ደኅንነት – የወረርሽኙ ማግስት ስጋት?

0
1031

ኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ዓለምን ማስጨነቁን ቀጥሏል። እድሜውን በቀናት ባረዘመ ቁጥር ዓለም ጉዳዩን እየተላመደችው ቢመስልም፣ መቼ ተጠራርጎ ይሄድ ይሆን የሚለውን መገመት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ወረርሽኙ የምጣኔ ሀብት እና ማኅበራዊ ሕይወት ላይ ከአሁን አልፎ ወደ ነገ ላይ የሚያደረሰው ተጽእኖ እንዳለ ሆኖ፣ የደኅንነትም ጉዳይ አሳሳቢ እንደሚሆን የዘርፉ ምሁራን ሲናገሩ ይሰማል።
የብሔር ፖለቲካ እየናጣት የቆየችው ኢትዮጵያ፣ በሕዳሴ ግድብ ምክንያት ከግብጽ ጋር ያለችበት ፍጥጫ ላይ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሚፈጥረው የምጣኔ ሀብት ቀውስና ሥራ አጥነት የድኅረ ኮሮና ደኅንነቷን አጣብቂኝ ውስጥ ያኖረዋል የሚሉ አሉ። አፍሪካ ላይ መሠረት ያደረጉ አሸባሪ ቡድኖችም ይህን በኢትዮጵያ ይኖራል ተብሎ የሚሰጋውን ሥራ አጥነት ተከትለው የራሳቸውን አጀንዳ መፈጸሚያ እንዳያደርጓት የሚል ስጋትም አለ። በተጓዳኝ ታድያ የደኅንነት መዋቅሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መምጣት በኋላ ተንገዳግዶ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን መልሶ እየጸና በመሆኑ ኃላፊነቱን በሚገባ ይወጣል የሚል ሙግት የሚያቀርቡም አሉ።
ይህን በሚመለከት ያሉ ነባራዊ እውነታዎችን፣ ስጋቶችንና አማራጭ መፍትሄ መንገዶችን በሚመለከት፣ መዛግብትን በማገላበጥና የሚመለከታቸውን በማነጋገር የአዲስ ማለዳው ኤርምያስ ሙሉጌታ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ብሎም በኢትዮጵያ ከተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በርካታ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሲነሱ እና ጥልቅ ትንታኔ ሲሰጥባቸው ቆይቷል። በተለይም ደግሞ በአገር ውስጥ በርካታ ዘርፍች የዓለም ዐቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ብሎም የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ ዳፋው ተርፏቸዋል። እናም ኢትዮጵያ እንደ አገር ይሆናሉ ያለቻቸውን የመከላከል እና ወረርሽኙ ሊያስከትል የሚችለውን የትኛውንም አይነት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመከላከል፣ በመንግሥት በኩል በርካታ የሀብት ማሰባሰብ ሥራዎችን ስትሠራ ቆይታለች፣ እየሠራችም ትገኛለች።

ይሁን እንጂ በበርካታ አገራት እንደታየው የወረርሽኙ የጉዳት መጠን ከቻሉ ለመከላከል ካልተቻ ደግሞ የከፋ እና ረጅም ጊዜያትን የሚቆይ ችግር ጥሎ እንዳያልፍ ከወዲሁ በርካታ እርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ። በተለይም ደግሞ ያደጉ አገራት መንግሥት ለግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ ከገቡበት ኪሳራ እና የንግድ እንቅስቃሴያቸው መቀዛቀዙን ተከትሎ፣ ሊገጥማቸው ከሚችለው ተግዳሮት እና ያንንም ተከትሎ ከሚከሰተው የሠራተኞች ቅነሳ እና ተያያዥ ማኅበራዊም ቀውስ አንጻር፣ ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮች እንዳይከሰቱ አስቀድመው ተዘጋጅተው እንደነበር ይታወቃል።

ይሁን እንጂ በአገራት በኩል የተወሰደው እርምጃ በቂ ካለመሆኑ ጋር የተነሳ ወደ ሥራ ተመልሰው እንዲገቡ የሚደረጉ እና የእለት ጉርሳቸውን ሸፍነው ችለው በቤት ውስጥ መቀመጥ የማይችሉ ሠርተው እንዲደግፉ ሲደረግ፣ በአደጉ አገራት እንደ አሜሪካ ያሉ አገራት ዘንድም እየተስተዋለ ነው።

በአገራችን ኢትዮጵያም ኮቪድ 19 መጀመሪያ መገኘቱ ከተረጋገጠ ከመጋቢት 4/2012 ጀምሮ መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድና ወረርሽኙ ሊያደርሰው ከሚችለው ዘርፈ ብዙ ችግር ለመዳን በርካታ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፣ እየተንቀሳቀሰም ይገኛል። በሲቪል ማኅበራት ዘንድም ወረርሽኙ በኢትዮጵያ ከመከሰቱ አስቀድሞ 12 አባላት ያሉት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እንዴት ለወረርሽኙ ምላሽ መስጠት እንደሚቻል ሐሳብ ሲያወጡና ሲያወርዱ ነበር። ወረርሽኙን ለመከላከል በሚደረጉ የርብርብ እርምጃዎችም ሊጎዱ የሚችሉ፣ ሥራቸው ከዕለት ጉርስ የማያልፍ ሰዎች በሚደርሰው ችግር ተጎጂ እንዳይሆኑ ማድረግም ቀድሞ የታሰበበት ጉዳይ መሆኑን፣ የሲቪል ማኅበራት ኢክሲኪዩቲቭ ዳይሬክተር ብሌን አስራት ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ።

በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተከትሎ በቅርቡ ብዙ የቪዲዮ ኮንፍረንስ ላይ ኢፌዴሪ የሥራ ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽር ዶክተር ኤፍሬም ተክሌ ወረርሽን ተከትሎ በርካታ ጉዳቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ እና በተለያዩ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች እና ንግዶች መቀዛቀዛቸው የማይቀር ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ በሚሊዮን የሚቆጠር ሰዎች ከሥራቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ አስቀምጠዋል።

ኤፍሬም አያይዘውም ከተለያዩ ዘርፎች ማለትም ከግብርና፣ ከግንባታ፣ ከሆቴልና ቱሪዝም እንዲሁም ከአምራች ዘርፉ ቁጥሩ በዛ ያለ የሰው ኃይል ከሥራ ሊፈናቀል እንደሚችል አስታውቀው ነበር። እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ የኮሮና ቫይረስ በአገሪቱ አሁን ባለበት ሁኔታ የሚገታ ከሆነ በአጭር ጊዜ ተጽዕኖው 800 ሺሕ ሰዎች፣ በመካከለኛ ተጽዕኖው 1.4 ሚሊዮን ሰዎች እንድሁም የቫይረሱ ሥርጭት በዚሁ ከቀጠለ 2 ሚሊዮን ሰዎች በቀጣይ ሦስት ወራት ከሥራ ገበታቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል። ኮሚሽነሩ አክለውም ቫይረሱ ወረርሽኝ ከሚቀጥሉት ሦስት ወራት ከዘለለ የሥራ አጥ ቁጥሩ በእጥፍ ሊጨምር እንደሚችል ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ ሊቀነስ የታሰበው የሰው ኃይል ባለበት እንዲቆይ መንግሥት ጥብቅ ትዕዛዝ ቢያደርግም ይህን ተላልፈው ግን ሠራተኞችን የሚያሰናብቱ ድርጅቶች ቁጥራቸው ጥቂት አይባልም። በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ የተሰማሩት ደግሞ ወደ አገር የሚገቡ ሰዎች እና ጎብኚዎች ካለመኖራቸው ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ሆነ የገቢ መቀዛቀዝ በመታየቱ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ሠራተኛ ቁጥር እየቀነሱ እንደሚገኙ አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም ለንባብ ባበቃቻቸው እትሞች በስፋት ተዳስሰዋል።

ይህን ወረርሽኝ እና ወረርኙን ተከትሎ ደግሞ የሥራ አጥነት ችግሩም ከመከሰቱ ጋር ተዳምሮ በተለይ ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል ወደ አልተፈለገ ወንጀል፣ የፖለቲካ መጠቀሚያ፣ ጽንፈኝነት፣ አክራሪነት ወደሚሰኙ እና አገርን፣ ቀጠናን ከፍ ሲልም ዓለምን እንቅልፍ ወደ ሚነሱ ተግባራት፣ አንዳንዴም ወደ ተደራጁ ወንጀሎች የመግባት አዝማሚያ እንደሚኖር በሰላም እና ደኅንነት ዙሪያ በርካታ ዓመታትን በሰላምና እና በደኀንነት ዘርፍ ተሰማርተው የሚሠሩ ባለሙያዎች ያብራራሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላምና ደኅንት ጥናት ተቋም የሦስተኛ ዲግሪያቸውን በማጠናቀቅ ላይ የሚገኙት ሙሉቀን ሀብቱ በዚህ ጉዳይ እና በድኅረ ኮቪድ 19 በኢትዮጵያ ብሎም በቀጠናው ላይ ሊታይ የሚችለውን የደኅንነት ስጋት በተመለከተ፣ አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ ያስረዳሉ። እንደ ሙሉቀን ገለጻ ወረርሽኙ በሚቆምበት ወቅት ደሃ አገር እንደመሆናችን የምጣኔ ሀብታችንን እንደሚያደቀው እና ይህም ደግሞ ለብዙዎች ከሥራ መፈናቀል ምክንያት እንደሚሆን ተናግረዋል። በተለይም ደግሞ ወጣቱ በሥራ ማጣት ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ በአገር እና በቀጠናው ላይ አደጋ ጣይ አካላት ሊገዙት እና መጠቀሚያ ሊያደርጉት እንደሚችሉ ስጋታቸውን አንስተዋል።

‹‹አሁን ያለንበት ወቅት በውስጥም ሆነ በውጭ የኢትዮጵያን አመቺ ጊዜ እና የተዳከመችበትን ወቅት በመጠባበቅ የተለያዩ አካላት የፖለቲካም ሆነ ሌላ ግባቸውን ሊያስተጋቡ የሚጥሩበት ወቅት ላይ ነው ያለነው። በዚህ ድርጊት ታዲያ ቀንደኛ ተዋናይ የሚሆነው እና ለእንደዚህ አይነት ተግባር ቀድሞ የሚገኘው ወጣቱ እንደመሆኑ መጠን ከሚፈጠረው የሥራ አጥነት ጋር ተዳምሮ እጅግ ፈታኝ የሆነ ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያ ልትገባ እንደምትችል እገምታለሁ። የዓባይ ጉዳይ አለ፣ የአገር ውስጥ አለመረጋጋቶች አሉ። እንዲሁም ቀጠናው የሰላም እጦት ከቀድሞው ጀምሮ በመኖሩ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል›› ሲሉ ይናገራሉ።

ሙሉቀን ቀጥለውም በአገር ውስጥ የሚታየው ውዥንብር እና ወጣቶችን መጠቀሚያ የማድረግ ሂደት የቆየ ቢሆንም፣ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ ሰላምና ወደ ልማት፣ ብልጽግና ባዞረችበት ወቅት እንቅፋት መሆኑ እንደማይቀር ጠቁመዋል። ይህንንም በሚመለከት ሙሉቀን እንደመፍትሔ ይሆናል ያሉትን ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ። ‹‹በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባን ብንወስድ በተቀማጭ ሀብት ነው እየተንቀሳቀሰች ያለችው። የሚደረገው ድጋፍ በሙሉ በተቀማጭ ሀብት ነው። ምክንያቱ ደግሞ ያልታሰበ ሁኔታ ስላጋጠመ ነው። ይህ ምንም ማለት አይደለም፤ ባይሆን ግን መንግሥት እየታዩ ያሉትን የመሬት ወረራዎች ማስቆም ይኖርበታል።
ምክንያም የመንግሥት ትልቁ ሀብት መሬት እንደመሆኑ መጠን ወደ ፊት ይህ ወረርሽኝ ባለቀ ጊዜ ለሚኖረው እና ተፈጥሮ ለሚቆየው ከፍተኛ ቁጥር ላለው የሥራ አጥ ቁጥር መቀነሻ የሚሆን ሀብት እንዲኖር ማድረግ ይቻላል›› ብለዋል።

አያይዘውም በአሁኑ ወቅት በመንግሥት በኩል እንዲደረግ የሚገባው ነገር ያሉትን ሲያነሱ፣ ‹‹ሀብት በሚገባ እና በአግባቡ በመጠቀም ወረርሽኙ እየጠነከረም ቢሄድ መቋቋም የሚችልበትን ወይም በአጭር ጊዜ የሚያበቃም ከሆነ በኹለቱም መንገድ ምጣኔ ሀብቱን ስለሚያደቀው እሱን ምክንያት ያደረገ የደኅንነት ስጋት ሊፈጠር ይችላል። በመሆኑም ዋነኛ ሀብት የሆነውን የመሬት ሀብት በተገቢው መንገድ መጠበቅ እና ወደ ፊት መሬቱን እየሸጠ በገንዘብም ሆነ በሌላ ረገድ፣ ሥራ አጥ ወጣቱን በመደገፍ ወደ ጥፋት ሊያመሩ የነበሩትንም መከላከል ይቻላል›› በሚል ሐሳባቸውን ይሰነዝራሉ።

የሙሉቀንን ሐሳብ የሚጋሩት ደግሞ በጸጥታ ዘርፍ በርካታ ዓመታት ልምድ ያላቸው እና አሁንም በሰላምና ጸጥታ ዘርፍ አገርን እያገለገሉ የሚገኙ ከፍተኛ ባለሙያ ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ፣ ከውጭ በተለይም ከግብጽ የሚሰነዘረው በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የሚላከው የማተራመስ ስልት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየረቀቀ እየመጣ እንደሆነና ይህ ደግሞ በቀጣይ ይፈጠራል ለሚባለው ሥራ አጥ ቁጥር ጋር ተዳምሮ ከባድ አደጋ ሊጥል እንደሚችል ያስረዳሉ።

‹‹በመጀመሪያ ደረጃ እንደ አገር ቀጠናውን ማሰስ (ሪጅን ስካኒንግ) የሚባለውን እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። ይህ ማለት ማን በኢትዮጵያ ላይ ምን አይነት አጀንዳ አለው? ምን ይፈልጋል? ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ጉዳይ በዲፕሎማሲያዊ ወይስ በወታደራዊ መንገድ ሊፈቱ የሚችሉ ጉዳዮች ናቸው የሚሉ እና በርካታ ጉዳዮችን ታሳቢ ያደረገ ቀጠናውን የማሰስ ሥራ መሥራት ይኖርበታል። ይህ ቅድሚያ ቢደረግም ወጣቶችን ግን ከሥራ ገበታቸው ላይ እንዲቆዩ ማድረግ ወይም የተከፈለው መስዋዕትነት ተከፍሎ ሥራ ተፈጥሮላቸው ራሳቸውን በሥራ እንዲጠምዱ እና ለውጭም ሆነ ለአገር ውስጥ ሐሳባቸውን በመነጋገር ፋንታ በብጥብጥና አለመረጋጋትን በመፍጠር ሊያስተጋቡ ለሚወዱ ሰዎች ተገዝተው ወይም በገንዘብ ተደልለው ተሳታፊ ሊሆኑ የሚችሉበት አቅም መኖሩ አያጠራጥርም።

የውጭ ኃይሎች እንኳን በአገር ውስጥ ያለውን ወጣት ነው በገንዘብ ገዝተው አለመረጋጋቶች እንዲፈጠረ የሚያደርጉት። ሥራ ባለመኖሩ የተነሳ የተገዛን ወጣት አንዳንድ ጊዜ አገር ከድተሃል ብለህ መወንጀል ራሱ ትንሽ ደረት የሚያስፋ ጉዳይ አይደለም። መጀመሪያ ሥራውን እንፍጠርለት። ከዛ ካለፈ እና ወደ ጥፋት ኃይሎች ከተመለከተ ግን በትክክል ያለ ምክንያት ትርምሱን ፈልጎታልና እርምጃም ቢወሰድበት አጥጋቢ ይሆናል›› ሲሉ ይናገራሉ።

የደኅንነት ባለሙያው በተለይ የዓባይ ጉዳይ ዓለም ዐቀፋዊ ጉዳይ በሆነበት ወቅት እና ከግብጽ በኩል እየተቃጣ የሚገኘው የእጅ አዙር አፍራሽ ተግባር ጭራሽ የወጣቶች ሥራ አጥነት ጋር ተዳምሮ በጣም አስፈሪ ደረጃ ላይ እንደሚደረስ ሳያነሱ አልቀሩም። በቅርቡ እንኳን በአባይ ግድብ የግንባታ ስፍራ ላይ በግብጽ የገንዘብ እርዳታ የታገዙ ወጣቶች ግንባታው እንዳይካሄድ አለመረጋጋት እና ሁከት ለመፍጠር ሲሞክሩ በደኅንነት እና በጸጥታ አካላት በእንጭጩ መቀጨቱን ያወሳሉ።
ከዚህም በተጨማሪ ከተለያዩ አገራት በተለይም ከጎረቤት አገራት ጋር ከዚህ ቀደም የነበረውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከመቼውም በበለጠ አጠናክረን መቀጠል እንዳለብን የሚመክሩት ደግሞ ሰላምና ደኅንነት ምሑሩ ሙሉቀን ሀብቱ ናቸው። ሙሉቀን እንደሚሉት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተግባራት ባለፈ ተጨማሪ የአግባቢ ባለሙያዎችን (ሎቢስት) በመቅጠርና በመመደብ በርካታ ጉዳዮችን አንድ በአንድ በማንሳት ማግባባት እና በቀጠናው ላይ ያለውን መልካዓ ምድራዊ ፖለቲካ አስጠብቆ መቀጠል ይገባል ሲሉ ያስረዳሉ።

በርካቶች አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በተለይ ደግሞ በዓባይ ጉዳይ ላይ የተፋሰስ አገራትን መያዝ እያለበት ወደ በለጸጉት አገራት በመሄድ የዳኝነቱን ሚና እንዲይዙ አድርጓል በሚል ስለሚተችበት ጉዳይም ሙሉቀን ሲመልሱ፣ በእርግጥ የተደረገው ጉዳይ ትክክል እንዳልነበርና በኢትዮጵያ ላይ አለመረጋጋት ቢፈጠር እንኳን ከጎረቤት አገራት ውጭ ከየትም ሊመጣ ወይም ሊጠነሰስ የማይችል ሴራ እንደሆነ ጠቅሰዋል። አያይዘውም የጎረቤት አገራትን በሚገባ በመያዝ አገርን ሰላም ማድረግ ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ያስረዳሉ።

‹‹ከዚህም በላይ ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በኹሉም የጎረቤት አገራት ውስጥ ወረርሽኙ የሚያሳድረው ጫና ቀላል አይሆንም። በመሆኑም እነሱም ከኢትዮጵያ የተለዩ ካለመሆናቸው ጋር ተያይዞ ወጣቶቻቸው ወደ ሽብር ቡድን እና ወደ ተደራጁ ወንጀሎች ድንበር ዘለሎችንም ጨምሮ ሊሳተፉ ይችላሉ። ይህ ታዲያ ቀጠናውን የትርምስ ቀጠና በማድረግ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን ከማዳከሙ ባለፈ ከድጡ ወደ ማጡ የሆነ አካሔድ በአገራት ላይ ሊያካሂድ ይችላል። በመሆኑን በቀጠና መዋቅደሩ ተቋማት እንደ የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት አይነት ተቋማት በጥምረት በመሆን በቀጠናው የሚከሰተውን የሥራ አጥነትን ተንተርሶ የሚመጣውን ቀጠናውን የሰላም መናጋት መቆጣጠር ይኖርበታል። ምክንያቱም የአንዱ ጎረቤት አገር ሰላም መደፍረስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያን መጉዳቱ የማይቀር ነው›› ሲሉ ይናገራሉ።

አያይዘውም በመጀመሪያ ደረጃ የኑሮ ውድነት የማይነካው የኅብረተሰብ ክፍል የለም ያሉ ሲሆን፣ ምናልባት ከፖለቲካው ርቆ የሚኖር እንኳን ቢሆን በኑሮ ውድነቱ ተማርሮ ግን አደባባይ በመውጣት ጩኸቱን የማያሰማ እንደማይኖር በልበ ሙሉነት ተናግረዋል። በጎረቤት አገር የሱዳን ጉዳይ እና የአረብ አገራትን አብዮት መነሻዎች እንደ አብነት ነክተዋል።

በዚህም ረገድ መንግሥት የተጠናከረ የደኅንነት መዋቅር ከሌለው ሕገ ወጥ ግብይቶችንና የዕቃ ክምችቶችን በመቆጣጠር ሰላማዊ እንቅስቃሴን በማስፈን ማስተዳደር ይከብደዋል የሚል ፍራቻ አለባቸው።

በአገር ውስጥ የዜጎችን ደኅንነት ባለማረጋገጥ የአገርን ሕልውና ማስጠበቅ ከባድ እንደሆነ የሰላምና ደኅንነት ልሒቃን በአንድ ድምፅ የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። አገር በውስጥ ጉዳይ መረጋጋት እና ደኅንነት ከሌለ ከውጭ ቀጥተኛ ወረራ እና ጥቃቶች መከላከል የማይታሰብ ነው። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ምሁራን ያለፉትን 27 ዓመታት እና አሁን ያለውን የለውጡ ኃይል ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ ያለውን በንፅፅር ያስቀምጣሉ።

ባለፉት ዓመታት መረጋጋቱ የተፈጠረበት መንገድ የሚደገፍ እና ትክክለኛ መንገድ ባይሆንም ነገር ግን በአንፃራዊነት መረጋጋቶች በኹሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የታዩበት ጊዜ ነበር ይላሉ። አያይዘውም ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ያለውን አገራዊ ደህንነት ከማረጋገጥ ባሻገርም በጎረቤት አገራት ላይ ቀጠናዊ የፖለቲካ የበላይነትን እስከመፍጠር የደረሰችበት ዘመን ነበር ብለዋል።

በአገር ውስጥ ከፍተኛ የሆኑ አለመረጋጋቶች ተፈጥረው በነበረበት ወቀት ከክልል ልዩ ኃይሎች ባለፈ የመከላከያ ሠራዊት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል በመሰማራት ከፍተኛ አገር የማረጋጋት ሥራ ሲሠራ እንደነበር የሚታወስ ነው። ይህን በሚመለከትም መከላከያ ሠራዊቱ ድንበርን ከመጠበቅ አኳያ ልል የነበረበት ወቅትም እንደነበርና ይህም ደግሞ አሁን ላይ ኢትዮጵያ እየሄደችበት ላለው መንገድ እጅግ አስፈላጊው ድንበር ጥበቃ መሆኑን ያስረገጡት ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የዘርፉ ምሁር ናቸው።

በተለይም ደግሞ በዓመታት ውስጥ ጠፋ ሲሉት ቅርጹን እየቀያየረ የሚከሰተውን የሱማሊያውን አሸባሪ ቡድን፣ ይልቁንም ደግሞ ራሱን የምሥራቅ አፍሪካ የአልቃይዳ ክንፍ ብሎ የሚጠራውን አልሸባብ ጉዳይ በተመለከተ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ አድርገው ምላሻቸውን አሰምተዋል።

በተለይም ደግሞ የደኅንነት ስጋተ በሆነው አልሸባብ ላይ በአሚሶም በኩል እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በቂ ነው ብለው እንደማያስቡ ይናገራሉ። ልዩ የተልዕኮው ቡድንም በተገቢው ሁኔታ ተልዕኮውን እየተወጣ ነው ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ። ከአሚሶም የሰላም ማስከበር ጦር ውስጥ 20 በመቶ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል የተወጣጣ ቢሆንም፣ 63 በመቶ የሚሆነውን የሰላም ማስከበር አካባቢውን ደግሞ የሚሸፍነው ይኸው 20 በመቶው የኢትዮጵያ ኃይል እንደሆነም ይጠቁማሉ። እንደምክንያት የሚያስቀምጡት ደግሞ አልሸባብ ከቀጥተኛ ውጊያ ይልቅ የደፈጣ ውጊያን ስለሚከተልና የኢትዮጵያ ጦርም ለዚህ አዲስ ባለመሆኑ በቀላሉ ሊቆጣጠረው እንደሚቻለው ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ እንደ ዘርፉ ምሁር አስተያየት አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከአልሸባብ ጥቃት ኢትዮጵያ በብቃት ራሷን መከላከል ትችላለች ብለው ለማመን እንደሚቸገሩ ያላቸውን ሥጋት ገልጸዋል። ‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ድንበር ላይ የሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት እየተሳበ ወደ መሃል አገር እየተመለሰ ነው የሚገኘው። ምክንያቱ ደግሞ በአገር ውስጥ ያለው አለመረጋጋት ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ ስለሚገኝ አልሸባብ ጥቃት ለማድረስ መግቢያው ከመቼውም በተለየ ክፍት ስለሚሆን›› የሚሉት ምሁሩ፣ አል ሸባብ በዋናነት እንደመግቢያ የሚጠቀመው ምሥራቃዊውን ክፍል በተለይ ደግሞ ሱማሌ ክልልን በመሆኑ አንድ ባሕል፣ አንድ ጎሣ፣ አንድ ሃይማኖት ባለው ኹለት ሕዝብ ውስጥ ሰርጎ መግባት ቀላል እንደሚሆነው ይጠቁማሉ።

በሰላምና ደኅንነት ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎችም ከምሁሩ ጋር ይስማማሉ። ሌሎች ምክንያቶችንም በምሁራኑ ይጠቀሳሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ካለው ለውጥ ጋር በተያያዘ የደኅንነት መዋቅሩ መዳከም ለሰርጎ ገቦች አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። ሰርጎ ገቦች ደግሞ በዋናነት ወጣቱን የኅብረተሰብ ክፍል ከመጠቀም አዝማሚያ ጋር ተያይዞ ሥራ አጡ ሲጨምር ለሰርጎ ገቦች የሚገዛው ወጣት ቁጥርም በዛው ልክ እንደሚጨምር ይገምታሉ።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ሆነው ወደ ክልሉ በመግባት የደኅንነት ሥራን የሚሠሩ ሰዎችንም ማግኘት ቀላል እንዳልሆነ ይናገራሉ። በተጨማሪም በሱማሌ ክልል የሚገኙ ያኮረፉ ቡድኖች ለውጭ ኃይሎች መጠቀሚያም የሚሆኑበት አጋጣሚዎች ሰፊ ሊሆን እንደሚችል ሌላው ተጠቃሽ ምክንያት ነው ይላሉ።

በሶማሊያ አሁን የሚገኘው የመንግሥት ቁመና መሰረት አድርገውም ሲናገሩ፤ የሶማሊያ መንግሥት መሣሪያ እንኳን እንዳይገዛ ዓለም ዐቀፍ ማዕቀብ ስላለበት በቀጥታ ለመታጠቅም ስለሚቸገር አልሸባብን ለመዋጋት ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሚኖርበት ገልፀው፣ በተባበሩት መንግሥታት በኩል ትጥቅ እንደሚያገኙም ተናግረዋል።
ከነባራዊው ሁኔታ ጋር ተያይዞ ኮቪድ 19 በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን በጎረቤት ብሎም በዓለም አገራት ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ከማድረሱም ባለፈ በቀጣይ ወረርሽኙን መቆጣጠር ከተቻለ በኋላ እንኳን ትልቅ የቤት ሥራ ለአገራት ሰጥቶ ያልፋል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ ያትታሉ። በዚህም ወቅት ታዲያ ሥራ አጥነት እና ድህነት ወጣቱን በአሸባሪ ቡድኖች የመሳብ እና ለዓላማቸው ማሳኪያ አይሆንም ወይ ለሚለው ጥያቄ ሰላምና ደኅንነት ምሁሩ ዳንኤል ከበደ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ ይህ ሊሆን የማይችልበት ምንም ምክንያት እንደሌለ ያስረዳሉ።

ከዚሁ በተመሳሳይ በምሥራቅ አፍሪካ የፀጥታ ሁኔታን በቅርበት የሚከታተሉት ማርቲን ፕላውት አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ ሲሰጡ፣ አልሸባብ ከአይኤስ በበለጠ የኢትዮጵያን ወጣቶች ለመማረክ እየሠራ ነው። ለዚህም ከቡድኑ የሥራ ቋንቋዎች አንዱ አፋን ኦሮሞ እንዲሆን ወስኖ በዚሁ ቋንቋም የተለያዩ መግለጫዎችን እያወጣ ነው።

ተንታኞች እንደሚሉት አልሸባብ በፕሮፓጋንዳ መሣሪያዎቹ ለወትሮው ከሱማሊኛ በተጨማሪ ይጠቀም የነበረው ቋንቋ እንግሊዝኛ፣ አረብኛና ስዋሒሊ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አፋን ኦሮሞም ተጨምሯል። ምናልባትም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉና የተከፉ ወጣቶችን ትኩረት ለመሳብ የተከተለው ዘዴ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

በዚህ ረገድ አይኤስ ግልጽ ነገር የለውም። በሚታወቁት ልሳኖቹ (‘አማቅ’ እና ‘ዊላያት’) በሶማሊያ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በተመለከተ የለቀቃቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎችም ሆኑ ጽሑፎች አዘውትሮ ከሚጠቀምበት ቋንቋ ተሻግሮ እንደ አልሸባብ የኢትዮጵያን ቋንቋዎች ሲጠቀም አልተስተዋለም።

ማርቲን ፕላውት በበኩላቸው ኢትዮጵያ ኦጋዴንን ለመጠቅለል ታስቦ በነበረው ጦርነት ሶማሊያ ጦር በለስ ባይቀናው እና እንደተዳከመ ቢቆይም፣ የአሁኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ብሔርን መሰረት ያደረገ መከፋፈል የቀደመውን የሶማሊያን ምኞት ሊያሳካ የሚችልበትን እድል ሊኖር እንደሚችል ግምታቸውን በማስቀመጥ የወደፊቱን መገመት በርግጥ ከባድ መሆኑን ግን አልሸሸጉም። ይህ ግን እንደ ማርቲን ትንበያ አሁን ያለው ዓለም ዐቀፋዊ ወረርሽኝ ወቅት ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ነገር በቅጡ ካልታሰበበት ከዚህ ቀደም አይሆኑም ያልናቸው ጉዳዮች መከሰታቸው እንደማይቀርና በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያ በቀጠናው ላይ ያላትን ጉልህ ሚና ለማድቀቅ የሚሠራ ሥራ ይኖራል ብለው እንደሚገምቱ ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ።

ማርቲን ፕላውት በኢትዮጵያ ያለውን የደኅንነት መዋቅርም በተመለከተ በርከት ያሉ አስተያየቶችን ሰንዝረዋል። ይህም ደግሞ ሊመጣ ላለው እና ይመጣል ተብሎ ለታሰበው የደኅንነት ስጋት ቅድመ ዝግጅት ሊደረግ ከመገባቱ ጋር ተያይዞ መደርጀት ይገባዋል ስለሚባል አንደኛው የጸጥታ መዋቅር ደኅንነት መዋቅሩ መሆኑን ያነሳሉ።
በቅርቡ በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ የከንቲባ ቢሮ አቅራቢያ በአንዲት እንስት አጥፍቶ ጠፊ በተፈፀመ ጥቃት የተማዋ ከንቲባ ጨምሮ በርካቶች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት ደርሶ እንደነበር ዓለም ዐቀፍ የዜና አውታሮች እየተቀባበሉ ሲዘግቡት የነበረ ጉዳይ ነው። ጥቃቱንም ሙሉ በሙሉ ኃላፊነቱን የወጣቶቹ ቡድን አልሸባብ አፍታ ሳይቆይ መውሰዱን አስታውቋል።

በዚህ ጥቃት የሞቃዲሾ ከተማ ከንቲባ አብድረህማን ኦማር ዑስማንን እስከ ወዲያኛው እንዲያሸልቡ አድርጓል። ከንቲባው ጥቃት በደረሰባቸው ወቅት ለተጨማሪ የሕክምና ዕርዳታ ወደ ኳታር አቅንተው የነበረ ቢሆንም ሐምሌ 25/ 2011 ከወደ ዶሃ ዜና ዕረፍታቸው ተሰምቷል። የአፍሪካ ኅብረት መራሹ የሰላም አስከባሪ አሚሶም በስፋት በሚንቀሳቀስበት ወቅት ይህን አይነት ከባድ ጥቃት ያውም በከፍተኛ መንግሥት ሹም እና መሥሪያ ቤት ላይ ማድረሱን አሚሶምን መነሻ አድርገው ይናገራሉ። ይህ ታዲያ በቅርቡ ይፈጠራል ተብሎ ለሚታሰበው የምጣኔ ሀብት ድቀት፣ ሥራ አጥነት እንዲሁም ኑሮ ውድነት ወጣቱን ወደ አልተፈለገ ቡድን እና አገርንም ወዳልታሰበ ሽብር ውስጥ የሚከት እንደሚሆን ያስረዳሉ።

አዲስ ማለዳ እንግዳ የነበሩት እና በደኅንነቱ ዘርፍ ረጅም ዓመታትን በማገልገል ያስቆጠሩት ባለሙያ ሲናገሩ በእርግጥ ለውጡ ከመጣበት ጊዜ ወዲህ በርካታ የደኅንነት መዋቅሩ ላይ አያሌ ለውጦች ተካሔደዋል። በየጊዜው የሥልጠና እና የአቅም ግንባታ ሥራዎች መሠራታቸውን እና በተቋሙ ሽብርን የመከላከል ቁመና ላይ ምንም አይነት ጥርጣሬ እንደሌላቸው ያስረዳሉ።

በርካታ አካላት የደኅንነት መዋቅሩ እምብዛም አይደለም ሲሉ እንደሚደመጡ እና ይህም ከእውነት የራቀ መሆኑን ያስረግጣሉ። በእርግጥ በመጀመሪያዎቹ የለውጡ ጊዜያት መዋቅሩ ፈራርሶ እንደነበርና ኢትዮጵያ ክፉኛ ለደኅንነት ስጋት ተጋልጣ እንደነበር አንስተው፣ አሁን ግን ራሱን እያደሰ በተገቢው ሁኔታ አገርን እና የሕዝብን አደራ ለመወጣት ቀን ከሌት የሚለፋ ተቋም ለመሆኑ የማያሻማ ጉዳይ መሆኑን አውስተዋል።

በዚህም ቀደም ባሉት ለጋ በነበረው ለውጥ አመራር ዘመን የተከሰቱ ኹነቶችን በመመርኮዝና በማንሳት የነበረውን ክፍተት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በፀጥታ ጉዳይ ከተባለ ከለውጡ በኋላ በለውጡ አመራሮች የተወሰደው ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ቢሮ ላይ የሪፎርም ሥራ ከፍተኛ ክፍተት ለማስከተሉ ምንም አይነት ጥርጣሬ እንደሌላቸው ያትታሉ።

በዚህ መሥሪያ ቤት የግድ ነባር ከፍተኛ አመራሮች እንዲቀመጡ ባይደረግ እንኳን ከታች በሙያቸው ሲሠሩ የነበሩና እስከ ታች ድረስ የደኅንነት መዋቅሩን የሚያውቁ ባለሙያዎች በነበሩበት ቦታ በመሆን የሪፎርሙ አካል ሆነው መቀጠል የሚችሉበት አጋጣሚዎች ቢኖሩ ለውጡ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የሚታዩት አገራዊ ችግሮች ባልተፈጠሩ ነበር።

ቀጥለውም አንድ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ የመጀመሪያው ሥራ መሆን የሚገባው የደኅንነት መሥሪያ ቤቱን ማጠናከር ሲሆን በመከላከያ ውስጥም በተጓዳኝ የመከላከያ ደኅንነትን ማጠናከር ይኖርበታል ሲሉ ይገልፃሉ። ለዚህ ደግሞ እንደምሳሌ የሚያነሱት በ2011 መጀመሪያዎቹ ወራት አካባቢ ከነሙሉ ትጥቃቸው ወደ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ጎራ ያሉትን የመከላከያ ኃይል አባላትን ነው።

‹‹የሚያነሱት ጥያቄ ይኖራቸዋል፤ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ተራ ግለሰቦች ሳይሆኑ የታጠቁ ግለሰቦች ናቸው። ስለዚህ በወታደር ደንብ ጥያቄያቸውን ማስተጋባት ይኖርባቸው ነበር። ነገር ግን ከኹሉም አስደንጋጩ ነገር ከተነሱበት ቦታ ቤተ መንግሥት እስኪደርሱ ድረስ በብሔራዊ ደኅንነት በኩል ወይም በመከላከያ ውስጥ ባለው የደኅንነት መረብ ቅንጅታዊ ሥራዎች ተሠርተው መንገድ ላይ መግታት ይቻል ነበር። ነገር ግን ክፍተቱ እጅግ ሰፊ ነበርና በቀጥታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉበት ቦታ ገብተዋል።›› ሲሉ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 80 ግንቦት 8 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here