በቀጣይ የምርት ዘመን የ12 በመቶ የምርት አቅርቦት እጥረት ሊከሰት እንደሚችል ተጠቆመ

0
706

ግብርና ሚኒስቴር በቀጣይ ዓመት የምርት ዘመን ላይ የ12 በመቶ የምርት አቅርቦት እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችል አስታወቀ። ሊያጋጥም ይችላል የተባለው የምርት እጥረት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና የበረሃ አንበጣ በመከሰቱ ነው ተብሏል።

በኢትዮጵያ ከተከሰተ ዓመት ሊሞላው የአንድ ወር ጊዜ የቀረው የበረሃ አንበጣ በቀጣይ የምርት ዘመን ላይ የአራት በመቶ እንዲሁም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ወረርሽኝ በመሆን ዓለምን እያመሰ በሚገኘው ኮቪድ-19፣ የስምንት በመቶ፣ በድምሩ በ12 በመቶ የምርት ማሽቆልቆል ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት እድገት ዳይሬክተር ኢሳያስ ለማ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

የበረሃ አንበጣ በምሥራቅ አፍሪካ ኹሉም አገሮች ላይ ስጋት መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ በተለይም በኢትዮጵያ ላይ ወቅቱ የዝናብና ሰብል የሚለማበት ጊዜ ከመሆኑ እና አገሪቱ በአብዛኛው በግብርና ልማት የምትለማበት ከመሆኑ አንፃር ስጋቱ ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።

ለምርት እጥረቱ ስጋት የሆነው ሌላኛው ችግር ኮቪድ-19 ዓለምን ከመፈተኑ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባው ምርት ሊቀንስ ይችላል የሚል መሆኑን ዳይሬክተሩ አመላክተዋል። በዚህም ሊከሰት የሚችለውን የምርት መቀነስና የፍላጎት መጨመር ለማጣጣም ከውጭ የሚገባውን ምርት በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት የተለያዩ አማራጭ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑ ተጠቁሟል።

እየተወሰዱ ካሉ አመራጭ ሥራዎች ተጨማሪ እስከ ግማሽ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሰብል ማልማት እና 40 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማስገባት አንዱ ዕቅድ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የምርት እጥረት እንዳያጋጥም ሊደርጉ ይችላሉ በተባሉት በኮቪደ-19 እና በበረሃ አንበጣ ምክንያት በኢትዮጵያ የተረጂዎች ቁጥር አሁን ካለበት ደረጃ በላይ ስለሚጨምር በተለይም በኮቪድ-19 ምክንያት ሥራ አጥ ሆነው እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች በእጅጉ ሊጨምር ስለሚችል የፍላጎትና የምርት መጠን አለመጣጣም ሊከሰት እንደሚችል ታስቧል።

በዚህም ምክንያት ምርትና ፍላጎትን ለማጣጣም እና ሊያጋጥም የሚችለውን ችግር ለመቋቋም አማራጮችን መመልከት በማስፈለጉ መንግሥት እስከ አሁን ያልለሙ መሬቶች በሚመጣው የምርት ዘመን በባለሀብቶችና በተደራጁ አምራቾች እንዲለሙ አቅጣጫ ይዟል ተብሏል።

እስከ አሁን በኢትዮጵያ 14 ሚሊዮን ተረጂዎች እንዳሉ የገለጹት ኢሳያስ፣ ወደፊት የተረጂ ቅጥር እየጨመረ እንደሚመጣ እና ከዚህ በፊት ለድጋፍ የሚቀርበው ምርት በቂ ስለማይሆን የምርት እጥረት እንዲከሰት ከሚያደርጉ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ነው ብለዋል።

እንደ ኢሳያስ ገለጻ በኮቪድ-19 በሚከሰተው የምግብ እጥረት ችግር ተጋላጭ የሚያደርገው ከድህነት ወለል በታች ያለውን ኅብረተሰብ መሆኑን ጠቁመዋል። በመሆኑም ሊፈጠር የሚችለውን የምግብ እጥረት ችግር ለመመለስ የግብርና ሚኒስቴር እቅድ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ አብራርተዋል። ኢሳያስ አክለውም ለሚፈጠረው ችግር ምላሽ ለመስጠት የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በበኩሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሌላኛው ለግብርናው ዘርፍ ጥላ ያጠላው የበረሃ አንበጣ ነው። የበረሃ አንበጣን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከዓለም ባንክ እና ከምሥራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መከላከል በተገኘ ድጋፍ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ኢሳያስ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

እስከ አሁን ድረስ ሦስት የአሰሳ ሔሊኮፕተሮች እና ስድስት አውሮፕላኖች እንደተገዙ እና የተለያዩ የመከላከያ ግብዓቶች በግዢ ሂደት ላይ መሆናቸውን ኢሳያስ ተናግረዋል። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግሥት የበረሃ አንበጣን ለመቆጣጠር ያለው አቅም ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የተሻለ ነው ብለዋል፤ ኢሳያስ።

ግብርና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ ለመከላከልና ለመቆጣጠርና 63 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ማስታወቁን አዲስ ማለዳ ባለፈው እትሟ መዘገቧ ይታወሳል።

የበረሃ አንበጣ በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ሰኔ 2011 የተከሰተ ሲሆን፣ በወቅቱ በአምስት ክልሎች በአፋር፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና ሱማሌ እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተከስቷል። አሁን ላይ በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎችም ስርጭቱ እየተሰፋፋ እንደሚገኝ የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 81 ግንቦት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here