በኢትዮጵያ የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ ለመከላከል 63 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተባለ

0
531

የግብርና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ ለመከላከልና ለመቆጣጠርና 63 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የበርሃ አንበጣ ምላሽ ፕሮጀክት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እቅድ ባዘጋጀው ፕሮጀክት፣ የበረሃ አንበጣውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተለያዩ ምድቦችን ያወጣ ሲሆን፣ ለዚህም ማስፈጸሚያ የሚሆን የ63 ሚሊዮን ዶላር በጀት እንደሚያስፈልግ ተጠቅሷል።

የታቀደው ፕሮጀክት አራት ምድቦች ያሉት ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ የመጀመሪያው የበርሃ አንበጣውን የመቆጣጠርና የቅኝት ሥራ ሲሆን፣ ለዚህ ፕሮጀክት 45 ነጥብ 10 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገዋል ተብሏል። በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ ከሚተገበሩ ተግባራት ውስጥ የበርሃ አንበጣው የሚገኝበትን ቦታ እንዲሁም ተጎጂ የሆኑ ቦታዎችን መለየት፣ አንበጣው የሚገኝበትን የሥነ-ምህዳር ሁኔታ መለየት እና አገር በቀል የሆኑ የበርሃ አንበጣ መለካከል ላይ የሚሠሩ ተቋማትን አቅም መገንባት ላይ የሚውል ነው ተብሏል።

በዚህ ምድብ ከሚከናወኑ ተግባራት ውስጥ በበርሃ አንበጣ ተጎጂ የሆኑ አካባቢዎችንና ማኅበረሰቦችን መለየት እና የመቆጣጠሪያ ዘዴዎችን ለመለየት ቀጣይነት ያለው ጥናት ማካሄድ ናቸው።

ሌላኛው የዚህ ምድብ ፕሮጀክት የበረሃ አንበጣን ብዛት ለመቀነስ እና ስርጭቱ ወደ አዲስ ቦታዎች እንዳይተላለፍ ባለበት ቦታ ላይ ስርጭቱን ለመግታት የሚወሰድ የቁጥጥር እርምጃ ነው ተብሏል። እንዲሁም በበረሃ አንበጣ ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን የአካባቢ ተጽዕኖ መቀነስና መቆጣጠር ናቸው።

ኹለተኛው በአንበጣ ሊጠቃ ይችላል የተባለውን ማኅበረሰብ መጠበቅ እና እንደ አዲሰ ማቋቋም ሲሆን፣ ለዚህም 16 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተብሏል። በዚህ ምድብ ለተመረጡ አርሶ አደሮች ችግኝ፣ ማዳበሪያና ፀረ-ተባይ ማጥፊያ እንደሚሰጥ ተጠቁሟል። ሌላኛው በዚህ ምድብ ውስጥ የድንገተኛ ጊዜ ምግብ ፍላጎትን ለመሸፈን እና የንብረት ሽያጭ ከሚያስከትለው ጭንቀት ለመከላከል የሚለው እንደሚካተት ተጠቅሷል።

ሦስተኛው የመከላከያ ፕሮጀክት እቅድ የቅድመ ማንቃትና የቅድመ ዝግጅት ሥራ ሲሆን፣ ለዚህ ፕሮጀክት አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ በእቅዱ ላይ ተመላክቷል። የበረሃ አንበጣውን የአሰፋፈር ሁኔታና ጸባይ ለማወቅ በኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር በኩል በተቀናጀ መልኩ ስርዓት መዘርጋት፣ የወደፊት ክስተቶችን አመላካች የሆኑና ቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎችን መሥራት መሆኑ ተጠቁሟል። በዚህ ፕሮጀክት ምድብ ስር ከተካተቱ ተግባራት ውስጥ ዓለም ዐቀፍና አገራዊ በሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች የፌዴራልና የክልል ባለሙያዎችን አቅም ማሳደግ ይገኝበታል።

አራተኛውና የመጨረሻው ፕሮጀክት አስተዳደራዊ ሥራ ሲሆን፣ ለዚህም ስድስት መቶ ሺሕ ዶላር ያስፈልጋል ተብሎለታል። በዚህ ፕሮጀክት ስር የሚከናወኑ ተግባራት የፋይናንስ አስተዳደርንና ተመሳሳይ ለሆኑ ቴክኒካል ጉዳዮች ማስፈጸሚያ እና ተግባቦትና የመረጃ ልውውጥ የሚሉትን ተግባራት ለማስፈጸም የሚውል መሆኑ ተጠቁሟል።

የዓለም ምግብና ግብርና ድርጅት በምሥራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣን ለመከላከል 175 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ግምቱን አስቀምጧል።
የበረሃ አንበጣን ለመዋጋት የሚወሰዱ አጠቃላይ ወጪ እንዲሁም ለተጎዱ ሰዎች ምግብ ለማቅረብ ከሚያስፈልገው በጀት ጋር ሲነጻጸር በቂ አለመሆኑን የግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር ዘብዲዎስ ፍላቶ ተናግረዋል። ዳይሬክተሩ አክለውም ሁሉም የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ጥረታቸውን በማስተባበር እና በመቆጣጠር ላይ ካላተኮሩ በስተቀር አንበጣውን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠርም ሆነ ለመከላከል አስቸጋሪ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

‹‹ለኮቪድ-19 ፈጣን ምላሽ ያስፈልጋል። ግን ረሀብም ሰዎችን ይገድላል።›› ያሉት ዘብዲዎስ፣ መንግሥት እና ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ በጋራ የኮቪድ-19 እና የበረሃ አንበጣን በተመሳሳይ እይታ ትኩረት እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል።

የበረሃ አንበጣ በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ሰኔ 2011 የተከሰተ ሲሆን፣ በወቅቱ በአምስት ክልሎች በአፋር፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና ሱማሌ እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተከስቷል። አሁን ላይ በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎችም ስርጭቱ እየተሰፋፋ እንደሚገኝ የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 80 ግንቦት 8 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here