን ኤርትራ ኢንግሊዝም ብትሄድ ያው ነው። ስለዚህ አልወጣም ነበር። እናም አልሄድም ብዬ መጨረሻ ግን አንዳርጋቸው ሲታሰር፣ ይህን ትግል ለመግደል ከሆነ ያሰሩት፣ ይህ ትግል የተቀጣጠለ መሆን አለበት፣ ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆንን ማሳየት አለብን ብለን እኔና ብርሃኑ መሄድ አለብን ብለን ሄድን።
ኤርትራ ስንሄድም ሆነ ትጥቅ ትግል ስንጀምር፣ ግንቦት 7 የነበርን ጊዜም እቅዳችን ሁለገብ ትግል ነው። ሰዎች አሁንም ድረስ ይጠይቁናል። ምንም ቦታ አልያዛችሁም ይላሉ። ሁለገብ የትግል ስልት ነው የተከተልነው። በአንድ በኩል በኁቡዕም ሆነ በሌላ መንገድ እሳት የሚቀጣጠልበትን መንገድ መፈለግ አለብህ። በተለይ የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ሕዝቡ የመሣሪያ ትግል የሚያውቅ ነው። ስለዚህ እዛ አካባቢ የሚሸፍት ሰው ካለ እንዳይሸፍት፣ እኛ ጋር እንዲመጣ። በዛ ላይ በደኅንነት ኃይሎች ዐይን የተጣለባቸው ሰዎች መጥተው ሠልጥነው ተደራጅተው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ማድረግ ነው። ሕዝባዊ እንቢተኝነትና ሕዝባዊ አመጽ ነው ሁለገብ ትግል። ሌላው ዲፖሎማሲ ትግል ነው። እነዚህን መቀላቀል አለብን።
ሕዝባዊ አመጽ ላይ ነው ትኩረታችን። ግን ዝም ብለን የማንመታ አካል መሆናችንን ማሳየት አለብን፣ ሕዝቡም እዚህ ጋር የሆነ ነገር አለ እንዲል ነበር እቅዱ። እንጂ ሕወሓትና ሻዕቢያ አንድ መቶ ሺሕ ሠራዊት አሰልፎ እንደገባው መግባት አልበረም ዓላማችን። እንደዛ ዓይነት ነገር እንዳይኖር ነው ፍላጎታችን። በገዢው ፓርቲ ሰዎች ጭንቅላት ውስጥ ጥርጣሬ መፍጠር ነው፣ የሚሄዱበት መንገድ ትክክል እንዳልሆነ።
ለዛም ኢሳትን እኛ ነን የፈጠርነው። ትንሣኤ ራድዮ፣ አባይ ሚድያ እኛ ውስጥ ያሉ ልጆች ናቸው የፈጠሩት። በመቀባበል የሚሠሩት ሥራ በገዢው ፓርቲ ውስጥ በነበሩት ጭምር እንዲፈጠር ነው። እነሱ ነበሩ መረጃ የሚሰጡት። ያንን በመጠቀም መረጃ ትጠቀማለህ። አሁን በመጣው ለውጥ ውስጥ የእኛ ድርጅቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበራቸው። አሁን ለመጣው ለውጥ ሚና አለን ብሎ ለመጋራት አይደለም። ሁለገብ የሆነ አካሄድ ነው የተከተልው ለማለት ነው።
ወታደራዊ ይዘት ግን ነበረው አይደለ?
አዎን ነበረው። ዝም ብለን የምንሞት አለመሆናችንን እንዲያዩ ነው። አሠልጥነን ወደ ኢትዮጵያ የመለስናቸው ሰዎች ዋናው ግባቸው ኢትዮጵያ መሣሪያ ይዞ መግባት እና ሌሎችን ማሠልጠን ነበር። መሣሪያ የሚገባባቸውን ቦታዎችም ለይቶ ማወቅ ነው። ትልቁ ችግር እሱ ነበር። ድሮ በጎንደር ወይም በትግራይ እንደፈለጉ ይገባ ነበር። አሁን በሙሉ ተዘግቷል። ወልቃይት ተዘግቶ የትግራይ ሆኗል።
በጎንደር የትጥቅ ትግል ሲጀመር በወሎ በኩል የገባ መሣሪያ እንዲደርስ አድርገናል። ከኤርትራ በአፋር በኩል ለማሳለፍም ጥረት ተደርጓል። በዛ ሁሉ መንገድ ውስጥ ማለፍ ነበረበት። በዛ ላይ አሜሪካ ውስጥ ሆነህ መገናኘት አትችልም። ከተነጋገርክ ሚድያ ላይ ይወጣል፣ የደኅንነት ሥራ መሥራት አትችልም። ኤርትራ ስትመጣ ግን፣ ወያኔ ስለእኛ ማወቅ ያልቻለው ኤርትራ ስንገባ ነው። በአንጻሩ ደግሞ የእኛ የሥራ አስፈጻሚ አካላትም የነበሩ ለወያኔ ቃል የሚያቀብሉ ነበሩ። እነማን እንደነበሩም እናውቃለን። እኛ ግን በምንም ተዓመር መልስ በሚድያ አንሰጥም ነበር።
እናም በጥቅሉ ወታደራዊ ሥልጠና የተሰጣቸው ብዙ ሰዎች አሉ። ወደ ኢትዮጵያም መጥተው ወታደራዊ ሥልጠና ይሰጣሉ። የተለያዩ ትንኮሳ የሚተነኩሱና አደጋ የሚያደርሱ፣ መሣሪያ ይዘው የሚገኙትም የእኛ ሰዎች ነበሩ።
ከሥልጠናው በኋላ የሚላኩ ሰዎች ምን እርምጃ ይወስዱ ነበር?
የወታደር መንገድ መዝጋት፣ ያለአግባብ የታሰሩ ሰዎችን ያስፈቱ ነበር። መጥተው መሣሪያ ለማስፈታት ሲሞክሩ ተዋግተው ይከላከሉ ነበር። በጊዜው ብዙ ሪፖርቶች ይደረጉ ነበር። ግን ግንቦት 7 አደረገ እንዲባል አንፈልግም። አገር ውስጥ ያለው ኃይል ቢፈልግም አርበኞች ግንቦት 7 አደረገው የሚለውን እኛ አንፈልግም። ለመንግሥት አንድ አይደለም፣ ለእኛ ኃይል ብዙ ወታደር ነው የሚልከው። እንደዛ ያለ ነገር እንዲፈጠር አንፈልግም፣ ለእኛ ዋናው ሥራው መሠራቱ ነበር።
አዘዞ ድረስ እየመጡ የእኛን ልጆች አስፈትተው የሄዱ አሉ። ከፖሊስ ጋር ግብ ግብ ገጥሞ ፖሊስ ገድሎ፣ ከትዕዛዝ ውጪም ቢሆን ራሱን ያጠፋ ሰውም አለ።
እናም ኤርትራ የሚሠለጥኑ ሰዎች ትልቁ ሥራቸው አገር ውስጥ ገብቶ ማሠልጠን ነበር። መሣሪያ ወደ አገር ውስጥ የሚገባበትን መንገድ መፈለግና ያንን የሚያስገቡ ታማኝ ሰዎችን መፈለግ ነው። ትልቁ ችግር መሣሪያ ወደ አገር ውስጥ ሲገባ መሣሪያውን በታማኝነት ለቡድን የሚጠቀሙ ሰዎች መኖር አለባቸው።
አንዱ ትልቁ ችግር፣ ከገበሬ የመጣ ኃይል ነው። ድፍረት እና ወኔ እንጂ ወታደራዊ ስልቶች የሉትም። መሬት ላይ ተኝተህ መተኮስ እንዴት እንዳለብህ ተማር ብትለው እንደ ፈሪ ተኝቼ ነው ወይ የምተኩሰው ይልሀል። እና እነዛን ማሠልጠን፣ በግልና በቡድን እንዴት እንደምትዋጋ፣ እንዴት እንደምትነጣጠልና የት እንደምትገናኝ፣ የራድዮ ግንኙነትን በሚመለከት ወዘተ የተማሩ ሰዎች አገር ውስጥ ይገባሉ።
ስለዚህ በቂ ወታደራዊ ሳይንስ የሚያውቁ ሰዎች ነበሩ ማለት ነው?
አዎን! የመጀመሪያዎቹ ሦስትና አራት ዙሮች የኤርትራ መንግሥት የግድ ማሠልጠን ነበረበት፣ እነሱ አሠልጥነዋል። የግንቦት 7 ኃይል ሕዝባዊ ሠራዊት ሲመሠረት ኮሩ የሠለጠነው በእነሱ ነው። ከዚያ በኋላ ግን የሠለጠኑት ማሰልጠን ጀመሩ። ኤርትራ ምድር ላይ ይህን ትምህርት መስጠት የሚችሉ ኻያና ሠላሳ ሰዎች አሉ። አንዱ ሰው እንደ ካርታ ማንበብ ያሉ ብዙ ወታደራዊ ሙያዎችን እንዲያውቅ ይደረጋል። እኛም ደግሞ ከውጪ የሄድነው የፖለቲካውን ክፍል እንወጣለን። ለምን እና ለማን ትዋጋለህ? ስትዋጋ ምን ማድረግ አለብህ? ምን ማድረግ የለብህም፣ የሚለውን እናሠለጥናለን። ጥልቅ ነው እንጂ ጥራዝ ነጠቅ አይደለም።
እንደሚታወቀው ወታደሮች ብዙ የሚፈጽሟቸው ጥፋቶች አሉና ያ እንዳይፈጸም ነው። እንደዛ ያደረገ ወታደር ምህረት እንደማይደረግለትም ነው። የፖለቲካ ትምህርቱ አንዱም ይሄ ነው። ያንን እንዲያውቀውና የእኔ ነው እንዲል እንጂ እንደ ካድሬ መልሶ እንዲተፋው አይደለም። ውጦ እሱን እንዲኖረው ነው።
ምን ያህል ይሆናል በዚህ መንገድ የተዘጋጀ ጦር?
እንዳልኩህ ኤርትራ ውስጥ ጦር የማዘጋጀት ዓላማ አልነበረንም። ትልቁ ዓላማ በተለያየ ዘርፍ እየሠለጠኑ የሚመለሱ ናቸው። 400 ሰው ነበር ወደዚህ ስንመጣ። እኔ ኤርትራ ከገባሁ በኋላ በተለያየ ዙር ብዙ ሰው ገብቷል። አንድ ዙር ሥልጠና ሦስት ወር ይፈጃል። በዓመት ቢያንስ ሦስት ጊዜ ሥልጠና ይኖራል። በአንድ ጊዜ እስከ 300 ሰው ሊሠለጥን ይችላል፣ አንዳንዴ 500 ሊሆን ይችላል።
በሌሎች አጋጣሚዎች ደግሞ ቁጥራቸው እስከ 500 የሚደርሱ ከ18-25 እድሜ የሚደርሱ ወጣቶች ተገፍተው በረሀ ይወጣሉ። እነዚህ ሲመጡ በብዛትም ስለሆነ በደንብ ታቅዶ፣ ማለፊያ መንገድ ተሠርቶ ይመጣሉ። የመጡት በጋራ ለብቻቸው ይሠለጥናሉ። እና ዋናው ቁጥሩ አይደለም። እዛ ምድር ላይ ደንበኛ የፖለቲካ ትምህርትና ወታደራዊ ትምህርት በተለያየ መልክ የተማሩ ሰዎች ኢትዮጵያ ገብተው ይህን የተማሩትን እንዲያስተምሩ ነው።
ለዓመታት በኦሮሚያ እና ሌሎችም ቦታዎች የነበረው ተቃውሞ በአማራ ክልል የትጥቅ ትግል ወደ ሚመስል ግጭት ተሸጋገረ። ይህ ነገር ሲፈጠር ለምንድን ነው አርበኞች ግንቦት 7 በዚያ ጊዜ መጥቶ እድሉን ያልተጠቀመው፣ ለምን ዝም አለ የሚል ተቃውሞ ይሰማል። ያኔ ለምን እድሉን አልተጠቀማችሁም?
ለሥልጠና ወደ ኤርትራ የገቡ ሰዎች ተመልሰው ወደ ኢትዮጵያ በሰፊው የሚገቡበት ሁኔታ አልነበረም። ሰዎች ለምን አልሆነም የሚለውን ብቻ እንጂ ሊሆን ሲል የደረሰውን ጥፋት አያውቁም። ገብርዬ የምንለው ሰው የሚመራው ኃይል ነበር። ያኔም የሚመጡልን መረጃዎች በሙሉ ቦታዎች እንደታጠሩ ነበር። ግን እነ ገብርዬ አሰባብረን መድረስ እንችላለን አሉ። ገብርዬም መሄድ አለብኝ አለ። እዛ (ኢትዮጵያ) ያደራጃቸው ኃይሎች ነበሩና እኔ ሄጄ ከእነርሱ ጋር መገናኘት አለብኝ አለ። በዚህ ጊዜ በጎንደር ገና ትግሉ ሲፋፋም ነው።
ከዛም አንድ ኃይል ከገብርዬ በፊት ይሂድ ሲባል እንቢ ብሎ ሄደ። የገብርዬ ኃይል የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግሮ ለሦስት ቀናት ሲዋጋ ነበር። 85 ሰዎች ሦስት ቀን ሙሉ ውጊያ ላይ ነበሩ። በኋላ ግን ገብርዬ በጦርነቱ ሞተ። በጦር ስልት ልምድና አቅም የነበረው ሰው ነው። ፈረሳንይ የወታደራዊ ትምህርት የተማረ ነው። እሱን ካየን በኋላ ሌላ ኹለተኛ ኃይል ለመላክ ሞከርን። የሚመጡ መረጃዎች እንዳይሆን የሚነግሩን ነበሩ። ቆይተን የቀረው ኃይል ይላክ ተባለ። እናም ፈቃደኛ የሆነ ሰው እንዲሄድ አለን። 15 ሰዎች ፈቃደኛ ሆኑ፣ በሙሉ ተያዙ።
ሰው ልከህ የማይደርስ ከሆነ መላክህ ዋጋ የለውም። እንጂ ብዙ ተሞክሯል። ወያኔ ከማናችንም በላይ ጫካውን ያውቃል። ምን እንደሚደረግ አስቀድመው ያውቃሉ። ምክንያቱም እነሱም ያለፉበት አካሔድ ስለነበር ነው። ስለዚህ የሚያደርጉት በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል መጠበቅ ነው። ሌላ መግቢያ የለም፣ በትግራይ ነው የምትገባው። በዚያ ድንበር ደግሞ የሬድዬ መነጋገሪያ የያዘ ሰው ብቻ ነው የምታገኘው። እንደታየህ ወዲያው ሄሊኮፕተር ነው የሚመጣብህ።
ሱዳን ደግሞ ያኔ እንዴት ይታመናል። አስቸጋሪ ነው። ጥይት ማጓጓዝ ብዙ አይከብድም። በጠየቁት ልክ ጥይት ይሄድላቸዋል። የነፍስ ወከፍና የቡድን መሣሪያዎች ወደ እነዚህ ሰዎች ለማድረስ የምትሠራው ሥራ፣ የምትከፍተው መንገድና የምታጠፋው ገንዘብ ቀላል አይደለም፣ አስቸጋሪ ነው። እና ያ ሁሉ ችግር ነበር። ከመንግሥት ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጠህ መሣሪያና ወታደር ማሰለፍ የሚያስችል ኃይል አልነበረንም፣ የታወቀ ነው።
ከመጀመሪያ ጀምሮ ያላችሁበትን ደረጃና የሠራችሁት እንዲታወቅ አለማድረጋችሁ፣ ከሕዝብ ጋር በሚድያ አለመገናኘታችሁ ጎድቷችሁ ይሆን?
ወያኔ አላስገባ አለን ብለን ነው ወይ የምንነግረው? እንዲህ ሲነገር ቀላል ነው። አገር ውስጥ ያሉ የእኛ ኃይሎች ያውቃሉ። እንደዛ ተደርጎ ነው እዚህ የተደረሰው። በእኛ የሠለጠነው፣ በእኛ መዋቅር ውስጥ ያለ ሰው ይህን በደንብ ያውቃል። ለእነርሱማ ይነገራቸዋል። እንዲህ ያለ ችግር ሲፈጠር ዋናው የሚመለከተው ከሰማ በቂ ነው። ቀጥታ ከሕዝቡ ጋር አይገናኝም፣ የት አሉ የሚለው የልሒቃን አስተያየት ነው። እነዚህ ሰዎች ግን (የሚመለከታቸው) ለምን መድረስ እንዳልቻልን፣ ግን እንደሞከርን ያውቃሉ።
ጎንደር ሆኖ ከደሴ መሣሪያ ሲደርሰው ሰዉ ያውቃል። ያ ቡድን ለምን እንደዛ እንደሆነ ያውቃል። የሚመጣልን መረጃ የኢትዮጵያን ጦር ከሚመሩ ሰዎች ነው የሚደርሰን። አትምጡ ይሉናል፣ የእኛ ሰዎች ናቸው እንደዛ የሚሉን። ይህን ደግሞ አገር ውስጥ ላሉ ለእኛ መሪዎች እናሳውቃለን። አትምጡ ብለዋል ስለዚህ መሣሪያ በዚህ ይደርሳችኋል ብለን እንነግራቸዋለን። በዛ እንገናኛለን።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ጦሩም ተበተነ፣ በዛ ላይ ብዙ ውዝግብ ይነሳል። የተፈጠረው ምን ነበር?
ከኤርትራ ስንመጣ በጣም ግልጽ ነበር። እኔ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ነበርኩኝ። ያኔ ዐቢይ ወደ ሥልጣን ሊመጣ አካባቢ ብርሃኑ አሜሪካ ነበር። ድርጅቱን እኔ ነበርኩኝ የምመራው። ወደ አገር ውስጥ እንደምንገባ ማሰብ የጀመርነው ዐቢይ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆነ ጀምሮ ነው። ስለዚህም ከአውሮፓ አገራት ጋር መነጋገር ጀመርን፣ ወደ ኢትዮጵያ ከገባን አምስት ሺሕ የሚሆን ሠራዊት አለ። ይህን ሠራዊት መበተን አለብን። እናም እባካችሁ ገንዘብ ፈልጉልን ማለት ጀመርን።
በውስጥ የነበርነው ደግሞ ለሠራዊቱ አባላት ወደ አገር ቤት እንደምንገባና ስንገባ በምን ሥራ ላይ መሰማራት እንደሚፈልጉ፣ መማር የሚፈልግ ወይ ንግድ የሚፈልግ ካልሆነ ግብርና፣ ወታደርም መሆን የሚፈልግ ካለ ከአሁኑ አስቡ አልናቸው። አንዳንዶች ግን ወደ አገር ቤት መግባትን ይቃወሙ ነበር።
መጨረሻ ላይ የመመለሱ ነገር እርግጥ ሲሆን ፎርም አስሞላን። ፎርሙን ከሞሉ 400/500 ሰዎች ውስጥ አንድም እንኳ ወታደር መሆን የሚፈልግ አልነበረም። በሙሉ የሚፈልጉትን ዘርፍ አሳወቁ። ነገሮች ግልጽ ሲሆኑና ከዐቢይ ጋር ስንገናኝ፣ ጦሩ በምን መስመር ማለፍ እንዳለበት አንስተን እኔ በረሃ ተመለስኩኝ። ቀኑ መቆረጡን አሳወቅን።
መንግሥት እናንተ ከውጪ ገንዘብ የምታስገኙ ከሆነ እንተባበራለን አለን። ጀርመንን አናገሩልን። ስናረጋግጥ ሐሳብ መቀያየር እንደሌለ አሳወቅን። አገር ቤት ስትገቡ የመንግሥት ናችሁ፣ ዜጎች ናችሁ። የግንቦት 7 አባልነት ግን ይቀጥላል። መሣሪያ አትይዙም አልናቸው። ካምፕ አንኖርም ያሉ የተወሰነ ገንዘብ ተሰጥቶ ከቤተሰብ ጋር ይቀላቀላሉ፣ ሠራዊቱ ሲፈርስ ገንዘብ ይሰጣችኋል ካምፕ ግን አትገቡም አልናቸው።
መበተኑ መቼ ነው የሚል ጥያቄ ነበር። መበተን ጊዜ ይፈጃል፣ እኛ በእኛ መንገድ ብቻ ነበር ያሰብነው፣ አምስት ሺሕ ሰዎችን ነው ያሰብነው። ወደ አገር ውስጥ ስንገባ፣ የተገኘው ገንዘብ ለሁሉም ጦር ለያዘ ሆነ፣ ኦነግ አለ፣ ኦብነግ አለ፣ ሌሎችም አሉ። ከዛ ችግር መጣ። እኛ ከአገር ቤት የመጣውም ከዛ፣ የመጣው 500 ነበር፣ ግን 11 ሺሕ ደረሰ። አይሆንም አልናቸው።
የጀርመን መንግሥት ጠንካራ ፕሮጀክት አምጡ አለ። እኛ አቅም የለንም እሱን የምንፈጥርበት። መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ተቋቋመ፣ ግን ብቻውን አልቻለም። የመንግሥት እጅ መኖር አለበት፣ 50 ሚሊዮን ዩሮ ብዙ ነው። መንግሥት አቋቋምኩኝ አለ ግን አቅም የለውም ተብሎ አልሆነም። ብዙ ተሞክሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ባቋቋመው የድጋፍ ተቋም 3000 በወር እንዲያገኙ ተደረገ፣ ካምፕ ተቀምጠው። ያንን ፕሮጀክት አጥንቶ የሚተገብረው አካል ግን እየሠራ አይደለም። ለዚህም የደረሰው የእኛ ድርጅት ስላለ ነው።
ሰዎች የማይገነዘቡት አርበኞች ግንቦት 7 መንግሥት አይደለም። የውጪ አገር ሰዎች አብረው ስለነበሩ ነው ጠንካራ የነበረው። ተከትለውት የገቡ ጥቂት ናቸው። ያ ሁሉ ያቋቋመ ውጪ የነበረ ኃይል እንዲህ ያለ ለውጥ ሲፈጠር ተረጋጋና ገንዘብ ማዋጣት አቆመ። ምን እናድርግ እኛ? አንድ ሰው ሊዋጋ ሲገባኮ ለአገሩ ነው እንጂ ለእኔ አይደለም። እኔ (ወደ አገሬ ከገባሁ) ኹለት ዓመቴ ነው ግን በራሴ ገንዘብ ነው የምኖረው። 2006 ደሞዝ ማግኘት አቁሜአለሁ። በቤተሰቦቼ ገንዘብ ነው የምኖረው። እና እንዲህ የሚኖር ድርጅት በዚህ ደረጃ ሰዎችን አምጥቶ ገንዘብ አስገኝቶ፣ በእኛ ሰበብ ሌሎቹም ገንዘብ አገኙ። በአጠቃላይ 35 ሺሕ ከሁሉም የተውጣጣ ጦር ነው የሚበተነው። አለ ገንዘቡ፤ እንዲለቀቅ ግን ቅድመ ሁኔታ አለ። ገንዘቡ እንዲለቀቅ የእኛ ድርጅት ብቻ ነው ደፋ ቀና ያለው። እንዲያውም ገንዘቡን ለማስለቀቅ ሔደን የምናናግራቸው ሰዎች የምትሰደቡት እናንተ፣ ሰው ሜዳ ላይ ጣላችሁ የምትባሉት እናንተ፤ ነገር ግን የምትደክሙት እናንተ ሌሎቹ ምንም አደረጉ አይባሉም ነው የሚሉን። እኛን ለማስጠላት የፈለገ ኃይል ሁሉ በተበተኑት ወታደሮች ይጠቀማል።
እና ሠራዊት የመበተን ሥራ በአንዴ የሚያልቅ ሥራ አይደለም። አሁን ከኤርትራ ሲመጡ ካምፕ አንገባም ብለው 10 ሺሕ ወስደው ነበር። ብሩ ሲያልቅ መጥተው ካምፕ ልግባ ይላሉ። ይህን ቃል ያስገባው የኢትዮጵያ መንግሥት ነው።
አንዳንዶቹ ሲመቻቸው ከእኛ ጋር ካልሆነ ከእኛ ጋር አይደሉም። መሣሪያ አናስቀምጥም አሉ። ስንቴ ለመንን፣ ሽማግሌ ላክን፣ አናስቀምጥም አሉ። አሳምነው (ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ጽጌ) ለአማራ ተዋጉ ሲላቸው ነው የሄዱት። የእርሱ ታሪክ ተዘግቶ ሲመለሱ እናግኝ አሉ። ከዛ ደገሞ ይኸው ጣሉን ይላሉ። ይህን ሕዝብ ማወቅ አለበት። አርበኞች ግንቦት ሰባት ከእርሱ ጋር የታገሉትን ሰዎች አንድም ቀን ጥሎ አያውቅም። ግንቦት 7 እንደ ድርጅቱ ሲከስም እነ አንዳርጋቸውን ጨምሮ አራት ሰዎች ሰራዊቱን የመበትን ሥራ ተሰጥቷቸው ነው። ድርጅቱ መጨረሻ የነበረውን 12 እና 13 ሚሊዮን ብር በላይ ያወጣው ሬሳ ወደ አገር ውስጥ ማስገቢያ፣ ቤተሰቦች ማቋቋሚና መሰል ተግባራት ላይ ነው። ነገር ግን ምንም ብታደርግ መከሰስህ አይቀርም።
ወደ እርስዎ ልምጣ፣ ኢዜማ ተፈጠረ። እርስዎ ግን አልገቡም፤ ከዜግነት (አሜሪካዊ) ጉዳይ ውጪ ያልገቡበት ምክንያት ምንድን ነው?
ከመጀመሪያም ግንቦት 7 ሲፈጠር ጀምሮ፣ ከትልልቆቹ መሪዎች ጋር በተለያየ መንገድ ተነጋግረናል። ከተነጋገርንበት ጉዳይ መካከል አንዱ ትግሉ ተሳክቶልን ኢትዮጵያ ከገባን የምርጫ ፖለቲካ ውስጥ አልገባም ብዬ ነበር። ለዚህ ነው በነጻነት የታገልኩት። የሆነ ግብ አስቀምጠህ ከታገልክ እሱ እንዲሳካ ነው የምትሠራው። እኔ እንዲሳካ የፈለኩት ኢትዮጵያ ውስጥ ነጻነት፣ ፍትህ እና ዴሞክራሲ እንዲመጣ ነው። እሱን የሚያግድ ነገር የለም። በዛም ላይ 59 ዓመቴ ነው። 30 እና አርባ የሆነው ይታገል።
አልፎም በፖለቲካ ስትገባ በትግል የመጣ ሥም ሊያስመርጥህ ይችላል። ግን ፍጹም ውጥንቅጡ የወጣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ገብቼ እንደገና ከሰዎች ጋር መዳረቅ አልፈለኩም። ግንቦት 7 እያለሁ እንዲሁም ከዛም በፊት እንዴት ያሉ የፖለቲካ ልኂቃን እንዳሉን አይቻለሁ።
የኖርኩት ዋሺግተን ዲሲ ነው። ከአዲስ አበባ ቀጥሎ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚገመድበትና የሚፈታበት ስፍራ ነው። በዛውም ምን ዓይነት በፍጹም የማንግባባ መሆናችንን አውቄአለሁ። መጥፎ ነን፣ ውሸታችንን እንጂ እንደ ኢትዮጵያዊ የማይግባባ ምሁር የለም። በፍጹም ለፖለቲካ የማንመች ሰዎች ነን። እንደ ኢትዮጵያ ያለ ፖለቲካ ታጋሸና ቻይ መሆን ይፈልጋል። የታገስንና የቻልን ምን እንደሆንን አየሁ።
ግንቦት 7 የሚባለው ድርጅት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከተጫወተው ትልም ሚና አንዱ የኦሮሞን ተገንጣይ ኃይሎች ወደ መሃል ማምጣቱ ነው። ሰዎች ግን ያንን አላዩም። እነዚህ ከዘረኞችና ከተገንጣዮች ጋር ሆኑ ይሉናል። ከተገንጣይ ጋር ተገናኝተህ ካተነጋገርክ ከማያስገነጥል ጋር ምን ትነጋገራለህ?
ለዚህ ነው ተስማምቶ አንድ ድርጅት የማይፈጠረው። ፈጥሮም በሳምንት የሚፈርሰው ለዚህ ነው። አንድም የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ያልገባሁት ለዛ ነበር። ተማሪ እያለሁም አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ሲፈጠርና ስብሰባ ሲኖር እሄዳለሁ። ሁሌም የማየው ግን አንድ ዓይነት ፊት ነው። አዲስ ድርጅት ሲፈጠርም እነሱ ናቸው። እንዴት ሰው ከእነዚህ ሰዎች ጋር ይሠራል?
አሁን ብትመጣም፣ አገር ውስጥ ያለውም ገና ለጋ ነው። የውጪው የ60ዎቹ ያሉበት ነው። እነዚህ ደግሞ ቢያንስ በጠንካራ የትምህርት ስርዓት እና የኢትዮጵያዊነት ስሜት ውስጥ ተገንብተው ያደጉ ናቸው። አሁን ደግሞ በደካማ የትምህርት ስርዓት ውስጥ እና ዘር ላይ ባተኮረ የሕወኀት ፖለቲካ ውስጥ ያደጉ ለስላሳና ደካማ ናቸው። አሳማኝ ነገር ስታስቀምጥ የሚሰድብህ እንጂ የሚጠይቅ ሰው አታገኝም። ወደ አንድ ወገን ተጠግቶ ቁንጽል ሐሳብ የሚያራመድ ዓይነት ነው ያለው። እንደገና መገንባትና ጥሩ የትምህርት ስርዓት ፈጥረን ጠንካራ ምኁር ካላፈራን በቀር ችግር ውስጥ ነን።
እናም ፖለቲካ ውስጥ ላለመግባት ነው የወሰንኩት። ኢዜማዎች በስትራቴጂ መንደፍና ምርጫ ዝግጅት አብረን እንሠራን። ቤቴ ቁጭ ብዬ የምሠራው እሱን ነው። ግን ከምርጫው በኋላ ሥልጣን ይዘው ከሄዱ በኋላ እንደ ድሮው ብሎገር እሆን ይሆናል። እነሱን ራሱ እተቻለሁ። እሱ ይሻላል።
አሁን በኢትዮጵያ እንዲያድግ የምጥረው ዘርፍ ሚድያው ነው። ሚድያው ጠንካራ የሚሆንበትን መንገድ ካገኘን ዴሞክሪሲ የሚያብበው በዚያ ነው ብዬ አስባለሁ። የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲገነባ የግድ ፓርላማ መግባት ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን የለብህም። አናይም እንጂ ዐቢይ ዴሞክራሲን ለመገንባት እንደሚያደረግው ጥረት ሁሉ፣ በቀላሉ በቁጥጥሩ ስር ያለውን ሚድያ ለቦርድ ለቅቆ፣ በፍጹም የመንግሥት አካል ሳይገባባቸው በነጻነት የፈለጉትን ከሠሩ የተሻለ ይሠራል። ግን እሱ ራሱ ለዚህ የደረሰ አይመስለኝም፣ ትንሽ ይቀረዋል። ወደ ሚድያ መጥቼ ልሠራ አይደለም። ግን መንገዱን እና እንዴት ጠንካራ ይሆናል የሚለውን ጉዳይ ነው የማስበው።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አሁን ካለው ሁኔታ አንጻር ከፊታችን የሚመጣው ምርጫ እንዴት የሚሆን ይመስልዎታል?
ኢትዮጵያ ስገባ አንድ ጋዜጠኛ ይህን ጠይቆኝ ነበር። ምርጫው ሲቃረብ ምን ታያለህ ሲለኝ፣ ከባዱ ነገር የሚጣመሩና የሚለያዩ ሰዎችና ፓርቲዎች ናቸው። የተጣሉ ሰዎች አንድ ፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ሲሠሩ ይታያሉ። አንዳንድ ፓርቲዎች ጥምረት ይፈጥራሉ፣ በግለሰብ ደረጃም እንደዛ ይኖራል። አሁን እያየን ነው።
ኮሮና በጣም አጋልጦናል። ጥሩ ነው። አንዳንዴ ለጉዳት የመጣ ነገር አቅምና ድክመትን ያሳያል። አሁን ልደቱና ጃዋር የነበሩበትን መድረክ ሳይ ነበር፣ ሕገመንግሥቱ ምርጫ እንዲራዘም አለመፍቀዱ ጠንካራ ጎን ነው አሉ፣ እንደውም ደካማው ጎን እሱ ነው።
ግን ለምሳሌ ምርጫ ይካሄዳል ሲል ምርጫ ትልቅ ነገር ነው፣ የኃይል ሽግግር ነው። በምርጫ ጊዜ ትልቅ የተፈጥሮ አደጋ ወይ ሰው ሠራሽ አደጋ አልያም ጦርነት ቢኖርስ፣ ምንድን ነው የሚሆነው? ምን ዓይነት መንግሥት መፈጠር አለበት? ወይስ ፕሬዝዳንት ተነስቶ እገሌ እገሌ ፓርቲዎች አሁን ከሚመራው ፓርቲ ጋር ሆናችሁ ምርጫው እስኪካሄድ አገር ትመራላችሁ፣ በዚህ መልክ ፓርላማ የሚወስነው ውሳኔ በአገሪቱ የረጅም ጊዜ ተጽእኖ የሚያመጣ ሳይሆን የእለት ከእለት እንቅስቃሴን ለመወሰን የሚያስችል ይሆናል የሚል፣ ብቻ የሆነ ነገር፣ እንዲህ ያሉ ነገሮች መናገር ነበረበት። የሌሎች አገራት ሕገ መንግሥቶች ይህን ይናገራሉ።
የሕገ መንግሥቱ ትልቅ ድክመት የወደፊቱን አላየም። መንግሥት ይመሠረታል ወይስ ይቀጥላል? በምን መልኩ? ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የአደራ መንግሥት ይቋቋማል? በምን መልኩ? ማን ነው ይቋቋም ብሎ መነሻ የሚያቀርበው? ይሄን ማሳየት ነበረበት። ድመክት ነው አላሳየም። ያ ድክመት ቀውስ ፈጥሯል።
አሁን ኮሮና ባለበት፣ ለእኛ አይደለም ለአሜሪካ ከብዷል። የብሔር ፖለቲካ ሌላ ችግር ነው። ግብጽ አደጋ ልትጥል ትችላለች። ሱዳን ከተባበረች አደጋው አደገኛ ነው የሚሆነው። ይህ አደጋ ባለበት ጊዜ ውስጥ አንድ የፖለቲካ ምሁር ከገዢ ፓርቲ ጋር መተባበር ሲኖርበት፤ ከመስከረም 30 በኋላ እያሉ መዛት ምን ማለት ነው?
በአንድ አገር ውስጥ ለአገር አሳቢ መሆን አለብን። እኔ ለወደፊቱ ኢትዮጵያ ነው የማስበው። እሱም ኮሮና ሲጠፋ፣ የብሔር ፖለቲካውን ስንገላገልና ከግብጽ ጋር አስተማማኝ ሰላም ውስጥ ስንገባ ነው። ከግብጽ ጋር አስተማማኝ ሰላም ውስጥ እስካልገባን ድረስ አደጋ ላይ ነን። ጀግንነት እንዳለ ሆኖ የድሮ አንድነት የለንም።
በመሣሪያ፣ በአየር ኃይል፣ በምድር ከግብጽ ጋር አንገናኝም። ይህ ሁሉ ባለበት የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን ይህንን ለምንድን ነው የማያስቡት?
ለወደፊቱስ ምን ያታይዎታል?
ዐቢይ ከሕገ መንግሥት ውጪ ምንም አናደርግም ማለቱ ደስ አላለኝም። ለኢትዮጵያ መድኃኒት ሕገ መንግሥት ብቻ አይደለም፣ በሽታዋም ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ነው ያለው። በሽታው ካለበት ቦታ መድኃኒቱ አይመጣም። ስለዚህ አገር ማዳን የእሱ ብቻ ኃላፊነት አይደለም፣ እሱ ብቻውን ይችላል ብዬ አላስብም። አሁን ካሉ ፓርቲዎች ውስጥ ኃላፊነት የሚሰማቸውን ሰዎችና ፓርቲዎችን መለየትና መሰብሰብ ያስፈልጋል ባይ ነኝ። ቁጥራቸውም መቀነስ አለበት። ከዛም በደንብ አወያይቶ የፖለቲካ ስምምነት መፍጠር ነው።
ሕግና ሕገ መንግሥት ያስገድዳል፣ ሕገ መንግሥቱን የማይፈልጉ ሰዎች ለምን በዚሁ ሕገ መንግሥት ይገደዳሉ። የፖለቲካ ስምምነት ግን እንዲህ እናድርግ ብለው የሚስማሙበት ነው።
እኔ የሚቀጥለው ምርጫ ጉዳዬ አይደለም። እንዴት እንደምንደርስና እስከሚደርስ ምን እንሥራ የሚለው ላይ የፖለቲካ ስምምነት ያስፈልጋል። እሰከ አሁን መንግሥት እየወሰነ ነው እዚህ የደረስነው፣ ውሳኔዎቹ ጥሩ አልነበሩም። አሁን ያለው መንግሥትም ከራሱ አንጻር ነው የሚያየው። እናም ከሱ ብቻ መፍትሄ ይመጣል ብዬ አልጠብቅም። ችግርን በተፈጠረበት ልክ አስቦ መፍታት አይቻልም። ችግሩ ከተፈጠረበት የበለጠ ጭንቅላት ያስፈልጋል።
ብልጽግናን መግፋት ሳይሆን እነሱም ሌሎችም ባሉበት የፖለቲካ ስምምነት ተደርጎ፣ ምርጫው መች ይካሄድ በዚህ ቀን፣ እስከዛ ማን አገር ይምራ የሚለውን እነሱ ይስማሙ። እነሱ ሳይስማሙ የሚጫን ነገር ግን ጥሩ አይደለም። የፖለቲካ ምሁራንን በጅምላ እያበሳጨንና ተስፋ እያስቆረጥን ከሄድን፣ ለወደፊትም የተስማማንበት ውጤት አይኖርም። ያ ከሌለ ጭቅጭቅ ብቻ ነው የሚሆነው። የጭቅጭቁን ታሪክ መዝጋት አለብን ብዬ አምናለሁ።
ጊዜ ይወስዳል እንጂ የፖለቲካ ስምምነት ይመጣል። ግን እነማን ናቸው ስምምነቱን ማድረግ የሚገባቸው የሚለው አስቸጋሪ ነው።
ቅጽ 2 ቁጥር 80 ግንቦት 8 2012