ዳሸን ባንክ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለኢኮኖሚ ጉዳት ተጋላጭ ለሆኑ ዘርፎች የባንክ አገልግሎት ማሻሻያ አደረገ

0
793

ዳሸን ባንክ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና እንደሚያሳድርባቸዉ በማጥናት በተለዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ ደንበኞቹ የወለድ ቅናሽ ፣ የብድር እፎይታና ማራዘሚያ ጊዜ ለመስጠት መወሰኑን አስታውቋል፡፡

ባንኩ ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው  የቫይረሱ ስርጭት በአገራችን ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የሚያደርሰዉን ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳት ለመከላከል በሚደረገዉ ጥረት የበኩሉን የጎላ ድርሻ ሲያበረክት መቆየቱ ያስታወቀ ሲሆን ፤ የቫይረሱ ስርጭት በተለይ በአንዳንድ በጥናት በተለዩ ዘርፎች ላይ እያስከተለ ያለው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን በመገንዘብ ቀደም ሲል በሌሎች ተጎጂ መስኮች ላይ እንዳደረገው ሁሉ በነዚህ ዘርፎች የተሰማሩ ደንበኞቹ እየደረሰባቸዉ ያለዉን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመጋራት መወሰኑን ገልጿል፡፡

በዚህም መሰረት በአበባና አትክልት ፣ በሆቴልና ማስጎብኘት ፣ በወጪ ንግድ  ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አምራቾች ፣ በአምራች  ፣ በህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት እና ትምህርት ተቋማት ዘርፎች ለተሰማሩና በሥራ ላይ ላሉ ደንበኞች እ.ኤ.አ. ከሰኔ 1 ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የወለድ ቅናሽ ፣ የብድር እፎይታና ማራዘሚያ ጊዜ መስጠቱን አስታውቋል፡፡

ባንኩ በአበባና አትክልት ዘርፍ ለተሰማሩ ተበዳሪዎች ቀደም ሲል በዝቅተኛ ወለድ እያበደረ የነበረ ቢሆንም ፤ ዘርፉ ከቫይረሱ ስርጭት ጋር ተያይዞ የደረሰበትን የኢኮኖሚ ጉዳት ከግምት ዉስጥ በማስገባት ከ 1 በመቶ እስከ 2 በመቶ ተጨማሪ ቅናሽ በማድረግ ፤ እ.ኤ.አ ከሰኔ 1 ጀምሮ በዘርፉ የተሰማሩ ደንበኞች 7 በመቶ የወለድ ምጣኔ ብቻ እንዲከፍሉ ወስኗል ፡፡ በተጨማሪም ተበዳሪዎች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሰረት የ 6 ወር የብድር ዕፎይታና እስከ 5 አመት የሚቆይ የብድር ማራዘሚያ በነጻ መፍቀዱን አስታውቋል፡፡

በሆቴልና ማስጎብኘት ዘርፍ የተሰማሩ ተበዳሪዎች ከዚህ በፊት እስከ 17 ነጥብ 5 በመቶ የሚደርስ ወለድ ይከፍሉ የነበረ ሲሆን ፤ እ.ኤ.አ ከሰኔ 1 ጀምሮ የሚከፍሉት የወለድ ምጣኔ ወደ 7 በመቶ እንዲቀንስና ተበዳሪዎቹ በሚያቀርቡት ጥያቄ መሰረት የስድስት ወር የብድር ዕፎይታ ጊዜና እስከ 5 ዓመት ድረስ የሚቆይ የብድር ማራዘሚያ ያለምንም የማራዘሚያ አገልግሎት ክፍያ እንያገኙ ለማድረግ መወሰኑም ተገልጿል፡፡

በውጪ ንግድ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አምራቾችም እንዲሁ ቀደም ሲል በዝቅተኛ ወለድ እየተበደሩ የነበረ ቢሆንም ፤ የተከሰተዉ ያልተጠበቀ ችግር የሚያሳድርባቸዉን የኢኮኖሚ ጫና ከግምት ዉስጥ በማስገባት እ.ኤ.አ ከሰኔ 1 ጀምሮ የወለድ ምጣኔ ቅናሹ ተጠቃሚ ሆነው ለሶስት ወራት 7 በመቶ ብቻ ወለድ እንዲከፍሉ ተደርጓል ፡፡ ከዚህም ሌላ በሚያቀርቡት ጥያቄ መሰረትም የሦስት ወር የብድር መክፈያ ዕፎይታ ጊዜና እስከ ሦስት ዓመት ያለምንም የብድር ማራዘሚያ ክፍያ እንዲስተናገዱ ተደርጓል፡፡

በአምራች ዘርፍ  ፣ በህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች  በትምህርት ዘርፎች የተሰማሩ ተበዳሪዎችም ጭምር በሚያቀርቡት ጥያቄ መሰረት እ.ኤ.አ ከሰኔ 1 ጀምሮ ለ 6 ወር የብድር መክፈያ እፎይታ ጊዜና እስከ 3 ዓመት ድረስ የብድር ማራዘሚያ ያለምንም የማራዘሚያ አገልግሎት ክፍያ ለመስጠት ወስኗል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዳሸን ባንክ ከላይ ለተጠቀሱትና በቫይረሱ ስርጭት ይበልጥ ለኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንሚዳረጉ በጥናት ለተለዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ተጨማሪ የወለድ ምጣኔ ማስተካከያ እንዲደረግላቸዉም ወስኗል ፡፡

ከ 17.5 በመቶ እስከ 18 በመቶ ወለድ ይከፍሉ የነበሩና ፤ በነዚህ ዘርፎች የተሰማሩ ደንበኞች የ 1.5 በመቶ ወለድ ቅናሽ ተደርጎላቸዉ 16 በመቶና 16.5 በመቶ ወለድ እንዲከፍሉ ተደርጓል ፡፡ ከ 14 በመቶ እስከ 17 በመቶ ወለድ ይከፍሉ የነበሩ ደግሞ የ 1 በመቶ ቅናሽ ተደርጎላቸዉ ከ 13 በመቶ እስከ 16 በመቶ ወለድ እንዲከፍሉ ተወስኗል ፡፡ ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱት ሁሉም የብድር አገልግሎት ማሻሻያ ዉሳኔዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከታወጀበት ጊዜ በፊት በተበላሸ ብድር ዝርዝር ዉስጥ ይገኙ የነበሩ ብድሮችን እንደማይጨምር ባንኩ አሳስቧል፡፡

ባንኩ በማርኬቲንግና ከስተመር ኤክስፐሪየንስ ዲፓርትመንቱ በኩል ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስሩም ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ አንድ መቶ አርባ የህዝብ ትራንስፖርት አስተናባሪዎችና ተራ አስጠባቂዎች ማኅበራት ፤ አገልግሎታቸውን ለማቀላጠፍና ህዝቡን ለማገልገል የሚያደርጉትን ጥረት ለማገዝ እንዲቻል በረካታ የፀሐይና የዝናብ መከላከያ ጃንጥላዎችን በየማኅበራቱ መሪዎች አማካኝነት ማስረከቡንም አስታውቋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ዳሸን ባንክ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት መንግስት የሚያደርገዉን ጥረት ለማገዝ 10 ሚሊዬን ብር ማበርከቱም ችሮታ ከማድረጉም ሌላ ፤ በቀዳሚነት ለተበዳሪዎቹ ከፈቀደዉ ከዚህ ማሻሻያ በፊት በቅርቡ በመላ አገራችን በሚገኙ አስራ ዘጠኝ የባንኩ የተለያዩ ህንፃዎች ላይ ለሚገኙ ተከራዮቹ በሙሉ ለ 3 ወራት የሚቆይ የ 50 በመቶ የኪራይ ቅናሽ ማድረጉ ፤ የቫይረሱ ስርጭት ከተከሰተ ጀምሮም በሽታዉ በደንበኞች ላይ ሊያደርስ የሚችለዉን የኢኮኖሚ ጫና ለመቀነስ ለኤልሲና ብድር ማራዘሚያ ይከፈሉ የነበሩ ክፍያዎችን ሙሉ በሙሉ እንዲሁም ለሲኤዲ ማራዘሚያ ይከፈል የነበረዉን ክፍያ 50 በመቶ ለ 6 ወራት ማንሳቱ እና ከባንኩ ኤቲኤም ማዉጣት የሚቻለዉን የገንዘብ መጠን ወደ 10 ሺ ብር ከፍ በማድረግ ለአገልግሎቱ ይከፈል የነበረዉን ክፍያም ነጻ እንዲሆን ማድረጉንም አስታውሷል፡፡

በአጠቃላይ ባንኩ ይህንን የብድር አገልግሎት ማሻሻያ ጨምሮ እስካሁን ለደንበኞች ያደረጋቸዉ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎችና ያበረከታቸዉ ድጋፎች በብዙ መቶ ሚሊየኖች የሚገመት ገቢ ለማጣት የሚዳርገዉ ቢሆንም ፤ ባንኩ በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑ ባንኮች አንዱ ለመሆን ለሚያደርገዉ ጉዞ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በተስተካከለ ቁመና ላይ መገኘት ወሳኝና አስፈላጊ መርሆ በማድረግ ማሻሻያዎቹንና ድጋፎችን ለማበርከት ሲወስን ፤ እንደተለመደው ሁሉ ወደ ፊትም ነባራዊ ኹነቶችን በመገምገም በጥናት ላይ በተመሠረተ እውነተኛ መርህ አገራችንን እና ህዝባችንን የሚያግዙ ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰዱን የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጧል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here