ግብፅ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ላቀረበችው ስሞታ ኢትዮጵያ የ22 ገፅ ደብዳቤ ምላሽ ሰጠች

0
524

ደብዳቤውም ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ በቀጣዩ ክረምት የያዘችውን የውሀ መሙላት እቅድ በመቃወም ግብፅ ለፀጥታው ምክርቤት ላቀረበችው የ17 ገጽ የተቃውሞ ደብዳቤ ምላሽ ነው፡፡.

በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በተፈረመና ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት (UNSC) በቀረበው ደብዳቤ ላይ ኢትዮጵያ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለመሙላት የማንንም ፈቃድ የመፈለግ የህግ ግዴታ የለባትም በማለት አስታውቃለች፡፡ በተጨማሪም በደብዳቤው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር በእንጥልጥል እንዲቀር በማድረጓ ግብፅን ተጠያቂ አድርጋለች፡፡

በሁለቱ ሀገራት መካከል የተከሰተው ይህ ሁኔታ በግብፅ ፣ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ቀደም ብሎ ሲካሄድ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር በኮቪድ-19 ወረርሽኝ  ምክንያት ወደኋላ በተጓተተበት ጊዜ ሲሆን በአሜሪካ የሽምግልና ውይይቶች ላይ ኢትዮጵያ ለመሳተፍ ሳትችል በመቅረቷ ነው፡፡

በዚህም መሰረት በሚያዝያ ወር 2012 በኢትዮጵያ ሊከናወን ታስቦ የነበረው የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት በተለይ አከራካሪ የነበረ ሲሆን ሱዳን የኢትዮጵያን ሀሳብ በመቀበል ረገድ ወደኋላ ስትል የተስተዋለችበትም ነበር፡፡ ሆኖም በመጪው ሐምሌ ወር የመጀመሪያ ምዕራፍ ሙሌትን ለመጀመር ኢትዮጵያ ዝግጅቷን መጠናቀቋን አስታውቃለች፡፡

ለሚያዚያ ተይዞ በነበረው የኢትዮጵያ የውሀ መሙላት እቅድ መሠረትም የመጀመሪያው ደረጃ የውሀ ሙሌትን ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመታት የሚፈጅ ሲሆን ግድቡ ከባህር ጠለል በላይ እስከ 595 ሜትር ከፍታ እንዲኖረውና 18.4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሀ እንዲይዝ ታቅዷል፡፡

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለፀጥታው ምክር ቤት በፃፉትም ደብዳቤ ይህ የመጀመሪያ ደረጃ የውሃ ሙሌት፤ የኃይል ማመንጨት ሙከራ ለማድረግና ውሀውንም በአግባቡ ወደታችኛው ተፋሰስ ለመልቀቅ ያለመ ነው በማለት ኢትዮጵያ በሚያዝያ ወር ውስጥ የያዘችውንም አቋም የበለጠ አብራርተዋል፡፡

በዚህም መሰረት በሁለት ዓመት ውስጥ፤ በአንደኛው ዓመት 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እና በሁለተኛው ዓመት 13.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የሚያዝ ሲሆን፤ ይህም ከ49 ቢሊዮን ክዩቢክ ሜትር አማካይ የአባይ አመታዊ የፈሰት መጠን አንፃር በታችኞቹ የተፋሰስ አገራት ላይ ተጨባጭ ጉዳትን አያስከትልም ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ይህ የመጀመሪያ ደረጃ የውሀ ሙሌት መመሪያ በኢትዮጵያ የተፈጠረ ሳይሆን ይልቁንም በሦስቱ አገራት ያለምንም ውዝግብ ከተዘጋጀው የጠቅላላ ‘መመሪያዎች እና ህጎች’ የተወሰዱ ናቸው በማለት ደብዳቤው ያብራራል፡፡

”ኢትዮጵያ ግድቡን ለመሙላት የግብፅን ይሁንታ የማግኘት የሕግ ግዴታ የለባትም፡፡ በተጨማሪም በሁለት ዙር ውስጥ 18.4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሀ በግድቡ መያዙ በግብፅ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አያስከትልም”፡፡ ”ስለሆነም ኢትዮጵያ ከመርህ ሰነዱ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማ እና ለግብፅ መልካምና ለጋስነት ያልተለየው የውሀ አሞላል ስርአት እየተከተለች መሆኑንም” አስረድተዋል ፡፡

ኢትዮጵያ ግብፅን ውጤታማ ንግግሮችን እንዳይኖሩ “ያለማቋረጥ እንቅፋት” እየሆነች እንደቆየችም ከሳለች፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ከግብጽ ጋር በመነጋገር ውጤት ላይ መድረስ እንዳልተቻለ ተችተዋል ፡፡ ባሳለፍነው የካቲት ወርም አሜሪካ ተገቢ እና ተቀባይነት የሌላቸውን ውሎች ኢትዮጵያ እንድትቀበል ጫና ስታሳድር መቆየቷል ሚኒስትሩ ጨምረው በደብዳቤው ገልፀዋል፡፡

“በየካቲት ወር አጋማሽ በዋሺንግተን ዲ.ሲ በተደረጉት ውይይቶች ላይም ያልተስማማንባቸውን ጉዳዮች ሳንፈታ በፍጥነት ስምምነት ላይ እንድንደርስ እና እንድንፈርም ጫና ይደረግብን ነበረ” ብለዋል፡፡

ገዱ በደብዳቤው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ታሪካዊ ስህተትን የሚያስተካክል ፕሮጀክት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውሃውን በማመንጨት ለሌሎች እንድትተው እንጂ እንድትነካው አልተፈለገም፤ ይህ ኢ-ፍትሃዊ ሁኔታ መቀጠል የሌለበት እና መታረም ያለበት ሁኔታ ነው ብለዋል።

“ከግብፅ በተለየ መልኩ የአስዋን ግድብ ግንባታ ስታከናውን የኢትዮጵያን ፍቃደኝነት አልጠየቀችም! የታላቁ የህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ የሚከሰተውን የድርቅ ተፅእኖን ለመቀነስ እና በኤሌክትሪክ እጥረት ለመቅረፍ ይረዳል”፡፡ “ከ 65 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ ኃይል የላቸውም ፣ ግን ሁሉም ግብፃዊያን ማለት ይቻላል የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አላቸው” ሲል ደብዳቤው ገልጿል፡፡ በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ ከሚገኙት ልጆች መካከል ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት ተማሪዎች በጨለማ ውስጥ እንዲቆዩ የተገደዱ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች አሁንም ውሃ እና ማገዶ ለማምጣት ረጅም ርቀት ይጓዛሉ ሲሉም ሚኒስሩ በደብዳቤው ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ የግድቡን የውሃ ሙሌት በዚህ አመት ሰኔ ወር ላይ መጀመር እንደምትፈልግ ቀድማና ደጋግማ አስታውቃለች፡፡ ጠ /ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ እንዳብራሩት “የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንኳን እቅዶቹን አያስተጓጉልም” ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊት በድርድሩ ወቅት ለኢትዮጵያ ሰፊ ድጋፍ ያበረከተችው ሱዳን የኢትዮጵያን የመጀመሪያ ደረጃ የውሀ ሙሌት ሂደትን ለማስቀጠል ያደረገችውን ​​ውሳኔ በመቃወም ሦስቱ አገራት “የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያው ሙሌት ከመጀመሩ በፊት” በሶስትዮሽ ስምምነት መድረስ አለባቸው ማለቷ ይታወሳል ፡፡

ሆኖም ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የላከችው ይህ ደብዳቤ በግብፅ ላይ ያተኮረ ሲሆን “በሚያሳዝን ሁኔታ ግብፅ ለኢትዮጵያ ጥሩ እምነት እና ተነሳሽነት የሰጠችው ምላሽ በጎ አለመሆኑን፣ እንዲሁም ግብፅ የመጀመሪያውን የስምምነት አቅጣጫ ለመጎተት እና በተቻለ መጠን ሂደቱን ለማዘግየት ጥረት እያደረገች መሆኑን የሚገልፅ እንደሆነ ተገልጿል።

ደብዳቤው የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት፣ በተባበሩት መንግስታት ቋሚ ተወካይ በሆኑት ታዬ አጽቀ ስላሴ በኩል የደረሰ ሲሆን በውኃ ሙሌቱ እና አፈሳሰስ ሂደት ላይ በጋራ ተጠቃሚነት ስምምነት ላይ የመድረስ ዓላማን ያነገበ የሶስትዮሽ ድርድር እንደገና እንዲጀመር ጥሪ እንደቀረበበትም ለማወቅ ተችሏል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here