ከ5 ሺሕ በላይ መኪኖች ላይ የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሣሪያ ተገጥሟል

0
591

በኢትዮጵያ ከፍጥነት በላይ በማሽከርከር የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ ለመቆጣጠር የሚያስችል መሣሪያ በ5 ሺሕ 403 ተሸከርካሪዎች ላይ ተገጥሞ ወደ ሥራ መግባቱ ተገለጸ።

የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የተሽከርካሪ ፍጥነት መገደቢያ መሣርያ ስለመግጠም እና ስለ ማስተዳደር በሚል በታኅሳስ ወር 2011 የጸደቀው መመርያ ቁጥር 27/2011 ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ፣ እስከ 2012 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ድረስ ከ5 ሺሕ በላይ በሆኑ የጭነት እና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ እንደተገጠመ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

የንግድ እና የጭነት ተሸከርካሪዎች ላይ የፍጥነት መቆጣጠርያ በፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ደረጃ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ አዳዲስ የንግድ እና የጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ እየተተገበረ እንደሆነም ባለሥልጣኑ ለአዲስ ማለዳ ጨምሮ አስታውቋል።

የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ይግዛው ዳኘው ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ በዚሁ በመመሪያው መሰረት መተግበር የጀመረው በ2011 ሲሆን ነገር ግን አሁን በፌዴራል ደረጃ እየተሠራ ያለው አዳዲስ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ላይ አስገዳጅ ሆኖ፣ ገና ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ መሣሪያውን ገጥመው እንዲገቡ እየተደረጉ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ከዛም በተጨማሪ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2000 የምርት ዓመት እና ከዛ በኋላ ባሉት ሥሪቶች የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ እንዲገጠም በሚል መመሪያ ወጥቶ እሱን ለማስተግበር እየተሠራም ነው ብለዋል።

ይግዛው ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ የጥራት ደረጃ እንዲወጣለት ተደርጎ በዚህም መሠረት የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያውን ለማስመጣት ከፌዴራል ትራንስፖርት ፈቃድ ወስደው ከ20 በላይ ድርጅቶች ይሄን መሣርያ ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት እና ተሽከርካሪዎች ላይ ለመግጠም የብቃት ማረጋገጫ ተሰጥቷቸው እየሠሩ ይገኛሉ ብለዋል።

በዚህም ከ13 ሺሕ 170 የፍጥነት መቆጣጠርያ ማሽን ከውጭ አስገብተዋል ብለዋል። በዚህም እስከ አሁን የተገጠሙት 5ሺሕ 403 በላይ መሆናቸው ለአዲስ ማለዳ ተገልጿል።

በተጨማሪም እንደ ሕዝብ ግንኙነቱ ገለፃ፣ ለአስመጪዎችም ይሄ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ከውጭ የሚያስገቧቸው መኪናዎች ላይ የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሣርያ እንዲያስገጥሙ ተነግሯቸዋል ብለዋል።

የግንዛቤ እጥረት ከመኖሩ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮች እንዳሉ ገልፀው ‹‹የፍጥነት መቆጣጠሪያ መግጠም ማለት በቀላሉ መግባት ስንችል መንገድ ላይ ያስረናል›› በሚል እንደማይፈልጉት ተናግረዋል። ነገር ግን ከፍተኛውን ቁጥር የሰው ህልፈት ከሚከሰትባቸው መካከል አንዱ የትራፊክ አደጋ መሆኑ ይታወቃል። በ2011 በትራፊክ አደጋ ብቻ 5 ሺሕ 497 ሰዎች መሞታቸውን እና ከዚህም በላይ በአካል እና በንብረት ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ ከባድ ነው።

ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ጠቃሚ ነገር ለተሽከርካሪዎች የፍጥነት መቆጣጠርያ እንዲጠቀሙ ማስገደድ ነው ሲሉ ይግዛው ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
በተያያዘም የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰመረ ጅላሎ፣ ይሄ አሰራር ተግባራዊ እንዲያደርጉት አሽከርካሪዎች ሕግ እየተዘጋጀ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ከዛ በተጨማሪ የተለያዩ ከተሞች ክልሎች ከራሳቸው ሁኔታ እንፃር የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣንን ሕግ መነሻ በማድረግ የራሳቸውን ሕጉ ሊያወጡ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት ይላሉ ሰመረ፣ አዲስ አበባ ውስጥ በራሳችን ፍጥነት ወሰን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ከሚያስገጥመው ፍጥነት ወሰን ልክ አዲስ አበባ ሲገቡ የአቅጣጫ መጠቆሚያ (GPS) ስለሚኖረው ከነበረው ፍጥነት እንዲቀንስ እንዲያደርጉልን ከፌዴራል ትራንፖርት ባለሥልጣን ጋር እየሠራን ነው ብለዋል።
ከዛም በተጨማሪ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰመረ እንደገለፁት፣ መመሪያው እንደተጠናቀቀ ለግምገማ ከቀረበ በኋላ ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ገብተው በሥራ ላይ የሆኑትን ከተማ ውስጥ በተቀመጠው በፍጥነት ልክ እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 81 ግንቦት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here